እውን መንግሥት ጋዜጠኞችን አያስርም? - ተመስገን ደሳለኝ ምንድነው?
ታሪኩ ደሳለኝ

የሕዝብን ሀሳብ በማናወጥ፣ ወጣቶችን ለአመፅ በማነሳሳት፣ የሀሰት ወሬዎችን በማቅረብ በሚል በመንግሥት ተከሶ 3 ዓመት ተፈርዶበት ወደ እስር ቤት ከገባ ዛሬ ታህሳስ 13/09 ዓ.ም. 2 ዓመት ከ2 ወር ከ11 ቀኑ ነው።
በነዚህ ግዜያት ውስጥ ሕክምና እንዳያገኝ፣ በቤተሰብ በጓደኛ በጠበቃ እንዳይጎበኝ ተደርጓል፣ የሚያነበው መጽሐፍ እንዳይገባለት ምንም አይነት ወረቀትም ሆነ ብዕር እንዳያገኝ ተደርጓል። የሰውነት መብቱ የነበረውን ሕገ-መንግሥቱ የሠጠው ሳይሆን ሕግ መንግሥቱ ይህን መብቱን ያወቀለትን ሁሉ በእስር ቤት በመንግሥት ተነጥቋል።
መንግሥት በአገሪቷ ውስጥ አንድም ጋዜጠኛ በመፃፉ አልታሰረም የሚለውን መከራከሪያ በእራሱ ፍርድ ቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን በመፃፉ ብቻ 3 ዓመት ተፈርዶበታል በማለት የራሱን ሕግ እራሱ መብላቱን በዓለም ፊት አሳይቷል።
መንግሥት በአገሪቷ ውስጥ በመፃፉ ብቻ አስሬዋለሁ ያለውን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ሲፈልግ ማንም አይጠይቀውም። ሲሻው የት አንዳለ አላውቅም እያለ ማድረግ የሚችለውን እያደረገ ይገኛል።
መንግሥት ይህን ሁሉ ነገር በተመስገን ላይ ለምን አደረገ ብለን ስናስብ፤ አንድ ሁለት ነገሮች ይታያሉ፤ የመጀመሪው በአሁን ሰዓት በአገሪቷ ውስጥ ያሉት ነገሮች ሁሉ እንዲፈጠሩ የተመስገን ጽሁፎች ዋነኛውን ቦታ ይወስዳሉ ብሎ ማመኑ (ይህን ምክንያት አመክሮ ካልሰጠንባቸው ምክንቶች አንዱ ነው ብለው የእስር ቤቱ ሹማምንቶች የተናገሩትን ልብ ይሏል)።
ሁለተኛው ተመስገን አመክሮ ተገምገም ሲሉት በዚህ መንግሥት አመክሮ አልገመገምም በማለቱ ተመስገን የት እንዳለ አናውቅም በማስባል ቤተሰቡን በማንገላታት ጫና ፈጥረው አመክሮ እገመገማለሁ እንዲል ለማደረግ የሄዱበት መንገድ ይመስለኛል።
ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን ተመስገንን ለአገሬ ስል ጉዞዬ እስከ ቀራኒዮ ነው ካለበት መንገዱ ውልፍ አያደርገውም። እስካሁንም አላደረገውም። ለምታደርጉት ግፍ ሁሉ ተመስገን የኛ ልጅ በርታ! በርታ! የሚል ድጋፍ አያስፈልገውም፤ እሱ ቅድሞም የበረታ ነው እና። መንግሥት ተመስገን የት እንዳለ አላውቅም ከማለት ተመስገንን መጠየቅ አይቻልም ወደ የሚል መንገድ ገብቷል። እኛ ከነገ ዛሬ ካየነው በሚል ዝዋይ እስር ቤት መመላለሳችንን ቀጥለናል።



