በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ሰሞኑን በተፈጠሩ ክስተቶች ላይ (ግርማ ካሣ)
ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ሐምሌ 22 ቀን 2001 ዓ.ም.
በአንድነት ውስጥ የተነሳው ውዝግብ የአንድነትን ጥንካሬን የሚያሳይ ነው!
ሰሞኑን በአንድነት ውስጥ ተፈጠረ የተባለውን ውዝግብ በተለይም አፍቃሪ ኢህአዲግ ድረ ገጾች ሎተሪ የወጣላቸው ይመስል ሲያራግቡትና ሲያሟሙቁት ሰንብተዋል።
ይህ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የታየው ክስተት በርግጥ የተለየ ክስተት ነው። የተለየ ክስተት የሆነበትም ምክንያት ፓርቲው የተለየ ፓርቲ በመሆኑ ነው። በጥቂት ሰዎች አምባገነንነት የሚመራ እንደ ኢህአዲግ ባለ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ እንዲህ አይነቱ ክስተት ሊፈጠር አይችልም። በጥቂት ጓደኛሞች በምስጢር በሚመራ ወይንም ደግሞ አንድ ወይንም ሁለት ሰዎች ብቻ ያሉበት ፓርቲ ውስጥ እንዲህ አይነቱ ችግር አይፈጠርም።
የአንድነት ፓርቲ ጠንካራ፣ በመርኅ ላይ የተመሰረቱ ደጋፊዎች ያሉት፣ መሪዎቹን ተጠያቂ የሚያደርግ፣ ከፍተኛ የሆነ ግልጽ የሃሳብ ክርክሮች የሚደረጉበት ድርጅት ነው። በእንደዚህ አይነት ድርጅቶች አለመስማማቶች፣ ክርክሮች፣ የሃሳብ ግጭቶች ይፈጠራሉ። መሪዎችን ማመስገን እንዳለ ሁሉ መሪዎችን መውቀስና መተቸትም አለ።
በሀገራችን መሪዎቻችንን መቃወም አልተለመደም። ብዙ ጊዜ አንድ የፖለቲካ መሪን ወይ ሙሉ ለሙሉ እንቃወመዋለን ወይንም ሙሉ ለሙሉ እንደግፈዋለን። አንድን የፖለቲካ መሪ ከተቃወምን ታማኝ ያልሆንን ተደርጎ ከፓርቲው እንድንወጣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ እንገደዳለን። ይህ መሪዎችን በጭፍን የመከተል፣ ስንቃወማቸው ደግሞ በጭፍን የመጥላት ባህል መስተካከል ያለበት ባህል ይመስለኛል።
በተለይም የአንድነት ፓርቲ ይህንን በኢትዮጵያ ያልተለመደ፣ መሪዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ አዲስ የሠለጠነን ፖለቲካ ለመዘርጋት የተነሳ ድርጅት እንደመሆኑ፤ አባላቱ ከአንድነት ፓርቲ ውስጥ ሳይወጡ መሪዎችን በድፍረት የመጠየቅና የመውቀሱን ሁኔታ አሁን እንዳየነው ሁሉ ወደፊትም የምናየው እየተደጋገመ የሚመጣ ነገር ነው። ስለሆነም ልንደናገጥና ልንፈራ አይገባም።
የአንድነት ፓርቲ አንዱ መርኅ ተጠያቂነት ነው። መሪዎች ለሚናገሩትም ሆነ ለሚያደርጉት ሁሉ መጠየቅ ይኖርባቸዋል። የድርጅቱ አባላት መሪዎቻቸውን ሲቃወሙ ሊበረታቱና ሊደገፉም ይገባል። ተቃውሞ ድርጅትን ያጠነክራል። ተቃውሞ መሪዎች ውጤት እንዲያሳዩ ይገፋፋል። ተቃውሞ በአንድ ዲሞክራሲያዊ ነኝ በሚል ፓርቲ ውስጥ ጤናማና ጠቃሚ ነው። አንድ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ነኝ ብሎ መሪዎቹ ተቃውሞን የሚፈሩ ከሆነ፣ በርግጥ ያ ፓርቲ ችግር አለበት ማለት ይቻላል።
በዚህ አንጻር እንግዲህ በአንድነት የሥራ አስፈጻሚው አካል ላይ የቀረቡት ወቀሳዎች፣ ወቀሳዎቹ ጠቃሚ ይሁኑም አይሁኑም፣ በመርኅ ደረጃ ሊበረታቱ የሚገቡ ናችው እላለሁ። በመሪዎቻችን ላይ ተቃውሞ ማሰማት ካልቻልንማ አንደኛውን ለምን ኢህአዲግን አንቀላቀልም?
እስቲ አስቡት የትኞቹ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በሀገር ቤት ያሉ ድርጅቶች ናቸው መሪዎቻቸውን ፊት ለፊት የሚቃወሙት? ታዲያ ይህ በአንድነት ውስጥ የሚታየው ክርክር የአንድነት ፓርቲ ጥንካሬን የሚያሳይ አይደለምን?
የድርጅቱ ሕግ መከበር አለበት
አንድ ድርጅት የራሱ አሠራርና ደንብ አለው። በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ከጠቅላላ ጉባዔው ቀጥሎ የበላይ አካል የሆነው የላዕላይ ምክር ቤቱ ነው። በድርጅቱ ውስጥ ባሉ መድረኮችም ሆነ በጋዜጦች ላይ አባላት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ። አንዳንዴ በሙሉ ድምፅ፣ አንዳንዴ ደግሞ የተወሰኑት እየተቃወሙም በድምፅ ብላጫ ውሳኔዎች ይወሰናሉ። ይህ ሕግና ሥርዓቱን የጠበቀና ዲሞክራሲያዊ የሆነ አሠራር ነው።
አባላት የድርጅቱን አመራሮች መቃወም ሙሉ መብታቸው የተረጋገጠ እንደሆነውም ሁሉ ከመብት ጋር የሚመጣ ግዴታም አለ። አባላቱ፣ ሃሳባቸው በድምፅ ብልጫ ተቀባይነት ካላገኘ፣ የአብላጫውን ድምፅ ማክበር ይኖርባቸዋል። አለበለዚያም ዲሞክራሲን ሳይሆን አናርኪንና ዘመነ መሣፍንትን ነው የምንዘረጋው ማለት ነው።
ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማሪያምና አንዳንድ የአንድነት ፓርቲ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት የፓርቲውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴን በእጅጉ የሚወቅስ ሁለት ወረቀቶችን በቅርቡ በትነዋል። ከበተኑት ወረቀት እንደተረዳሁት ላዕላይ ምክር ቤቱ አንድ ቀን በተሰበሰበ ጊዜ፣ በአንድ አጀንዳ ላይ ውይይት እንዲደረግ ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ይህ ውይይት እንዲደረግበት የተፈለገው አጀንዳ፣ የሥራ አስፈጻሚውን የሥራ ሂደት ለማሻሻል ከሁለት ሦስት ወራት በፊት በምክር ቤቱ ስብሰባ በተወሰኑ ሃያ ሁለት ነጥቦች ላይ፣ የሥራ አስፈጻሚው ምን እያደረገ እንዳለ የሚጠይቅ አጀንዳ ነበር።
የሥራ አስፈጻሚው የቀረበውን አጀንዳ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍና ውይይቱ በመድረክ ዙሪያ እንዲደረግ ሃሳብ አቀረበ። የመድረክ ጉዳይ ሀገራዊ ትኩረትን የሳበና የሌሎች ድርጅቶችን የሚነካ በመሆኑና ለወራት ሲደከምበት የነበረው የመድረኩ ማኒፊስቶ በመጠናቀቁ ይመስለኛል፣ የላዕላይ ምክር ቤቱ በቅድሚያ በመድረክ ዙሪያ እንዲወያይበት የሥራ አስፈጻሚ የጠየቀው።
“የትኛው አጀንዳ ይቅደም?” በሚል ክርክሮች ተደረጉ። አብዛኛው የላዕላይ ምክር ቤት አባል በመድረክ ዙሪያ የዚያን ቀን መወያየትን መረጠ።
እነ ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማሪያም “… ያለፈው ቃለ-ጉባዔ ከተነበበ በኋላ በየትም ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅና ሥርዓትን ሁሉ በሚጥስ አሠራር ሎሌዎቻቸውን አሰልፈው በድምፅ ብልጫ ቃለ-ጉባዔው ውይይት ተደርጎበት እንዳይፀድቅ አድርገው የስብሰባ ደንብንና ሥርዓትን በመሻር ወደሚያንገበግባቸው የመድረክ ጉዳያቸው ተንደርድረው ገቡ። …” በማለት ነበር ቅሬታቸውን ያቀረቡት።
እዚህ ላይ ከላይ እንደጠቀስኩት የነፕሮፌሠር መስፍን ትችት በመርኅ ደረጃ የሚደገፍ ቢሆንም የትችታቸው ይዘት ላይ ግን ሦስት ችግሮችን አያለሁ።
- እነ ፕሮፌሠር መስፍን በላዕላይ ምክር ቤት ውስጥ በድምፅ ብልጫ እንደተረቱ አልካዱም። ለዚህም ነው “በድምፅ ብልጫ” ብለው የጻፉት። በድምፅ ብልጫ የተወሰነን ውሳኔ ከመቀበል ውጭ ሌላ ምን ማድረግ እንደሚቻል ቢነግሩንና ሌላ አማራጮች ካላቸው ቢጠቁሙን ጥሩ ነበር። ተከራክሮ፣ በድምፅ ብልጫ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ውሳኔዎች ማሳለፉ ከሥርዓት ውጭ ከተባለ፤ የቱ ነው ታዲያ ሥርዓትን የተከተለ አካሄድ የሚባለው?
- የላዕላይ ምክር ቤት አባላት፣ ከየክልሉ የተወጣጡ ኢትዮጵያውያን ያሉበት የጠቅላላ ጉባዔ የመረጣቸው ዜጎች ናቸው። የላዕላይ ምክር ቤቱ ከጠቅላላ ጉባዔው ቀጥሎ የድርጅቱ የበላይ አካል እንደመሆኑ፣ የላዕላይ ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ የሚወስነው ውሳኔ የፓርቲው የመጨረሻ ውሳኔ ነው። ታዲያ የምክር ቤቱ አባላት እኛ እንደምንፈልገው ድምፃቸውን አለመስጠታቸው “ሎሌዎች” ተብለው ሊያስጠራቸው ይገባልን? የላዕላይ ምክር ቤትን እንደ መሳደብ፣ የሕግ የበላይነትን እንደ መናቅ አድርገው ሰዎች ቢወስዱት ተሳሳቱ ማለት ይቻላልን?
- መድረክ የተለያዩ ድርጅቶችን ለማቀራረብ እየሞከረ ያለ አካል ነው። ከዚህ በፊት በተለያዩ መንገድ ይሄዱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ተቀምጠው፣ በጋራ አንዲት ኢትዮጵያን ለመገንባት እያደረጉት ያለ ጠቃሚ ምክክር ነው። አሁን ያለው የኢህአዲግ አገዛዝ ሀገሪቷን በዘር እየከፋፈለ ባለበት ሁኔታ፣ ከዘር ፖለቲካ አልፎ በመሄድ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር አብሮ ለመሥራታና ለመቀራረብ የሚደረግ ማናቸውም ጥረት ሊደነቅና ሊደገፍ የሚገባው ነው እላለሁ።
የተጎዳነው በዘር በመከፋፈላችን፣ አንዳችን ሌላውን በጎሪጥ ማየታችን፣ ከሚያቀራርበንና ከሚያገናኘን ይልቅ የሚለያየንንና የሚያጣላንን መፈለጋችን፣ አንዳንች በአንዳችን ላይ የጥራጣሬን ክፉ መንፈሥ ማሳደራችን … ነው። በአሁን ጊዜ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ጨለምተኝነትን የሚያስወግድና ልጆችዋን የሚያቀራርብ በጎ እንቅስቃሴ ነው።
ታዲያ የአንድነት ፓርቲ በመድረክ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ለማቀራረብ የሚያደርገውን ጠቃሚ ሂደት “ወደ ሚያንገበግባቸው የመድረክ ጉዳያቸው” በማላት ማጥላላት ተገቢ ነውን? ከመድረክ ጋር የአንድነት ፓርቲ መሥራት የሚችልበትን ሁኔታ እንዲፈጠር ለሥራ አስፈጻሚው ውክልና የሰጠው የላዕላይ ምክር ቤቱ አይደለምን? በመድረክ ማኒፌስቶ ውስጥ መሻሻል ያለባቸው እንዲሻሻሉ፣ በጎሣ ላይ ብቻ ሳይሆን ጂኦግራፊን፣ ኢኮኖሚን፣ የህዝብ ፍላጎትንና ሌሎች ጠቃሚ መስፈርቶችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ፌደራል አወቃቀርን የመሳሰሉትን ቁልፍ የአንድነት እሴቶችን መድረኩ እንዲቀበል ማሳመንና መገፋፋት፣ ስህተት ተሠራ ከተባለ ደግሞ ለማረም መጣር ይገባል እንጂ ሀገርን ሊጠቅም የሚችልን አካል የኛ ጉዳይ እንዳልሆነ በመቁጠር “ጉዳያቸው” ይባላልን?
ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማሪያም ሃሳባቸውን ለመግለጽ የማይፈሩ፣ መንግሥቱ ኃይለማሪያምን ከሥልጣን ውረድ ያሉ ቆራጥ የዲሞክራሲ አባት ናቸው። ነገር ግን ሰው ናቸውና እርሳቸውም የሚሳሳቱበት ጊዜ ይኖራል።
ከላይ እንደጠቀስኩት የሥራ አስፈጻሚውን መውቀሳቸውና መተቸታቸው በመርኅ ደረጃ የሚደገፍ ቢሆንም፤ ሰሞኑን በበተኑት ሚዛን የማይደፋ ወረቀት ግን እርሳቸውና አብረዋቸው ያሉት ወገኖች መሳሳታቸውን በአክብሮት ለመግለጽ እወዳለሁ። ማንም የተበተኑትን ወረቀቶች ያነበበ ሰው፣ ወረቀቶቹ ፀሐፊዎቹን እራሳቸውን የሚያስገምቱ እንደሆነ ይረዳል ብዬ አስባለሁ።
ከስህተቶቻችን ተምረን፣ በግለሰቦች ላይ “እንዲህ አደረገ፣ እንዲህ አደረገች” የሚሉ ተራ አሉባልታዎችን አቁመን፣ መስተካከል አለባቸው ለምንላቸው አጀንዳዎች በሠለጠነና የድርጅቱን ሕገ ደንብ በጠበቀ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀት ያለብን ይመስለኛል። ተቃውሟችን አስፈላጊ ነውና እንቀጥልበት። ነገር ግን የድርጅቱን ሕግና ሥርዓት በማክበርና በፍቅር እናድርገው። የሰው ስም እየጠራን መሳደባችንን እናቁምና የምንጠቀማቸውን ቃላቶች እየመረጥን በመከባበር እንወቃቀስ።
አጭር መልዕክት ለአንድነት አመራር አባላት
ይህን ብዬ ለአንድነት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አጭር መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የሚደግፈው ፓርቲ አመራር አባላት ናችሁ። ሰሞኑን አንዳንዶቻችሁ በግለሰብ ደረጃ ብዙ ውርዥብኝ እንደደረሰባችሁ አንብቤአለሁ። ልታዝኑና ልትጎዱ እንደምትችሉም ይገባኛል።
የዚያኑ ያህል ደግሞ ብዙ ስህተቶች እንደሠራችሁና የቀረበቡባችሁ አንዳንድ ወቀሳዎችም መሰረት ያላቸው እንደሆኑ እናንተም የምታጡት አይመስለኝም።
ስለዚህ የቀረቡትን ቅሬታዎች በቅንነትና በትህትና ተቀብላችሁ፣ አሁን የሚደግፏችሁ የበለጠ እንዲደግፏችሁ፣ የሚቃወሟችሁ ደግሞ ከመቃወም ወደ ድጋፍ ሰጪነት እንዲመለሱ የማድረግ ተጨባጭ ሥራ መሥራት አለባችሁ እላለሁ። መሪ ማለት የሚቃወሙትን የሚያስወግድ ሳይሆን የሚቃወሙትን አሳምኖ ወደ ትግሉ ጎራ መልሶ የሚያመጣ ነው። መሪ ማለት “እኔ ለምን ተነካሁ?!” ብሎ በእልህ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን ረጋ ብሎ የሀገርንና የህዝብን ጥቅም የሚያስጠብቅ ማለት ነው። እንግዲህ ይህን አይነት በሳል አመራር አሳይታችሁን እንደምታኮሩን ትልቅ ተስፋ አለኝ።
ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ሐምሌ 22 ቀን 2001 ዓ.ም.



