ነቢዩ ሲራክ

"... በሕብረት መኖር አለብን ብሎ የሚመክር የሚዘክር ድንቅ ሰው ነበር፣ አቡኬ"

Abukee Alex, አቡኬ አሌክስ

በያዝነው ሣምንት ... በአብዛኛው የሐበሻ መገናኛ መንደር፣ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ዋንኛ መድረክ በFacebook መስኮት አንድ መሪር መርዶ ተሰምቷል። የትሁት፣ አስተዋይና አርቆ አስተዋዩ በጎ ሰው፣ የጎልማሳው የአቡኬ አሌክስ ህልፈት። የአቡኬ አሌክስ በድንገት መለየት ጥልቅ ኀዘናን ሁላችንንም አንገብግቦናል። "ከሞቱ አሟሟቱ" እንዲሉ አቡኬ ባንድ ጀንበር ታይቶ በርቶ፣ ባንዱ ጀንበር ሳይታሰብ ጠፍቶብናል። እናም በቅርብ ከሚያውቁት፣ ቤተሰብ ዘመድ አዝማድ ጓደኞች እኩል በሥራው በዝና የምናውቀው በኀዘኑ አዝነን ከፍቶናል።

የጎልማሳው በጎ ሰው አቡኬ አሌክስ መረጃዎች የቅርብ ተከታታይ የሆነችው ባለቤቴ፤ በህልፈቱ ጥልቅ ኀዘን ከተሰማቸው መካከል አንዷ ናት። ስለአቡኬ ስትገልጽ እንዲህ ብላኛለች፤ "አቡኬ ብሩህ አዕምሮ የነበረው፣ ኢትዮጵያውያንን በዘር እና በኃይማኖት ሳንለያይ በሕብረት መኖር አለብን ብሎ የሚመክር፣ የሚዘክር ድንቅ ሰው ነበር፣ አቡኬ!" ብላኛለች ... አዎ! ሁላችንም በፌስ ቡክ የመረጃ መለዋወጫ መድረክ ሃሳቡን በነጻነት አንሸራሻሪ፣ መረጃ አቀባይና ተቀባይ፣ ሩቅ አሳቢ መልካም ሰው አቡኬ አሌክስን አጥተናል ... በእርግጥም ተጎድተናል ...

እንደኔ እንደኔ አቡኬ ሲለየን ያመመን፣ አቡኬ እንደ ተመራማሪ ታዋቂ የሀገር አውራ ሰው መለየት ያስቆጠረን፣ የብዙኀኑ መሪር ኀዘን የመሆኑ የታየን እውነታና ሚስጥር አለው። ለእኔ የአቡኬ መልካምነት ገኖ መውጣት ውስጠ ምስጥሩ ... ጎልማሳው ማኅበራዊ መገናኛዎቻችን በመልካም ጎኑ ተጠቃሚ፣ የሀገርና የህዝብ የሁለትዮሽ እሴቶታችን መሰረት የሆነው የሕብረታችን አድማቂ፣ መረጃዎችን አቅራቢና አስተላላፊ በመሆን ጊዜውን ለቁም ነገርና ለመልካም ሥራ ያዋለ አርቆ አሳቢ በመሆኑ ይመስለኛል! አቡኬ አሌክስ ...

የአቡኬ ሳይታሰብ በድንገት የሕይወት ጉዞ ፍጻሜ የብዙዎቻችንን ቅስም ሰባሪ አሳዛኝ ኀዘንና መርዶ ነው፤ በህልፈቱ ለተጎዱት ለመላ ቤተሰቡ፣ ለጓደኞቹና ዘመድ አዝማድ አድናቂዎቹ መጽናናትን እመኛለሁ!

ነፍስ ይማር አቡኬ!

ነቢዩ ሲራክ

ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ