በሳውዲ ዐረቢያ የኢትዮጵያውያን መከራ - የተደበቁ እውነቶች!

እስር ቤት ሰበራ!

ክፍል ሦስት

ነቢዩ ሲራክ - ከሳውዲ ዐረቢያ

የረመዳን ዋዜማን ተንተርሸ ከክፍል አንድ ሁለት ያደረስኩትን ቀጣይ መጣጥፍ ሰፋ አድርጌ ለማስቃኘት ያያዝኩትን ዕቅድ የሚያሰናክል አጋጣሚ ተፈጥሯል። ምሽት ላይ ተርሂል ተብሎ ከሚጠራው የጅዳ ጊዜያዊ እስር ቤት ያገኙሁት የስልክ መልእክት ያላሰብኩት የአካሄድ ለውጥ ጠቋሚ ነበር! የተርሂል እስር ቤትን መከራ ሁለንተናዊ ገጽታና የወንድም እህቶቸን መከራ በቀጣይነት ላነሳው የነበረ ጉዳይ ቢሆንም ዛሬ አነሳው ዘንድ ተገደጃለሁ። ታሳሪዎች እጂግ ተማርረዋል። ሁኔታው መልኩን እየቀየረ መመጣቱን ከሚሰጡት የምሬትና የተስፋ መቁረጥ ቃላት መገመት ይቻላል።

ሁኔታ ቢያሳስበኝም ምንም ማድረግ አልችልም! ሌሊቱን እንቅልፍ ባይኔ ትውር ሳይል ነጋ። እየሆነ ያለውን ሳወጣና ሳወርድ አንዴ ሲያሸልበኝ መልሸ ስነቃ የተጋመሰው ሌሊት ተገባዶ ጎህ ለመቅደድ ማንገራገሩን ይዟል። ከአልጋየ ተነስቸ ወደ ስራ ለመሄድ ዝግጅት ከማድረጌ አስቀድሞ እንደተለመደው የተንቀሳቃሽ ስልኬን መልዕክቶች ከፍቸ አንድ ባንድ ማድመጥ ጀመርኩ። አስደንጋጭ የሆነውን መልዕክት ከታሳሪዎች አንደበት እሰማ ጀመር! ሆዴን ሰፋ አድርጌ ተራ በተራ አደመጥኳቸው። በሪያድና በጀዛን የታሳሮሪዎች እንባ የተቀላቀለበት ሮሮ የለመድኩት ቢሆንም የሰሞኑ ወጋወጌ ማጠንጠኛ ከሆኑት ስደተኛ ታሳሪ ወገኖች መከከል የጅዳዎች ባልተጠበቀ አደጋ መከበባቸውን የሚያረዳው እንባና ሲቃ የተቀላቀለበት መልዕክት ስሜትን ጨምድዶ ያዘው! ያስቀመጡት መልዕክት ደጋግሜ አደመጥኩት! የተሰማኝ ድንጋጤ በአዲስ ዓመትና በደመራው በአል የቁዋጠርኩትን ብሩህ የአዲስ ዓመት ተስፋ በታተነብኝ! ... እስር ቤቱ ተሰብሯል! ለማረጋገጥ ወደ ታሳሪዎች መደወል ነበረብኝና ደወልኩ! በነብስ አውጭኝ ግብግብ ላይ ያሉት ወንድሞቸ እስር ቤት ሰብረው መውጣታቸውን አረጋገጥኩ! በቃ እኔኑ ሲቃ ተናነቀኝ... የምይዝ የምጨብጠው አጣሁ! ሊያምኑት የሚከብድ የተደበቀ እውነት!

ላንዳፍታ ዞር ብየ እየገፉ ያለውን የመከራ ኑሮ፤ በተለይም ከሰሞኑ በተደጋጋሚ የሰጡኝን ቃል እያመላለስኩ መቃኘት ገባሁ ...

በሺዎች የሚቆጠሩ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ እስር ቤቶች ታጉረው ለወራት በእንግልት ላይ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በጅዳ ጊዜያዊ ማቆያ ብቻ ከሶስት ሺህ የማያንሱ ዜጎች በፖሊስ ጊዜያዊ ማስተላለፊያ እስር ቤት ከሶስት እስከ አምስት ወራት ላላነሰ ጊዜ ፍዳቸውን እየቆጠሩ እንደሚገኙ ተጨባጭ መረጃዎች ብቅ ብቅ ማለት ከቅርብ ወራት ወዲህ ነበር። የከፋ ወንጀል የፈጸሙ አይደሉም። ድህነታቸው አስገድዷቸው ህግን ጥሰዋልና ከሃገር መባረራቸው ቢታወቅም ወደ ትውልድ ሃገራቸው መግባት ግን አልቻሉም። የሳውዲ መንግሥት ህገ-ወጥ ናቸው የሚላቸውን የኛን ዜጎች "ወደ ሃገራቸው ለመላክ ዝግጁ ነኝ" ይላል። የኛ መንግሥት ደግሞ "ሰርጎ ገብ አሸባሪዎችን ለመለየት ዜግነታቸውን ማጣራት አለብኝ " ይላል። ግጥሚያው የዝሆኖች መካከል ተጎጂው እንደሳሩ ዜጎች ሆነዋል! ከሁሉም የሚያስገርመው የታሳሪዎች ለወራት በህክምና እጦት አሳር ፍዳ የማየታቸው መልሱ የጠፋብን እንቆቅልሽ ነው! ሰቆቃው በቃላት ሊገለጽ አይቻልም! በዚህ ሁኔታ በስቅየት የሚገፉት ኑሮ ግን መጨረሻ የሌለው ሆኖባቸዋል። ታሳሪዎች በእስር ላይ እንዳሉ በበሽታና በመጨናነቅ በርካታ የእስር ጓዶቻቸውን መርዳት ሳይችሉ እየቀሩ አይናቸው እያየ ለቀባሪ እንዳይመቹ ሆነው እጃቸው ላይ በሞት ይለዩዋቸዋል! ካንዴም ሁለት ሶስት አራት አምስቴ ይህ ተደጋግሟል! አብዛኞቹ ትግርኛ፤ ኦሮምኛ፤ ትንሽ ትንሽ አማርኛ ይናገሩ ነበር አሉ! ዜግነታቸው ግን አልተጣራም! ታሳሪዎች በእቅፋቸው ስለሚጠፉት ወንድሞቻቸው የሚናገሩትን "እህ" ብሎ ለማድመጥ እዘነ ልቦና ለሰጠው ሟች በህይወት ግቢና ውጭ ግብግቡን ውስጥ እስከ ተሸነፉባት ሰአት ኢትዮጵያዊ ሆነው ማለፋቸውን እንጂ ሌላ አያውቁም። ያወጉዋቸው ሶማሌ ሆነ ስለመቃድሾ፤ ስለቦሳሶ አልነበረም። ኤርትራዊ ሆነው ስለ ከረን ተሰኔና አቁረደት "ስለ ደሃይ አስመራ " አልነበረም...! የጂማ አርሲ ወለጋ፤ የትግራይ፤ የጎንደር፤ የወሎና የሌላም ሌላ የመጡበትን የትውልድ ሃረግ የውልደት እድገታቸውን አጫውተዋቸዋልና ስለ ኢትዮጵያዊነታቸው ቅንጣት ታክል አይጠራጠሩም! በበርካታ ቁጥር መሞታቸው አደባባይ ያልወጣ እውነት ቢሆንም እርግጥ ለመሆኑ አሁንም የዓይን ምስክሮን ያደመጥኩት እኔው ሳይቀር ነብስ የተለያትን የጥቂቶችን ሬሳ አይቻለሁና የምስክንነት ቃሌ ቢመርም እንካችሁ! የሁኔታውን አስከፊነት ለማስረዳት ቢገድም የሙቾችን ቁጥር ትገምቱ ዘንድ በረመዳን ወር ውስጥ ባሉት አስራ አምስት ቀናት ብቻ ከአስር ያላነሱት በዚያው እስር ቤት መሞታቸውን ልንገራችሁ! ለዛሬ ይህንን በዚህ እንለፈው ...! ይህ ሰቆቃ ምሬትን ፈጠረ!

የቀረው ዓለም ያለው ኢትዮጵያዊ ችግሩ ዘልቆ አልገባውም መሰል ዝምታን መርጦዋል ... በውጭው ዓለም ያለው የእህት ብርቱካን ሚደቅሳ ትፈታ ጥያቄ፤ አዎዛጋቢ እየሆነ የመጣውን የደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ የብዕር ጠብታ ኢላማዎች አዎዛጋቢነት እየገነኑ መጥተዋል። ይህንና የመሳሰሉት የኢትዮጵያውያን ድህረ ገጾችን ቦታ አጣበዋል። በሃገር ቤት በአንጻሩ ይህ መሰሉ ወሬ ረገብ ብሎ በለሰለሰ "ቅኝት" በነጻ ጋዜጦች ቢራገብም ጣራ የነካው የኑሮ ውድነት፤ የኢሃዴግ ባለሥልጣናት መተካካት፤የሹም ሽሩና የአዲሱ ፓርላማ ጉዳይ ለሃገሬው ብቸኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆነው ሰንብተዋል። እኛ ግን ዝም አላልንም... በስራ ባልደረቦቸና በነዋሪው ቅን ትብብር ይህ ችግር ካንድም ሁለት ሶስቴ በራዲዮ ጣቢያ በኩል ተላለፈ ... የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከተን ወገኖችና ታሳሪዎች ሳይቀሩ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እንዲያሰሙ የውይይት መድረክ ሳይቀር ቀረበ። ያም ሆኖ ከንፈርን ከመምጠጥ ባለፈ ሰሚ ግን አልተገኘም። እናም ሁኔታወች እየከፉ ሄዱ። እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ሌት ተቀን እከታተላለሁ! እሰማለሁ! ሲቀናኝ ደግሞ አያለሁ! በተቻለኝ አቅም የመንግሥት ኃላፊዎችን፤ የቆንስል መስሪያ ቤት ባለሥልጣናትና የሰብዓዊ መብት ኃላፊዎችን እየሄድኩ አቤት ማለቴን አላቋረጥኩም! እኒህኞች የኛዎች " አንተን እንዲህ የሚያንገበግብህ ምንድን ነው? ህገ-ወጦች መሆናቸውን ረሳህው እኮ!" ይሉኛል! እኒያኞች ባዕዶቹ ደግሞ "ተቆርኩዋሪና ያገባኛል ባይ የመንግሥት ተወካይ አላችሁን?" እያሉ ይሳለቁብኛል! ጠያቂውን አግድመው እየጠየቁ የማልመልሰውን ጥያቄ እየጠየቁ በሰብዕናየ ውስጥ እየተሹለከለኩ ቢያሙዋርቱብኝም የታሳሪዎች ህክምና እንዲሻሻልና መጨናነቁ ረገብ እንዲል አድርገዋልና ምስጋና ሳልቸራቸው አላልፍም!

ንጹህ የሰላም አየር የምንተነፍሰው በዚህ መሰል እንቆቅልሽ ስንደባበቅ እየታመሙ እየሞቱ የሚኖሩት ታሳሪዎች ሁኔታ ከፍቷል። ሲመራቸውና ሲያንገፈግፋቸው በር እየደበበቡ ጠባቂዎቻቸውን "መላ በሉን?" ብለው ሲጠይቁ "መንግስታችሁ አይፈልጋቸሁም! " እና ሌላም ሌላ ይሏቸዋል... ይህ ሁኔታ ታሳሪዎቹ በነብሳቸው ቆርጠው ህግን ይተላለፉ ዘንድ ምክንያት ነበር ማለት ይቻላል። መላው ሲጠፋ በተንቀሳቃሽ የሞባይል ስልክና በባንግላዲሽ የጽዳት ሰራተኞች ተላላኪነት መልዕክት ይለዋወጣሉ። በቁራሽ ወረቀት እየተጻጻፉ "ምን ይሻላል?" ይሉ ይመከሩ ጀመር። ሁሉም ተስማሙ ብዙም ሳይቆዩ በተንቀሳቃሽ ስልኬ ላይ ደወለው አሳወቁኝ! ስልኩን ከማንሳቴ ... አዲስ ነገ አለ ነበር? ስል ጠየቅኩ ደዋዩን ታሳሪ! (እነሱን ሳገኝ ከሰላምታ በፊት ሁሌ የማዘወትረው የማቀርበው ጥያቄ ነው)

"የደወንልህ መስማማታችን ልንገልጽልህ ነው ... መቁረጣችን!"

ምን? ... አልግባኝምና ... ጠየቅኩ

"አዎ ተስማምተናል"

ለምኑ?

"ያሻንን እርምጃ ለመውሰድ ነዋ!" ባልተለመደ ኃይለ-ቃል

እንዴት?

"እዚህም ሞት እዚያም ሞት . አሁንም እኮ እየኖርን አይደለም!"

"ጉዳያችሁ በተለያየ መንገድ ህዝብና መንግሥት እየተሰማ ነው። መፍትሄ በሚገኝበት ሰአት እንዴት ከዚህ መሰል ውሳኔ ትደርሳላችሁ?" ስል በተማጽኖ ዓይንነት ጥያቄየን አቀረብኩ

"እሱን ለኛ ተወው። ድምጻችን ልታሰማ የምትችል አንተ ነህና የምስክር ቃላችን ልትቀበል ይገባልና ስማ" ተባልኩ ቁጣ በተቀላቀለበት የንዴት መንፈስ...! እናም የደረሱበትን ውሳኔ አነበቡልኝ! በዚህ ሁኔታ "ለኛ የዛሬ ስቅየት የታሪክ ምስክር ነህና ቃላችን ተቀበል!" ተብያለሁና እንደጋዜጠኛ ቃላቸውን ስቀበል፤ እንደ ዜጋና እንደ ወንድም ሃሳባቸውን ለማስለወጥ የገጠምኩት ሙግት አለመሳካቱን ያወቅኩት ታሳሪው ብረት አጥር ለምስበር ሲቀጠቅጥ ሲነሱና ሲወድቁ የሚሰማው ጩኽት፤ የወታደር መኪናውና የአንቡላስ ጩኽት የታከለበት መልዕክት ስሰማ ነበር! ላፍታ ያህል ራሴን አረጋግቸ የተቀበልኩትን የኑዛዜ የሚመስል የተቀረጸ ቃል ከፍቸ መስማት ጀመርኩ!

እንዲህ ያላል ...

እኛ በሳውዲ ዐረቢያ ጅዳ ተርሂል ማቆያ እስር ቤት የምንገኝ ኢትዮያውያን ያለንበትን ችግር በማስመልከት ለሳውዲ መንግሥት መልዕክታችን ከዚህ በታች እናቀርባለን! እኛ በተርሂል የምንገኝ ኢትዮጵያውያን እዚህ ውስጥ ከአንድ ወርና ከዚያም በላይ ያለምንም ጥፋት ወይንም ወንጀል በእስር ላይ ቆይተናል። አሁን አሁን ትዕግስታቸን እያለቀ በየጊዜው ወንድሞቻችን በሞት እየተለዩን ሌላው ደግሞ በበሽታ እየተሰቃዩ ባለበት ሁኔታ ከሳውዲም ሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከሁለቱም ወገን መፍትሄ የሚሰጠን ባለማግኘታችን እንዲሁም ችግራችን የሚገልጽልን ባለማግኘታቸን ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደናል። አሁንም ጥያቄያችን እንደሚከተለው ነው፤ አንደኛ የሳውዲም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ሁለትና ሶስት ቀን ውስጥ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲያደርጉልን እንጠይቃለን።ሁለተኛ ከዚህ በነጻ ልቀቁን ማለት የማይሆን ነገር እንደሆነ እናውቃለን፤ ሶስተኛ ወደ ሌላ ሃገር ውሰዱን ወይም ለተባበሩት መንግስታት ስጡን ለማለት የሚከብድና ጊዜ የሚወስድ መሆኑ እናውቃለን፤ አራተኛ የምግብ አድማ ማድረግና ራሳችን መስዋዕት ማድረግ የሚከለክለን ስለሌለ እኛ በምግብ አድማም ሆነ ለምንም ነገር ራሳችን እንዳዘጋጀን ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።

ከሰላምታ ጋር!

ጅዳ ተርሂል የምንገኝ ኢትዮጽያውያን ታሳሪዎች

(ድምጹን የጻፍኩት ቃል በቃል ነው!)

ደጋግሜ ሰማሁት ...የሰማሁት ድምጽ በበሽታ ከደከመ ሞራሉ ከደቀቀ ወጣት የሚወጣ አይመስልም! ያሉትን አደረጉት አልኩ ሰምቸ እንደጨረስኩ ለራሴ! ይህን መሰሉን ጭንቅ ለማን ይነግሩታል? ለማንስ ያማክሩታል ...? ጭንቀቴ የሚገባው አንድ ጉዋደኛየ ቢኖርም እሱንም ባማክረው "በሳት አትጫወት ... ልጆችህን አሳድግ ... ለምትወድህና ለምትወዳት እናትህ ኑርላት!" እያለ የጭንቀቱን ይብተከተክብኝ ይዟልና የሚያማክሩት ጉዋደኛ አልሆነም! ብቻየን አዝኘ ተከዝኩ!

ብዙም ሳይቆይ በግርግሩ መካከል እየደወሉ መረጃን የሚያቀብሉኝ የጨነቃቸው የጠበባቸውን ታሳሪዎች ለማጽናናት እየሞከርኩ ችግሩ ወደ ተከሰተበት እስር ቤት አቀናሁ። መኪና ያለው በመኪናው፤ ታክሲ የሚይዘው በየታክሲው እየተሳፈረ የእለት ጉርሱን ሊያበስል ወደ ሰራ ለመሄድ ይጣደፋል። ማለዳ በመሆኑ አውራ ጎዳናወች የተጨናነቁ አይደሉም። የጠዋቱዋ ጸሃይም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አልወጣችም። ከረመዳን ወዲህ አየሩ በረድ እያለ መጥቶዋልና የመኪናየን መስኮት ከፍቸ ነፋሻውን አየር እየቀዘፍኩ ከሺዎች የሚቆጠሩ ታሳሪ ኢትዮጵያውያን ወደ ሚገኙበትና በአደጋ ወደ ተከበበው ቦታ ገሰገስኩ። ወደ ጅዳ ተርሂል! የመስቀል በአል ከተከበረ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል። የሳውዲ አሚሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይን አፍሰው ያሰሯቸው ድልድዮችና አቆራራጭ ሰፋፊ መንገዶች ጠዋት ስራ ለመግባት የግፊያ ያህል እየታከኩ የሚግተለተሉትን መኪኖች ጉዞ አቃለውታል። መንገዴን እየፈጨሁ በሃሳብ የመስቀልን አከባበር የቋጠርኩትን አዲስ ህልም እያሰላሰልኩ ጉዞየን ቀጠልኩ።

በዚህ ጭንቅ ሰአት ደመራውን ማስታዎሴ በቅርቡ በስቲያ በኢቲቪ የቀጥታ ስርጭቱ የተከታተልኩት የመስቀል በአል የደመራውን መሰሶ ተመርኩዠ ዳግም ያደስኩት የአዲስ ዓመት ብሩት ተስፋ አስታወስኩትና ነው! እናም ባደግኩበት ቀየ የደመራው መሰሶው በሰሜን፤ ደቡብ፤ምስራቅ ሆነ በምዕራብ ሲዎድቅ አመቱ የሰላም፤ የጦርነት፤ የቸነፈርና የጥጋብ ጠቁዋሚ ነው የሚሉት ከጥንት ጀምሮ የነበረ በውርስ የመጣ ይትበሃል አላቸው! ... ያንን የቆየ አባባል አስታውሸ የደመራውን መሰሶ አቅጣጫ በምሻው አጋድሜ ዛሬ ተሰባሪ የሚመስል ተስፋየን ደጋግፌ ካሰብኩት የረብሻ ቦታ የቅርብ ርቀት ደረስኩ። ኢትዮጵያውያኑ ከሚገኙበት የማቆያ እስር ቤት ... ተርሒል! በቦታው እንደደረስኩ ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ አስተዋልኩ። አካባቢው በወታደር ተከቧል።

አምቡላንሶችና የወታደር መኪናወች በጣራቸው ላይ የገጠሙሟቸውን ሰማያዊና ቀይ መብራቶች እያንቦገቦጉና ወሬ ነጋሪ የድንገተኛ ስምጻቸውን እያጮሁ ወደ እስር ቤቱ ግቢ ይገባሉ ... ይወጣሉ! የምጠይቀው ሰው የለም! ጸጥና ረጭ ባይልም ማን ምን ተብሎ ይጠየቃል? በቅርብ ርቀት ወዳለው የኢምግሬሽን መስሪያ ቤት መኪና ይዞ መግባት ተከልክሏል። መኪናየን ከግቢው በር ከአንድ ፎቅ ታዛ አቁሜ በእግሬ ጉዳይ እንዳለው ባለጉዳይ ገባሁ። ቡራቡሬ የለበሱ የልዩ ጥበቃ ኮማንዶወች በትላልቅና በትናንሽ መኪና እየተጫኑ ይገባሉ። የፓስፖርት መስሪያ ቤት ፖሊሶች ባልተለመደ ሁኔታ ከላሺንኮቫቸውን ወድረው ገቢና ወጭውን ይቆጣጠራሉ። ወደ ውስጥ እየገባሁ እንዳለሁ አሁንም ከፊት ለፊቴ በአሻጋሪ ከማየው ማጎሪያ ነብስ ውጭ ነብስ ግቢ ከገጠሙት ኢትዮጵያ ታሳሪዎች በተደጋጋሚ ተደወለልኝ። ድምጹ ዘግቸ ጥሪውን እዲርገበገብ ያደረግኩትን ስልክ ወጣ አድርጌ ተመለከትኩት። በግማሽ ሰአት ልዩነት ወደ ሃያ የሚሆን ጊዜ ተደውሎልኛል። ያም ሆኖ አካባቢው የተረጋጋ ሁኔታ ስለማይታይ የአገሬውን ነጭ ለባሽ እንቅስቃሴ ስለሚገባኝ ስልኩን ማንሳት ምን ሊያስከትል እንደሚችል በመገመቴ ላነሳውም ሆነ መልሸ መደወል አልቻልኩም። እንዲያ እንዲያ እያልኩ ወደ ኢምግሬሽን ኃላፊዎች ጠጋ ብየ አንድ የማውቀውን መኮንን በዓይን ማፈላለግና ማጣያየቅ ጀመርኩ። ሁሉም የበላይ ኃላፊዎች ወደ ታሳሪዎች እንደገቡ ጸሃፊው ወታደር ገለጸልኝ። እሱም ስልክ በመደወልና በማስተናገድ ተጠምዶዋል። ብቻ ከአለቃው ጋር ያለኝን ግንኙነት ያውቅ ነበርና እንደ ሌሎቹ " ያላ! ያላ! እዚህ አካባቢ ሂዱ! ዛሬ ስራ የለም ቅዳሜ ተመለሱ!" ብሎ እንደተቀሩት ወታደሮች ሊያመናጭቀኝ አልመከጀሉ ደስ አለኝ። ልሰናበተው እጀን ለሰላምታ ዘርግቸ እያለሁ በአካባቢው የተፈጠረ አዲስ ነገር ስለመኖሩ ሳልጠይቀው አላለፍኩም። አጭር መልስ ሰጠኝ "የናንተ ዜጎች በመሩት አመጽ ታሳሪዎች እስር ቤቶች ሰብረው ወጡ . " ብሎ ለሰላምታ የዘረጋሁትን እጀን ተሎ ምንጭቅ እንደማድረግ አድርጎ ለቀቅ አደረገኝ ... መልሱ እዚህ ጥፋ የማለት ያህል መሰለኝና የቆሪጥም ቢሆን እያየሁት አመስግኘው ቢሮውን ለቅቄ ወጣሁ!

ስልኬ ትጮሃላች ... ግን አላነሳትም! አሁን ከማለዳ ሶስት ሰአት ወደ መሆኑ ነው። በቅርቡ የሳውዲ ዐረቢያ 80 ዓመት ብሄራዊ በአልን አስታኮ መንግሥት አዲስ የምህረት አዋጂ አውጥቷል። ህገወጥ ነዋሪዎች ያለ እስርና ቅጣት በቀጥታ ወደ ሃገር ቤት መመለስ ይችላሉ የሚለው ይህን የምህረት አዋጅ ተጠቅመው ወደየ ሃገራቸው ለመግባት የሚፈልጉ የተለያዩ ዜጎች አሻራ ለመስጠጥ በኢምግሬሽም መስሪያ ቤት የተገኙት በጠዋቱ ነው። ብዙ ናቸው ባይባልም አልፎ አልፎ አበሾች ይታያሉ። ወታደሮች ዛሬ እንግዳ ማስተናገድም ሆነ አሻራ መቀበል እንደማይችሉ በማስታወቅ ባለጉዳዮች ግቢውን ለቀው እንዲዎጡ በማሳሰብ ላይ ናቸው። አብዛኛው በሁኔታው ግራ ተጋብቶ መውጣት ይዞዋል። እኔም እንደተቀሩት በመውጣት ላይ እንዳለሁ ሁለት ኢትዮጵያውያን ጎልማሶች አግኝቸ የሰሙት ያዩት እንዳለ መጠየቄ አልቀረም። እነሱም እንደኔው ከታሳሪዎች ረብሻውን እንደሰሙና ከጠዋት ጀምረው የወታደር የአንቡላንስና ውሃ የሚረጩ የእሳት አደጋ ትላልቅ መኪኖች ወደ እስር ቤቱ በብዛት መግባታቸው ገለጹልኝና ተለያየን። ከውስጥ የተፈጠረውን ግርግር ከውጭ ማየት የሚቻልበት ምንም መንገድ የለም።እናም ወደ ቁዋሚ ስራየ ለማምራት መኪናየን አስነስቸ ከመንቀሳቀሴ በፊት አንድ የስልክ ጥሪ ተቀበልኩ። ረብሻውን ሰምተው መረጃ ለጋዜጠኛው ሊያደርሱና አዲስ መረጃም ካለ ሊቀበሉ የሚፈልጉ የታሳሪ ቤተሰቦችና ወሬውን የደረሳቸው ወንድምና እህቶች ነበሩ። ስልኬን ማንሳት አልፈለግኩም። ከእስር ቤት ለሚደወሉልኝ ስልኮች ብቻ መለያ ምልክት አድርጌያለሁና ከነሱ ውጭ ጥሪ መቀበል አቆሜያለሁ። ትንሽ እንደተጉዋዝኩ የእስር ቤቱን አካባቢ ሳልርቅ ከታሳሪውችን አንዱ ደውሎ እየተንቀጠቀጠ እየሆነ ያለውን አወጋኝ። ሁኔታውን ከእስር ቤቱ ጀርባ ባለው ሜዳ አሻግሬ ማየት እንደምችል ገለጸልኝና መንገዴ አስተካክየ ወደዚያው አመራሁ። እውነት ነው ... ከርቀቱ አንጻር ስምጽ የሚባል ነገር የለም። የወታደር መአትና ጥቋቁር የልዩ ጥበቃ ፖሊሶች ውር ውር ሲሉ በርቀት ቢታይም እየሆነ ያለውን ለመረዳት የሚያስችል አንድም ነገር የለም። እናም ሰውነቴ እየራደ ወደ ስራየ አመራሁ። ከእስር ቤት ተነስቸ ቢሮ እስክገባ ከ70 የማያንሱ ጥሪዎች የተደረጉ መሆኑን የተረዳሁት የለመድኩትን ቀጭን የጠዋት ቡና ፉት ከምልበት ቦሮየ ተቀምጨ ነበር። እንዳልኳችሁ የታሳሪዎች ወይም በቅርብ የማውቀው ሰቅክ ቁጥር ካልሆነ ስልክ ማንሳቱን አልወደድኩትም። ሆኖም ከአንድ ወዳጀ የመጣውን ጥሪ መቀበል ነበረብኝና አነሳሁት። ይህ ወዳጀ ከጀሮው "ሳተላይት ዲሽ" ያስገጠመ ያህል መረጃን በማግኘት የሚደርስበት የለም። እናም አዲስ ነገር ይዞ እንደደወለልኝ ገባኝ። " አለቃ ከች ትላለህ በላ ... ከሽ በል በቶሎ" አለኝ የሚቀናውን ያራዶች ንግግር ተጠቅሞ ...ግምቴ ትክክል ነው! አዲስ ነገር አለ! ጊዜ አላባከንኩም የ20 ደቂቃውን መንገድ በ10 ደቂቃ ፉት ብየ ተወርውሬ እቦታው ደረስኩ። ከአንድም ሁለት ሶስት ከእስር ያመለጡ የዓይን ምስክሮችን አገኘሁ! የሆነውን ተጀምሮ እስኪያልቅ አጫዎቱኝ... እንደቆቅ ጀሮየን ቀና አድርጌ ሰማሁ! በቂ መረጃን ይዣለሁና ወደ ቢሮ ተመልሸ ማስታወሻየን መያዝ ነበረብኝና ያንን አደረግኩ!

በትርፍ ስራየ ለመስራት የጀመርኩት የዘጋቢነት ስራ ሙሉ ቀን እንዲህ ስባትል ልጆቸን የማሳድግበትና እኔንም እንዲህ እንደፈለግኩ የሚያዘናክተኝን ስራየን እንዳይጎዳው ጥናቃቄ ከማድረግ ግን ተቆጥቤ አላውቅም። መስራት ያለብኝን ሥራ በተገቢው ሰአትና ሙያዊ ስነምግባር እፈጽማለሁ። ከተቀመጥኩበት ቢሮ ሆኘ ኢሜይሎችን ተመለከትኩ... የምቀበለውን ተቀብየ ደብዳቤ የሚጻፈውን ጽፌ ጨረስኩ። ቴክኒካዊ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚመጡልኝ የፎቶ መረጃወች በጥንቃቄ መርምሬ ውሳኔ ሰጠሁ! የሚሆነውን በአጭር ጊዜ አደረግኩ። አሁን መስሪያ ቤቱ ከኔ የሚጠብቀው ነገር የለም ...ስራየን በተገቢ ሁኔታ ሰርቻለሁና! ከዚህ በኋላ ምንም መስራት አልቻልኩምና ምክንያት ቀበጣጥሬ አለቃየን አስፈቅጀ ወጣሁ። ያመራሁት ሌሎች አመለጡ የተባሉ እስረኞች አሉ ወደ ተባልኩበት አካባቢዎች ነበር። ካንድ ፋብሪካ የተመፈበረከ የሚመስለውን እውነታ ቀንቶኝ ከተለያየ አቅጣጫ ኮምኮምክት። በመቶዎች የሚቆጠሩ እንዳመለጡ፤ ያልቀናቸው ወደ ሃያና ሰላሳ የሚደርሱ እንደቆሰሉ ሰማሁ። ከፎቅና ከአጥር ሲዘሉ የቆሰሉትን በፖሊስ ሲያዙ ተደብድበው ስለቆሰሉትና አምልጠው መንገድ ሲያቁዋርጡ የመኪና አደጋ ገጠማቸው ስለተባሉት የሰሙትን ሳይሆን ያዩትን አዎጉኝ። ጉስቁልናው ከሰውነታቸው የሚነበበው ወንድሞቸ ያሳለፉትን መከራ ሰውነታቸው ይገልጸዋል። በዚህ ሰውነት እንዴት ችለው አጥር ሰብረው እንደወጡ ግን ተአምር ሆኖብኛል። ወሬው ባያስደስትም በቂ መረጃን ከውጭና ከውስጥ ያዝኩ! ልብ በሉ ... የምላችሁ ሁሉ መረጃወች በድምጽ የተያዙ ናቸው!

በቀጣይ ምን ማድረግ እንደሚገባኝ ሳወጣና ሳወርድ ወደ ጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት ደወልኩና ዋና ኃላፊውን አገኘሁዋቸው። የተለመደ ሰላምታየን አቅርቤ ከማለዳ ጀምሮ በማቆያ እስር ቤቱ እየሆነ ስላለው መረጃ ደርሶዋቸው እንደሁ ጠይቄያቸው ጉዳዩን እየተከታተሉት እንደሆነና እንዲያውም ወደ ሳውዲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሊሄዱ ሲዘጋጁ እንደደወልኩላቸው ገልጸውልኝ በቀጠሮ ተለያየን። ይህ ሁሉ የሚሆነው ያሳለፍነው ሮብ መስከረም 19 ቀን 2003 ዓ.ም. ነው ...

ያመለጡ ታሳሪዎችን ታዩ ተብሏልና የተሻለ መረጃም ካለ በሚል እኩለ ቀን ላይ ወደ ጅዳ ቆንስል ሄድኩ። የሳምንቱ የስራ የመጨረሻ ቀን ከመሆኑ ጋር ከሰሞኑ በሳውዲ መንግሥት ለህገ-ወጥ ነዋሪውች በነጻ ሳይታሰሩ ይወጡ ዘንድ ለ6 ወር የሰጠውን የምህረት አዋጂ ለመጠቀም በርካታ ነዋሪዎች ቆንስሉን ሞልተውታል። በቂ መረጃን የሚሰጣቸው ያገኙ አይመስሉም። ሁሉም ስለሁኔታው ያገኙትን ሁሉ ይጠይቃሉ። አምባሳደሩ የታሳሪዎችን ጉዳይ ለመከታተል እንደወጡ አልተመለሱም ስለተባልኩ የማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊውን በጉዳዩ ዙሪያ ለማነጋገር ወረፋ ይዣለሁ።

ተራየን እየጠበቅኩ አልሞላ ካለው የግል ኑሮየ ተንደርድሬ የኛን ኑሮ በሚለው ማጥ ውስጥ ራሴን በሃሳብ ወሽቄ ማሰላሰል ከማውጣትና ከማውረድ አልቦዘንኩም። ለመደብኝ መሰል በቆንስሉና በኮሚኒቲው ጎራ ካልኩ ዙሪያ ገቡን ማየት ይቀናኛል። ከቀናት በፊት በቆንስሉ ግቢ የአንዲት ወጣትን ልጅ ሬሳ አንስተናል። ምንም እንኩዋን በበሽታ ተጠቅታ ብትመጣም ለሳምንት በግቢው ወድቃ ውላ ስታድር አምቡላንስ ለማስጠራት የአንድ ወንድሜ ፊርማ ስናፈላልግ አመለጠችን። ሃኪም ቤት የሚባል ሳይነካት ማስታገሻ ከኒናም ሆነ መርፌ የሚያስወጋት አጥታ ለእኛው ጸጸት ሆናብን አልፋለች። በዚያ አጋጣሚ ያየሁዋቸው አራት ያህል በሽተኞች አንድ ጤነኛ የምትመስል የአእምሮ በሽተኛ ይገኛሉ። ምንም ማድረግ ባልችልም ፊቴን አስመትቻቸው ተመለስኩ።ውደ ባለሥልጣኑ ለመግባት ወረፋ ስጠባበቅ ታዲያ እግረ መንገዴን የአንዳንድ ባለጉዳዮችን ጉዳይ መስማቴና መጠየቄ አልቀረም። እናንተየ ጋዜጠኛ ወሬ ይዎዳል የሚሉት እውነት አይደለም ትላላችሁ? አላፊ አግዳሚ ሰው ወሬውን ወሬ ይለዋል... እኔና ጓደኞቸ ደግሞ ወሬውን መረጃ እያልን እናሰማምረዋለን ... መረጃም እንበለው ወሬ ሁሉም ግን ወደ አንድ አቅጣጫ አይወስዱም በተለያየ አቅጣጫ ወስደው ተገቢ እውነታውን ያስጨብጣሉ ... መከተሉ አይከፋም ... ደግሞም በኛ መንደር እውነቶች የተደበቁ ናቸው! ተከተሉኝ! መስማቱ አይከፋም ...!

መቶ ሺህ ይደርሳል ተብሎ ከሚገመተው ነዋሪ ከሰማያ ሺህ የማያንሰው በጅዳና አካባቢዋ ይኖራል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ ቁጥር መካከል ሶስት አራተኛው ደግሞ ህገ-ወጥ መሆኑ ከግምት ያለፈ አይደለም። ህገ-ወጥም ሆኖ ታዲያ ተጠንቅቀው መግባትና መውጣት የቻሉ ከመውለድ መክበድ አልፈው የቀሩ ቤተሰቦቻቸውን በህጋዊነት በማስመጣት ኑሮዋቸውን ተረጋግተው በመግፋት ላይ ያሉት ቁጥር በርካታ ነው። ድሮ ድሮ ... የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ቢያዙ እንኳ የሚቀረው ሻንጣቸውን ከምረው እንደኮሩ በቦሌ መግባት ብቻ ነበር። ከዚያም እረፍት አድርገው በቀጣዩ ሃጂና ኦምራ ከተፍ ማለት ይቻላል! " ማፊ ሙሽክላ" ችግር የለም! ያ ታዲያ ድሮ ነው...! በቀን ከ9 ሚሊዮን በርሚል በላይ ነዳጂን ለዓለም ገበያ በሚያቀርቡት የፔትሮል ሃብት የናጠጡት ሳውዲዎች አሁን አሁን ነገር አለሙ ገብቷቸው ነቅተዋል። የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን ሃገራቸውን ለማዘመን ብቻ ሳይሆን ብሄራዊ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ ከዓለም የሚገዙትን ጥበብ ይጠቀሙበት ይዘዋል። ዜጎቻቸውን ጨምሮ 27 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅና በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳውዲ የሚገቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለመከላከል ይቻል አዲስ የተከተሉት የጣት አሻራ ነዋሪውን ወለም ዘለም አላደግ ብሎታል። ከሃገር ሲወጣም ሆነ ሲገባ ያለ ጣት አሻራ ነቅነቅ የለም! መውጫ መግቢያው ጥብቅ ሆኗል። እናም እንደ ድሮው ሲያዙ በእስር ቤት አድርጎ ሄዶ በጸሎት ሰበብ መምጣት የሚባል ነገር ተረት ከሆነ ሁለትና ሶስት ዓመት ሆኖታል። ህገ-ወጥ ሆነው ከተያዙና ወደ እስር ቤት ሲዎርዱ አሻራ ይነሳሉ።በህጋዊነት ሲኖሩ አሻራ ይነሳሉ። ከዚያ በኋላ የእርስዎ ነገር አከተመ! ህጋዊ ከሆኑ በህጋዊነት በአሻራዎ እየተለዩ ወጥተው ይገባሉ። ህገ- ወጥ ሆነው ከተያዙና አሻራ ከተነሱ በኋላ ካገር ይባረራሉ። አንዴ ከሳውዲ ከተባረሩ ስምዎን ማንቴስ ብለው ቀይረውና እድሜዎች ቆልለው ወደ ሳውዲ በጸሎትም ሆነ በቪዛ ዳግም እመለሳለሁ ብሎ እንደ ድሮው ማሰብ በራሱ ዘበት ሆኖዋል። "ለሃጣን የመጣ ለጻድቃን" እንዲሉ የብዙዎች ሰላማዊ ነዋሪ ኢትዮጵያውያንን ቤት ማናጋት የጀመረውን የጣት አሻራውን መዘዝ ስንክሳር የሰማሁት በቆንስል መስሪያ ቤቱ ማህበራዊ ጉዳይ ኃላፊ ቢሮ ለመግባት ተራ ስጠባበቅ ነበር።

በዚህ ዙሪያ አሳዛኝ የግል ታሪኩን ያጫዎተኝ መልከ መልካም ጎልማሳ በወሬ ወሬ አድርጌ በውስጤ ያለውን የረብሻውን ጉዳይ ጠየቅኩት። እዚሁ ከቆንስሉ አካባቢ ያመለጡ ልብሳቸው የተቀዳደደና የተጎሰቋቆሉ ወጣቶችን አግኝቶ የኔኑ ያህል መስማቱን ገለጸልኝ። ግድ የሰጠው አይነት ግን አይደለም። ሰባዕናው ግርም አለኝ! ይባስ ብሎ እነሱ ጠፉ ተብሎ በሚደረገው አሰሳ ማለቃችን ነው የሚል አይነት ቃል ወረወረልኝ! ምን ያህል የከበደ ችግር ቢሆን ነው ለወራት በበሽታ አለቁ ሲባሉ የነበሩት ወገኖች ዛሬ ደግሞ ሌላ የሰቆቃ ቀንበር ተጫናቸው ሲባል ሌላው ቢቀር የለመድናትን ከንፈር ያልመጠጠ ስል ራሴን ጠየቅኩ። ጭራሽ " ሊያስጨርሱን ነው" እስከሚል አስተያየት ያደረሰው ምን እንደሆነ ጠየቅኩትና "ሰው ሰራሽ " ስለሚለው ስለራሱ ችግር ያጫውተኝ ገባ። "ፈጣሪ ያመጣባቸው ችግር ነው" ያላቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ታሳሪዎች ችግር ለአንድየ ሰጥቸ በዚህች አጋጣሚ ቆንስል መስሪያ ቤቱ ወረፋ ያገናኘኝን የወድሜን የግለሰቡን ችግር አፌን ከፍቸ እኮመኮኩም ዘንድ ተገደድኩ።

ይህ ለግላጋ ጠይም መልከ መልካም ወንድም በእቅፉ የሶስት ዓመት የሚገመት ልጁን ታቅፏል። በሌላ እጁ እድሜውን ለመገመት የሚያስቸግር የደስ ደስ ያለው ወፍራም ልጁን ይዟል። በአይኑ ልጆቸን ተመልከት በሚል ስሜት የተጋረጠበትን ፈተና ጀመረልኝ። ... ከሰባት ዓመት በፊት ከሰው ጋር ተጋጭቶ ዘብጥያ ሲዎርድ ወደ ፖሊስ በቀረበበት አጋጣሚ የጣት አሻራ በመስጠቱ ዛሬ ያ ሰበብ ሆኖ በእርሱና በመላ ቤተሰቡ ላይ ያላሰበው አደጋ ተከስቷል። ከአሻራው በሁዋላ የመሰረተው ትዳርና ያፈራቸው አራት ልጆቹ በስሩ ስለሚተዳደሩ የችግሩ ዋና ዳፋ ቀማሽ ሆነዋል። ከወር በኋላ መኖሪያ ፈቃዱን ለማደስ በሚሰጠው አሻራ የመኖር መባረሩ ጉዳይ የሚወሰን ይሆናልና በሺ ብር ተርዷል። ይህ ሆነና በዓለም ላይ ያለ ምንም አይነት ችግር ችግሩ አይደለም። በቃ! ከሱ የበለጠ ችግር ያለበት ሰው አለ ብሎ እንዳያምን አይኑን ጨፍኖታል። ንግግሩን ሲጀምር የተረዳሁት ይህንኑ ነበር።... በዚህ ሁኔታ በተለያየ ወንጀል ተከሰው ለፖሊስ የጣት አሻራ የሰጡ የማንም ሃገር ዜጎች ችግር ላይ ወድቀዋል የሚለው የአንድ ሰሞን ወሬ ታወሰኝ። በአዲስ መልክ አሻራ ሲሰጡ ቀድሞ የሰጡት አሻራ ይገኛልና እድላቸው ባንድ ጀንበር ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ወደ ሃገር ቤት መሸኘት እርምጃ አሰቃቂ ቢሆንም በሃገሪቱ ህግ ሆኖ ተደንግጓልና ምንም ማድረግ አይቻልም! ለዓመታት ኑሮውን በሰላማዊ መንገድ እየመራ ባልታሰበ አጋጣሚ የከንፈር ወዳጅ ቀንቶት ቆንጅትን በመኪናው አሳፍሮ ከተገኘ፤ ከሰው ጋር ከተደባደበ፤ "ሰዲቂ" ጉዋደኛየ እየተባለች የምትታወቀውን አረቂ ሲጉመጠመጥ ከተያዘ፤ እና ሌላም ሌላ ሸሪአ የማይፈቅዳቸውን ሲፈጽም ከተያዘ ሁሉም ወንጀሎች ናቸው! አንዴ በወንጀሉ ተይዞ አሻራ ከሰጠ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳዩ ቢዘጋም ለፖሊስ የተሰጠው አሻራ መዘዝ አይለቅም! ዛሬ ላይ የአሻራ ነገር የብዙወችን ቤት በመነቅነቅ ላይ መሆኑን የሰማሁ ቢሆንም የአሁኑ የወንድሜ ትረካ ደግሞ ሁኔታውን በግልጽ አስቀመጠልኝ። ከሁሉም በላይ በላቡ እየሰራ ልጆች ወልዶ ሲያሳድግ ሃገር ቤት ጥሪት ላልቋጠረው ወንድሜም ሆነ ለነገው ባለተራ የኔ ቢጤ መከራው የከፋም ብቻ ሳይሆን ዘግናኝ ነው። "ከፈለግክ መረጃወችን ላቀርብልህ እችላላሁ." የምትለውን ቃል ይደጋግማታል። በጨዋታ መካከል አልፎ አልፎ የሚሰነዝራት ይህች አረፍተ ነገር ማለት የፈለገው ምን እንደሆነ ይገባኛል። ጋዜጠኛ መሆኔን አሳምሮ እንደሚያውቅ ገባኝ። ጭንቀቱ ቢገባኝና ቢያስጨንቀኝም የኒያ ወገኖቹን ችግር "የሰማይ ቤት" የሱን ችግር "ሰው ሰራሽ" ብሎ የመዘነበት ሚዛን ግን አልተመቸኝም። ምልከታው ከራስ ወዳድነቱ የመነጨ ነው በሚል የሰው ችግር ስላልገባው አዝኘበታለሁና እርሱ ለሌሎች ሊላው ቢቀር እስካልራራ ችግሩ ለማንም ሊገባ እንደማይችል አፍረጥርጨ ነገርኩት! ተማምነን እኩል ማሰብ ይዘናል።

ጎልማሳው ወንድሜ ጨንቆት የሁኔታውን አሳሳቢነት ተከታትየ የመንግሥት ኃላፊዎችን አነጋግሬ መፍትሄ አመላክት ዘንድ እንደሚሻ የውስጥ ፍላጎቱ መሆኑን ተረድቻለሁ። ያም ሆኖ ከአሻራው ሌላ "ሰው ሰራሽ" የሚለው ችግር በቆንስሉ ዙሪያ ተከስቶበታል። የሳውዲ መኖሪያ ፈቃዱን ለማሳደስ የሱና የቤተሰቡን ፓስፖርት ለማሳደስ ወደቆንስሉ ካስገባ ወር ሊሞላው የቀሩት ጥቂት ቀናት ብቻ ናቸው። እድሳቱ ግን ባላወቀም ምክንያት ተንቀራፏል። ከዚህ በፊት ጠዋት ገብቶ ከቀትር በኋላ ይታደስ የነበረው ፓስፖት ዛሬ የሚታደሰው አዲስ አበባ ሄዶና ተጣርቶ በመሆኑ " ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ" እንዲሉ "ሰው ሰራሽ " እና "ሃገር በቀል ችግሩ" ሌላ ሰንቃራ ፈጥሮበታል። ወንድሜን አጣብቂኝ ያስገባው የአዲሱ የሳውዲ የጣት አሻራ ህግ ሰውነቱን እየጨረሰው እንደ እርጉዝ ቀኑዋን በመቁጠር ላይ ቢሆንም ከዚሁ ባልተናነሰ የአሁኑ የፓስፖርት እድሳት መጉዋተት ሌላ ራስ ምታት ሆኖበታል። ይህ መሰሉ የፓስፖት እድሳት ማጣራት መዘግየት ደግሞ የእርሱ ብቻ ሳይሆን ከአጠገባችን የተደረደሩት አብዛኛው ነዋሪዎች ጉዳይ መሆኑን ተረዳሁ። በዚህ ዙሪያ ከአምስት ዓመት በፊት በቀላል ወንጀል የተያዘ የጣት አሸራ የሚነሳበት የውስጥ መመሪያ መኖሩን የሰማሁበት የመንግሥት ክፍል እንዳለ ልቤ ቢያውቀውም አጓዋጉል ተስፋ ሰጥቸ ልቡን ላሳብጠው ስላልፈለግኩ የማውቀው መረጃ ካለ እንለዋወጣለን በሚል አድራሻ ተለዋዎጥን።

ወንድሜ ከአንድ ሰአት ላላነሰ ቆይታችን ትኩረት ባልሰጠሁባቸው ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንድሰጥ ፍንጭ ሰጥቶብኝ ወረፋው ደረሰና ገባ። ብዙም ሳይቆይ ፊቱ ተለዋውጦ ወጣ! አዎጣጡ በስጨት ያለ እንደነበርና ሲዎታም እያጉተመተመ ነበር። ሁኔታው ስለገባኝ ወደ ሄደበት አቅጣጫ ሄድኩ ... ላገኘው አልቻልኩም። ልጆቹን በአዳራሹ ላለችው ለናታቸው ወርውሮ መምጣቱንና በደረጃ ላይ አይኑ ደም መስሎ በንዴት ከግቢ ደረጃ ላይ ሲጃራውን እያቦነነ እንደሚገኝ እየፈለግኩት እንደነበር የታዘበች እህት ነገረችኝ። ያ ወንድም ተቀይሮ ፊቱ ደም መስሎ ደም የጎረሰ አይኑን እያጉረጠረጠ አገኘሁት። ምነዋ? አልኩት "አልታደሰም" አለኝ ክችም ብሎ። እንዲረጋጋ ለማድረግ ሞከርኩ። የመኖሪያ ፈቃዱን ተቀብየ የሚታደስበትን ቀን ስመለከተው የእድሳቱ ጊዜ ገና ወር ከ13 ቀን ገደማ ይቀረዋል። ስጋት ሊያድርበት እንደማይገባ የፈቃዱ ማብቂያ ቀን እስኪደርስ ፓስፖርቱ በወር ውስጥ ታድሶ ሊመጣለት እንደሚችል በመግለጽ በማላውቀው ጉዳይ ራሴው አስገብቸ ተብተከተኩ። አቀራረቤ የልቡን ያጫውተኝ ዘንድ አባበለው መሰል ሁኔታውን በሰከነ መንፈስ ይነግረኝ ገባ ... በፓስፖርቱ ዙሪያ ስላለው ችግር የሆድ የሆዱን ካጫወተኝ በኋላ ስጋቱ ገባኝ። በእርግጥም ለአስራ ስምንት ዓመታት የሚገለገልበት ፓስፖርት አዲስ አበባ ሄዶ ተጣርቶ ያታደሳል የሚለው አስግቶታል። ፓስፖርቱ በህጋዊ መንገድ የወጣ ስለመሆኑም ሆነ በማንነቱ ዙሪያ ችግር የለም... ነገሩ እንዲህ ነው... ከዛሬ አስራ ዘጠኝ ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በኦምራ ጸሎት አሳቦ ወደ ሳውዲ ለስራ ሲመጣ የያዛት ፓስፖርት ትክክለኛ ማንነቱን የምትገልጽ ቢሆንም በህገ-ወጥ መንገድ ሳውዲ ገብቶ ተደብቆ እየሰራ ሳለ ከስራ ቦታው ተይዞ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሱ ችግር ተፈጠረ። በወንድም ጓደኞቹ ብርታት ከነበረችው ጥቂት ገንዘብ ተጨማምሮ ቪዛ ተገዝቶለታል። አሁን ራሱን ረድቶ በድህነት አረንቁዋ የሚታሹ ቤተሰቦቹን መጻኤ ህይወት ለማሳመር ቁርጠኛ ውሳኔ መውሰድ አለበት። የተሻለ ለመኖር ሲል የሚወዳቸው ወላጆቹ ያወጡለትን ስምና እድሜ አሽቀንጥሮ መጣሉ ግድ ነው። ስሙ ሲጠራ ቀልጥፎ "አቤት" የሚልበት የሚያስታውሰው አዲስ ስም መርጦ ፓስፖርት የማውጣት እንቅስቃሴውን ጀመረ። የፓስፖርቱ ጉዳይ በቀልጣፋ የመርካቶና የጥቁር አንበሳ ደላሎች ግቡን መታ። ዳግም ወደ ሳውዲ ለመመለስ ያችን ዋና ስም መልሶ መጠቀም አይችልምና ከልጂነት እስከ እውቀት የሚጠራበት ስሙን ባይ ባይ ይል ዘንድ የግድ ነበር። ፓስፖርቱ ወጣ! በፓስፖርቱ የሰፈሩት መረጃዎች ከቁመቱ፤ ከከለሩ፤ ከኢትዮጵያዊነቱና ከፎቶው ውጭ ስሙ እድሜውና የትውልድ ቦታው ግን እሱነቱን ፈጽሞ አይገልጹትም። መከራው እዚህ ላይ ነው! የዛሬው ማጣራት አቀበት ገደል ቁልቁለት የሆነበት ይህንን እውነት ለካስ በውስጡ እየተገላበጠ ነበር! ጭንቀቱ ገባኝ! ከአስራ ስምንት ዓመት በኋላ ፓስፖርቱ ይጣራ ተብሏል። የዚህ ወንድም ፓስፖርት ለማጣራት ተልኳል። እንዴት ነው ፓስፖርቱ ተጣርቶ የሚመለስ? በትውልድ ቦታ? በስም? በእድሜ? ራሱን የበጠበጡት መልስ ያጣላቸው ጥያቄወች ናቸው። በቃ! ከክቡር ኢትዮጵያዊነቱ ባለፈ ሁሉም ነገ ለቁራሽ እንጀራ ሲባል ተቀያይሯል! ማጣራት እንዴት ነው የሚከወነው? እንዴትስ ነው የሚሆነው? የምንሆነው.? አልገባውም! አልገባኝም! አልገባንም! አይገባም! በዚህ ሁኔታ ከወንድሜ ጋር ተለያየን!

በዚሁ የፓስፖርት እድሣት ጉዳይ ተመሳሳይ ቅሬታ እንዳላቸው ያጫወቱኝን ሌላዋ እናትና አንዲት እህት ከባለሥልጣኑ በር እንደኔው ተራ ሲጠብቁ አግኝቻቸው ተመሳሳይ ሃሳባቸውን አጋርተውኛል። የሃገር ደህንነትን ለማስጠበቅ ስራ አይሰራ የሚል ባይኖርም የማጣራት ስራው ሲከወን በዘፈቀደ ሳይሆን በጥናትና ነባራዊ የዜጎችን መሰረታዊ ችግር ባገናዘበ መንገድ መሆን አለበት የሚለውን አስተያየት ብዙዎች እንደሚጋሩት ተረድቻለሁ። በቅርቡ በታሳሪዎች መካከል በዜግነት ማጣራት ምክንያት የታየውን እንግልት በቅርብ ተመልክቻለሁና ጉዳዩ ይገባኛል። አሁን ደግሞ በህጋዊው ነዋሪ ላይ ማጣራቱ ሌላ ጣጣ እንዳያመጣ ስጋር ጋርጧል። በሳውዲ አንድ ህጋዊ ነዋሪ በአሰሪው ጥላ ስር የመሆኑ ጣጣ ብዙ ችግር እንዳለበት ይታወቃል። በተለይም በአንዳንድ አሰሪዎች ዘንድ የመኖሪያ ፈቃዱን ለማሳደስ ፓስፖርትን እንደፈለጉ መውሰድ ቀርቶ ሃሳቡን ማምጣት የማይቻልበት ሁኔታ የተለመደ ነው። ይህ መሰሉን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ በሚወርዱ መመሪያና ህጎች ከመውጣታቸው በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዴት ጥናት አያደርግም? የሚለው ጥያቄ ተጠይቆ መልስ የሚገኝበት ቦታ ሁሉ መልስ አጥቻለሁ። "የሃገር ደህንነት ነውና የምንደራደረው compromise የሚደረግ አይደለም" የሚለው መልስ አላጠግብ ብሎናል። አማራጮች ለምን አልታዩም? ለሚለው አሁንም መልሱ ያው ነው! ወረፋው ብዙ ነው። በእስር ቤቱ ረብሻ ዙሪያ ላነጋግረው ከምፈልገው ባለሥልጣን ሊነግሩኝ የሚችሉትን አዲስ ነገር ምን ሊሆን ይችላል? ብየ እራሴን ጠየቅኩ ... ትንሽ ቆይቸው በጉዳዩ ዙሪያ ላገኘው የምችለውን መረጃወች አዲስ ሊሆኑ እንደማይችሉ በመገመት መቆየቱ አልዋጥልህ አለኝ። የሰማሁትን በልቤ አድርጌ በአግራሞት ወደ ቤቴ ማቅናት ነበረብኝ ተንቀሳቀስኩ።

በእስር ቤቱ ረብሻ ዙሪያ ስለቆሰሉትና ስላመለጡት ዝርዝር ዜና ለመስራት ሰአቱ ባይኖርም ለመረጃ ያህል በዜና እወጃው ሊቀርብ የሚያስችሉ መረጃዎችን ወደምሰራበት ራዲዮ ላኩ። ያም ሆኖ በዜናው መቅረብ ዙሪያ ተስፋ የምጥልበት አለመሆኑን ምልክቶች ጠቁመውኛል። የምፈልጋቸው ሰወች ደወልኩ። መልስ የለም። ደገምኩ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ሰማሁ። ስብሰባ፤ ስራ ላይ መሆንና ሌላ ሌላ ምክንያቶች ቢደረደሩም አልተገናኘንም ... የጥልቅ ስሜቴን አድማስ አልፎ እኔን ሆኖ የሚረዳልኝ፤ ሙቀቴ ይሞቀዋል የምለው ሳተናም ሆነ የበሰለ ሙያዊ ምክሩ ጠብ የማይለው ወንድም ተረኛ አይደሉምና የልቤ ሳይሞላ ቀረ! እንዳመመኝ መሽቶ ነጋ ... የማይሆንበት ምክንያት አላሳመነኝምና ከፍቶኛል ... የማድረግ ፍላጎቴ እየጦዘ ደሜ ሲንተከተክና የጎልማሳነት እድሜየ እልህ ደሜ ውስጥ ውስጥ ለውስጥ ሲንሸራሸር ታወቀኝ። በአረቡ ዓለም በተለይም በሳውዲ ዐረቢያ ጋዜጠኝነት በፈተና የሚሰራው ስራ እንጂ እንደቀረው ዓለም በቀላል ፈተናዎች ብቻ ታልፎ የሚከወን አይደለም። በአንድ ወቅት ለዓመታት ታግዶ የነበረው የታዋቂው የአልጀዚራ ጋዜጠኛ የሆነ ወዳጀ "ጋዜጠኛ በጣም የማከብረውና የምወደው ስራ ነው! ጦርነት በቀለጠባቸው በባግዳድና ሁከት በማይጠፋበት በጋዛም ቢሆን ... ጋዜጠኝነቴን እወደዋለሁና የምሰራው በደስታ ነው! በሳውዲ እንዴት ነው ብትለኝ ግን ጋዜጠኝነቱ ቢቀር ይሻላል።" ሲል የመለሰልኝ ሙያው ምንያህል አስቸጋሪ መሆኑን ገላጭ ይመስለኛል። ያም ሆኖ ሁሉን ችለን እንስራ ላልን ስራው ተደክሞበት ከሰሚው ጀሮ በሰአቱ ሳይደርስ ሲቀር እንደሚያም የሚያውቀው የደረሰበት ብቻ ይመስለኛል... ስሜቴ ቢጎዳም ደግ ደጉን ማሰብ ያዝኩ። በትርፍ ሰአቴ የምሰራው የጋዜጠኝነት ሙያ ባለሁበት ሃገር ነጻ ሆኖና ዘና ተብሎ የሚሰራበት አይደለም። ወንድሜ እንዳለው በጋዜጠኝነት ሙያ ሳውዲ ውስጥ መስራት የመረገምን ያህል የመረረ ነው። መርጃን በቀላሉ ማግኘት፤ ባለሥልጣናትን ቀርቶ ተራ ሰውን መቅረጸ ድምጽ ይዞ ነዋሪውን ማነጋገርና ፎቶ ማንሳይ አልተለመደም። ያም ሆኖ የምወደው ሙያ መፈንገሉን ላልመረጠ የኔ ቢጤ ስራው ሁሌ ባደጋ ተከቦ መስራት ቢሆንም ያረካል ... የሚገኘው እርካታ እንጂ የሚገኘው ጥቅም ከዘንድሮ ሞባይል ካርድ የሚያልፍ አለመሆኑን ያላየ አያምነምና ዝም ማለቱ ይሻላል። ከሁሉም በላይ በሙያው ፍቅር እየተንቀለቀለ ላደገ ጎልማሳ ስራ ተሰርቶ በተሎ የሚታይበትና በተሰራው ስራ የህዝብ ፍርድ በቅጽበት የሚገልጽበት ሙያ ጋዜጠኝነት ነውና ደስተኛ ነኝ። ሙያውን ይበልጥ እወደው ዘንድ ደግሞ የስራ ባልደረቦቸ ምክንያት ሆነውኛል። ሁሉም አንደበተ ርቱዕ ናቸው። የሚሰሩትን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ልምዱ፤እውቀቱ፤ የሙያዊው ስነ ምግባር ከየራሳቸው የተፈጥሮ ክህሎት አቀራረብ ጋር የየግል ችሎታቸውና ዝግጅቶቻቸውም መለያ ሆነዋቸዋል። የላኩትን በመረጃ የተደገፈ ትኩስ ወሬ በዜና እወጃው አለመቅረብ እያሰላሰልኩ በሙያውና በስራ በልደረቦቸ ዙሪያ ይህችን ታህል አውጥቸ ያወርድኩትን ፋይል በዚህ ይዘጋ ...

ወደ ቆንስል መስያ ቤቱ መረጃን ለማሰባሰብ ሄጀ እንደ ባለጉዳይ ሆኘ የሰማሁት ታሪክም ሆነ የምከታተለው የግፉአን እስረኞች ምክንያቱ የዜግነት ማጣራት እንደሆነ ገሃድ የሚታይ እውነታ ሆኖዋል። ማጣራቱ ባይከፋም ያለጥናት መጀመሩ ወጌን የጀመርኩበት የታሳሪዎች እስር ቤትን ሊያሰብር ያስቻለው አመጽ ምክንያት መሆኑን መካድ ከቶውን አይቻለንም። ለወራት የእስር እንግልት በህክምና እጦት ለሞት መዳረጋቸው ምን ምክንያት ሊቀርብለት ይችላል? ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ በታሳሪዎች የጀመረው የማጣራቱ ምስቅልቅል ወደ ህጋዊ ነዋሪው የሚሸጋገርበት መንገድ በሰፊው መስተዋል ጀምሯል።

ከቅርብ ጊዜ ሳምንታት ወዲህ የጉዳዩ በዓለም አቀፍ ደረጃ መራገብን ተከትሎ በሳውዲ ዐረቢያ የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማቶቻችን መንቀሳቀስ ጀምረዋል። አምስት ወራት ዞር ብለው ያላዩዋቸውን ዜጎች ዲፕሎማቶች ጉዳይ ፈጻሚ ከመላክ ባለፈ አይተዋቸው የማያውቁዋቸውን በሺዎችን የሚቆጠሩ ታሳሪዎች ማየት ጀምረዋል። እሰየው ነው! ረብሻውን ተከትሎ ችግሩ እንደተፈጠረና ማታውኑ በአምባሳደሩ የሚመራ የዲፕሎማት ቡድን ኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች የሚገኙበትን የረብሻ ቦታ ጎብኝተው ተስፋ ለቆረጡት ተስፋ ሰጥተዋቸዋል። አንድ ሺህ ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች የመጓጓዣ ሰነድ የማከፋፈላቸውን ብስራት እንቅስቃሴዋን ሁሉ የሚያስረዱኝ ታሳሪዎች ሁኔታውን ሲገልጹልኝ አነበው የነበር ደስታ የዋሉበትን መከራ ያስረዳ እንደነበር አፍን ሞልቶ መናገር ያስችላል።

ቀጣይ ስራየ ትናንት ማታ ታሳሪዎችን ሲያነጋግሩ ያመሹትን አምባሳደር ተክለአብ ከበደን በጉዳዩ ዙሪያ መረጃን ለማግኘት ማነጋገር ነው። ወድ አምባሳደር ተክለአብ ለመደወል ሰአቱ ጥሩ አልነበረምና በተንቀሳቃሽ ስልካቸው መልዕክት አስተላለፍኩ። ቃለ መጠይቁን ለማድረግ ፍቃደኛ መሆናቸውን ገለጹልኝ። ያልጠበቅኩት ነበርና ደስታየ ወሰን አጣ። አምባሳደሩን በቀጠሮ አግኝቻቸው በጉዳዩ ዙሪያ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ማነጋገራቸውንና የቆሰሉ ኢትዮጵያውያን ካሉም መረጃ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ገለጹልኝ። ስለ እስረኞች ሁኔታ ከታሳሪዎች ያገኘሁትን ተመሳሳይ መረጃ ጠቃሚ መረጃን ሰጡኝና በምስጋና ተለያየን። ደግሞም ትናንት ወሬው በትኩሱ ለምን አልቀረበም ብየ ብነጫነጭም ዛሬ እንደሚቀርብ ሌላ ማረጋገጫ በማለዳው ደርሶኛልና የአየር ሰአቱ ተቃርቧል። ቃለ መጠይቁን ከኔው መግቢያ ጋር አቀላቅየ ማቅረብ ይጠበቅብኛልና ተቻኩየ ወደ ቤቴ አቀናሁ ... ደግሞም አስተናጋጁ የኔ ነገር የሚገባው ወንድም መሆኑ ደግም ደስ ብሎኛልና የምሰራ በሞራል ነው!... አብዛኛው የጅዳና አካባቢው ነዋሪ መነጋግሪያ በሆነው ረብሻ ዙሪያ እስረኞች ሞተዋል የሚልና ሌላም ያልተጨበጡ መረጃወች እየተበተኑ መሆኑን ስምቻለሁና ያዛሬው ዜና ትክክለኛ መረጃን እንደሚሰጥ እምነት አለኝ።ደግሞም ተስፋፍቶ የተነገረው የሞቱ ቆሰሉ ወሬው ከወላጂ ሲደርስ የሚፈጥረውን ስሜት አልወደድኩትም ነበርና አየር ላይ ሲውል የተሰማኝን ስሜት መግለጽ አልተቻለኝም። እለተ ሃሙስ መስከረም 20 ቀን 2003 ዓ.ም. ...

እርግጥ ነው ዲፕሎማቶቻቸን አሁን አሁን የሚያሳዩት እንቅስቃሴ ወዴት ከረመ ያስብላል። ከዚህ ቀደም የዜጎቻቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚወስዱት እርምጃ እምብዛም አያስደስትም ስንል በአስተማሪነቱ ሊወሰድ ይገባለና ችግሮች መጠቆማቸው ጉዳት አይኖረም። ስራ አልተሰራ ለማለት ባልዳዳም ሌት ተቀን ተሰርቶ የሚገኘው ውጤት አላጠገበንም የኔና የመሰሎቸ ሃሳብ ሳይሆን ከነዋሪው የቃረምነው መልስ ነው። ለዚህም በዋቢነት ከሁለት ወራት በፊት አምስት ኢትጵያውያን ሞተዋል ተብሎ የሳውዲ ሰብዓዊ መብት ተከራካሪና የሃገሪቱ ጋዜጦች ሳይቀር ይፋ ያደረጉትን የጀዛን እስር ቤት ታሪክ መመልከት እንችላለን። ዜጎች ሞቱ ከተባለና የእስር ቤቱ አያያዝ አስከፊ ነው ከተባለ ሁለት ወር የደፈነ ቢሆንም እስካሁን ድረስ አንድም ዲፕሎማት ሄዶ የሞቱትን ማጣራት ይቅርና በቁማቸው እየሞቱ ስላሉት ዜጎች የጠየቀ የለም። ለምን? "የሳውዲ መንግሥት ለዲፕሎማቶች የመጎንኛ ፈቃድ አልተገኘም።" ባሳለፍነው ሳምንት በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርኩዋቸው አንድ ልጅ እግር ዲፕሎማት ገልጸልኛል። ይህ ትክክለኛ መልስ ሊሆን ይችላል። ለሰሚው ግን የማይዋጥ መምሰል ሊያስደንቅ አይገባም። ቁም ነገሩ ያለው ግን እንኳንስ ዜጎች በግፍ ሞተዋል ተብሎ በሃገሪቱ ጋዜጣወች እየተነገረ አፋጦ መጠየቅና መብትን ማስከበር ቀርቶ ዲፕሎማቶቻችን እስር ቤት ያሉትን ዜጎቹን ለመጎብኘት የማይቻለው ከሆነ ሁኔታው አደገኛ ነው። እንደተባለው ለሁለት ወራት እስር ቤት ለመጎብኘትም ሆነ ስለሞቱት ለመጠየቅ ፈቃድ የማይገኝ ከሆነ ዜጎችን መጠበቅ መሰረታዊ አላማ አድርጎ የተነሳው የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ስራ ህልውና አደጋላ ነው ያስብላል! ከዚህ ባለፈ ምን ማለት ይችላል? ይህ እንደ ቀለል ሊታይ አይገባም። በሃገር ደረጃ ጉዳዩ ተነስቶ መላ ሊፈለግበት ይገባል። የዜግነትን ማጣራቱን በሚመለከትም ቢሆን በተለይም በሳውዲ ዐረቢያ የሚገኙ የመንግስታችን ተወካዮች መመሪያ ሲወርድላቸው ከመቀበላቸው አስቀድመው ሊያጠኑትና ሊመክሩበት ይገባል! መመሪያ ሲወርድ ተቀብሎ የሚያስፈጽም ሳይሆን የመመሪያውን አተገባበር ከነባራዊ ሁኔታዎች የሚያገናዝቡ ኃላፊዎችን እንሻለን ...! በተለያዩ እስር ቤቶች ተሸፋፍኖ የሚገኘው የኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች ጉዳይ ትኩረት ይሰጥበት ዘንድ የፓለቲካ ጎራ ሳንለይ ልንተይቀውና መፍጥሄ ሊሰጠው የሚገባ በመሆኑ ሁሉም የተቻለውን ያድርግ! ... ይህ ጉዳይ እልባት ካላገኘ መላው፤ መያዣና ማጣፊያው እንዳይገድ ያሰጋል! ሁኔታውን በማስተካከሉ ረገድ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ አንድ ሊሉት ይገባል! መሪዎቻችን የአብዛኛው ነዋሪ ሮሮ ሊያደምጡለት ይገባል! የተደበቁ እውነቶቻችን ብዙ ቢሆኑም ለዛሬው ትኩረት የሚሻው ይህ ይመስለኛል! የረመዳን ዋዜማ እስከ ኢድ በሚዘልቀው ወጋ ወጌ የተደበቁ እውነቶች አቅም የፈቀደውን ያህል እንወገውጋቸዋለንና ... በቸር ይግጠመን! ... (ይቀጥላል ...)


ነቢዩ ሲራክ - ከሳውዲ ዐረቢያ

መስከረም 23 ቀን 2003 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!