የኦርቶዶክስንና አማራን አከርካሪ የመምታት የመጨረሻው ምዕራፍ

“ኦርቶዶክስም አሁን ለምትገኝበት የነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ አሳሳቢ ደረጃ የደረሰችው የራሷን የመታነቂያ ገመድ ራሷው ፈትላ ነው”
ምሕረት ዘገዬ
1. የጠ/ሚንስትሩ የመደመር ልቦለድ መጽሐፍ እየተመረቀ ባለበት በአሁኑ ቅጽበት በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ምን እየተደረገ ነው?
- መዝገብ የያዙና በሥውር የፖሊስ ኃይል ጥበቃ የሚደረግላቸው የወለጋና አርሲ ቄሮዎች በጀሞና በሌሎች የአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ ይዞታዎች ሥር የሚገኙ መሬቶችን እየተከፋፈሉ ነው። ካለበቂ ጥበቃ የሚገኙ ኮንዶሚኒየሞችን በር በመስበርም እየተሻሙ ነው። እነሱን ሃይ የሚል ግሕግ የለም። …
- የሌሎች ዜጎች በተለይም የአማሮች ቀደምት ይዞታዎች በሻማና በኩራዝ እየታሰሱ እንዲፈርሱና ሰዎቹ ወደው ባልተፈጠሩበት ነገዳቸው ምክንያት ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ከቦታቸውና ከአገራቸው እንዲፈናቀሉ እንዲሰደዱም እየተደረገ ነው - በአዲስ አበባ ዙሪያ ሁሉ። …
- አማሮች ከያዟቸው የፌዴራልና የክልል ሥልጣንና ኃላፊነቶች እየተነሱ የገዢው ኃይል ታማኝ የሆኑ ሆዳሞችና ምሥጢረኞች እንዲሁም የአማራን መጠሪያ ስሞችና የአማራነትን ዘውጋዊ የውሸት ማንነት በዳግም ጥምቀት ያገኙ አሰለጦች እየተተኩ ነው። አማራ በቋንቋውም ሆነ በባህሉ ለማንምና ለሁሉም እኩል ክፍት በመሆኑ ይህ ሁኔታው ክፉኛ እያስጠቃው ይገኛል። በተቅጠፈጠፈ አፉና በአስመሳይ ኢትዮጵያዊ የሥነ ልቦና ቀመሩ ሠርጎ የሚገባ ዘረኛ ሁላ፤ አማራን በቀላሉ ለጥቃት ይዳርገዋልና ለዚህ ዐይነቱ ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ካልተገኘ ችግራችን እንደጠነነ መቀጠሉ ነው። ለዚህም አንዱ ምሣሌ ከአማራ ሕዝብና አዴፓ አባላት ጋር ውኃና ዘይት የሆነው የጠሚው ልዑክ - ስሙም ጠፋኝ - የአማራው ክልል አዲስ ፕሬዝዳንት ነው። ይህ ሰው መንፈስ ቢጤ ሳይሆን አይቀርም። የት ነው ያለው ግን? ምን እየሠራስ ነው? ዋና ተልእኮው ለጠሚው ነው ወይንስ ለአማራ? የዘር ሐረጉ የሆነውን ይሁን ግዴለም - ግን ለክልሉ ምን እየፈየደ ነው? በፍንጭ ሰጭ ቃላት ጉግል አድርጌ ስሙን አሁን አገኘሁት - እውነቴን ነው - ተመስገን ጥሩነህ። ወይ መሪና ተመሪ! ተለያየን።