ክፍል አንድ (ማስተዋል አዳነ)

ጊዜው በአገራችን ክረምት ሊገባ ጥቂት ጊዜያት የቀሩበት ወቅት ነበር፤ የአሁኑ ክረምት። ወደአገር ቤት ለመሄድ የወሰንኩት ቤተሰብ፣ ጓደኛና ዘመድ ለመጠየቅና በአጠቃላይ የአገራችን የኑሮ ሁኔታ በጣም ስለናፈቀኝ፤ ይህንን ደግሞ ከተወሰነ አመት የትምህርት ቆይታ በኋላ ተመልሼ ማየት አለብኝ የሚል ውሳኔ ላይ ስለደረስኩ ነበር። ተማሪ ስለሆንኩና የእረፍት ጊዜዬንም በዚሁ አጋጣሚውን መጠቀሙ ጥሩ አማራጭ ስለሆነ ከፍራንክፈርት ወደአዲስ አበባ ትኬት ቆርጬ ግንቦት መጨረሻ ላይ ወደአገር ቤት ለመሄድ ተሰናዳሁ። የበረራ ቀን ሰኞ ነበር።

 

የአውሮፕላኑ አስተናጋጆች በጥሩ ሁኔታ አስተናግደውን ወደውስጥ ገባን። እንደጀርመን ሰአት አቆጣጠር ከቀኑ 11፡30 አካባቢ ይሆናል። ሉፍታንዛ በጣም የሚደላ አየር መንገድ ነው። ከመሬት ውስጥ ተተኩሶ ወደሰማይ ቀርቦ በጉም ውስጥ ይከንፍ ጀመር። አውሮፓን አቋርጠን እስከምንወጣ ድረስ በጉም የተዥጎረጎረው አረንጓዴ ለምለም መልክአምድር አልፎ አልፎ በደመና መካከል በአውሮፕላኑ መስኮት ይታያል። አንዳንዴም አነስተኛ ሃይቆች በየአካባቢው ይታያሉ። ምናልባትም ሰው ሰራሽ ሃይቆች ይሆኑ? አዎ ይመስለኛል። አገራችንስ መቼ ይሆን እንዲህ አይነት ሰው ሰራሽ ሃይቆችን ገንብታ ወደጎረቤት አገሮች ለም አፈር እየጠረገ የሚወስደውን ውሃ ገድባ ለረሷ ፍጆታ በማዋል የእለት ጉርሷን የምታሟላው? እያልኩ ራሴን መጠየቅ ያዝኩ።

 

በጉዞ ወቅትም ማንም ኢትዮጵያዊ በቅንነት የሚያስበው ሃሳብ በአእምሮዬ ውስጥ ይመላለሳል፤ ሁሉም ተባብሮ ቢሰራ፣ ውጭ ያለው ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊ ገንዘቡን፣ እውቀቱንና ልምዱን ይዞ በመምጣት እንደየእውቀቱና ችሎታው ቢሰማራና አገር ውስጥ ካለው ሃይል ጋር ቢቀናጅ ከድህነት የማንወጣበት ምንም ምክንያት የለም በማለት በእርግጠኝነት አሰብኩ። ግን ግን እኮ ይህም መንግስት በተደጋጋሚ ጥሪ እያደረገ አይደል? ጥረት ይሏል ይህ ነው። ይሁን እንጂ ለምንስ እስካሁን ሳይሳካ ቀረ? ውድ የሆነው መሬታችንስ ለምን ለውጭ አገር ባለሃብቶች ወይም የመንግስት ባለስልጣናት ሽርካዎች በዘፈቀደ እንደቅርጫ ስጋ ይከፋፈላል እየተባለ ይወራል? የችግሩን ምንጭስ ምን ይሆን እያልኩ እያሰላሰልኩ የተዘበራረቀ ሃሳብ አሁንም አሁንም በአእምሮዬ ይጉላላል። በዋናነት ግን መንግስት ሁኔታዎችን ሳያስተካክል የተናጠል እናልማ ጥሪ ማቅረቡ ተቀባይነት የሌለው ፍሬ አልባ ሃሳብ እንደሆነ ገባኝ። የሚገርመው እኮ ነጻነት በሌለበት አገር፤ መንግስት ከህግ አግባብ ውጪ እንደፈለገ እርምጃ በሚወስድበት አገር ዜጎች ተሸማቀው በሚኖሩበት አገር፤ ለኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ “አገር እናልማ” ጥሪ ምንድን ነው? ምንድነው የሚለማውስ? መንገድና ህንጻ ብቻ ነው? ተቃዋሚዎችን በሆነ ባልሆነ ሰበብ እየፈጠረ አንዳንዶችን የፈንጅ ወረዳ የረገጡ፣ ሌሎችን ደግሞ የልማት ጸር፣ የቀሩትን ደግሞ የጥፋት ሃይሎች የሚል ታርጋ በመለጠፍ ራስ ራሳቸውን በመምታት ከትግል ሜዳ ዘወር የሚያደርግ መንግስት እንዴት ነው ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት፣ ሰላምና ብልጽግና አስፈላጊ ምሰሶ የሆኑትን እሴቶችን ሁሉ በመተው በመንገድና በህንጻ ልማት ላይ ብቻ እናተኩር በማለት ለዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጥሪ እያስተላለፈ ያለው? ገንዘብና እድገት መንግስት ከዜጎች ፈልጎ፤ ግን ደግሞ ስለነጻነትና ዲሞክራሲ ጥያቄ አታንሱ በማለት ነፍጎ ኢትዮጵያዊያን በሁሉም አቅጣጫ እንዳይሳተፉ መከልከል ምን ማለት ነው? ምን አይነት እድገትስ ነው የሚታሰበው? እድገት ማለት ሁለንተናዊ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እሴቶች በአንድ ላይ ተጣምረው የሚመጣ ለውጥ እንጂ የአንድ የኢኮኖሚ እድገት ብቻ አለመሆኑን ብዙ ምሁራን ስለተነተኑት እዚህ ማብራራት አስፈላጊ አይመስለኝም። የገዢው ፓርቲ አባላትና ተቀጽላዎቹ እንደፈለጉ የአገሪቱን ገንዘብና ሃብት በሚዘርፉበት አገር፣ ህግና ስርአት የሆኑት በራሱ በህወሃት ኢህአዴግ ግንባር የተጻፉው ህገመንግስትና በተዋረድ ያሉ የአገሪቱ ህጎች ተሸርሽረው የገዢው ፓርቲ አባላት ብቻ ህግ በሆኑበት አገር፣ መንግስት አላማውን የሚያስፈጽሙለት ካድሬዎች በየቤተክርስቲያናቱና በየመስጊዱ እንኳን ሳይቀር ባሰማራበት አገር ማን ማንን አምኖ ውጭ አገር ስንት ጥሮ ግሮ ያፈራውን ገንዘብ ለቀን ጅብ ይሰጣል? በብሄራዊ ባንክ ሳይቀር ባሌስትራ ወርቅ አስመስለው የሚያስቀምጡት ከህወሃት ኢህአዴግ የተጠጉ ባለጊዜዎች አይደሉም እንዴ? በአረመኔነቱ ስሙ በተደጋጋሚ የሚነሳው ደርግስ እንዲህ አይነት ድርጊት ፈጽሞ ይሆን? ይህንን የመሳሰሉ ሃሳቦች በአዕምሮዬ ይጉላላሉ።

 

አውሮፕላኑም በረራውን ቀጥሏል፤ ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጦ ወደ አፍሪካ አህጉር እየገባ ነው፤። እኛ ያልታደልን ሆነን ነው እንጂ አገራችን ኢትዮጵያ ከተወሰኑ የአፍሪካ አገሮች የተሻለ አየር ንብረት ያላት አገር ትመሰለኛለች። ይህንንም በደንብ የተገነዘብኩት የግብጽንና የሱዳንን የአየር ክልል ውስጥ ሰንገባ ነው። በተለይም በግብጽ ደረቅ ምድረበዳ መሬት የሚበዛ መሆኑን በአየር ላይ ሆኖ ያየ ማንም ሰው በደንብ ይረዳል። በእውነት ይህንን አገር ይዘው ከእኛ በእጥፍ በተሻለ የኑሮ ደረጃ ያሉ ለመሆናቸው እጅግ በጣም ይገርማል። ሆኖም አውሮፕላኑ ወደአዲስአበባ ጉዞውን ባቀና ቁጥር አልፎ አልፎ የተፈጥሮ ይሁን ሰው ሰራሽ ደኖች አለፍ አለፍ ብለው መታየታቸው አልቀረም። ከፊት ለፊቴ ያለውን የአውሮፕላኑ ርቀት አመልካች ቴሌቪዥን ስክሪን ሳይ ሱዳንን አልፈን እንዲያውም ወደአገራችን ድንበር እየተጠጋን መሆናችንን አወቅሁ። ለእርሻ እጅግ ምቹ የሆነ ሰፋፊ መሬት ተንጣሎ ይታያል። የቴሌቪዥን ስከሪኑን ቀና ብዬ አየሁ። ስክሪኑ ኢትዮጵያ ውስጥ እየገባን መሆኑን ያመላክታል። በመሆኑ ይህንን ለም የእርሻ መሬት የኢትዮጵያ መንግስት ለሱዳን በስምምነታቸው መሰረት ቆርሶ የሰጠው ገጸበረከት መሆን አለበት ብዬ አሰብኩ። መቼስ ይህ መንግስት በገዛ ዜጎቹ ላይ ምን ያክል አረመኔያዊ ተግባር የሚፈጽም መሆኑን ግፉን የቀመሰው ኢትዮጵያዊ ያውቀዋል። በተለያየ ጊዜ በህወሃት ኢህአዴግ ድጋፍ በሱዳን የጸጥታ ሃይሎች ተወስደው የተገረፉና ደብዛቸው የጠፉ ሰዎችን ቤት ይቁጠራቸው። ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ባለመሰልቸት ኢትዮጵያ አንድነቷና ዳር ድንበሯ ተከብሮ ለዘላለም እንድትኖር ብርቱ ጥረት አድርገዋል፤ አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ። እኛስ ይህንን የህወሃት ኢህአዴግ መሬት ቆርሶ የመስጠት ሴራ በዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያን የተቀናጀ የማጋለጥ ስራ አወቅነው እንጂ ማን ይነግረን ነበር? ምስጋና ለአሜሪካ፣ ለጀርመንና ለተቃዋሚ ሬዲዮ ጣቢያዎችና ድህረገጾች! የድንበሩን መቆረስ ጉዳይ እነሱ አይደሉም እንዴ በአለም ዙሪያ ለሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ቃለመጠይቅ በማድረግና የዜና መጽሄት በማዘጋጀት ያሰራጩት? ይህ ለም መሬት ለሱዳን መሰጠት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፎች በማቀናበርና ጋዜጣዊ መግለጫዎች በመስጠት በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ የከፈለውን መስዋትነት ዜጎችን እጅግ በጣም የሚያኮራ ድርጊት መሆኑን እነአቶ መለስም ቢሆኑ የሚክዱ አይመስለኝም። ታዲያ እንዴት ነው ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያንን በልማት ብቻ ተሳታፊ ሁኑ እየተባለ ያለው? እንኳንስ አገር ቤት ገብቶ በውጭ አገርም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ ነው፤ ስለኢትዮጵያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያገባዋል።

*******************************************************************

በአገር ቤት ቆይታዬ በተለያየዩ ቦታዎች ተዘዋውሬያለሁ፤ ናዝሬት፣ አዋሳ፣ ጂማ፣ ደብረማርቆስና ባህርዳር የመሳሰሉትን ከተሞች ለመጎብኘት ችያለሁ። በዚህ የጉብኝት ወቅት ግን በአጋጣሚ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር በአውቶቡስ ውስጥ፣ ሻይ ቤት፣ ወይም በአጋጣሚ ዘመድ ጓደኛ ቤት ሁሉንም ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የዳሰሱ ወሬዎች ለማውራት ችያለሁ። ስለህዝቡ የኑሮ ሁኔታ፣ ተመዘገበ ሰለሚባለው የኢኮኖሚ እድገት፣ ስለሚፈጸመው አድሎና ዘረኝነት፣ ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች የወደፊት እጣ ፋንታና በአጠቃላይ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ በሰፊው አውርተናል። ለማውራት እድል የገጠሙኝ አብዛኞቹ ሰዎች ፍርሃት ይታይባቸዋል። ስለመንግስት የሚወራ ማንኛውም ጉዳይ ፖለቲካ በመሆኑ “የፈንጅ ወረዳ” ለመግባት ወይም “ቀይ መስመር ለመርገጥ” ጊዜ ይወስድባቸዋል። ለአንዳንዶቹ ፖለቲካ ማውራት ነውር (taboo) ነው። ለሌሎቹ ደግሞ ስለመንግስት ማውራት ለአደጋ ይዳርጋል። አንዳንዶቹ የእኔን ማንነት በመጀመሪያ ማወቅ ይፈልጋሉ ምክንያቱም በየሰፈሩ የበግ ለምድ ለብሰው ለቁጥር የሚታክቱ የህወሃት ኢህአዴግ ሰላዮች ስለተሰማሩና እኔም ከእነሱ ውስጥ አንዱ ልሆን እንደምችል በመገመታቸው ነበር። እንዲያውም ሰዎቹ የሚፈሩት ከዚያ ባለፈ የሚመጣውን አደጋ ነው፣ ሁሉም እንደሚሉት ከሆነ በየትኛውም ሰአት ሊታሰሩ ሊገረፉ ወይም በአንዱ ማጎሪያ ደብዛቸውን ሊጠፏቸው ስለሚችል ከፖለቲካ ውይይት ራሳቸውን መቆጠብን መርጠዋል።

 

ጅማን በስሙ ብቻ እንጂ አገሩን አላውቀውም ነበር። ወደዚያው ባቀናሁ ሰሞን በጅማ ዩንቨርስቲ የሚመረቅ አንድ ዘመድ ስለነበረኝና አካባቢውንም አይቼ ሰለማላውቅ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ በማለት ጉዞዬን ለመጀመር ተሰናዳሁ። ከአዲስ አበባ አውቶቡስ መናኸሪያ የጅማ አውቶብሶች ትኬት ቆርጠው ስለጨረሱ በአጋሮ አውቶቡስ የመጨረሻ መቀመጫ በማግኘቴ ትኬት ቆረጥኩ። መቀመጫ ያገኘሁት ከመጨረሻ ስድስት ከሚይዘው ወንበር ላይ ነበር። በቀኝ በኩል ሁለት የቆዳ ጃኬት የለበሱ ወንዶች በአንድ ጎን (በኋላ እንደነገሩኝ የአንድ መስሪያ ቤት የስራ ባልደርቦች ናቸው) በሌላ ጎን በግራ በኩል ደግሞ አጋሮ ድረስ የምትሄድ አንድ ወጣትና ሁለት አዛውንት ሴቶች ሆነን ቁጭ አልን። ሆኖም ከሁዋላ 6 የሚይዘው መቀመጫ አምስቱ ስለያዙት በረዳቱ “ከኋላ 6” ትዕዛዝ ከተንሸራሸሩ በሁዋላ ለእኔ ያለመደገፊያ ጥቂት ቦታ ለቀቁልኝ።

 

አውቶቡሱ መጓዝ እንደጀመረ በኦሮምኛ ብቻ ያወሩ ከነበሩት ወንዶች አንዱ “ይህ ላፕቶፕ ነው እንዴ?” ብሎ በአማርኛ ጠየቀኝ ማስቀመጫ ቦታ በማጣት በእጄ የያዝኩትን ላፕቶፕ እያየ።

“አዎ” የሚል መልስ መለስኩለት።

“ምን እኮ….ማንም ሰው ሊኖረው የሚገባው ግን በጣም ውድ የሆነ አቃ ነው።” በማለት ጨዋታውን ቀጠለ።

 

ከጎኑ የተቀመጠው ሰው ግን ምንም ሳይናገር ለረጅም ጊዜ የምናወራውን ያዳምጥ ነበር። በጨዋታ መካከል ላፕቶፑን ለምን አገልግሎት እንደገዛሁት ወይም የትኛው መስሪያቤት እንደሰጠኝ ጠየቀኝ። ተማሪ እንደሆንኩና አውሮፓ አገር ለጊዜው እንደምኖር ስነግረው መንግስት ስላከናወነው ልማት ምን አስተያየት እንዳለኝ በተደጋጋሚ ይጠይቀኝ ጀመር። በመጀመሪያ ያነሳው በመንገድ ግንባታ ምን ያክል ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሆንን ነበር። በዝምታ ያዳምጠን የነበረው ሰው ባሰበት። እኔም የተሰሩትን ነገሮች አመስግኜ ያልተሰሩት ብዙ ነገሮች እንዳሉ ስነግራቸው ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን (እኔንም ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመደመር) ሁሉ ለአገራችን ልማትና ብልጽግናን መመኘት ሳይሆን ውድቀቷንና ድህነቷን ሁሌ የሚመኙ መሆናቸውን ሳያመነቱ ሁለቱም እየተቀባበሉ ተረኩልኝ። እንዲያውም በአገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ነኝ ባይ ፓርቲዎች ከውጭ አገር ካሉት ኢትዮጵያውያን ጋር ተመሳጥረው የአገሪቷን ሃብት ለምዕራብያዊን አገሮች በተለይም ለአሜሪካ ለመሸጥ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ሆኖም ግን በኢህአዴግ ፓርቲና በአቶ መለስ ያላሰለሰ ቆራጥ አመራር አገሪቷ ከአደጋ እንደዳነች፤ ለዚህም ምሳሌ ሊሆን የሚችለው 1997 ምርጫ ማግስት ተሞክሮ የከሸፈው ውስጥ ውስጡን በምዕራባውያን አገሮችና በምርጫ ታዛቢዎች ጭምር ሳይቀር ሲደገፍ የነበረው የቀለም አብዮት ነው በማለት ጉዳዩን ለእኔ ለማስረዳት ሞከሩ። ስለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአመራር ችሎታ ደግሞ ከየትኛውም የአለም መሪ ሁሉ የሚሻሉ አስተዋይና ብልህ መሪ እንደሆኑ ያለምንም ሃፍረት ማውራት ጀመሩ። እንዲያውም “ነብይ በአገሩ አይከበርም” በማለት ይሁዳዊያን እየሱስ ክርስቶስን እንዴት ያጥላሉ እንደነበርና ይህም ትንቢት በእኛ አገር ታሪክ ውስጥ መተኪያ በሌለው መሪ በአቶ መለስ ዜናዊ ላይ እየደረሰ እንደሆነ እኔም እነሱም በማናውቀው የፖለቲካ ይሁን የሃይማኖት ትንታኔ ሊጠምቁኝ ሞከሩ። እንዲያውም እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ የሚያስብ ቆራጥ መሪ (ቆራጥ የምትለዋ ቃል ከጓድ መንግስቱ የተወሰደች መሰለኝ) በአገሪቱም ይሁን በውጭ አገር እንደሌለ፤ አገራችን ኢትዮጵያም ካለእሳቸው ውጭ ሌላ አርቆ አሳቢ መሪ በታሪኳ አግኝታ እንደማታውቅ ወደፊትም እንዲህ ራዕይ ያለው መሪ እንደማታገኝ በዝርዝር ለማሰረዳት ሞከሩ። የኢህአዴግ አባላት ከልባቸው ይሁን ከአንገት በላይ አቶ መለስን ምን ያክል እንደሚያመልኩ በእርግጠኝነት የተረዳሁት ያኔ ከእነሱ ጋር ካደረግኩት ውይይት በኋላ ነበር።

 

ለተወሰነ ጊዜ ካዳመጥኳቸው በኋላ ሌላ ጥያቄ አስከተልኩ። “ለመሆኑ እዚህ አገር የፖለቲካ ነጻነት አለ ወይ?” ብዬ ስጠይቅ መልሳቸው ሁለቱም አንድ አይነት ነው፤ ባለማመንታት “አዎ” የሚል። ስለፖለቲካ እስረኞች (ለምሳሌ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ)፣ ስለ 1997 እና 2002 ምርጫዎች፡ ስለፍትህ መጓደልና የሚዲያ ነጻነት አወራን። እንደእነሱ ገለጻ ከሆነ ሁለቱም ምርጫዎች “እንከን የለሽ” ነበሩ። በተለይ ደግሞ የ2002 ምርጫ ውጤት ህዝቡ ከ1997 ከፈጸመው “ስህተት” በመማር ለኢህአዴግ የሰጠው የምራኝ ይሁንታ ነው። በጣም የገረመኝ ነገር ቢኖር ከላይ እስከታች ድረስ ያሉት ሁሉም የኢህአዴግ አባላት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመ ነገር ሁሉ የኢህአዴግ እጅ እንደሌለበት መካዳቸው ነው። ለምሳሌ በ1997 ምርጫ ማግስት በገፍ ለተገደሉና ደብዛቸው ለጠፉ ሰዎች ተጠያቂው ማን ነው በማለት ለጠየቅሁት ጥያቄ በጣም የሚዘገንን መልስ ነው የሰጡት። ሁለቱም ካድሬዎች “ተጠያቂዎቹ ሟቾቹ ናቸው! ኢህአዴግ ከሰው በላው ደርግ ነጻ ባወጣው አገር ለምንስ ነጻ አውጪውን ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣሉ?” በሚል ጥያቄዬን በጥያቄ መለሱት። መንግስት የለም በሚያሰኝ ሁኔታ በወለጋ በኦሮሞና በአማራ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈጸሙትን ጭፍጨፋዎች ማን እንደፈጸማቸው ስጠይቃቸው ምናልባትም አንዳንድ “አክራሪዎች” በሴራው ሊኖሩበት ይችላሉ የሚል መልስ ሰጥተውኛል። የህወኋት ኢህአዴግ እጅ እንዳለበት ማመን ግን አልፈለጉም። በሌላ አባባል ይህንን ሁሉ የዘር መከፋፈል ኢህአዴግ የሚከተለው የዘረኝነት ፖሊሲ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በለስላሳ ቃላት ስጠቁማቸው ሁለቱም ዝምታን መረጡ። ከውይይታችን እንደተረዳሁት የኢህአዴግ አባላት እርስ በእርስ እጅግ በጣም ይፈራራሉ ወይም የፖለቲካ ካቲካላቸው ውሸት ብቻ የሚያስወራቸው ይመስለኛል።

 

አውቶቡሱም መንገዱን ተያይዞታል፤ እኛም ወሬያችንን ቀጥለናል። የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ እንደደረስን ለመንገድ የሚሆን ጫት መግዛት ነበረባቸው። ትንሽ እንደተጓዝን እኔም ከጫት ድግስ እንድቋደስ ጋበዙኝ። እንደማልቅም ነግሬያቸው እንደገና ወሬያችንን ስጀምር ከሁለቱ አንደኛው ሻንጣውንና በእጅ የሚያዝ እቃ ማሰናዳት ጀመረ። “ለትራንስፖርት የከፈለው እስከአጋሮ፣ የሚወርደው ደግሞ እዚህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብዬ ስጠይቅ ለሁለት ሳምንት የኦህዴድ ፖለቲካ ስልጠና እንደሚሳተፍና ስብሰባውም በጦላይ (ስሙን የረሳሁት መሰለኝ) እንደሚካሄድ ተነገረኝ። በተገንጣይ መንገድ ላይ አውቶቡሱን አሰቆሞ ለኔም መልካም ተመኝቶልኝ ወረደ። ወሬዬን በመቀጠል ቀደም ብሎ በደንብ ሲያወራኝ የነበረውን ወጣት የህወሃት ኦህዴድ ካድሬ በአባልነቱ ምን ያክል እንደሚያምንበት ጠየቅሁት፤ በአጠገባችን ያሉትን ሰዎች በደንብ ካስተዋለ በኋላ “እኔ አምኜበት ሳይሆን የእንጀራ ጉዳይ ሆኖብኝ ነው” የሚል አስገራሚና ያልጠበቅሁት መልስ በለሆሳስ ነገረኝ። እኔም በጣም ገረመኝ። ወጣቱ ካድሬ እንደነገረኝ ከሆነ ከአዋሳ ዩንቨርስቲ ግብርና ኮሌጅ በቅርብ ጊዜ ተመርቆ እጅግ ሩቅ ገጠር እንዲሰራ ይመደባል። አንድ አመት ሰርቶ ኑሮ አልስተካከል ሲለው በፈቃደኝነት የኦህዴድ አባል በመሆኑ ወደ ተሻለ ከተማ ያስጠጉታል። እሱ እንደነገረኝ ወደ ተሻለ ከተማ ያመጡት ምክንያት ማንኛውንም ፈጽም የተባለውን ነገር ሁሉ በፍጹም ታማኝነት ስለሚያከናውንና ለዚህ ውለታ ከውሎአበልም ከደመወዝም ዳጎስ ያለ ንዋይ እንደሚሰጡት አጫወተኝ።

 

ጨዋታችን ደራ፤ ጫቱንም በውሃ ማወራረድ ጀመረ። በእኔ በኩል ያለውን ጉንጭ ጥቅጥቅ አድርጎ ወጥሮታል። አሁን በደንብ የልቡን ማውራት ጀመረ። እንደካድሬው አባባል ሁኔታዎቹ ከተቀየሩ በዚህ “ዘረኛ መንግስት” ላይ መሳሪያ የሚያነሳ የመጀመሪያ ኢትየጵያዊ ቢኖር እሱ ራሱ እንደሚሆን በአጠገባችን ማንም ሰው እንደማያዳምጠን አማትሮ ካየ በኋላ ሳይደብቅ ነገረኝ። ቀደም ብዬ በሶስትዮሽ ውይይት እኔ ያነሳኋቸው ነገሮች ሁሉ እውነት እንደሆኑና የአኔን ሃሳብ እንደሚጋራ ነገር ግን ከባልደርባው ፊት ካመነ ነገ ከነገ ወዲያ ወደ ግምገማ በሚቀርቡበት ጊዜ ችግን እንደሚፈጥርበት፤ በአቋሙ እንደሚያስገመግመው ይህ ደግሞ ህይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን በደንብ ስለተረዳ በመሆኑ እንደዋሸኝ ለጋ ጫት እየቀነጠበ በሃዘኔታ አጫወተኝ። ስለዋሸኝም ከልቤ ይቅርታ እንዳደርግለት ለመነኝ። በመቀጠልም ባልደርባውም ጭምር የኦህዴድ አባል የሆነው ለጊዜው ለእንጀራው ብሎ እንጂ በምንም መልኩ አምኖበት እንዳልሆነ በግልጽ አስረዳኝ። ሆኖም ደጋግሞ የነገረኝ ነገር ቢኖር ማንኛውንም የህወሃት የበላይነትን የሚገረስስ ሃይል ካገኘ በቅርቡ እንደሚቀላቀል ነው። የኢህአዴግ ቤት ውስጡ ምስጥ የበላው እንጨት መሆኑን በተደጋጋሚ ገለጸልኝ። ድርጅቱን ለመጣልም ብዙ ሃይል ሳይሆን ጥቂት ግን በአግባቡ የተደራጀ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን የሚወክልና በሁሉም አካባቢዎች ድጋፍ ያለው ድርጅት አስፈላጊ እንደሆነ በዝርዝር አስረዳኝ። የዳያስፖራና በአገር ውስጥ ነፍጥ አንስተው የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ይህንን ማቀናጀት የአለመቻላቸው ጉዳይ በጣም እንደሚያሳዝነው በቁጭት አወጋኝ። እንደእሱ እምነት ከሆነ ህወሃት ኢህአዴግ በምንም መልኩ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ስልጣን አይለቅም! እናም በኢህአዴግ ዘመን በምርጫ መሳተፉ ትርፉ በሰላም የሚኖረውን ህዝብ ማስገደል ማሳሰርና ደብዛ ማስጠፋት ብቻ ነው አለኝ። በመሆኑም መንግስት፣ ፓርቲና የሃይማኖት ድርጅቶች በአንድ ሰፈር ልጆች በሚመሩበት አገር በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶቸና ግለሰቦች ኢህአዴግን በምርጫ ለማሸነፍ አፋቸውን ሞልተው ሲናገሩ ሲሰማ ሁሌ እንደሚገርመውና በምንም መልኩ የማይታሰብ ድርጊት እየሞከሩ መሆኑን ገለጸልኝ። በመቀጠልም አብዛኛው የኦህዴድ አባል የህወሃት ኢህአዴግ አባል የሆነበት ምክንያት ከራሱ ጀምሮ ከርሱን ለመሙላት እንጂ አይዲዮሎጂው አማልሎት አይደለም።

***************************************************

ይኸው በአባጅፋር ዋና ከተማ ሶስት ቀን አሳልፌ ወደአዲስ አበባ በሚኒባስ ልመለስ ከሾፌሩ በስተኋላ 2 ረድፍ ርቄ በመስኮት በኩል ቁጭ ብያለሁ። ከመናኸሪያ ሳንወጣ አንድ በ30ዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለ ወጣት አጠገቤ ተቀምጦ በእኔ በኩል አሻግሮ በመስኮት ከቆመች ወጣት ሴት ጋር ያወራል። ኦሮምኛ በትንሹ ስለምችል የሚባባሉት ይገባኛል። ፍቅረኞች ናቸው። በፍቅረኞች መካከል የሚደረግ ወሬ ቢያዳምጡት አይጠገብም። የመለያያቸውን እያወሩ ስለነበረ ብዙ ርዕስ አንስተዋል። ከአይናቸው ውስጥም የሰቀቀንና ናፍቆት ነበልባል ይነበባል። ሚኒባሱ ቀስ ብሎ መንቀሳቀስ ሲጀምር ፍቅረኛዋም አፍቃሪዋን ከጫነችው ሚኒባስ ጎን ጎን ተከትላ አብራን ተንቀሳቀሰች። ሁኔታቸው እየገረመኝ ነበር። እሱም ቢሆን አይኑን ከእሷ አልነቀለም፤ እሷም ፍቅረኛዋን ከጫነው መኪና ጋር ውድድር የምትገጥም ትመስላለች። ነገር ግን መኪናው ጉልበቱን ጨምሮ ወደፊት በፍጥነት በረረ። ወጣቱም ለመጨረሻ ጊዜ ውድ ፍቅረኛውን ለማየት አንገቱን ጠመዘዘ፤ አይ ብዙ ርቀናል!

 

ትንሽ እንደሄድን ይህ ወጣት ሰው ተደላድሎ ሲቀመጥ ያልጠበቅሁትን ነገር በጎን በኩል ገፋ አረገኝ! ከለበሰው ጃኬት ውስጥ በግራ በኩል ያነገተው ሽጉጥ መሆኑን ተረዳሁ። ምንም መልስ አልሰጠሁትም፤ እሱም እኔን ገርመም እያደረገ ከማየት የቦዘነበት ጊዜ የለም። ጸጉረ ልውጥ መሆኔን ተገንዝቧል። በእውነቱም የህወሃት ኢህአዴግ ነገር ስለማይታመን በእኔ ላይ እርምጃ ሊወስድብኝ የመጣ የደህንነት አባል መሰለኝ። በዚሁ ቅጽበት ደግሞ ብዙ ሃሳቦች በአእምሮዬ መመላለስ ያዙ። በአንድ በኩል ከአራት ቀን በፊት ከአዲስ አበባ ወደጅማ ስሄድ ያገኘኋቸው ካድሬዎች እርምጃ እንዲወስድብኝ የላኩት መሰለኝ። በሌላ በኩል ደግሞ በአጋጣሚ የተሳፈረ የደህንነት አባል ሊሆን ይችላል ብዬ ራሴን ለማረጋጋት ሞከርኩ! ታዲያ ባለጊዜ ካልሆነ በቀር ማን በጠራራ ጸሃይ ሽጉጥ ይይዛል? ለምንስ እኔ እንዳውቅ አደረገ? በሰላም አገር ለምንስ ሽጉጥ መያዝ ያስፈልጋል? በዚህ ሃሳብ ባህር ውስጥ ሰምጬ ባለሁበት ሰአት ሚኒባሱ ስለሚሞቅ በትንሹ መስኮት እንድከፍትለት ጠየቀኝ። እኔም ራሴ ሞቆኝ ስለነበር በደስታ የምከፍትለት መሆኑን፣ ለጤናችንም ቢሆን ንጹህ አየር እንደሚያስፈልገን እያወራን እያለን ስማችንንና የምንሰራበትን መስሪያቤት ተለዋወጥን። እኔ ለጊዜው ባላምነውም የፍቅር ጓደኛውን ሊያስመርቅ የመጣ የጉምሩክ ሰራተኛ መሆኑን አስረዳኝ። አሁን ግን ሴት ጓደኛው አንዳንድ ፎርማሊቲዎችን ጨርሳ መምጣት ስለሚኖርባት እስከዚያው ድረስ እሱ በመስሪያቤቱ በጣም አስፈላጊ ሰው በመሆኑ ቶሎ መሄድ እንዳለበት ነገረኝ። ከጅማ እስከአዲስ አበባ ድረስ በሚኒባስ ታሪፍ የሚከፈለውን የሁለታችንንም ትራንስፖርት ሂሳብ ከኪሱ ከ 300 ብር አውጥቶ ለረዳቱ ሰጠ። እኔ የምዕራብያውያንን የኑሮ ስልት ስለቀመስኩ የራሴን ለመክፈል ብከራከርም እሱ እንደሆነ ኢትዮጵያዊ ሩህሩህነት ስላለበት የሁለታችንንም እከፍላለሁ ብሎ አሻፈረኝ አለ። የምረቃ ሰሞን ስለነበረ የሚኒባሱ ሂሳብ በመቶ አምሳ ታሪፍ ጭማሪ ነበረው። ከዚያም ብዙ ነገር አልተነጋገርንም። እኔ እንደፈራሁት ነው፤ አላመንኩትም። እሱም ቦታው ስላልተመቸው ይመስለኛል ዝም ብሏል።

 

መኪናዋ በሙቀት ስላአደባየችን ላብ በሰውነታችን ይንጠፋጠፋል፤ ተሳፋሪዎች አብዛኞቹ ነጋዴዎች ይመስሉኛል። የ “ጀበና” በሚል ቅጽል በ 130 ብር ጫት ተገዛ። በዚህ አጠቃቀም ቃሉ ለእኔ አዲስ ስለነበር ማብራሪያ ጠየቅሁ። “ሰዎች ገንዘብ አዋጥተው ጫት ይገዙና በኋላ በእኩል መጠን ለባለድርሻዎቹ የሚከፋፈል” መሆኑን ሹክ አለኝ። ጊቤ ወንዝን አቋርጠን የምሳ ሰአት ደረሰ ተባለና አንድ ሰሟን ከረሳኋት ከተማ ሹፌሩ መኪናውን አቆመልን። ባለሽጉጡ ወጣት አብረን እንድንበላና እንድንጠጣ ጋበዘኝ። ግበዣውን መቀበል ነበረብኝ፤ እንደግዴታም አይነት መሰለኝ። ሆኖም አሁን ይበልጥ ጥርጣሬ ገባኝ። “ይህ ሰው እያታለለኝ ነው እንጂ ደህንነት መሆን አለበት” በማለት ለሚመጣው ሁሉ ራሴን አዘጋጀሁ። ሁለት ጥብስ ካዘዝን በኋላ አስተናጋጁ ሁሌ እንደዳዊት የሚደግመውን ሃረግ “የሚጠጣ ነገር ምን ይምጣ?” በማለት ጠየቀን። እኔ ውሃ አዘዝኩ፤ አዲሱ በሚኒባስ የተዋወቅሁት ጓደኛዬ ግን የኔን ምርጫ ተቃወመ። “ለሁለታችንም ድራፍት አምጣልን!” አለው። እኔም የራሴን ተቃውሞ አሰማሁ። መድሃኒት እየዋጥኩ ስለሆነ አልኮል ይዘት ያለው ነገር እንደማልጠጣ በአንድ ሁለት ኡኡታ ሳል መረጃ አስደግፌ አስረዳሁት። ተስማማን። እኔም ከውሃው አዲሱ ጓደኛዬ ደግሞ ከድራፍቱ አንድ ሁለት አልንለት።

 

በመቀጠል ስራው እንዴት እንደሆነ ጠየቅሁት። ወጣቱ መልከመልካም ነው። ፈገግ ብሎ፣ “ስራ? እኔ እኮ ለደሞዝ አይደለም የምሰራው! አንዳንዴ እንዲያውም ወሩ አልፎ ደሞዜን ሳልወስድ እቀርና ሂሳብ ክፍሎቹ ለማወራረድ እንዲመቻቸው ስልክ ደውለው እንድወስድ ይለምኑኛል” አለኝ። ልመና? ወይ ጉድ! ለምን ደሞዙን በጊዜው እንደማይወስድ ስጠይቀው በመንግስት የሚከፈለው ደሞዝ ከሶስት ቀን ወጪው በላይ ሊሆን እንደማይችልና ይህንን ደግሞ አስታውሶ መውሰድ ሌላ ከባድ ፈተና እንደሆነበት በዝርዝር አጫወተኝ። ከዚያም ዙሪያውን አማተረ፤ ገበታው ሳይነሳ የምኖርበት አገር መታወቂያ እንዳሳየው ጠየቀኝ። በድንጋጤ ክው አልኩ፤ ሆኖም የነበረኝ መታወቂያ ፓስፖርት ብቻ ስለነበር ከላፕቶፕ ቦርሳዬ አውጥቼ አሳየሁት። ቀጥሎም “እኔ አሁን የቸገረኝ ነገር እንዴት ከዚህ መስሪያ ቤት ለቅቄ እንደምወጣ መላ ማጣቴ ነው” አለኝ። ከስራው በቀን በአስር ሺ የሚቆጠር ብር በጉቦና በድርድር መልክ አንደሚያኝ፤ በጣም በቂ ሃብት እንዳለው ሆኖም ያከማቸውን ገንዘብ በሌሎች ዘመዶቹ ስም አዛውሮ የጊዜን አመቺነት እየጠበቀ እንደሚገኝ አጋጣሚውን ካገኘ ደግሞ አገር ጥሎ ሊጠፋ እንዳሰበ በዝርዝር አጫወተኝ። መታወቂያ የጠየቀኝ እሱ ተጠራጥሮኝ ኖሯል፤ ያመነኝ ፓስፖርቴንና በላዩ ላይ የተመታውን ቪዛ ካየ በሁዋላ ነው። ከጊዜው አንጻር እዚህ ቦታ ላይ ከተነጋገርነው በላይ ማውራት ስላልቻልን ወደመኪናችን ከመመለሳችን በፊት የተመገብንበት ሂሳብ መከፈል ነበረበት። አሁን እኔ እከፍላለሁ ብዬ መቶ ብር ሳወጣ እጄን ለመታጠብ በሄድኩበት ጊዜ አስተናጋጁ ጓደኛዬ እንደከፈለው አስረዳኝ። እጁን ታጥቦ ሲመጣ ለምን እኔ መክፈል ሲገባኝ እሱ እንደከፈለ ስጠይቀው “አንተ ገና ብዙ የምትረዳኝ ነገር አለ!” ነበር መልሱ። ምን ይሆን የምረዳው በማለት ዝም አልኩ።

 

መኪናችን ይዛን ወደአዲስ አበባ በረረች። የየግል ጉዳያችንን እያወራን አዲስ አበባ እንደደረስን ወደናዝሬት እሄዳለሁ አለኝ። እኔም ወደናዝሬት እየሄድኩ ስለነበር አብረን መሄድ እንዳለብን ተስማማን። ሆኖም አዲስ አበባ እንደደረስን ደክሞን ስለነበር ትኩስ ሻይ ቡና ፉት እያልን አብረን ለአንድ ሰአት ያክል አወራን። በእዚህ ጽሁፍ መግለጽ የማልችለውን ብዙ የመስሪያ ቤቱን ምስጢር በዝርዝር አወራኝ። በተወሰኑ ነገሮች እንዳላመንኩት ሲገባው መታወቂያውን አውጥቶ አሳየኝ። የኢህአዴግ አባል ነው። ስልጣኑን መከታ በማድረግ ዘመድ አዝማድ በራሱ መስሪያ ቤት እንዳስቀጠረ የጀግንነት ታሪኩን አወጋልኝ። በእርግጥም የጉምሩክ ሰራተኛ ወሳኝ ከሆነ ቦታ የተቀመጠ ሰው። ሰውየው በአሁኑ ጊዜ ያፈራውን ንብረት በዝርዝር ቆጠረልኝ። የትየለሌ ነው። ከ 10 የማያንሱ የድርጅትና የመኖሪያ ቤቶች በአዲስ አበባ፣ ደብረዘይት፣ ሞጆና ናዝሬት፤ የተለያዩ ኤሮትራከር የጭነት መኪናዎች መለስተኛ አውቶቡሶች አይሱዙ ኤፍ ኤስ አርና የድንጋይ መጫኛ ገልባጭ መኪኖዎች (ሁሉም ንብረቶች በቤተሰብ ስም የተገዙ) በባንክ በቤተሰብ ስም የተቀመጠ ጥሬ ገንዘብ ወዘተ አንድ በአንድ ተረከልኝ። ሆኖም በራሱ ስም ከ 3ሺ ብር ያልበለጠ ገንዘብ በባንክ እንዳለሁ አስረድቶኝ “አህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበርም” አለኝ የዘመድን አንጀት አለመለያያት ሲያብረራልኝ። ከቤተሰብ ጋር ጸብ እንኳን ቢፈጠር እነሱ የሚወስዱት ትንሽ ገንዘብ ብቻ እንደሆነና እንደማይጨክኑበት አብራራልኝ። ቀጥሎም አንዳንድ ጊዜ በቀን 10ሺ ብር ድረስ በጎቦ መልክ እንደሚያገኝና የአገራችን የሙስና ቅሌት ምን እንሚመስል በራሱ ምሳሌ አስረዳኝ። ይህንን ሁሉ ገንዘብ እንዴት በጉቦ መልክ ሊቀበል እንደቻለ ስጠይቀው ሁሉም የሚዘርፍበት አገር ስለሆነ እሱም ሌሎችን ዘራፊዎችን መመሳሰል እንዳለበት አለበለዚያ ግን ወይ ሊያስሩት አለበለዚያ ባላሰበው መንገድ ሊያስወግዱት እንደሚችሉ በተደጋጋሚ እንደተነገረው ተረከልኝ። ሆኖም በዚያን ጊዜ ያልተሟላለት አንድ ችግር ነበረበት፤ አገር ጥሎ መውጣት እንዴት እንደሚቻል አለማወቁ። ለዚህ ደግሞ መንገዱን እኔ እንድነግረው ወይም ወደአውሮፓ እንዲወጣ እኔ እንድጋብዘው ለዚህም ወረታውን በማንኛውም ጊዜ ሊከፍለኝ እንደሚችል (ካለው አጠቃላይ ንብረት አንድ ሁለት ቤት ከፈለግሁበት ቦታ በስሜ ሊያዛውርልኝ) በራስ በመተማመን መንፈስ አጫወተኝ። እኔም በውስጤ እስቅ ጀመር፤ ሞኝነቱም አሳዘነኝ። ስልክ ተለዋወጥን።

 

በአጋጣሚ የተገናኘን ሰዎች ናዝሬት ድረስ በአንድ ወንበር ላይ ተሳፈርን። በጨዋታችን መካከል እኔና ውጭ አገር ያለው ዳያስፖራ መሰሎቼ ስለሁኔታው ሳንገነዘብ ዝም ብለን ከመለፍለፍ ውጪ ይህ መንግስት ምን እንደሚሰራ በእርግጠኝነት እንደማናውቅ በዝርዝር አጫወተኝ። የስርአቱ ዋናው አንቀሳቃሽ መሳሪያ ህዝብ ሳይሆን ገንዘብ ብቻ እንደሆነ አስረግጦ ነገረኝ። “ገንዘብ ካለህ ማንንም ሰው እንደባሪያ ትገዛዋለህ። የፈለከውን ነገር ታሰራዋለህ። ገንዘብ ካለህ ሰው ታስገድላለህ! የሚነካህ የለም ምክንያቱም በየደረጃው ጉቦ ትሰጥና ዳኞቹንም ሆነ መርማሪ ፖሊሶችን ዝም ማሰኘት ብቻ ሳይሆን መረጃውንም ደብዛውን ታስጠፋዋለህ። የኢህአዴግ አባላትም ገንዘብ ስለሚከፈላቸው ምንም ነገር አድርጉ ብትላቸው ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ለዚህ እኮ ነው የህወሃት አባላት በሙሉ ወደቢዝነስ አለም የገቡት! ማንንም ሰው በፈለጉበት ጊዜ መግዛት ይችላሉ” ነበር ያለው። በተዘዋዋሪ እኔንም እሱ ወደውጭ አገር እንዲወጣ ቢዝነስ ውስጥ አስገባኝ ማለት አይደል? የኢህአዴግ ሰዎች የሚያስቡት እንዲህ ሆኗል፤ ማንኛውንም ሰው በገንዘብ መግዛት ይቻላል።

 

ናዝሬት በመድረሳችን መለያየት ነበረብን። ሁኔታዎቹንም በጥሞና እንድንነጋገር ለችግሩ መፍትሄ እንድንፈልግ ከአደራ ጋር አብይ ቀጠሮ ሰጠኝ። ውሃ የመሰለ የቤት መኪና አቅርቦም ወደምሄድበት ላድርስህ አለኝ። ሆኖም ላደረገልኝ ሁሉ አመስግኜ የላድርስህ ግብዣ ሳልቀበል ቀረሁ። ከዚያ ቀን በኋላ ከ20 ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ደውሎ እንድንገናኝ መፍትሄውንም እንድነግረው ይጠይቀኝ ነበር። ነገር ግን በሆነ ባልሆነ አስባብ ግብዣውን ሳልቀበል ወደባህርዳር ጉዞዬን ቀጠልኩ። ወደባህርዳር ስሄድ በአውቶቡስ ውስጥ የገጠሙኝም የኢህአዴግ ብአዴን ሰዎች ነበሩ።

(ክፍል ሁለት ይቀጥላል!)


ማስተዋል አዳነ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ