ወደ ራሴ ስመለከት - እንደ እኔ ላለ ዲሞክራሲ፣ ነፃነትና ሀገር አይገባውም (ዳኛቸው ቢ.)
ዳኛቸው ቢያድግልኝ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
ብዙ ተቺዎች ወይም ሃያሲዎች ወቃሾችና ከሳሾች ባሉበት ሀገር ታታሪና ትጉህ ሰራተኞች ጥቂት ናቸው። ጣት መጠንቆል ቀርቶ ወደራስ መመልከት ተገቢ የሆነበት ደረጃ ላይ በመድረሳችን “ሌሎች ምን?” ሠሩ ሳይሆን፤ “እኔ ምን ስለሠራሁ ነው ፍትህ፣ ነፃነት ሀገርና ዲሞክራሲ ይገባኛል ማለት የምችለው?” የሚለው ጥያቄ በነፍስ ወከፍ መመለስ ያለበት ይመስለኛል።
ይህ ጥያቄ አሁን ለሚደርስብን በደልና ለትውልድ ለምናቆየውም ጥፋት መልስ ሰጪ ነውና አመልካች ጣታችንን ለጊዜው ረስተን ወደ ራሳችን ለሚጠቁሙት አብላጫ ጣቶች ጥያቄ መልስ እንስጥ። ብዙዎቻችን አሁን ባለንበት እንቀጥል የምንል ከሆነ በድምፅ ብልጫ ሽንፈትን ተቀብለናል ማለት ነው። እኔ በበኩሌ እንዲህ እራሴን አየሁ። እናም መለወጥ እንዳለብኝ አመንኩ። እናንተስ? አንቺሽ? እርስዎስ?
በመጀመሪያ እኔ ሀገር አልባ፣ ለትግል ዘወር ካሉት ጋር የማልቆጠር፣ ሀገሬን ለጠላት ትቼ ነብሴን ለማዳን ወይንም ኑሮዬን ለማሸንፍ የፈረጠጥኩ ፈሪ ሰው ነኝ። ቆሜ መሞገት ያልቻልኩ ወይም ተጨቆንኩ ከሚለው አእላፍ ወገኔ ጋር መተባበር ማስተባበርና ፈሪውን ጠላቴን ማሸነፍ ያልቻልኩ ደካማ ሰው ነኝ። ስሜም ላይ ቅጽል ገብቶለታል። “ስደተኛ” የሚል። የሚሰደድ ባለበት መኖር የማይችል ነው። ታድያ ስደት መብቴ ይመስል የተሰደድኩባቸውን ሀገሮች ሳማርር ለጉድ ነው። የሚሉኝን ስለማላውቅ፤ ባውቅም ጆሮ ዳባ ልበስ ስለምል እንጂ በድህነቴ የሚሳቅብኝ፣ አብሮ ለመብላት እንጂ አብሮ ለመሥራት የማይችሉ፤ ለመበተን የፈቀዱ ህዝቦች እንደሚሉኝ ብቀበል ደግ ነበር።
ይህን ባውቅም ግን እኔ ራሴን ከጥሩዎች መድቤ ሌሎቹ ሁሉ መጥፎ በመሆናቸው ነው እያልኩኝ ስደትን እንደ ማዕረግ ይዤ ወንድም እህቶቼን ለስደት እጋብዛለሁ። ከሀገሬ ጋር ያለኝ ቁርኝት ወደ ትዝታነት ከዞረ እኮ ያለቀ ነገር ነው። ሀገሬ የምትታሰበኝ እናት አባቶቼ፣ ወንድም እህቶቼ እስካሉ ድረስ ብቻ ከሆነ ቁርኝቴ የላላ ነው። ሀገሬን የምናፍቃት ልፈነጭባት፣ ከሰው በልጬ ልታይባት ከሆነ የሥነልቡና ችግር ያለብኝ ሰው ነኝ ማለት ነው። የተሠራሁበት አፈርና ውሃ፣ ያነጸኝ ህዝብና ባህል፣ ያኮራኝ ታሪክና ቅርስ በደምና ስጋዬ ውስጥ ከሌሉና በሄድኩበት የምለምድ ከሆነ ግጦሽ በተገኘበት የምሰፍር ዓለም አቀፍ ዘላን እንጂ በህዝብ የተከለለ በመልከዓ ምድር የተከተረ ሀገር ባለሀብት አይደለሁም። ከነበርኩበትም ካለሁበትም ጠንካራ ቁርኝት ከሌለኝ በታሰርኩበት የገመድ እርዝማኔ ለዕለት ጉርሴ መንቀሳቀስ እንጂ የኔ የምለው ሀገር እንዲኖረኝ የምተጋ አይደለሁምና ለወገኔ ዲሞክራሲና ነፃነትስ ምን ገዶኝ?
የኔ ነገር ለጉድ ነው። ሀገር ስትፈርስ ቆሜ ዝርዝር አወጣለሁ። “እንዲህ አደረጉ …”፣ “እንዲህም አደረጉ …”፣ “እንዲህ ደግሞ ሊያደርጉ ነው …”፣ … እያልኩ ስዘግብ የስታትስቲክስ ጽሕፈት ቤት የቀጠረኝ ባለሞያ እንጂ ሀገሩን የተነጠቀ ባለሀገር አልመስልም። በቀደም ንጹኀን ሰዎችን ገደሉ፣ ትናንት ሕጻናትን አረዱ ስል የጠላቶቼን ጀብዱ እኔ የማወራላቸው እመስላለሁ። በእኔ ቢጤ የተሞላ ሁነኛ ሰው ያነሰበት መሬት ደግሞ ከሰፌድ ላይ እንደሚንገዋለል ብጣሪ እኔን ከድንበር ባሻገር በትነው ሀገሬን ገዢዎቼ ይሸጣሉ።
እንዲያ እያለ እንደ ‘Osmosis’ የተፈጥሮ ሕግ ሀገሪቱ እንዳለች ሆና ባለሀገሮቹ ሌሎች ይሆናሉ። ይህን በዓይኔ በብረቱ እያየሁ “በቃ!” ብዬ በደልን ለማስቆም የራሴን ድርሻ ለማበርከት ሀሞት የለኝም። እኛ እናስጥልህ የሚሉኝን አላምናቸውምም፣ አልደግፋቸውምም። ነገር ግን ሰዉ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ባቆመው ሀገር ውስጥ በድንግዝግዝ ፋይል ገብቼ በእርጥባን እየኖርኩ ድሎትንም እየተመኘሁ “ከእንግዲህ ይህ ዓለም ፍጹም ቤቴ አይደለም” እያልኩ እግዜርንም እዋሻለሁ። ሀገሬንም አሻሽጬ በገነት ለምሠራው ቤቴ ‘ኢንቨስት’ አደርጋለሁ። ታድያ ለእኔ ሀገር፣ ዲሞክራሲና ነፃነት እንደምን ይገቡኛል?
በቀደም ዕለት ስለሀገር ስናወራ ስንቱን ጉድ ስናዝረጠርጠው አመሸን። መተባበር እንደሚያስፈልግ ድጋፍ መስጠት እንደሚያሻ ተነጋገርን። የገረመኝ የአንደበታችን ስለት፣ የሃሳባችን ስምምነት ነበር። በስተመጨረሻ አንዱ ጉድ አደረገን። ከመካከላችን አንዱ፤ “እስቲ ማውራት መልካም ነው፣ መሥራት ደግሞ ድንቅ ነገር ነው …”፤ እያለ ከሁዋላ ኪሱ ቦርሳ ውስጥ በትልቁ 100 የተጻፈበት ኖት አወጣና “… እስቲ የኢትዮጵያ ጉዳይ ግዴ ነው ለሚል ለአንዱ ድጋፍ እንስጥ” አለ። እኔም፤ “ጥሩ ሃሳብ! መልካም ጅምር! …” እያልኩ እጄን በየአቅጣጫው ብልከው ቦርሳዬ ለምን አይጠፋብኝም። እጄ ለዚህ ሲሆን ይደናገረዋል መሰለኝ ወዲህ ብዳብስ ወዲያ ብዳብስ ኪሴ ውስጥ ያሉትን ኖቶችም እጄ አይመዛቸውም። ለካስ ብዙዎቹ እንደ እኔው ናቸው። ሲያወሩ ነው የሚመቻቸው።
አንደኛው ሃሳቡ ሸጋ እንደሆነ ገልጾ ከትናንት ወዲያ ለታማሚ እናቱ ያለችውን ጠራርጎ ባይልክ ኖሮ ብዙ ገንዘብ ለዚህ ቅዱስ ሃሳብ ይሰጥ እንደነበረ አስተዛዝኖ ነገረን። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀገር ቤት ስለአለው ሕክምና መጥፎነት ግማሽ ሰዓት አወራልን። ሌላኛው ለሠርግ የነበረበትን ወጪ ዘርዝሮ ዘርዝሮ ሲነግረን ምነው እንዲህ ያለ ሃሳብ ውስጥ ከሚገባ ባላገባ ኖሮ እስክንል ድረስ ቅቤ በጠጣ ክትፎ እያወራረደ ችግሩን ነገረን። ሌሎቻችን በወይን እያጣጣምን ሰማነው። ቁምነገር በበር ሲገባ ተግባር በመስኮት ሹልክ አለ። በመጨረሻም በመጣልኝ ሃሳብ ፋይሉ ተዘጋ።
“እንዲያው ለስማችንም እንዲሆን በደንብ አስበንበት፤ አለ አይደለም በደንብ ተዘጋጅተንበት በቅርቡ አንድ ነገር እናድርግ …” ስል ሁሉም ተመችቶአቸው በፈገግታ በሞቅታ ሃሳቤን ተቀበሉት። ሁሉም የእፎይታ ይመስል መለኪያ ውስጥ ያላቸውን መጠጥ በአንድ ትንፋሽ ጭልጥ አደረጉ። ምክንያቱም ይቺ ነገር የማርገቢያ ዘዴ መሆንዋን ሁላችንም እናውቃለና። ከዚህ ቀደም ስንቱን ብለን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷላ! እናም ከደርዘን ሰዎች መካከል ወጥታ የነበረችው አንድ መቶ እንደ አወጣጥዋ ተመልሳ መግባት ተገደደች።
በምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ ሃምሳ ሎሚ የተሸከመ ሰው ባይ ላግዝህ ከምለው ይልቅ፤ “በእጁ ከሚያንጠለጥለው በአናቱ ላይ ቢሸከመው ይቀለው ነበር”፣ ወይም “መሸከሙ ካልቀረ ለምን መቶ አያደርገውም” እያልኩ መከራከርን እመርጣለሁ እንጂ፤ “እስቲ ላግዝህ?” ምን ሲደረግ? የሚገርመው ምላሴ የወቀሳ ብራቁን፣ የትችት መድፉን፣ የመፍትሔ ሃሳቡን ያንጣጣዋል። እናም እኔ መፍትሔ ጠቋሚ ነኝ፣ እኔ የተሳሳቱትን አራሚ ነኝ። በተገኘው መድረክ ሁሉ ወግ የምጠርቅ ከሥራው ቦታ ለመገኘት ግን ያልቻልኩ የመፍትሔው አካል የመሆን አቅም ያነሰኝ ልፍስፍስ ያልኩ ፍጡር ነኝ - በቃ!! ተግተው የአቅማቸውን እንሥራ የሚሉትም ለኔ ወቀሳና ክስ መልስ ሲያዘጋጁ ጊዜው ይባክናል።
እንዲያው የሚገርመኝ አንድ ሰው ቢላ ይዞ አንገቴን መገዝገዝ ቢጀምር፤ “ቻይና እንዲህ ያለ ቢላ ባታመርት ኖሮ ስቃዬ አይበዛም ነበር” እል እንደሆን እንጂ፤ ለመንፈራገጥ እንኳ መሞከሬን እንጃ። ምክንያት መፈለግ ለምዶብኛላ። ይህ እውነት ባይሆን ወያኔ እንዲህ ባላፌዘብኝ ነበር። ታድያ ለኔ ለተሸናፊው ዲሞክራሲ፣ ነፃነትና ሀገር ስለምን ሊኖረኝ ይገባል? በማን መስዋዕትነት? በማን ትግል? በማን ደም? - በነሽብሬ? በጨቅላዎቹ? በነብርቱ? በነቴዲ ነው ወይስ በአረጋውያኑ? ሽብር ተመችቶኝ፣ ስድብ አበረታቶኝ፣ ውርደት ማዕረግ ሆኖልኝ ሳላፍር፣ ሳልሸማቀቅ፣ ሳልቆጣና በቃ! ሳልል፤ “የባሰ አታምጣ!” እያልኩ የሸክም ጫንቃዬን እያደነደንኩ የምኖር ከሆነ፣ ለእኔና እንደ እኔ ላሉቱ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ዲሞክራሲ እና ሀገር ሊኖረን እንዴት ይቻለናል?
አሁን እንዲያው ወያኔ ኢትዮጵያን ቢሸረካክታት፣ ቢቀረዳድዳት ማን ከልክሎት? ቢሻው ለቻይና ቢሸጣት፣ ለዐረብ ቢመጸውታት ወይ ለሕንድ ቢቸረችራት ከቢጤዎቼ ጋር ሰብሰብ ብዬ፤ “ዋጋው አነሰ፣ በዛ” እያልኩ ከማውራትና ማን ቢገዛ ይሻል እንደነበር ከማስረዳት እልፍ እል ይሆን? እንኳን ሀገሬን እኔን እራሴን “ታላቅ ቅናሽ!” የሚል ለጥፎብኝ ቢሸጠኝ ገዢ ፍለጋ እቁለጨለጭ እንደሁ እንጂ፤ ሌላ ማድረግ የምችል አይመስለኝም። ከአደጋ በእጅጉ እርቄ በነፃነት እየኖርኩ ነፃነት ለተጠሙ ወገኖቼ ምንም ማድረግ ከተሳነኝ ለጥፋት ፈርጄባቸዋለሁ ወይም አንድ የጎደለኝ ነገር አለ። አይመስላችሁም? ታድያ እንደ እኔ ላለ ዲሞክራሲ፣ ነፃነት ብሎም ሀገር ስለምን ይገቡኛል?
ዳኛቸው ቢያድግልኝ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )