Dr. Fikru Maru

እንደ ፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር በ1975 ፍቅሩ ማሩ እናት አገራቸውን ለቀው በስዊድን የስደተኝነትን ሕይወት መምራት ጀምረዋል። በስዊድን ቆይታቸው በልብ ሕክምና ስፔሻላይዝድ በማድረግ ዶክትሬታቸውን የሠሩት ፍቅሩ፣ ረዘም ላሉ ዓመታት በስደተኝነት በተቀበለቻቸውና ባስተማረቻቸው ስዊድን በሚገኘው ኹዲክስቫል ሆስፒታል (Hudiksvall) በሞያቸው ሲያገለግሉና በአገሪቱ ዮኒቨርሲቲዎች ሲያስተምሩ ቆይተዋል።

ዶክተር ፍቅሩ ለስደት የዳረጋቸው ደርግ ከወደቀ ረዘም ያሉ ዓመታት በኋላ የትውልድ አገራቸውን በሞያቸው ለማገልገል በማሰብ ከስዊድን ያገኙትን የገንዘብ ድጋፍ በመያዝ ጭምር ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልለው የገቡት እ.ኤ.አ. በ2010 ነበር።

ዶ/ር ፍቅሩ በአዲስ አበባ ከተማ ለአገሪቱ የመጀመሪያው የሆነውን የግል የልብ ሕክምና ክሊኒክ በመክፈት አገልግሎት በመስጠት ለልብ ሕክምና ወደ ውጪ አገራት ማምራት ግድ ይላቸው የነበሩ የአገራቸውን ልጆች ከተጨማሪ ወጪዎች ሲታደጉ ቆይተዋል።

በ2013 እ.ኤ.አ. ኢህአዴግ የአገር ውስጥ ገቢ ሚንስትሩን ጨምሮ ብዛት ያላቸውን የንግድ ሰዎች በቁጥጥር ስር ሲያውልም፤ ዶክተር ፍቅሩ ”ለልብ ሕክምና የሚውሉ መሳሪያዎችን ከባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠርና ጉቦ በመስጠት በዝቅተኛ የግብር ዋጋ አስገብተዋል” ተብለው ለእስር ተዳረጉ።

አቃቤ ሕግ በፍቅሩ ላይ በመጀመሪያ አቅርቦት የነበረው ክስ በግዜ ሂደት እየተቀናነሰ መምጣቱ ቢታወቅም፤ ፍርድ ቤቱ በአራት ዓመት ከስምንት ወራት እስራት በየነባቸው።

የ66 ዓመቱ የልብ ሕክምና ዶክተር በፍርድ ቤቱ የተጣለባቸውን የእስር ቅጣት ያጠናቀቁ ቢሆንም እስካሁን ድረስ አመክሮው ታስቦላቸው ሊለቀቁ አለመቻላቸው ብዙዎችን በተለይም የዶክተሩን ቤተሰቦች አሳስቧል።

በቅርቡ ዶክተሩ በሚገኙበት ወህኒ ቤት ራሳቸውን ስተው በመውደቃቸው ረዘም ያሉ ሳምንታትን በሆስፒታል ውስጥ ለማሳለፍ ተገደዋል። ዶክተሩ የመተንፈሻ አካል ችግር ያለባቸው በመሆኑም የቀዶ ሕክምና ማድረግ እንደሚገባቸው ተነግሯል።

የዶክተሩ የመጀመሪያ ልጅ ኤሚ ማሩ የአባትዋን ፈለግ በመከተል በስዊድን በቅርቡ በዶክትሬት ተመርቃለች። አባትዋ ሊፈቱ እንደሚችሉ ተስፋ በማድረጓም በአዲስ አበባ ተገኝታ ነበር። ነገር ግን ዶክተሩ ራሳቸውን ስተው በሆስፒታል ያገኘቻቸው ከመሆኑም በላይ፤ እስካሁን ድረስ ነጻነታቸውን አላገኙም።

ኤሚ በአባትዋ ጤንነትና ያለመፈታት ግራ በተጋባ ስሜት ሆና ”ለምን እንዳልለቀቁት ሊገባን አልቻለም” ያለች ሲሆን፤ የፍቅሩ ጠበቃ ሃንስ ባግነር በበኩሉ ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ጊዜው አሁን መሆኑን አምኗል።

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የልብ ስፔሻሊስት በወህኒ ቤት ለማጣት የተቃረበችበት ታሪክ ይለወጥ ዘንድ እንጮሃለን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ