የመለስ ቀልዶች
ተስፋዬ ገብረአብ
ወያኔ ጉባዔውን አዳማ ላይ አካሄደ።
እናም ጉባዔው በአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ንግግር ተቋጨ። አቶ መለስ ዜናዊም በኃይሌ ንግግር ሲስቅ በቴሌቭዥን ተመለከትነው። አቶ መለስ ዜናዊ፣ “በአምስት ዓመታት አጠናቅቀዋለሁ” ያለውን ትንግርታዊ፣ አስማታዊና ሰማያዊ የልማት ዕቅድ ዶክተር ኃይሌ ከአቶ መለስ ብሶ፣ “በሁለት ዓመታት እንጨርሰዋለን” ሲል ቃል ገባ። አያይዞም አትሌት ኃይሌ፣ “ስለ ሰከንድ ማሰብ አለብን” ሲል ተናገረ።
ኃይሌ ሀብቱንም ሆነ ክብሩን ያገኘው ባቋራጭ ሳይሆን፣ ላቡን ጠብ! አድርጎ በመሆኑ አከብረዋለሁ። የኃይሌ ክብር የግል ሳይሆን የሀገሪቱ ጭምር በመሆኑ ደግሞ ለኃይሌ ያለኝ አክብሮት ድርብ ነው።
ሻለቃ ኃይሌ ወደ ወያኔ ጉባዔ ሄዶ ያደረገውን የተሳከረ ዲስኩር ግን አልወደድኩለትም። በዚህ ድርጊቱ ኃይሌን የመኮነን ፍላጎት የለኝም። ኃይሌ ከወያኔ ሰዎች የሚደርስበትን ጫና በቅርብ ከሚያውቁት አንዱ ስሆን፣ ገንዘብ በጥሬው እንዲያመጣ ጭምር እንደሚያስገድዱት መረጃዎች አሉ።
ኃይሌ ገንዘብ ለባለሥልጣናቱ የሚሰጠው በምትኩ ሌላ ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን፣ የችግር ወሬ እያወሩ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ስለሚጫኑት ነው። በዚህ በወያኔ ዘመን ባለገንዘብ ከሆንክ የግዴታ አጠገብህ ለሚገኝ ባለሥልጣን ግብር መክፈል አለብህ። ይህ በስውር የፀደቀ የሥርዓቱ ሕግ ነው።
ሆኖም ኃይሌ አዳማ በተካሄደው የኢህአዴግ ጉባዔ ላይ ተገኝቶ ያንን ግራ የተጋባ ንግግር ያደርግ ዘንድ ያስገደደው አልነበረም።
“ጉባዔያችሁን በማጠናቀቃችሁ፣ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብል ብቻ አመስግኖ በዘዴ ሹልክ ብሎ ማምለጥ ይችል ነበር።
ባለቅኔ መንግሥቱ ለማ “ለአረንጓዴው አብዮት አረንጓዴ እንቁላል ውለዱ” በሚል መርኅ፣ የኢሠፓን ምስረታ በግጥም እንዲያሞግሱ ሲጠየቁ እንዴት ሸውደው እንዳለፉ የምንረሳው አይደለም። ጳውሎስ ኞኞም፣ “ሠርቶአደር ጋዜጣን ትወደዋለህ ወይ?” ተብሎ ሲጠየቅ ምን እንደመለሰ አንረሳውም።
ምን ነበር ያለው?
“ማርያምን ትወዳታለህ ወይ?” ተብሎ የሚጠየቅ ሰው ምን ብሎ መለሰ?
“ከግንድ የሚያላጋ ልጅ እያላት እንዴት ነው የማልወዳት?”
በርግጥ እየሱስ ክርስቶስ የፍቅር አምላክ ነው። ጳውልስ ኞኞ አባባሉን ለማጣፈጥ ያለው ይሆናል።
ኃይሌ ግን በየዋህነት ለአቶ መለስ ቀልድ ተመቸ። ጉባዔው ላይ ቀርቦ፣ በደቂቃ ልዩነት አንድ ሚሊዮን ድላር ስለማግኘትና ስለማጣት መፈላሰፍ ባላስፈለገው ነበር። የአትሌቲክስን የማሸነፍና የመሸነፍ ልምዱን ቀመር እንደ ወረደ አምጥቶ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አጀንዳ ላይ አለበሰው።
በኃይሌ ንግግር አቶ መለስ ከአንጀቱ ሲስቅ አይተነዋል። አቶ መለስ የሳቀው በኃይሌ ንግግር ተደስቶ ሳይሆን፣ በኃይሌ የዋህነት ተገርሞ መሆን አለበት። ምክንያቱም እዚያ ጉባዔ ላይ የሚበተነው የልማት ተስፋና አበባ በመጪው አምስት ዓመታት እንደማይፈፀም አቶ መለስ ዜናዊ አሳምሮ ያውቅ ነበር።
ይህን ካሰብኩ በኋላ ጥቂት ተከዝኩ። እናም አንዴ የካህሊል ጊብራን ወግ ትዝ አለችኝ። መጽሐፉ አጠገቤ ስለሌለ በራሴው መንገድ ላውጋችሁ፣
በጥንት ዘመን አንድ አማኝ ቄስና ኢአማኒ ፈላስፋ የአንድ ከተማ ነዋሪዎችን ሰብስበው በእግዚአብሔር ጉዳይ ላይ ክርክር ያካሂዱ ነበር።
አማኙ ቄስ “እግዚአብሔር ፈጣሪ አምላካችን ነው” ሲል መጽሐፍ ቅዱስን እየጠቀሰ ረጅም ሰዓት ሰበከ።
ኢአማኒው ፈላስፋ በበኩለ “እግዚአብሔር የሚባል ነገር የለም። የሰው ፈጠራ ነው” ብሎ ህዝቡን ለማሳመን ሲፈላሰፍ ዋለ።
ሙግቱ እንዳበቃ ተሟጋቾችም፣ ህዝቡም ወደየቤቱ ተበተነ።
አማኙ ቄስ ታዲያ ቤቱ እንደገባ መጽሐፍ ቅዱሱን አቃጠለና ከዚያች ዕለት ጀምሮ “እግዚአብሔር የለም” ሲል ደመደመ።
ኢአማኒው ፈላስፋ በበኩሉ ቤቱ እንደደረሰ መሬት ላይ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ፀለየ፣
“አምላኬ ሆይ! በዛሬው ዕለት አንተ ፈጣሪዬ እንደሆንክ አመንኩ! እስከዛሬ ስለካድኩህ ይቅር በለኝ!!”
ተስፋዬ ገብረአብ



