የቀን እንጀራ (አሥራደው)
የቀን እንጀራ
አሥራደው - ከፈረንሣይ
በጭንቅ በመከራ ተዘርቶ፤
በስንት ውጣ ውረድ ተመርቶ፤
ውሃ በቋጠረ መዳፍ ተፈጭቶ፤
በወጉ ያልተፈጨ የተከካ፤
በ’ንባ ታሽቶ የተቦካ፤
ኩፍ ያለ በደም አብሲት፤
ስጋ የሆነው መጨቅጨቂት፤
ባጥንት ማገዶ የተጋገረ፤
መከራ በዝቶበት ያረረ፤
የቀን እንጀራ ለገሰኝ፤
እንካ ብሎ ሰጠኝ፤
የማታውን ነስቶኝ።
ቸገረኝ እንዳልተወው፤
አረረብኝ እንዳልበላው፤
የማታውን እንጀራ ስጠኝ፤ ምነው አምላኬ ምነው?!
እንዴት አድርጌ ልብላው?!
መራቤን እያወ’ከው፤
መራቤን እያወ’ከው።
አሥራደው - ከፈረንሣይ
ሐምሌ 3 ቀን @002 ዓ.ም. (July 10/2010)



