በሳውዲ ዐረቢያ የኢትዮጵያውያን መከራ - የተደበቁ እውነቶች - በረመዳን ዋዜማ (ክፍል ሁለት)

ነቢዩ ሲራክ - ከሳውዲ ዐረቢያ

ረመዳን ለመግባት የቀሩት ጥቂት ቀናት ናቸው። በመጀመሪያ ክፍል መጣጥፌ እየተውተረተርኩ ለማስረዳት እንደሞከርኩት "የዐረብ ሀገር ኑሮ መረረን! ኑሮ አንገሸገሸን በቃን! ወደ ሀገራችን እንገባ!?" በሚል በፖሊስ ለመያዝ ድልድይ ስለወደቁት ወገኖችና በሳውዲ ስለ ረመዳንን አቀባበል ሽር ጉድ የታዘብኩትን ለማሳየት ሞክሬያለሁ። አብዛኛው እህቶችና ጥቂት ወንድሞቸ ከተኮለኮሉበት ድልድይ ስር በደረሰባቸው የወረበላ ወከባ፤ መደብደብና መደፈር ተማርረው ጂዳ ወደ ሚገኘው ቆንስል መስሪያ ቤት ቢያቀኑም ምላሽ አለማግኘታቸውን ለማስቃኘት መዳዳቴን አትረሱትም። በአምስት ቀን ቆይታቸውን ካየሁትና ከግፉዓኑ የሰማሁትን የምስክርነት ቃል ላጋራችሁም ሞክሬያለሁ። ማንበብ እንዳላሰለቻችሁ በሚል የመጣጥፌን ሃሳቦች ሰብሰብ ለማድረግ በግርድፍ በግርድፉ ለማስቀመጥ ስሞክር አልፎ አልፎም ቢሆን የዓረፍተ ነገር መጣረስ የፊደል ግድፈት አልጠፋም። ለዚህም ይቅርታ ጠይቄ ወደ ዛሬ ወጋ ወጌ ላቅና ...

በድልድይ ስር ለወራት ተጠልለው ስለሚገኙት አቅመ ደካሞችና ወደ ሀገራቸው ኢንባሲ ስሞታ ሊያሰሙ ስለተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መፍትሄው ምንድን ነው? ምንስ ማድረግ ይቻላል? በማለት የሳውዲ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችንና የሰብዓዊ መብት መስሪያ ቤቶች በር ማንኳኳት ይዣለሁ። በተለያዩ ጉዳዮች ምክርን የሚሰጡኝ The National Society for Human Rights ተብሎ የሚጠራው ሀገር በቀል የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ መስሪያ ቤት ኃላፊዎችን በጉዳዩ ዙሪያ አማከርኩዋቸው። ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑንና መስሪያ ቤታቸው በችግሩ ዙሪያ ጥናታዊ ፊልም ድረስ ሰርቶ ለከፍተኛ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ለማሳወቅ የወሰዱትን እርምጃ እየተረኩልኝ የተጋበዝኩትን ፊልም ተመለከትኩ። "... ዲፕሎማቶች ለዜጎቻቸው አዝነው የሚቻላቸውን ካላደረጉ እጃቸውን መጠምዘዝ አይቻል!" አለኝ በጥናታዊ ፍፊልሙ አርታኢ ሳውዲ ወንድም ... ያልገባኝ የተሸፈነብኝ ሃቅ መውጣት ይዟዋል! የሳውዲ ፖስፖርት መስሪያ ቤት ፖሊስ ኃላፊዎችም ስለ ኢትዮጵያውያኑ ጉዳይ ሳነጋገራቸው "... እንኳንስ ከድልድይ ስር ልንይዝ ቆንስል መስሪያ ቤታችሁ በእስር ላሉት በሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች የመጓጓዣ ሰነድ ባለማቅረቡ ችግር አለብን። ችግሩ ከኛ አይደለም። ሁኔታውን በትክክል መረዳት ከፈለግክ ሂድና ተወካዮቻችሁን አነጋግር።" በማለት የጊዜያዊ ማጎሪያው ኃላፊ ከፍተኛ መኮንን ገልጸውልኛል። ይህን ሲሉ ግን የሰጡኝን መረጃ መጠቀም ብችልም ስማቸው በየትኛውም መንገድ በራዲዮና በቴሌቪዥን ሊጠቀስ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ሳያሳስቡኝ አልቀረም።

ከሁሉም አቅጣጫ የተሰጠኝን መረጃ ወደ ጂዳ ቆንስል መስሪያ ያመላክታልና ወደዚያው አመራሁ ... ዕለተ ረቡዕ የቆንስሉ ሆነ የተላያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የመጨረሻ የሥራ ቀን በመሆኑ በርካታ ባለጉዳዮች ጉዳያቸውን በጊዜ ለመከወን ከወዲያ ወዲህ ይሯሯጣሉ። የፓስፖር ጥያቄ፤ የእድሳት፤ የጋብቻ ቃልኪዳን፤ የፍች፤ የቪዛ ማረጋገጫ፤ የሰነድ ማረጋገጫ፤ የውክልና፤ ገንዘቤን በቪዛ ነጋዴ ተበላሁ ክስ፤ የዜግነት ማጣራት፤ ፓስፖርታቸውን ለማደስ አስገብተው በአንድ ወር ውስጥ ታድሶ ያልመጣላቸው ቅሬታ፤ በሀገር ቤት ልማት ለመካፈል ፍላጎት ያላቸው ነዋሪዎች የትብብር ደብዳቤ ጥያቄና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሚፈልጉ የተለያዩ ሀገር ዜጎች የቆንስል መስሪያ ቤቱን ከአፍ እስከደገፉ ጢም አድርገውታል።

ወደ ቆንስል መስሪያ ቤቱ ባለሥልጣናት ያመጣኝ ጉዳይ በእስር ስላሉ ዜጎች እንግልት ነው። በዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ የቆንስል ባለሥልጣናትን ስጠይቅ "... ትልቁ ችግር የዜግነት መለያ መታወቂያ ሳይዙ በባህርና በተለያዩ ሕገ-ወጥ መንገዶች ወደ ሳውዲ መግባታቸው ነው" የሚል ተደጋጋሚ መልስ ሰጥተውኛል። ሕገ-ወጥ ተብለው በተለያዩ እስር ቤቶች የታጨቁ ዜጎች ለወራት እንግልት እየደረሰባቸው የመገኘቱ ሚስጥር ግን ሰምተን "ጀሮ ዳባ ልበስ" ካልን ከጥቂቶች ውጭ ለብዙዎች ገሃድ አይደለም። ሕገ-ወጥ ተብለው ሕገ-ወጥ እርምጃ ሲዎሰድባቸው ማየት የቻልን ባንጠፋም፤ ፍርሃታችን ሕገ-ወጡን ድርጊት ሳንዎድ በግድ አምነን እንድንቀበል አድርጎናል። የታሳሪዎች ለረዥም ወራት ያለ ህክምና መንገላታትና ለከፋ ደዌ በሽታና ለቅስፈታቸው ምክንያትና ሰበቡ ማን ነው? ብሎ በመጠየቅ ችግሩን በእርግጠኝነት ለመረዳት ባደረግኩት ሙከራ መልስ የምሻው የቆንስል መስሪያ ቤቱን ብቻ ሆኗል። ከዚህ ቀደም ባደረግኳቸው ክትትሎች የሳውዲ መንግሥት እጅ የሌለበት መሆኑን ከተለያየ አቅጣጫ የማገኛቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። በማቆያ እስር ቤቶች በሚታየው የእስረኛ ብዛት በመጨናናቁ የሚፈጠረው ችግርና በእስረኛ አያያዙ ዙሪያ የሚታየው ጉድለት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ብዙዎችን ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የሳውዲ መንግሥት ኃላፊዎችን ሳይቀር እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ሆኗል። ያም ሆኖ የሳውዲ መንግሥት ባለሥልጣናት ለዜጎች ለረጅም ወራት በጊዜያዊው እስር ቤት መቆየት ምክንያት የቆንስልና የኢንባሲ መስሪያ ቤት ነው በማለት መውቀሳቸው አልቀረም። ሕገ-ወጥ ነዋሪዎች በጊዜያዊ እስር ቤት ለጥቂት ሳምንታት በማስቀመጥና በማጣራት ከምግብ አልፎ የቲኬት እየከፈሉ ወደ ሀገራቸው እንደሚልኩ ሰነዶችን በእማኝነት በማቅረብ የሚናገሩት የፓስፖርት ከፍል ከፍተኛ ኃላፊዎች መንግሥታቸው እንደ ጲላጦስ እጁ ከደሙ ንጹህ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ እውነት ይሆን? የዚህን ጥያቄ መልስ ከማገኝበት በር ላይ እገኛለሁ ... በጂዳ ቆንስሉ ጽ/ቤት ...

ባለሥልጣኑን ለማግኘት ከአንድ ሰዓት ላላነሰ ጊዜ ወረፋ መጠበቅ ነበረብኝ። ሰዓቴ እስኪደርስ ከወዲያ ወዲህ እየተንጎራደድኩ የባለ ጉዳዩን ብዛት ቃኘሁ። አንዳንዱ ጉዳዩ ተሳክቶለት ግልጋሎቱን እያወደሰ ደስ ብሎት እየፈነደቀና እየሳቀ ይወጣል። አንዳንዱ የመጣበት ሳይሳካ ቀርቶ ከፍቶት እየተሳደበ ኩርምት፤ ኩምሽሽ ብሎ ቅስሙ ተሰብሮ ውልቅ ይላል። ከስድስት የማይበልጡ ዲፕሎማቶችና ሃያ የማይደርሱ ቅጥር ሠራተኞች በቀን ከ300 እስከ 500 ለሚደርሱ ባለ ጉዳዮች ህዝባዊ ግልጋሎትን ይሰጣሉ። የተገልጋዩና የግልጋሎት አቅራቢው ቁጥር አይመጣጠንም። ያም ሆኖ ከማእከላዊ መንግሥት ያለ ጥናት የሚወርዱ መመሪያና ትዕዛዞች ደንቃራ እየሆኑም ቢሆን የተቀላጠፈ ግልጋሎት ለመስጠት የሚደረገው ሙከራ አላዳከመውም። ሁሉም ባለው ኃይል ስለሚሰራ በተገቢ መንገድ ሰው ይስተናገዳል። የማህበራዊ ኑሮ ኃላፊ የሆኑትን አጠርና ደልዳል ያሉት ወንዳወንድ ዲፕሎማትን ለማግኘት ከግማሽ እስከ አንድ ሰዓት መጠበቁ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩን ያሳያል። ይህን መሰሉ ችግር ተቋቁመው የሚስተናገዱት ባለጉዳዮችና አስተናጋጅ ሠራተኞች ህዝባዊ ግልጋሎት ፍጹም ትዕግስትን እንደሚጠይቅ ለመረዳት አያዳግትም። ይህንና ያንን ሳሰላስል ተራየ ደረሰና ወደ ባለሥልጣኑ ቢሮ ገባሁ ...

በቢሮው ውስጥ በርካታ ባለጉዳዮች አሉ። የገባው ባለጉዳይ ጉዳዩን ጨርሶ ሲወጣ የሚታየው አልፎ አልፎ ነው። የሚፈራረሙ፤ የሚመሰክሩና ሌላም ሌላ ጉዳይ ያላቸው ሰወች ቢሮውን ሞልተዋል። ባለልጣኑ - በቀኝ በኩል ያለውን በኦሮምኛ፤ ከፊት ለፊት ያለውን በአማርኛ፤ ትንሽ ይቆዩና ደግሞ የስልክ ጥሪውን ይመልሳሉ፤ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፤ መልዕክት ይቀበላሉ! ... ሁሉንም ናቸው! ፍጥነታቸው ብቻም ሳይሆን ትዕግስታቸው "አጃኢብ" ነው! በዲፕሎማሲው መስክ ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነታቸው ተመርጠው ልክ የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ ሳውዲ ሲመጡ ያየናቸው ቁጡ ወንድሜ የአሁን ማንነት በእጂጉ ተቀያይሮዋል! ከአብዮታዊ ካድሬነት ወደ ህዝባዊነት የተቀየሩበትን ፍጥነት አሰላሰልኩትና አስደመመኝ ... ተራየ ቢሆንም ከማያቸው በርካታ ባለጉዳዮች ተራ ይደርስ ዘንድ ብዙ ሰዓት ማጥፋት አልፈለግኩም ... ደግሞም ጉዳየ አስቸኳይ ካለመሆኑም ጭምር ጥያቄየን ሰብሰብ አድርጌ በአጭሩ አቀረብኩላቸው። ሥራ በዝቶባቸውም ይሁን ሌላ፤ ሆድ የማይሞላ መልስ ሰጡኝ። እንዲያው በደፈናው "ችግሩ ያለው በነዋሪዎች ሕጋዊ አለመሆን ዙሪያ ነው" በማለት ከእቁብ ግባ የማይባለው መልሳቸው ለመረጃ ያህል እንጂ በመገናኛ ብዙሃን ሊቀርብ የሚችል ባለመሆኑ በሌላ ጊዜ በሰፊው ለመነጋገር በቀጠሮ ተለያየን።

ሃቁን ለማግኘት ... ጥረቴን አላቁዋረጥኩም ... ፍተሻየን ቀጥያለሁ። ከጂዳ አልፎ በቢሻ፤ በአብሃ፤ በከሚስ ምሸት እና ሃበዞች እንደቸው በተበተንንባቸው የተለያዩ የሳውዲ ከተሞች ተመሳሳይ ችግሮች ጎልተው መውጣት ይዘዋል። በተለይም በሳውዲና በየመን የጠረፍ ከተማ በጀዛን የኢትዮጵያውያኑን የመከራ ህይወት ሳላስበው የዓይን ምስክር መረጃዎችን አገኘሁ። በጀዛን የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤት መኖሩ ትዝ አለኝና ወዳጀ እየሆኑ የመጡትን የጂዳና መካ ኃላፊ ስልክ ደውየ ጠየቅኳቸው። አጋጣሚው ተመቻቸላቸው መሰል "ቀልጠፍ ብለህ ና " አሉኝ ... ብዙ ሳልቆይ ከጂዳን ከተማ ሰሜናዊ አቅጣጫ ይዠ ከምሰራበት የኢንዱስትሪ ከተማ ቀይ ባህርን በግራየ እያየሁ ወደ አየር ጣቢያው የሚወስደውን የቀለበት መንገድ ይዥ ገሰገስኩ። ሙቀቱ የመኪና ማቀዝቀዣ ሊቋቋመው ከሚችለው በላይ ደርሷልና ወበቀኝ ... ማቀዝቀዙ ቀርቶ ሳት ከሚተፋው የመኪና "ሙከየፍ" ማቀዝቀዣ መስኮቱ ይሻላል ብየ መስኮት ከፈትኩ። በሁሉም መስኮቶች በጸጥታ ከሚስገመገመው ከቀይ ባህር የሚመጣው ነፋሻ አየር ከበረሃው ሃሩር ጋር እየተጋጨ ከሙቀት ጋር የተቀላቀለ ነፋስ እየማግኩ ቆራርጨ ከከተማው ትንሽ ወጣ ብሎ በሚገኘው የሰብዓዊ መብት መስሪያ ቤት ቢሮ ደረስኩ።

በሳውዲ ሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ጽ/ቤት ልደርስ አካባቢ እኒያ የድርጂቱ ባልደረባ ጉዋደኛየ ደወሉልኝ " ስማ ... ዛሬ እኔን ልትጠይቅ ነው የመጣህ . ጓደኛየ ነህ። " አሉኝና ሁሌም በቅንነታቸው የምደምቅባቸውና በሰብዓዊ ፍጹም ርህራሄያቸው የሚያስደምሙኝ፤ በሃሳባቸው በተግባቢነታቸው የምደሰትባቸውን ወንድም ምክር በእሺታ ተቀበልኩ ... ቢሮ የደረስኩት ፈጥኘ ቢሆንም አንድ ባለጉዳይ ቀድሞኝ ነበር። ጸሃፊያቸው ተራ እንድጠብቅ ጠይቆኝ ያቀረበልኝን ቀዝቃዛ ውሃ እየተጎነጨሁ የድርጂቱን ዓላማ የምታስረዳ ቁራጭ ወረቀት አገኘሁና እሷኑ ከላይ እስከ ታች አንብቤ ጨረስኩ። ተራየ ደረሰና እንድገባ ተጋበዝኩ። ሰተት ብየ በለመደ እግሬ ገባሁ። ከሚያምረው ዘመናዊ ቢሮ ውስጥ ወለል ብሎ ከሚታየው የሚያምር ጠረጴዛ መካከል እኒያ ወንድሜ በግርማ ሞገስ ተቀምጠዋል። ከጠረጴዛው በቀኝ ጎን "አላህ ወአክበር" የሚል ዐረብኛ ነጭ ጽሁፍና ከስሩ ጎራዴ የተጋደመበት አረንጓዴ የሳውዲ ባንዴራ በወርቃማ ጦር መሳይ ብረት ተሰክቶ በጥሩ ግርማ ተሰቅሏል። ሠላም ያላቸውና ለሰብዓዊ መስሪያ ቤቱ ተስማሚ የሆኑትን ወንድም የሳውዲ ባህላዊ "ቶባቸውን" ለብሰዋል።"ቁድራ" እየተባለ የሚጠራውን ቀይ ሻሽና ከቁድራው ላይ ጣል የምትደረገውን "ኢጋል" ተብላ የምትታወቅ ጥቁር ክብ ገመድ መሳይ በራስ ቅላቸው አላጠለቋትም። ከግራ ጎናችው ከሚገኝ የሚያምር ቁዋሚ የልብስ መስቀያ አንተልጥዋታል። ቢሮዋቸው ሰፊ እንደ መሆኑ ከዋና መቀመጫቸው ካሉት የሚያማምሩ ባለድሎት ወንበሮች በተጨማሪ በቀኝ በኩል የመሰብሰቢያ ረጅም ጠረጴዛና ከፊት ለፊት ደግሞ ከቆዳ የተሰራ አረንጓዴ ቆዳ የፎቴ ወንበር ይስተዋላል። ከሥራቸው ምስጥራዊነትና ካለው ስነምግባር አንጻር ምንግዜም ቢሆን ባለጉዳይን በተናጠል ማነጋገርን ይመርጣሉ። ይህን ሲያደርጉም ለባለጉዳዮች ቀለል ብሎ ለመታየት የሳውዲ ባህላዊ ልብሳቸውን እንደማያዘወትሩ ነግረውኝ ነበርና የዛሬው በምዕራባውያኑ ሱፍ ሸክ ማለት ልዩና አዲስ ነገር እንዳለ ጠቆሞኛል። ገብቸ ሠላምታ እንደተለዋወጥን ከቢሮዋቸው ያገኘሁት ወጣት ለሥራ ባልደረባቸው የጀዛን ጉዳይ ፈጻሚ መሆኑን ሲያስተዋውቁኝ እኔን ረጅም ጊዜ የምንተዋወቅ ጓደኛሞች አስመስለው አስተዋወቁኝ። በመጠኑም ቢሆን ሊያሳዩኝ የሚፈልጉት ነገር እንዳለ ገባኝ። ያም ሆኖ የሀገራቸውን መንግሥት የሚያሳጣ ነገር ለጋዜጠኛው እንደማያቀብሉ ደጋግሜ ስለተገነዘብኩ የተዘጋጀልኝ የራሴ ጉድ እንደሆነ ጠርጥሬያለሁ። እኔ በቢሮ እንደደረስኩ አንድ የፊሊፒን ዜጋ የኮረንቲ መፍቻ መሳሪያውን ይዞ የገባው ከኔ ጋር ቢሆንም የወጣው እኔ ገብቸ የሞቀ ጫወታችን ስናደራ ነበር። በጫዎታችን መካከል "አሁን መቀጠል ትችላላችሁ ... ይሰራል።" የሚል ቃሉን ሰጥቶን ወጣ- ፊሊፒኑ የኮረንቲ ሠራተኛ ...

ወደ መሰብሰያ ጠረጴዛ እንድንሄድ የቢሮው ኃላፊ ጋበዙ። የፈለጉኝ ቪዲዮ ሊያሳዩኝና ቪዲዮው ውስጥ የሐበሾችን ንግግር እንድተረጉምላቸው መሆኑን ገለጹልኝና ተጀመረ ... ፊልሙ የተነሳው ሁዴዳና ሃድራሞት ከሚባሉ የየመን የቀይ ባህር ወደብ እስከ ሳውዲ የጠረፍ ከተማ ቆባና ጀዛንን ያካትታል። የበረሃው ጉዞና ያልቀናችው ተይዘው የሚታጎሩበት የሳውዲ ጊዜያዊ እስር ቤቶች ያለውን መከራ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። በሁሉም አቅጣጫ በተነሱት ፊልሞች ሶማልያ፤ ኢትዮጵያ ኤርትራ ወጣት ሴትና ወንድሞቻችን ሳያውቁት የዚያ ፊልም ተዋናኝ ናቸው። እንደሚቀረጹ እንኳ አያውቁትም ... ብቻ ሲተኙ ከልሆነ በቀር ቀን አብሮ የሚውል፤ ሲመሽ የሚያማሽ፤ የባህር የበረሃውን የተደበቁ እውነቶች ... ያሳየናል ... እውነት ሞልተው ተርፎበታል ... ፊልሙ! ብቻ ተጀምሮ እስኪጨረስ በድብቅ የተነሳ በመሆኑ ድምጹ ፍንትው ብሎ የመሰማቱን ያህል ምስሎችን በጥራት አያሳይም። እንቅስቃሴ ይበዛበታል። ወጣቱ በቪዲዮው ውስጥ አልፎ አልፎ ብቅ ጥልቅ ይላል። ፊልሙን እያየሁ ለማረጋገጥ ያህል ደግሞ የጎሪጥ እየሰረቅኩ ማየቴ አልቀረም። በተለይም በማጎሪያ እስር ቤቶች ውስጥ ያለውን ቃለ-መጠይቅ የሰራው ለመሆኑ ብዙ ማረጋገጫ አገኘሁ። ፊልሙን እያየን የሚሉትን እነግራቸዋለሁ። ኢትዮጵያውያን የሚበዙባቸው ስደተኞች ከአዲስ አበባ ጀምረው እስከሚያዙባቸው የሳውዲ ከተሞች ያለው ችግር ቃላት ሊገልጸው አይችልም።

"ለምን ያህል ጊዜ መጣህ?" ይጠይቃል ጠያቂ

"ለሁለተኛ ጊዜ ነው የመጣሁ "ይላል

". ይህን መከራ እያየህ እንዴት ትመጣለህ? "ይለዋል

"... የድሃ ልጅ ነኝ ... ሥራ የለኝም ... ሀገሬ ድሃ ናት ... ምን ልሥራ ... ቢሳካ ጥሩ ነበር። አልተሳካልኝም ... በሀገራችን ወንድ ልጅ ጠንካራ ነው። ወንድ ልጅ ነኝ ለችግር የተፈጠርኩ አይደለሁምን? እንዴ!" ሲል ሲቃ እየተናነቀው ይመልሳል የኛ ወንድም ሐበሻው ...! ደረቁን ሃቅ እንካ ይለዋል! በረሃብ በቸነፈር በበረሃው ሳያንስ በእስር ቤት በሽታ የተጎሳቆለው የኛ ወንድም!

ያየሁትንና የሰማሁትን በዚህች አነስተኛ መጣጥፍ ሊሰፍር የሚችል አይሆንም። ፊልሙ አልቆ ተዘጋና የዓይን ምስክሩን መስማት ጀመርን ... ያግተለትለው ገባ። ምስጋናን ከኃላፊዎቹ ለማግኘት ጭምር ነው እንዳልል ከሚያወራው በላይ ገላጭ የሆኑ የወንድሞቸ ተንቀሳቃሽ የበድን ምስሎችን ተመልክቻለሁ። ብቻ ... አጋጣሚውን ሳስታውስ ይህችን ማስታወሻ ስጽፍ ራሱ ያ ስሜት እየመጣ ያውከኛል ... ይከብዳል! ብዙ ጊዜ ሰው እንደመሆናችን ማየት መስማት፤መልበስ መብላት መጠጣት እናም ሌላም ሌላም መልካም መልካሙ ቢሆንልን እንመርጣለን ... ችግር፤ መከራ፤ ሰቆቃን መስማት ሊከብደን ወይም አንፈልግ ይሆናል፤ ነገር ግን ሳንፈልግ ሁኔታዎች እንድንሰማና እንድናውቅ ያስገድዱናል ...! በኔ ላይ የሆነው ግን እንዲያ አልነበረም ... የሰማሁት ማወቅ የምፈልገውን ቢሆንም የሰማሁት ልሰማ የጠበቅኩት አልነበረም ...! ያም ሆኖ ባላሰብኩት አጋጣሚ ከታመነ ምንጭ የሟላ አዲስ መረጃን ለማግኘት እድሉን አገኘሁ! ... ይህ ወንድም እንደ ሰብዓዊ መብት ሠራተኛም ብቻ ሳይሆን በጥሩ ስነ-ምግባር ያደገ መሆኑን በግል ተቆርቁሮ ችግረኞችን ለመደገፍ ሲያደርግ አይቻለሁና በሚያደርገው ነፍሴ ረክታለች ... ያያቸው የመብት ገፋፋዎች ግን ያለ ጠንካራ ከለላ በቀላሉ ፍትህን ማግኘት እንደማይቻላቸው ይገባኛል ...

በሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት በተለያዩ እርከን የሚገኙ ኃላፊዎች ለዲፕሎማሲ መስሪያ ቤቶች ያላቸው ክብር ከፍ ያለ ቢሆንም የሚሰጡት ክብር ሀገሪቱ ልታሳድረው ከሚችለው ተጻዕኖ የተወሰነ ብቻ ሳይሆን ከየሀገራቱ ተወካዮች ጥንካሬያቸው ጋር የሚወሰንበትን እንደሆነ በተደጋጋሚ ታዝቤያለሁ ... ዲፕሎማት ደረጃ ቀርቶ ሀገር አልባ በተራ ዜጋነት የሚፈረጁት ሶማሌዎች ክብራቸውን ላለማስነካትና ላለመደፈር የሚያሳዩት የቁጠኝነት ባህሪ ሲያስከብራቸው ይታያል ... ፊሊፒኖች መብታቸው ሲነካ ግልፍ ብለው እንደ ሱማሌዎች እንደባደብ ባይሉም ሲበደሉ የሚቆሙላቸውንና ለክብራቸው የሚተጉትን የሀገራቸው መንግሥት ተወካዮች " ሃሎ" ማለቱ ይቀናቸዋል! ከጎናቸው ይቆሙላቸዋልና! ... ከሁሉም በቀዳሚነት በክብር እንታወቅ የነበርነው ሐበሾች ግን ያለመታደል ሆኖ ክብራችን እየተገፈፈ ያታያል! ያለ ነገር አይደለም ... አሁን አሁን የምንሰራው ሳይቀር አላምር እያለ፤ ሳንሰራ ሰራን ስንባል ተከላካይ እያጣን ስማችን ጥሩ አይነሳም ... ተንቀናል ... እንደፈራለን ... የአንድ ሀገር ዜጎች በውጭ ሀገር ሲኖሩ የመብታቸው ተሟጋች የሀገራቸው ሚሲዮኖች ቢሆኑም በሳውዲ የከተምን ኢትዮጵያውያን ለዚህ አልታደልንም ... አደግን ሰለጠንን በተባለበት ... ዘንድሮ ደግሞ የተለየ ሆኖዋል! የኛ ዲፕሎማቶች ሰልጥነው የተላኩበት ዓላማ የዜጎችንና የሀገርን ደህንነት ማስጠበቅ ሳይሆን የማህበራትን ማደራጀትና የፖለቲካ ሥራን መሥራት አስመስሎባቸዋል። ሰልጥነው የመጡት በኢትዮጵያዊ ባንዴራ ጥላ ዜጎችን ከማሰባሰብና ችግራቸው ከመፍታት ይልቅ ዜጎችን በተለያየ የየክልሉ ባንዴራ ስር በፖለቲካ በማቡዋደን ከጎናቸው ማህበራትን ከማደራጀት ሌት ተቀን ይሰራሉ። ከዚህ ባለፈ የዜጎችን መብት ሲያስከብሩ አለመታየቱ ብዙዎችን ተስፋ ያስቆረጠ ጉዳይ ሆኗል። እልፍ አእላፍ ዜጎች ባህር ቆርጠው ወደ ሳውዲና የመን ይገባሉ።

ከሁሉም በላይ ወንጀላቸው ድህነት ሆኖ ባሳር በመከራ ድንበር ጥሰው ሲገቡ ይያዙና ግፍ ይፈጸምባቸዋል። ይደበደባሉ፣ ይደፈራሉ ... ይገደላሉ ... ከሁሉም የሚያንገበግበው ዲፕሎማቶቻችን ሌላው ቀርቶ በዜጎች ላይ የሚወሰድን የጭካኔ እርምጃ የሚያረጋግጥ የዜጋቸውን ሬሳ ይዘው የት መሄድና ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያውቁት አይመስልም ... በዓለማችን የሰው ልጅ በግፍ ሲፈጸምበትና በተለይም ሲገደል አፋጣኝ ፍርድ የሚሰጥባት ሀገር ሳውዲ ነች ብል ማጋነን አይሆንም። ይህን ሃቅ ስናገር አሳማኝ እማኞችን ማቅረብም እችላለህ። አይኑን ላጠፋ አይኑን አጥፋ፤ የሰረቀን እጁን ቁረጥ የሚለው የሸሪአው ሕግ የገደለ ይገደላል ስለሚል ጥፋቱ ከተረጋገጠ ምህረት የሚገኘው ምናልባትም የተበዳይ ቤተሰቦች ይቅርታ ካሉ ብቻ ነው የሚሆነው ... ከዚህ ውጭ ግን ምህረት የለም ... ግፍ ይፈጸማል ... ምህረት የሚባል ነገር የለም። ገዳይ የገደለ እጁ የፍጥኝ ታስሮ በአደባበይ እየተንጨበጨበ በጎራዴ አንገቱን ይቀላል! ይህን ሁሌ የምንሰማው ሳይሆን የምናየው እየኖርኩበት ያለው የገሃዱ አለም እውነታ ነው ... የምናውቀው የተደበቀ አይደለም! ግናስ ማን ይከራከርልን! በግፍ የሞተብን ጠፍቶ ይሆን? አይመስለኝም!

በኛ ጊዜ ልበል መሰል ... ከአስር ዓመት በፊት ገደማ ወደ ሳውዲና ወደ ተለያዩ ዐረብ ሀገራት ሲመጣ እቅዱ ወርቅ ለማፈስ አለያም "ሚኒ ባስዋን" ሽር አድርጎ ወደ ሀገር ቤት ለማስገባት ነበር ... ህልሙ! እየቆየ እየቆየ ... ፍላጎቱና ምኞቱ የማይጨበጥ እየሆነ መጣ ... እውነታው ጎለል ... ጎለል እያለ መጣና ዛሬ ያ ሁሉ ተስፋ እንደ ሃምሌ ጉም ጠፋ። አሁን አሁን ሥራ ሰርቶ ራስን ለመርዳትና ከፍ ሲል ደግሞ ወላጅ እህት ወንድምን ለመደገፍ ሆኗል። ድህነት አስመርሯቸውና አልሞላ ሲላቸው የሚሰደዱ ወጣቶች በእርግጥም ሕግ ጥሰዋልና ወንጀለኞች ናቸው። ሕግ የጣሰ ደግሞ የሚዳኘው በሀገሪቱ ሕግ ነው። ሕግ የተላለፈ በሕግ ይዳኛል እንጂ በአንዲት ጠባብ ክፍል ከ300.400 እስረኛን ታጭቆ በተላላፊ በበሽታ ይርመጥመጥ የሚል ሕግ የለም! ይህንን መሰሉን ሰብዓዊ ጥፋት ከሁሉም በላይ የሸሪአ ሕግ ይቃወመዋል። ሕግን መሰረት አድርጎ የሚሞግትልን ግን ካጣን ከራርመናል! በጀዳ፤ በጀዛን፤ በቆባ፤ በቢሻ፤ በአብሃ በከሚስ ምሸትና በተለያዩ የሳውዲ የመን ድንበር ከተሞች ግፉ በርትቶዋል። ዜጎች በእስር ቤት መጨናነቅና በተላላፊ በሽታ ለወራት በሚቆዩበት ጊዜያዊ የማቆያ እስር ቤት ህይዎታቸውን ማጣታቸው ይነገራል። ከሞቱ አሟሟቱ እንዲሉ የአሟሟቱ ነገር ባይነሳ ይሻላል ... ማንቴስ ተብሎና ተብላ ድንበር የተሻገሩ ወንድም እህቶች እጣ መሪር እየሆነ መጥቷል። ሳውዲ ሲገባ ስሙን ለመመሳሰልም ይሁን ለመደበቅ አስቦ ይቀያይረዋል … እህት ወንድሞቹ ወገኖቹን ከድህነት ለማውጣት የተሰደዱ ወገኖች እመቤት ፋጡማ ተብላ፤ ጎይቶም ሙስጦፋ ወይም አህመድ እርዚቅ ተብሎ ተብለው ማንነታችው ሳይታወቅ እንደወጡ ይቀራሉ ... አምጣ የወለደች እናት ከተሰደዱ ልጆችዋ ብዙ ስትጠብቅ የመኖር የመዳናቸውን ዜና እንኳ የምታወቅበትና መርዶ የሚያሰማት እንኳ አታገኝም ... በረሃ ላይ ይቅሩ ... በእስር ቤት ይሙቱ የሚታወቅ ነገር አይኖርም። ስሙን ቀያይሮ ማንነቱ ሳይታወቅ ኑሯልና እስከ ወዲያኛው ሳይታወቅ ለቀሪ ጸጸት ሆኖ ህልም እልም ሆኖ ይቀራል ...! ህክምና በሌለበት ሁኔታ መተፋፈን ሲበዛ እንኩዋን በአሰልችው መንገድ የደከመ ጤነኛውን እንኩዋ ይሸበርካል።

በእስር ቤት ሞቱ ሲበረታ ምነው ሞተ ሲባ መልሱ ታሞ ነው ይባላል። ይህንን አቤት ብለን መቀበልን ተላምደነዋል! ምክንያቱ ይጣራ? በማቆያ እስር ቤት በተፈጠረ መጨናነቅ በህክምናና በእስር እንግልት የሞቱት ዜጎች ፍትህን ያግኙ ... ካሳ ይከፈላቸው! የሚልልን ከጠፋ ቆይቶዋል ... ስደት ተንሰራፍቶ ሞት ረክሶዋልና ኑሮዋንችን እንዲህ ሆኖዋል ...! የጀዛንን እስር ቤት የወጣቱን ንግግር ተክለትሎ በሃሳብ ጠፋሁ ... እየሆነ ያለውና ወጣቱ የታዘበው መሰረት በማድረግ ከአለቆቹ ጋር ተነጋግሮ እስር ቤቱን ለመጎብኘት ቀጠሮ ሲያመቻች ከሄድኩበት ሃሳብ ነቃሁ! በጉዳዩ ዙሪያ በቂ መረጃ ለመያዝና በሌላ ቀጠሮ ለመምከር ቀጠሮ በመያዝ ወደ ጀመርኩት የጂዳ እስር ቤትና በድልድይ ስር ስለወደቁት ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የረመዳን ዋዜማ ወጌ ልቀጥል! ይህንን መሰል ግፍ በዜጎች ላይ ሲፈጸም ሃቁን የማውጣትና የማሳወቅና መረጃ የማቀበል ኃላፊነት እንዳለብኝና ይሰማኛል ... ስለሰማሁትና ስላየሁት መረጃ ለማሰባሰብ ከዚህም ከዚያም መቆፋፈር ያዝኩ። መጀመሪያ ከአፍንጫየ ስር ያለውን የጂዳን ሁኔታ ለማጣራት ቅድሚያ ሰጠሁ። በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ያሉ ኢትዮጵያውያን እስረኞች ጉዳይ የመጉዋጉዋዣ ሰነድ አለመቅረብ ነው ብለው ሊገምቱት የሚገድ አይነት ችግር በመስተዋል ላይ ነው። ከተለያየ አቅጣጫ የሚሰማውን ሮሮ መገመት ይቻላል። የችግሮች መደራረብ ከርሴን ለመሙላት ከምፋለምበት ቁዋሚ የኩባንያ ሥራ ደግሞ ጫና አብዝቶብኛል። በየቀኑ እንቅስቃሴዎች ማስታወሻ እይዛለሁ። በእጀ የሚገኙ መረጃዎችን ነገሮችን አቅጀ መሥራት ይቀለኛል። አሁን አሁን ግን በእቅድና በፕሮግራም መመራት የሚባል ነገር ጠፍቶብኛል። የምይዘው የምጨብጠው አጣለሁ … ይሄን ልይዝ ስል ያ ይፈታና ... እዚያ ሄጀ እቀራለሁ ... አንዱን ላጣራ ስባትል ሌላ አገኝና ... ያንን እይዛለሁ። የጀመርኩትን ሳልጨርስ ያልጀመርኩት አስቸኳይ ይሆናል ... ብቻ ምን አለፋችሁ መብተክተክ ይዣላሁ!

ከሰብዓዊ መብት መስሪያ ቤቱ ያገኘሁትን መረጃ ዋቢ አድርጌ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ታሳሪዎች መደወልና ማጣራት ነበረብኝ። ያጋጣሚ ነገር ሆኖ በድልድይ ስር እጎበኛቸው የነበሩ የ75 ዓመት እናት ተንቀሳቃሽ ስልኬን ይዘው ነበርና ደወሉልኝ። "አሳ ጎርጎዋሪ ዘንዶ ያወጣል " እንዲሉ ላለፉት በርካታ ሳምንታት በእስር የሚገኙ ወደ ሶስት ሺህ የሚጠጉ ታሳሪዎች በአውሮፕላን እጥረት በመሰቃየት ላይ መሆናቸውን ሰማሁ። ከታሳሪዎች መካከል የ75 ዓመት ባለጸጋ የሆኑት እናት የሚገኙባቸው ታሳሪዎች ያለምንም መፍትሄ በጠና ህመም ላይ በመሰቃየት መሆናችውን ከባለጉዳዮች ሰማሁ። እኒህን እናት በመርዳት ላይ የሚገኙ ወጣት ታሳሪዎች በበኩላቸው መንግሥት የታሳሪዎችን ጉዳይ በመከታተሉ ረገድ ድክመት እንዳለበት በማሳወቅ ሌላው ቢቀር ህጻናትና አዛውንቱዋ እናት በበሽታ ከመጠቃታቸው በፊት አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ ይታደጋቸው ዘንድ በሰጡት አስተያየት እያነቡ ገለጹልኝ። የበጅዳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መስሪያ በበረራው መተጓጎል ዙሪያ መረጃ ይሰጡኝ ዘንድ ጠየቅኩ አልተሳካም። ጅዳ ለሚታየው ጅዳ ያሉ ኃላፊዎች መልስ እንዳይሰጡ መስሪያ ቤቱ ማዕከላዊ የመረጃ አቅርቦት ውጭ መረጃን አይሰጥም ነበር ያሉኝ። ስልጡን የሚባለው አየር መንገዳችን በተተበተብንበት ቢሮክራሲያዊ አሰራር ከማዘን ውጭ ምን ይባላል? የታሳሪዎችን መዘግየት ጉዳይ ያነጋገርኩዋቸው ዲፕሎማት የአውሮፕላን እጥረቱን ችግር ለመፍታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ነው በማለት ገለጹልኝ። በአንጻሩ የሰብዓዊ መብት ኃላፊዎች ሃቁ የቆንስልና የኢንባሲ መስሪያ ቤቶች የመጓጓዣ ሰነድ እለማያቀርቡ ነው የሚል አንድምታ ያለው መግለጫ ሰጡኝና ይህንንም በምሰራበት ራዲዮ በኩል ተላለፈ።

አሁን ነገሮች ገሃድ መውጣት ጀመረዋል። The National Society for Human Rights ድርጅት የመካና የጂዳ አካባቢ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት እስር ቤቶችንና በድልድይ የሚገኙትን ዜጎች ጎብኝተው ያወጡት መግለጫ በሀገሪቱ ታዋቂ ጋዜጦች ላይ ሳይቀር ይፋ ወጣ። የሰብዓዊ መብት መስሪያ ቤት የጂዳና መካ ሙከረማ ዋና ኃላፊ ቃለ መጠይቅ አደረግኩላቸው። ችግሩ ከሳውዲ መንግሥት ሳይሆን ከቆንስልና ከኢንባሲ መስሪያ ቤቶች መሆኑን አጋለጡ። እስር ቤቶችን እንደጎበኙ ያስታወቁት ኃላፊ ማቱክ አልሸሪፍ የስደተኞችን የወራት እንግልት ትክክለኛ መሆኑን በማስረገጥ በተለይም ወንጀል ሳይኖርባቸው የታሰሩ ዜጎችን ጉዳይ በማቀላጠፉ ረገድ ኢምባሲዎችን ለቆንስል መስሪያ ቤቶች አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዱ ዘንድ ተማጸኑ። በዚህ ዙሪያ የተሻለ መረጃን ለማግኘት በሚል በስደተኞች አቤቱታ ዙሪያ ያነጋገርኩዋቸው የሰብዓዊ መብት ተሙዋጋች ቡድኑ ምክትል ፕሬዘደንት ዶር ሳላህ አል ከትመያን በበኩላቸው ከላይ የተገለጸው አይነት ተመሳሳይ አስተያየት ሰጡ።

የነዋሪዎችን ወቀሳና የሰብዓዊ መብት ድርጂቱን አስተያየት ተከትሎ መረጃን ማግኘት ይቻል ዘንድ የጂዳ ቆንስል መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረግኩት ሙከራ መደናቀፍ ጀመረ። ይህንን ስደውል ያረዱኝ ዲፕሎማት ይባስ ብለው እንዲህ የሚል ውንጀላን ለከኩብኝ። " ዜጎች በድልድይ እንዲሰበሰቡና ወደ ቆንስሉ እንዲመጡ የሚገፋፉ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ኢትዮጵያውያን አሉበት። አንተም በዚህ ረገድ ግፊት እንደምታደርግ መረጃ አለን። ፓለቲካውን ከፈለግን ሀገር ቤት ሂደን ብንገጥም ይሻላል ..." የሚልና ሌላም ሌላ ተናገሩ። ይህ የሆነው ባልጠበቅኩት ሁኔታ ነበርና ራሴ ስቤ አስተያየታቸውንና ስሜት የተሞላበት ንግግራቸውን ማውጣት ማውረድ ጀመርኩ። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻም ሳይሆን የሙያ ግዴታውን መወጣት እንዳለበት እንደ አንድ ተራ ጋዜጠኛ በጉዳዩ ዙሪያ መረጃን ለማሰባሰብ ስንቀሳቀስ ፈተናወች አልገጠሙኝም አይባልም። ከላይ ባየነው በከፍተኛ የመንግሥት ተሿሚ ደረጃ ግን አልነበረም። ከወርሃ ሚያዝያ ይህንን ጉዳይ በቅርበት ለመከታተል ከጀመርኩበት ሰዓት አንስቶ እስካሁን ባለው ሂደት ከማገኘው የማበረታቻ ሙገሳና መልካም ቃላት ባልተናነሰ አንዳንድ ቅን ከሆኑ ወንድሞቸ በስልክ የሚደርሰኝ ማስጠንቀቂያ፤ ማስፈራርያና ዛቻ እዚህ ግባ ባይባልም መሰማቱ አልቀረም። "… የምታደርገውን ሁሉ እንከታተላለን ... የምትሰራው ሥራ መንግሥትን ለማሳጣት ነው ... ልጆችህን ብታሳድግ ይሻላል ... አርፈህ ተቀመጥ ..." ይሉኛል። በዚህ መሰሉ መጣጣጥፍ ለመግለጽ አስፈላጊ ያልሆኑ አስነዋሪ ስድቦችን ሳይቀር ማስተናገድ የግድ ነበር። ያም ሆኖ ሁሉም ጥሪዎች የሚደረጉት ከህዝብ መገልገያ የስልክ ማስደወያና ከመንገድ ዳር ከሚገዙ የሞባይል "ሲም" ካርዶች ስለሆነ የደዋዩን ማንነታት ለማወቅ የሚቻል አልነበረም። መልሴ አንድ አይነት ነበር። ሁኔታውን ለማስረዳት ሞክሬ ሲሳነኝ ደም ካላችሁ የምከታተለውን የወገኖቻችሁ በደል ተመልከቱ ... ዓላማየን ተረዱ በማለት ለማስረዳት ብሞክርም አይሳካም። ብቻ ... ስድቡና ዛቻው አያባራም ...

ባንድ አጋጣሚ ከግፉአኑ ጋር አረፋፍጀ በጉዳዩ ዙሪያ ከአንድ ጉዋደኛየ ቢሮ በመሄድ የቆጥ የባጡን ስንጨዋወት ስልክ ተደወለልኝ። አነሳሁት ... እኒያ ተሳዳቢ ወንድሞቸ ነበሩ። ስሜን ጠርተው አሁን የት እንደ ነበርክ እናውቃለን! ብለው በድልድይ ስር እንደነበርኩ ሰአቱ ሳይቀር ተገለጸልኝ። ያጋጣሚ ነገር ሆነና በስልክ የጦፈ ሙግት አይሉት ክርክር ሳደርግ አይኑን አፍጥጦ ይስማ ለነበረው ጉዋደኛየ እየሆነ ያለው ምንድነው ሲል በአግራሞት ጠየቀኝ። ሁኔታውን አስረዳሁት። የጎሪጥ እያየኝ የስላቅ ሳቁን እየሳቀ "... ነብሴ ጠርጥር የሚባል ነገር አለ ...! መጠርጠሩ አይከፋም ..." የሚል ወንድማዊ ምክሩን ሲለግሰኝ ወደ ኋላ ተጉዞ ምሳሌ ማጣቀሱን ያዘ። በሳውዲ ዐረቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀበሻ በሚል መጠሪያ የጀመርኩዋትን በማህበራዊ ኑሮ ላይ የምታተኩር የኔና የጉዋደኞቸን ጋዜጣ ውልደትና ውድቀት፡ እገዳና ክስ እያነሳ ጣለና በአይነ ህሊናየ አስቃኘኝ። ቀጠለና ... ከሁለት ዓመት በፊት በሕጋዊ መንገድ ፋይል ሳይከፈት የተመሰረተብኝን የሀገር ክህደት ክስ፤ ፓስፖርት ለማደስ ስሄድ ለጊዜውም ቢሆን የተጣለብኝ ሂደት፤ የኢትዮጵያ ባንዲራ ከሚውለበለቡባቸው ከቆንስሉና ከኮሚኒቲው ድርስ እንዳትል የተባልኩበትን አጋጣሚ! የኮሚኒቲ አባልነቴ በቆንስሉ ኃላፊ ታእዛዝ የተነጠቅኩበትን፤ ከኔም ጋር ተዳብለው "ነጻ" የተባለው የኮሚኒቲ መስሪያ ቤት ሕግ የተጣሰበትን ሁኔታ፤ህዝብ የመረጣቸው የኮሚኒቲ ሥራ አስፈጻሚ አባላት በቆንስል መስሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች ቀጭን ትእዛዝ ከኃላፊነት የተነሱበት፤ የሻሂ ቤት የገንዘብ ያዥ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ከሥራ ተባራ ከብዙ እንግልት በኋላ ሀገር የገባችበትን አሳዛኝ ትዕይንት፤ በተለይም በዜጎች ደህንነት ኃላፊ የነበሩት ወንድም በተደጋጋሚ ቢሮዋቸው ድረስ እየጠሩ ያደርሱብኝን የነበረውን እንግልት ረስቸው የነበረ ቢሆንም የነገረ ፈጁ ልጅ ጉዋደኛየ በዝርዝር አስታወሰኝና በጉዳዩ ዙሪያ አንዳንድ ነገር እያነሳሳ አሳቀኝ። በተለይ ደግሞ ያ መርማሪየ ዲፕሎማት ዛሬ የመን ከዜጎችን ጎን በመቆም መብታቸውን ለማስከበር ትልቁን ሥራ እየሰራ መሆኑን ወሬ ሽው ቢለኝም ያኔ እኔን ሲመረምሩ ያደረሱብኝ ውክበት አይጣል ነበር።

ጉዋደኛየ ሰውየውን አስታውሶ አንዴ የቅንጂት አባል ነህ አንዴ ከሃዲ ነህ በሚል መንፈስ ሲወለጋገዱብኝ "የአርበኛ አጎቴ ድምድም ጓንዴ ጠመንጃ እኳዋ ቢቀር ግሩም ጀንፎ ያላት የአራሹ አጎቴ የአያ ጋሻ ባለ ጀንፎ ቆመጥ ናፈቀችኝ" ያልኩትን የማይረሳ ትዝታ ነካ ነካ አድርገን የምሩን ቀልድ አድርገን በመጨዋወት ተለያየን። ከራሴ ጋር ማውራትና ማሰላልሰልን ያዝኩ። በጂዳ ቆንስል መስሪያ ቤት ስር ይህን መሰል በደል ቢፈጸምብኝም ብላቴና ልጀን አንጠልጥየ ደካማ እናቴና ቤተሰቦቸን ለመጠየቅ ወደ ሀገሬ ሳቀና ብዙዎች ከማስጠንቀቅ አልፈው ስንብት እንዳደረጉልኝ አስታውሳለሁ። የቃል ክስ ከተከሰስኩ ጊዜ አንስቶ ወደ ሀገር ቤት አትገባም የሚሉ ዛቻዎችን የኔ ነበሩና ... ለምጃቸዋለሁ። ያም ሆኖ በመንግሥት ስልጣን ላይ የተቀመጡ ኃላፊዎች ህዝባዊ ግልጋሎትን ይስጡ በሚል በአደባባይ በማቀርባቸው የሰሉ ሂሶች አሳሬን አብልተውኛል። የፈለጉትን የፖለቲካ አመለካከት የማራመድ መብት እንዳለኝ አሳምሬ ባውቅም የማወራው የማየው የማህበራዊ ኑሮ ድቀት ነበርና ወደ ፖለቲካ የሚይጠጋጋ አንድምታ የላቸውም ነበርና በፖለቲከኝነት ሊያስፈርጀኝ የሚችል ነገር በዙሪያየ የለም።

በዚህ ረገድ ማንነቴንና ፍላጎቴን ብሎም ልኬን አውቀዋለሁ። ብቻ ውሾ ከተባልኩ ወዲያም ማስፈራሪያው ባየለበት ሁኔታ ወደ ሀገር ቤት ሄጃለሁ። እግዚአብሄር ምስክሬ ነው አንዳችም ቀን ማንገራገር ደርሶብኝ አያውቅም። ያም ሆኖ የጉዋደኞቸም የዘመድ አዝማድም ሆነ የሚሳሱልኝ የማላውቃቸው ምክር ገብቶኛል ... ድጋፋቸው ብርታቴ ነው! በአንጻሩ ጠልፈው ሊጥሉኝ የሚፈልጉት ወገኖች ሥራየን እንድመረምርና ተጠንቅቄ እንድሄድ ምክንያት ሆነዋልና ሁሉንም አመሰግናቸዋለሁ! እንቅስቃሴየን የማይወዱት ባለሥልጣናትና ጀሌዎቻቸው በሚተበትቡብኝ ማናቸውን ነገር ሳላስበው ችግር ውስጥ ተሰንቅሬ እንደምቀር ቢገባኝም ሆዴ ግን አይባባም ... ደፋር ያደረገኝን አባዜ ግን አላውቀውም ነበር ... አንድ ቀን አንድ አልባሌ ወንድሜ ግን የውስጤን በተገቢው መንገድ መግለጹን አስታውሰዋለሁ ... "እውነት በውስጥህ ካለ አትፈራም ..." ነበር ያለኝ አባባሉ በቀላል መንገድ ስለተገለጸ ቀላል ሊመስል ይችላል ... ትልቅ እጂግ ግዙፍ ... እውነታ ግን አለው ... ህይወት ግን ያስተማረችኝ ይህንን ነው! "እውነት በውስጥህ ካለ አትፈራም ..." እናም ትልቅ እውነት ይዣለሁና ልቤ አልባባም፤ አልፈራሁም። ደግሞስ ለምን እፈራለሁ! ዜጎች በጠራራ ፀሐይ በደል ይደርስባቸዋል ... ተከላካይ ቀርቶ አይዞህ ባይ አጥተዋል ... ከዚህ ያለፈ እውነት የት ይምጣ? ... ደግሞ በርካቶች በግፍ እየተበደሉ ድምጻቸውን ለማሰማት የሚውተረተር አልባሌ ጋዜጠኛን ከመደገፍ ይልቅ ጠልፎ መጣሉ እውን አንድ በኢትዮጵያዊነቱ ከሚኮራ ዜጋ ይጠበቃል? ... የዜጎች መብት ተገፈፈ፤ መብታቸው ይከበር! ያሉ ሰወች ያጠፉት ምን ላይ ነው? ለምንስ ክትትል ይደረግባቸዋል? እንደዜጋ የሚቆረቆሩ ከሆነ የተበዳዮችን ጥያቄ ለምን ለመንግሥት ኃላፊዎች አቅርበው ችግሩ እንዲፈታ እንኩዋን አያደርጉም? ሲያመኝ ለራሴ የማነሳው ቢሆንም እኒያን የሚደውሉልኝን ወገኖች ጠይቄያቸው መልስ ያላገኘሁለት ጥያቄ ሆኖ ቀጥሎዋል ... (ይቀጥላል ...)

ቸር ይግጠመን!

መስከረም 2002


ነቢዩ ሲራክ - ከሳውዲ ዐረቢያ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!