ፍቅር ወርቁ

Prof. Almariam

እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት/የገና በዓል በሰላምና በጤና አደርስዎ! እንዲሁም ወንድማዊ የአክብሮት ሰላምታዬ ባሉበት ይድረስዎ!

በየሳምንቱ ጠለቅና ሰፋ ያለ የትንታኔ ጽሑፍዎ/Commentary ይደርሰኛል። እንዲሁም በውድ አገራችን ኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ ጊዜያት፣ በበርካታ ወቅታዊ አገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አተኩረው የሚጽፏቸውን ጽሑፍዎችዎንም በሚገባ እከታተላለሁ። ለአገርዎ ያለዎትን እንደ እቶን እሳት የሚንቀለቀል ቅናትዎን፣ (መጽሐፍ፣ "ቅንዓተ ቤትከ በልአኒ፤ የቤትህ ቅናት በላኝ።") እንዲል። የኢትዮጵያን አምላክ የሚማፀን "ተስፋንና ፍጻሜን" የተሞላ ራዕይዎን እና ትጋትዎትን፣ መጽሐፋችን/አይሁዳዊው ንጉሥ፣ ጠቢቡ ሰለሞን፣ ("ትጋት ለሰው የከበረ ሀብት ነው።") እንዳለ። በእጅጉ አደንቃለሁ፣ አከብራለሁም።

የተወደዱ ፕ/ር የምዕራባውያኑን የChristmas እና የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓል በማድረግ ለአገርዎና ለወገንዎ ያለዎትን ሕልም፣ ራዕይ፣ ምኞትዎንና የመልካም ምኞት መግለጫዎን ካነበብኩ በኋላ ይህችን አጠር ያለች ጦማር ላደረስዎ ወደድሁ።

ምዕራባውያኑ "የገና/የልደት በዓል - It is the holiday of Gifts and Forgiveness / የፍቅር ስጦታ መለዋወጫና የይቅርታ በዓል፤" እንደሆነ የሚያስረግጥ የቆየ ተወዳጅ ብሂል አላቸው። እንደ ኃይማኖት ሊቃውንት አስተምህሮም የገና በዓል - በሀጢአትና በአለመታዘዝ ጠንቅ ከፈጣሪ፣ ከተፈጥሮ፣ ከራሱ፣ ከሌላው ወንድሙ/ወገኑ የተጣላው፣ የተለያየው የሰው ልጅ ከፈጣሪው፣ ከተፈጥሮ፣ ከመላዕክት፣ ከወገኑ ጋር ዕርቀ-ሰላም አውርዶና በአንድነት ሆኖ በፍጹም ደስታ እያሸበሸበ፤

"ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ ሃሌ ሉያ!" በማለት ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት/አብሮነት የዘመሩበት፣ ያዜሙበት፣ ልዩ የሆነ ሰማያዊ ቅኔን የተቀኙበት - ታላቅ የፍቅር፣ የሰላም፣ የይቅርታ በዓል ነው። ገና ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከእስያ እስከ አውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ - ከኢየሩሳሌም ቤተልሔም እስከ ሩቅ ምሥራቅ፣ ጃፓንና ቻይና፣ ላቲን አሜሪካና ካሪቢያን ድረስ በታላቅ ኃይማኖታዊ ደማቅ ሥነ ሥርዓትና በብዙ ተናፋቂ ባህላዊ ዝግጅቶች የሚከበር በዓል ነው።

ገና የሰላም፣ የዕርቅ በዓል ነው ... የታሪክ ድርሳናት እንደሚያትቱትም ምዕራባውያን 50 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ከሞቱበትና ዓለማችንን ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከዳረጋት የሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ፤ በገና በዓል ሰሞን ተግባራዊ የሚሆን አንድ "የሰላም ስምምነት ሕግ" አውጥተው ነበር። ይሄውም በጠላትነትና በጦርነት ውስጥ ያሉ የባላንጣ አገራት ወታደሮች - የገና በዓል ዕለትና ሰሞን ስለ ሰላም ሲሉ ነጭ ርግብ ይለቃሉ፣ ስጦታ ይለዋወጣሉ፣ ጠላትነታቸውን ለጊዜውም ቢሆን ረስተው በገና በዓል ሰሞን ሰላምታ ይለዋወጣሉ። በዚህ ጦርነት፣ ጠላትነት በገነነበት የጥላቻ አየር ውስጥ ሽው የሚል የዕርቀ-ሰላም ያለህ የሰላም ናፍቆትን "the Christmas Truce" ሲሉ ይጠሩታል።

የተከበሩ ፕ/ር አለማርያም ነገሬን አስረዘምኩት መሰለኝ። ጦማሬን ለዛሬ በዚህ ላጠናቅቅ። ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም በተበሰረበት የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል መታሰቢያ ለዓለም፣ ለሰው ልጆች ሁሉ፣ ለአገራችንና ለሕዝባችን ሰላምን በመመኘት ልሰናበት።

ሰላም! ሻሎም!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ