በጅዳ ሽሜሲ በር ላይ ወድቃለች የተባለችው እኅት ጉዳይ! - የማለዳ ወግ
ነቢዩ ሲራክ
* በሳውዲ ለተቸገሩት ተወካዮቻችን በቀዳሚነት ሊደርሱልን ይገባል
* ከኢንባሲና ከቆንስላ ውጭ አማራጭ የለም
* የቆንስሉ ሹማምንትና ሠራተኞች ለፈጣሪ ብላችሁ እርዷት፣ ተለመኑን!
ከትናንት ጅዳ ውስጥ በጠና ታማ እሷና ልጇ አደጋ ላይ አሉ ስለተባለችው እኅት እየተሰራጨ ያለው መረጃ ደርሶኛል። መረጃውን በዝርዝር ያገኘሁት ከሊያ ሾው ነበር፣ ታመመች የተባለችውን እኅት በቪዲዮ የተደገፈ መረጃ እንደደረሰኝ ወደ ጅዳ ቆንስል ደውዬ ለማጣራት ሞክሬ ነበር! በጅዳ ቆንስላ መረጃ ለማግኘት ከባድ እየሆነ መጥቷል፣ አንዳንዶች ኃላፊዎች ከዚህ ቀደም በማቀርባቸው ተጨባጭ ሂሶች አኩርፈው መረጃ ላለመስጠት ስልካቸውን ይዘጉብኛል፣ አንዳንዶች ደግሞ መረጃም ሆነ ጥያቄ ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም! እጅ አዙር በሆነ መንገድ የጅዳ ቆንስል መረጃው እንዳልደረሰው ተነግሮኛል!
ይህች እኅት በሽሜሲ ጊዜያዊ እስር ቤት በር ላይ ተጥላለች መባሉን ሰምቸ ወደ ቦታው የሚያጣራልኝ የሥራ ባልደረባዬን ልኬም ነበር፣ ዛሬ ረፋድ ላይ በር ላይ ተዟዙሮ የወደቀ ሰው አለመኖሩን አረጋግጦልኛል! ይህን ካደረግኩ በኋላ ምናልባት ይህች እኅት በእስር ቤት ትገኝ እንደሁ ቢረዷት ለማሳሰብ ወደ ቆንስላው የሺሜሲ ተወካዮች ወደ አቶ ቡሩና አቶ አብርሃ ደወልኩ፣ ሁለቱም ስልክ አያነሱም። መልሸ ወደ ቆንስል ያለለት ደወልኩ ስልኬ ብሎክ የመደረጉ ምልክት ሰጠኝ። በዚህ ሁኔታ እስካሁን ከቆንስሉ ያገኘሁት መረጃ የለምና ወደ ሺሜሲ አመራሁ!
ሽሜሲ በር ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ቦታ በመሆኑ በአካል ሄጄ በአካባቢው ወድቃለች የተባለቸውን እኅት ዘወር ዘወር ብዬ ፈለግኳት፣ የለችም። ይሁን እንጅ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ወድቃ የነበረች እኅት ስለመኖርዋና ልጇንም እሷንም ለመርዳት ሞክረው አቅሙ ስለሌላቸው መረጃ የሚቻሉትን አደርገውላት የሄዱትን እኅቶች ምስልና ምስክርነት ደርሶኝ ተመልክቸዋለሁ! ዛሬ እኔ ባላገኛትም ትናንትና ከትናንት በፊት ያገኟት እንዳሉ መረጋገጥ ችያለሁ! እንግዲህ ሊሆን ስለሚችለው ብቻ በግምት ልናገር ... በትክክል ቪዲዮው የተቀረጸው ጅዳ ሽሚሲ ስለመሆኑ መረጃው ደርሶኛል፣ ልጅቱ በእስር ላይ የምትገኝ ይመስለኛል፣ የቆንስሉ ተወካዮች ለምን ወደ ሕክምና እንዳልወሰዷት አልገባኝም። አንድ በቦታው የነበረች እማኝ ይህች እኅት ከእነ ልጇ ለቀናት ስትሰቃይ ማንም እንዳልደረሰላት ተናግራለች። አሁንም በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ወይ በጠና ታማ ሐኪም ቤት ተወስዳለች አልያም ወደ ማረፊያ ወስደዋት ይሆናል፣ በመጠለያ ካለችም ተከታትለው ሕክምና እንድታገኝ የእኛ ተወካዮች ሥራ አልሠሩ ይሆናል፣ በቅርብ ሰዓታት በደረሰኝ መረጃ መሰረት "ይህች እኅት ከእስር ቤት አስወጥተው የጣሏት የሳውዲ ፖሊሶች ናቸው!" የሚለው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን በሊያ በኩል ተስተካክሎ ሰምቻለሁ!
በትክክል የሆነው በጠና በመታመሟ ወደ አገር ለመላክ አንችልም መባሏን ነው፣ ይህ በመሆኑ ያለ ማንም ረዳት በበር ብርድና ጸሀይ እየተፈራረቀባት መሰንበቷ ልብን በኀዘን ይሰብራል። አሁንም አልመሸም፣ ያለችበት ቦታ ተጣርቶ ከተገኘች በጅዳ ቆንስል ተወካዮች ጎትጓችነት ወደ ሕክምና ሊወስዷት ይችላሉ! ይህን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ! አገሩ ሳውዲ ነውና በጠና በታመመና እስር ቤት ያለን የወገን ጉዳይ ተከታትሎ ሕክምና እንዲያገኙና ወደ አገር ለመላክ ከኤምባሲና ከቆንስላ ውጭ አማራጭ የለም! ጌቱና ሊያ ሾው የወገን ጉዳይ ያገባኛል ብላችሁ የወገናችሁን ድምጽ በማሰማት ላደረሳችሁን መረጃ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ!
እንዲህ አይነት የወገን ጉዳት ሲደርስ፣ በተለይ ሰው በጠና ሲታመምና ወደ አገር ቤት ልግባ ብሎ እጁን የሰጠ ዜጋ በማቆያ እስር ቤት ስማቅቅ ተራው ነዋሪ ሰው ለመደገፍ አቅሙ የለውም፣ ብቸኛው ደራሽ እውቅና ያለው የመንግሥት ተወካዮች ብቻ ናቸው! ለማጠቃለል ያህል ይህ መረጃ የሚደርሳችሁ የቆንስሉ ሹማምንትና ሠራተኞች ለፈጣሪ ብላችሁ ከነልጇ የምትከላተመው እኅት ዜጋ ናትና እርዷት፣ መረጃ ስጡን ተለመኑን!
ቸር ያሰማን!
ነቢዩ ሲራክ
ኅዳር 14 ቀን 2009 ዓ.ም.
(ከዚህ ጋር ያያዝኩትን ፎቶ ያገኘሁት ከሊያ ሾው ነው)