በገዛ ዳቦዬ
አስፋ ጫቦ
ዛሬ በሌላ ሰበብ በጨረፍታም ቢሆን ለማየትና ለማሳየት የምሞክረው አሜሪካ ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በንግዱ ዘርፍ ተሳታፊነት ነው። ዲያስፖራ አላልኩም! ቃሉን ስለማልወደው ነው! ሌላ ቀን እንወያይበታለን!
ገና አሜሪካ እንደመጣሁ 1984 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1992)፣ በፊት የሚያውቁኝና አዲስ ያወቁኝም አሜሪካኖች ዋሺንግቶን ዲ.ሲ.፤ ጆርጅ ታውን (Goergetown) በሚባለው የሀብታሞች መንደር፤ አበሻ ምግብ ቤት ምሳ ጋበዙኝ። በጫወታችን መካከል በእንግድነቴ በዞርኩበት ስለኢትዮጵያውያን የታዘብኩትንና ያለኝን አስተያየት ሰጠሁ። ወረዱብኝ! በተለይም ዲን ጀምስ ፖል (James Paul) ወረዱብኝ። ”አንደኛ እንደሕግ ባለሙያ አልተናገርክም! በቂ ማስረጃ ሳትይዝ ወደድምዳሜ ተሸጋገርክ! ሁለተኛም እዚህ ያሉትን ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያውያን ባህርይ ልብ አላልክም። ኢትዮጵያዊው በተፈጥሮ ልታይ ልታይ የማይል (Low Profile) ሕዝብ ነው። እንጅ ለመሆኑ ከአፍሪቃ የትኛው አገር ነው ቤተክርስቲያናት፤ መስጊዶች፤ የባህል ማዕከሎች (Community Centers)፤ የምግብና ሌሎች አገራቸውን ነክ የሆነ ነገር ያዘጋጀና ያደራጀ፣ በከፍተኛ ሥልጣንና በየዩኒቨርስቲዎቹ ...” ይቅርታ ብጤ ጠይቄ ተለያየን። ከዚያ ወዲህ የበለጠ ልብ እንድል ረድቶኛል።
* * *
የዛሬ ወር ገደማ ይመስለኛል የትራምፕን የአሜሪካንን ፕሬዚደንት ምርጫ ማሸነፍ ሰበብ ሆኖ “በማግስቱ!” የሚል ጽፌ ነበር። ማኅበራዊ ገጽ (Facebook) እና ድረገጻት (Online) ሁሉ ለጥፌው ነበር። አዲሳባ አዲስ አድማስም ላይ ወቷል። እንዳሉኝ ከሆነ ቁጥር ስፍር የሌለው ሰው ማንበብ፣ አስተያየት መስጠት ብቻ ሳይሆን አዳርሰውታልም (Share)። ደስ አለኝ! ”የወለዱትን ሲስሙለት የደገሱትን ሲበሉለት!” እንደሚባለው መሆኑ ነው።፣ ”በማግስቱ!” መዝጊያው ላይ አንዳንድ ስለ አሜሪካን የምታዘባቸውን አልፎ አልፎ ማቅረብ እሞክራለህ ብዬ ነበር። ይኸ ያ መሆኑ ነው! የትራምፕን መመረጥ ጥቁር አሜሪካውያን (Afirican Americans) እንዴት እንዳዩት በጨረፍታ ለማየትና ለማሳየት ሙከራ መሆኑ ነው ።
የዛሬ ዓመት ይሁን እንዲያ ሌላ የጻፍኩትም ነበረኝ። ሙሉ ለሙሉ አላስታውሰውም። የማስታውሰውን ያክል ካለሁበት ከዳላስ ወደዋሽንግቶን ዲ.ሲ. ለመብረር ዳላስ Love Field Airport አውሮፕላን ማረፊያ ሄደኩ። ፈታሹ የያዝኩትን ቡና “ድፋው!” አለኝና ደፋሁት። የሚጠጣ ነገር የታሸገም ቢሆን አውሮፕላን ይዞ መውጣት ከተከለከለ ቆይቷል። ለወዳጆቼ ይሆናል ብዬ የገዛሁትን ውስኪና የወይን ጠጅ “ወይ ጠጣው ወይ ድፋው!” አለኝ። ሰጠሁት እንጅ አልደፋትም! የጸጥታው ጉዳይ ነው። በዛሬው ዘመን ፈንጂ ምን ማን መስሎ እንደሚመጣ አይታውቅምና! “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ!” የሚሉት አይነት መሆኑ ነው።
እኔ አውሮፕላን መብረር ይስለቸኛል! ረዥም ሰዓታት ቁጭ የሚያሰኝም በረራ አውቃለሁ። ከዳላስ ዋሽንግቶን ዲ.ሲ. 3 ሰዓት ከሩብ ነው። ቢሆንም ይሰለቸኛልና ጋዜጦች፤ መጻሕፍት፣ ቡና ይዤ ተሳፍሬ አባብለዋለሁ። አውሮላንኑ ላይ የሚሰጠውን ነጻ ቡናና ቁርሳ-ቁርስ (Snack) አልወደውም። የለበጣና የይስሙላ ይመስለኛልና! የአሁኑን አላውቅም እንጅ ለዓለም አቀፍ በረራ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የጀርመን አየር መንገድ ይመስል የለም። የአገር ውስጥ በረራ ሁሌም፤ የትም የማስተናገዱ ደረጃው ዝቅ ይላል።
ስለዚህም ቡናና ቁርሳ-ቁርስ (Snack) ለመግዛት አውሮፕላን ማረፈፊያ አዳራሽ (Terminal) ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስል ብዙ ኢትዮጵያዊያንን አየሁ። አሁን አቡነ ባርናባስ የሆኑት አባ ወልደትንሳኤ አንዴ ሎስ አንጀለስ (Los Angeles) ጫዋታ ላይ “አቶ አስፋ እባክዎ ይተዉኝ! አበሻን እንኳንስ ፊቱን አይቼ ከማጅራቱም ቢሆን እለያለሁ!” ያሉኝን አስታወሰኝ። አንዳንድ ኢትዮጵያውያን እንግሊዚኛውን በቅጡ የማይችሉ በአማርኛ ሲያናግሯቸው በእንግሊዚኛ የሚመልሱትን አንስተን ስንጫወት ነበር። አሁን ይህንን ያነሳሁት ኢትዮጵያውያንና ብዛቱን ለመለየት ችግር አልነበረብኝም ለማለት ነው።
ቡና ፍለጋ የገባሁበት አንዲት ወደወጣትነት የምታደላ ልጅ አገኘሁና “አንቺ ይህንን አየር ማረፊያ ተቆጣጠርነው አይደለም እንዴ!” አልኳት። ይህንን እዚህ አሜሪካኖቹ “ትንሽ ጫዋታ” (Small Talk) ብለው የሚጠሩት አይነት መሆኑ ነው። በአብዛኛው ፈረንጆቹ ዘው ብለው ወደፍሬ ሃሳብና ወደሚያከራክርና ወደሚያወያይ ጉዳይ አይገቡም። ገራ ገሩንና የማያሻማው ላይ ያተኩራሉ። ብዙ ጊዜ የአየር ጠባይ ተዘውትሮ የዚህ ደንበኛና መደበኛ ርዕስ ወይም ስፖርት ነው። አየሩ ባለቤት የሌለው የሁሉም ንብረት ነውና!
ኢትዮጵያዊው፤ በአብዛኛው፤ ከሰላምታ በኋላ፣ ”ምን የአገራችን ነገርኮ ...!” ብሎ ይጀመራል። ቢያውቅህም! በቅጡ ባያውቅህም! ዛሬ ጥዋት ተገናኝታችሁ ከሆነም! “የአገር ፍቅር!” መሆኑ መሰለኝ። ቢሆንም ይህን የመሰለ ጉዳይ ቦታ ቦታና ወቅትም የሚፈልግ ይመስለኛል። “ከምንና ስለምን፣ ከማንስ ጋር!” የሚለው አስቀድሞ የሚታወቅና ካደረው ከሰነበተው ቢጀመር የሚሻል ይመስለኛል። ያለበለዚያ የሚገባውን ክብደት ያጣና የለበጣ ያስመስለዋል ብዬ እፈራለሁ። የሚያወሩትን ማጣትም ሳይሆን ይቀራል? “ዝም አይነቅዝም!” ጥሩ አማራጭ ይመስለኛል። መስመር የለቀቅሁ መሰለኝ! የኔነገር!
ታዲያ “አንቺ ይህንን አየር ማረፊያ ተቆጣጠርነው አይደለም እንዴ፦” ያልኳት ልጅ “አይ! ገና ነው! ገና ነው!” አለችኝ። ኮስተርና ፍርጥም ብላ! ጥያቄዬን እንደዋዛና ለሰላምታ በር መክፈቻ እንዳቀርብኩት አልቆጠርችውም። የምታየውንና የሚታያትን እውነት የተናገረች መሰለኝ። ከዚህ ተነስቼ አንድ ለማስረጃነት የሚሆን አቀርባለሁ።
* * *
7–Eleven የሚባል በአሜሪካ ሁሉ የተዳረሰ፤ ዛሬ በሌላውም ዓለም ያለ፤ ከብዙ ዓመታት በፊት ቴክሳስ የተጀመረ ኩባንያ ነው። ስሙ 7-Eleven መሆኑ በወቅቱ ያ ሱቅ ክፍት የሚሆንበትን ሰዓት ማመልከቱ ነው። ከጥዋቱ 1 ሰዓት ይከፈትና ማታ በ5 ሰዓት ይዘጋል ለማለት ነው። አሁን ሰዓቱ ቀርቶ ስሙ ብቻ ነው የተረፈው! 24 ሰዓት ክፍት ነው። እንዲህ አይነት ሱቆችን Convenience Store ይሏቸዋል። ትርጉሙ።
Convenience store - Wikipedia - A convenience store is a small retail business that stocks a range of everyday items such as groceries, snack foods, confectionery, soft drinks, tobacco products, over-the-counter drugs, toiletries, newspapers, and magazines.
ዳላስ Dawntown መርካቶ ማለት ነው፤ ያለው 7-Eleven አንድ ሲቀር በሙሉ በኢትዮጵያዊያን የሚካሔድ ነው። የሚካሔድ ያልኩትን በኋላ አስረዳለሁ።
የዛሬ 3 ዓመት ገደማ ይመስለኛል የመጀመሪያውን 7-Eleven ያየሁት Gaston and Peak መንገድ ነበር። ቡናና ሲጋር ልገዛ ገብቼ ኢትዮጵያውን ብቻ ሳይ አንዱን ጠየቅኩት፤ ”የኛው ነው!” አለኝ። የቻልኩትን ያክል አመሰገንኩ፤ አበረታታሁና ወጣሁ። ከዚያ በኋላ ባለፈው ሁለት ዓመት ነው አራት አዳዲስ 7-Eleven መርካቶ ያየሁት።
የመርካቶው ሲገርመኝ የዛሬ ዓመት ገደማ ይመስለኛል አዲስ የተከፈተውን ቢጫ (Yellow Line) የባቡር መስመር መጨረሻ መቆሚያ ለማየት ተሳፈርኩና Buckner የሚባል መንገድ ደረስኩ። ከመቆሚያው ማዶ አንድ 7-Elevem አየሁና የሆነ ነገር ለማግዛት ስሔድ፤ ሻጩ ኢትዮጵያዊ ነው። እኔ ለየሁት! እሱ አለየኝም! በአማርኛ ሰላምታ ስሰጠው ደነገጠ! ጥቁር አሜሪካዊ ብለው የሚገምቱኝ አይጠፉም! ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያዊ መሆኔ ወዲያውን የማይረዱ ያጋጥሙኛል። ይኸኛው ከዚያ አንዱ ነው። ደስ አለው! ፈነደቀ! እዚያ አካባቢ ብዙ ኢትዮጵያዊ አያዘወትርም መስለኝ። ደጋግሜ እንድመጣም ጋበዘኝ። ዕቃ ለመግዛት ሳይሆን አገሩን እንዳስታውሰው አይነት መስለኝ። ከወደጎንደር የመጣ መሰለኝም። አማርኛውም አስተነጋገዱም ሞቅና ለየት ያለ ነበር።
ዳላስ የተለያዩ ከተሞች አቀፍ (Metropolitan) ከተማ ነው። በአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤቶችና ሱቁች አሉበት። በተለይም Park Lane በሚባለው መንገድ ሞቅና ደመቅ ያሉ የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤቶችና ሱቆች እንደልብ ናቸው። ይህ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት ከተማ የተለመደ ነው። ተመጋቢው፣ ሸማቹ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ፈረንጁንም ይጨምራል። ሎስ አንጀለስ የነበርኩ ጊዜ፤ መርካቶ፣ የዳዊት ምግብ ቤት፣ ፈረንጁ ከአበሻው ጋር መሳ ለመሳ ሲሆንም አይቻለሁ። ሽሮውን፤ ጎመኑና የክክ ወጡን ጤናማ ምግብ (Health Food) ሲሉም ሰምቻለሁ። የበለጠ ደምቆ ያየሁት በዋሽንግቶን ዲሲ፤ በሜሪላንድ (አገር ማርያም) እና በቨርጂኒያ ነበር። አንድ ቀን ሲለኝ እመለስበታለሁ። አሁን ወደተነሳሁበት ልመለስ።
ይህንን 7-Eleven አይነቱን የንግድ ሥራ ፍራንቻይ (Franchise) ይሉታል። ትርጉሙ ይኸውና።
Franchise; an authorization granted by a government or company to an individual or group enabling them to carry out specified commercial activities, e.g., providing a broadcasting service or acting as an agent for a company’s products
ገባ ብለን ብናየው ዘመናዊ ገባርነት መሆኑ መሰለኝ። ባለሀብቱ፣ ኩባኒያው፣ ምን መሸጥ እንዳለበት ዋጋውን ጨምሮ ይነግረውና ይህንኑ በሱ ፈቃድ ስም እንዲሸጥ ይፈቅድለታል። ፈቃዱን አከራየው ማለት ነው። ለዚያ በስምምነቱ መሠረት ለባለሀብቱ ይገብራል። እሱ(ሷ)ም ድርሻ አላቸው!
ይኸ ነገር ኢትዮጵያም አለ። ይህ ሁሉ ነዳጅ ማደያ፤ የግል የራዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያ ፍራንቻይዝ መሆኑ ነው።
ይኸ ሁሉ ሲሆን በአብዛኛው የአሜሪካ ከተሞች ሱቆቹና ንግዱ የሚካኼደው በፈረንጅ ካልሆነ እንደኢትዮጵያዊው በመጤው ነው። የሚበዙት ላቲኖ የሚባሉ አሜሪካኖች፤ ማለትም የስፔይን ዝርያ ነን በሚሉት፤ በቻናውያን፤ በፓኪስታና ሕንድ ... ምኑ ተቆጥሮ ነው። “ጥቁሩ አሜሪካዊ የለበትም!” ለማለት ነው።
“ለምን፣ ስለምን ጥቁር አሜሪካዊ ንግድ ሥራው ውስጥ የለበትም?” ጥሩ ጥያቄ ነው! መልሱ የአሜሪካን ታሪክ አካል ነው! አብርሐም ሊንክን ተብሎ በሚዘመርለት ፕሬዚዳንታቸው ዘመን “ነጻ ወጡ!” (Emancipation Declaration) ተባለ። ከዚያ በፊት በተለይ ደቡብ ክፍል በጌቶቻቸው መሬት ላይ የሚያርሱ፤ የሚኖሩ ነበሩ። “ነጻ ወጣ!” ሲባል ባሪያ አሳዳሪው ከመሬቱ አባረራቸው! ወደከተማ ገቡ! ትምህርት፤ ዕውቀት፤ የሥራ ልምድ፣ ገንዘብ ሳይኖራቸው መለመላቸውን ነው የተነቀሉት። በዚህም በየከተማው የተረገጠ የተረሳ ጥጋ ጥግ ታጎሩ! ተጠራቀሙ! ጌቶ (Ghetto) የሚባለው ይህ ነው! አሜሪካ ጥቁሩ አብዛኛው የሚኖረው ጌቶ ነው። “ኑሮ ካሉ መቃብር ይሞቃል!”ም የሚባለውንም የሚያሟላ አይመስልም።
የንግድ ሥራ አሁን ትምህርት ቤት ተግብቶ የሚማሩት ሙያ ቢሆንም፤ ከትውልድ ትውልድ ለዘመናት የሚተላለፍ ነው። ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያ የነጋዴ ልጅ ቢሆን ባይሆንም ስለንግድ እውቀት አለው። ገቢያ ሲሔድ፤ ሲገዛ፤ ሲሸጥ ሲለዋወጥ እያየ ነው ያደገው። ስለዚህም ንግድ ሲጀምር የሚጀምረው ከሀ አይደለም። ያ ለዘመናት የተወራረደው አለው። እርሾ ማለት ነው! ይህ ለኢትዮጵያ ያልኩት ለቻይናዎቹ፤ ሕንዶቹ፤ ፓኪስታኖቹ ለሌሎች ሁሉ ይሠራል። ጥቁር አሜሪካኑ ይህ የትውልድ ውርስና ቅርስ የለውም! ሊጀምር እንኳን ቢል ንግድ የውድድር ጉዳይ ነውና አብረው መወዳደሪያው ሜዳ የተሰለፉት በዘመናት ይቀድሙታልና ከስሮ ይወጣል ማለት ነው።
አሜሪካን ጥቁሮቹ በትግላቸው ያስገኙት (Civil Rights Movement) ብዙ መብቶች አሉ። ይህ እነማርቲን ሉተር ኪንግ የታገሉለትና የሞቱለት! የዚህ ትግል ወጤት ለቁጥር-አናሳ (Minority) ለሆኑ ዜጌች ለትምህርትም ሆነ ለንግድ የተሻለ ዕድል በሕግ መድቧል። እነዚህ ከሌላ የመጡት፤ ኢትዮጵያውያኑን ጨመሮ የዚህ የጥቁሩ አሜሪካዊ የትግል ውጤት የሆነውን መብት ተጠቃሚ ናቸው። ቁጥር-አናሳ (Minority) ናቸውና!! ጥቁር አብዛኛው አልተጠቀበትም! ሊጠቅምበትም አይችልም! ከላይ በገለጽኩት ምክንያት! እርሾው የለውምና!
* * *
አሁን ወደተሳሁበት ከፊል ዋንኛው ነጥብ ልግባ። ይህም የጥቁር አሜሪካኖችና የዶናልድ ትራምፕ ምርጫ መሆኑ ነው። በተለምዶ ጥቁር አሜሪካውያን ዴሞክራቶች ናቸው። ይህም ማለት ሂለሪ ክሊንተንን ይደግፋሉና ይመርጣሉ እንደማለት ነው። በውድድሩ ወቅት “ጥቁሮቹ በዚህ ምርጫ ትራምፕን ነው የሚደግፉት!” የሚል ዜና አልፎ አልፎ ቢናኝም ለማመን የሚያስቸግር ነበር።
ለማመን የሚያስቸግረው ክሊንተን ለጥቁር አድማጮችዋ ያ የተለመደውን ዴሞክራት ተወዳዳሪ የሚለውን አለች። የተጠናውን! ትራምፕ ግን ግልጽ ነበር። “እኔን ምረጡኝ! ሁሌ ዴሞክራት መርጣችሁ ያለፈላችሁ ነገር የለም! እኔን ብትመርጡ የምታጡት ነገር የለም! What have You Got to Loose! ማንም ሆነ ማን ሊያደርግላችሁ የሚችለው ነገር የለም! እንደማለት ነው። “ያው በገሌ! ናችሁ!” ማለት ነው። እውነትም ነው! ስድብም ነው!
ትራምፕ ሌላ ያለው ነገር አለ። ”እዚህ የተጠራቀመውን የውጭ ዜጋ በተለይም ሜክሲካኖችን አስወጣና፤ እንዳይገቡም አጥር አጥራለሁ!” አለ። ለጥቁር አሜሪካኖች ያቃጨለው ይህ ነው። ጠራርጎ ሲያስወጣልን ሥራ እናገኛለን ነው።
እኔ ብዙ ጥቁር አሜሪካውያን ወዳጆች አሉኝ። አሜሪካዊ ወዳጅ የሚባል ነገር ካለ! ስለዚህም በምርጫውም ውስጥ ከምርጫውም በኋላ እናወራለን። ”ለመሆኑ መቼ ነው የምትሔደው?” ይላሉ። “አይ አልሔድም ቴክሳስ ተስማምቶኛል” እላለሁ። “የለም ወደ አገርህ ማለታችን ነው!” ይላሉ። ከዚያም አጠገባችን ያሉ ሜክሲካኖችን ያሙልኛል። ”ቆይ ታዘበኝ አሁን ትራምፕ ተመርጧልና በሚመጣው ሳምንት አታገኛቸውም!” ይላሉ። ይኸው ነው። ይህ ለኢትዮያውንም የሚሆን ነው። የደረሱበት አዘቅት ሥርዓቱ መሆኑን ትተው “መጤው ነው እንጅ!” ማለታቸው ነው። እውነቱን ከፍቶ ለማየት አለመቻል፤ ወይም አለመፈለግ፤ ወይም ምርጫ እንደማጣት ነው። “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ...!” አይነት መሆኑ ነው።
የሚገርመው ወይም የሚያስቀው ይህ እናስወጣለን የሚሉት መክስኮዊ ይህ ያለበት አገር፤ አሜሪካ አገሩ፤ ትላንት Spanish American War, Mexican American War በሚሉት ጦርነት የተወሰደ ነው። ለምሳሌ ተክሳሳን ተክሳስ ብለን የምንጠራው በእንግሊዚኛ ሲሆን ነው። ያለበለዚያ ቴሐስ ነው። X በስፓኒኛ ሀ ተብሎ ነው የሚነበበው። ከዚህምሌላ የግዛቶቹ ስም፣ ካሊፎርኒያ፤ ኔቫዳ፤ ነው መክሲኮ፤ ኮሎራዶ፤ አሪዞና እንዳለ በስፔይን ቋንቋ ነው። በተለየ ካሊፎርኒያ ከሳን ፍራንሲስኮ እስከ ሳን ዲያጎ ሎስ አንጀለስን ጨምሮ የካቶሊክ ቅዱሳን ስም ነው፤ የካሊፎርኒያ ዋና ከተማ ስም ሳክራሜንቶ (Sacramento) “ቅዱስ ቁርባን” ማለት ነው።
ይህን መነሻ በማድረግ ሰፋ ተደርጎ ከታየ ትልቁ ምስል የሚታይ ይመስለኛል።
“ከኋላ የመጣ ቀንድ አወጣም!”ንም የሚያጣ አይመስለኝም። “በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት!” ማለትም ይኽው ይመስለኛል!
አንድ ቀን ሲመቸኝ ወይም ሲለኝ ስለ “ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ!” እመለስበታለሁ።