አስፋ ጫቦ (Corpus Chirsti, Texas, USA)

Donald Trump.
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ “አርብ ማታ ስዊድን የደረሰው አደጋ!” አለ። ስዊድኖቹ “እንዴት እኛ ሳናይ፣ ሳንስማ ትርምፕ ሰማ!” አሉና አሽሟጠጡት። ይህንን ዜና ያገኘው ከFox ነበር።

አሜሪካ ዛሬም በሁለንተናው ግምባር ቀደም ነኝ ስለምትል (“ያማ ያለፈ ወሬ ነው!) የሚሉ ሞልተዋል) በፕሬዚዳንቱ፤ በዶናልድ ትራምፕ፤ ልጀመር። ”የኔ ጠላት የአሜሪካን ሕዝብ ጠላት ነው”፣ “They are not my enmeies but the enemy of the American people) ብሎ አረፈው።

የፈረንሳይ ንጉሥ የነበውን ልዊ 14ኛውን አስታወሰኝ። ”ፈረንሳይ ማለት እኔ ነኝ!” አለ! L’Etat Se Moi! ጠላቴ የሚለው የሕዝብ መገናኛውን እንዳለ ነው። አንድ ሁለት በራሱ ቅጥረኛ የሚታተሙና አንድ የማይሆን ዜና አቀባይ የሆነ ቴሌቪዥን ጣቢያ፤ Fox፤ ከዚህ ውስጥ አስወጥቷል። “አርብ ማታ ስዊድን የደረሰው አደጋ!” አለ። ስዊድኖቹ “እንዴት እኛ ሳናይ፣ ሳንስማ ትርምፕ ሰማ!” አሉና አሽሟጠጡት። ይህንን ዜና ያገኘው ከFox ነበር።

ጠላቴ የሚለውን መገናኛ ብዙኅን ነበር። አሜሪካኖቹ አራተኛው የመንግሥት ዘርፍ ይሏቸዋል። The Fourth Branch of Government! ሦስቱ ያው የታወቁት ሕግ አመንጭ፤ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ የሚባለው ነው። ትራምፕ እንግዲህ እልቅናው ለዚህ ለፈጻሚው ክፍል ነው። ፈጽም ተብሎ የተሰጠውን!!

“አንድ እስላም ድርሽ እንዳይልብን!” ብሎ ያወጣውን ሕግ፤ አንድ የፌዴራል ዳኛ አቀበው። የትራምፕ ሰዎች ይግባኝ ብለው ወደሚቀጥለው ፍርድ ቤት ሲሔድ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ”ይግባኝ አላችሁ እንጅ፤ ለምን ይግባኝ ስለአላችሁ ልታስረዱን አልቻላችሁም” ብለው ያንኑ የታችናውን ፍርድ ቤት ውሳኔ አጸደቀ። ከዚያ ትራምፕ ዳኞቹን “ዳኛ ተብዬ!” ብሎ ዘለፋቸው።

እንደልቡ ተነጋሪ ነው? ዘረጦ ነው ማለት ሳይሻል አይቀረም! የአሜሪካንን መንግሥት ሥርዓት ሀ ሁ ሳይውቅ እንዴት እንደተመረጠ አሁን መጠየቁ “ጅብ ከሔድ ውሻ ጮኸ!” እንደማለት ነው። ከሁለት ወር በፊት “በማግስቱ!” ብዬ በሳጻፍኩት በመጠኑ አንስቻለሁ።። የአሜሪካን መንግሥት ሥርዓት “ሀ ሁ” መንግሥት በሦስት ቅርንጫፍ ይከፍላል የሚለውን ያልሰማ መሆኑ ነው። አራተኛው ቅርንጫፍ የሚባለው “የሕዝብ መገናኛ” Mass Media፤ ሦስቱንም ሲያበጁ “አበጀህ!”፣ ሲያጠፉ ”አጠፋህ!”፤ ሲማግጡ “ማጋጥክ!” የሚለው ነው። ትራምፕ አልሰማ ሆኖ እንጅ ይህ ነገር ወደ 300 ዓመት ሊሆነው ነው። የኢትዮጵያ ጠረን አለው ልበል?

“ኧረ ወየው ወየው! መጨረሻውን ላየው!” ይላል የኛ ሰው። የትራምፕ መጨረሻው ምን ይሆን?

* * * * * * * *

በቨይታምን ጦርነት ዘመን የተሰለፈውን ያክል የአሜሪካ ሕዝም በየግዛቶቹና በየከተማዎቹ ሁሉ ይሰለፋል። ትላንትን የፕሬዝዳንቶች ቀን (Presidents Day) ተብሎ በሚከበረው ዕለት ሕዝብ በገፍ ወቶ ተሰለፈ። የያዙት መፈክር ይናገራል! “Dump Trump! ያላል አብዛኛው። “ትራምፕን ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ወርውረው!” እንደማለት ነው። ሌላው “የኔ ፕሬዚዳንት አይደለም!” (Not My President!) የሚል ነው። ይህ እንግዲህ የአሜሪካ ሕዝብ ነው። ትራምፕ ደግሞ የኔ ጠላት ሁሉ የአሜሪካ ሕዝብ ጠላት ነው ብሏል። ቀረብ ብለው ሲተርጉሙት፤ የአሜሪካ ሕዝብ ጠላቴ ነው እንዳለ የሚያስቆጥር አንድምታ ያለው ይመስለኛል። ሕዝቡ ነዋ “ወግድልን!” የሚለው።

የትራምፕ መጨረሻ ተንታኞች ሁለት አማራጭ ዕይታ አሏቸው። አንዱ በቅርቡ ይወገዳል (Impeached) የሚል ነው። ይህ የተጧጧፈው የሕዝብ አመጽ ወደዚያ ያመራል በሚል ነው። ሁለተኛው አማራጭ የመንፈቁን ምርጫ (Mid Term Election) መጠበቅ ነው። ለአሜሪካ ምክር ቤት በየሁለት ዓመቱ ምርጫ ይደርጋል፤ በዚህ ምርጫ ዴሞክራቶቹ የላይኛውንም የታችኛውንም ቤት (Sanate and House) መቀመጫ ያሸንፋሉ። በአሸናፉ ማግስት መጀመሪያ የሚያረቁት ሕግ የትራምፕን ማስወገጃ ሕግ (Impeacheament) ነው ይላሉ። የዚያ ሰው ይበለን!

ትራምፕ በእንግሊዝኛው ሲጻፍ ሁለት አጻጻፍ አለው። አንደኛው በ”u” ሌላው በ”a”። በ”a” የሚጻፈው ትራምፕ Tramp አልባሌ፣ ማጋጣ እንደማለት ነው። “እርግጠኛ ስሙ ይኸኛ ይሆን” የሚያሰኝ ነገር ያመጣብኛል። የአንጎል ጅምናስቲክ mental acrobatics መሆኑ ነው።

* * * * * * * *

ከዚህ ከዓለም ጉዳይ ሳንወጣ ግሬስ ሙጋቤ፤ የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት የሮበርት ሙጋቤ ባሌቤት ስለባለቤትዋ የሰጠችው አስተያየትና በአደባባይ የተናገርችው ነው። “አይበለውና ሙጋቤ ሞቶ ተቀብሮ እንደገና ከመቃብሩ ተነስቶ ቢመጣም፤ የዚምባብዌ ሕዝብ በደስታ ይመርጠዋል!” አለች። ለሚቀጥለው የፕሬዝዳንት ምርጫ ሊገቡ ያሰቡትን “አትቋምጡ! አታገኟትም!” ለማለት ፈልጋ ነው።

ሙጋቤ አሁን 92 ዓመቱ ነው። ሥልጣን ላይ ደግሞ 37 ዓመት ሆኖታል። ባሌቤቱ ዕድሜዋ 51 ዓመት ነው። ብዙ ነገር አሳሰበኝ። አንዱ ኦሪት ውስጥ የአይሁድ ንጉሥ የነበረውን ዳዊትን ነው። ከጠነዛ አልጋ ላይ ከዋለ በኋላ ወጣት ሚስት እየተፈለገ አብሮት እንዲተኛና ሙቀት እንዲሰጠው ይደረግ ነበር ይላል መጽሐፉ። ይህ ሁሉ ታስቦ ቅዱስ ዳዊትም ተብሏል።

ግሬስ ሙጋቤ ”አትቋምጡ!” ስትል መልዕክቱ፤ ዋንኛው ምልዕክት፣ ”አልጋ ወርሽ እኔ ነኝ!” ለማለት ነው። ድፍረቱ፤ የሕዝብ ንቀቱ፤ ፕሬዚዳንት መባሉ፤ ሬፑብሊክ መባሉ ሁሉ ይደንቀኛል።

* * * * * * * *

ሦስተኛናው፤ በሳምንቱ ውስጥ ከገረመኝ አንዱ የሰሜን ኮሪያው “ንጉሥ” ሥራ ነበር። ንጉሥ ያልኩት ማዕረጉን ሁሌ መሪ (The Leader) ስለሚሉ ነው። በዚህ ላይ ከቀደመ-አያቱ ጀምሮ “ዘውዱ” ከዚያ ቤት አልወጣምና ነው።

ማለዥያ አውሮፕላን ማረፊያ ትልቅ ወንድሙን ያስገድላል። አስተዳደሩ ኋላ ቀረ ነው። አስገዳደሉ ግን ዘመናይ ነበር። ድሮ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ያየሁትን Candid Camera አስትወሰኝ። ትንሽ ገንዘብ ይከፍሉና ሰው ላይ ሳይስቡ ውኃ የሚረጩ፤ የሚያስረጩ ያንኑ ቪዲዮ ሠርቶ የሚታዳደሩ አሉ። በዚህ አሠራር አንድ፤ ይህንኑ ስትሠራ የነበረች ሴትን “እዚህ ሰውዬ ላይ ውኃ እርጭበት!” ይሏትና ትራጫለች። የአሁኑ ውኃ ሳይሆን መርዝ ነውና ሰውዬ ይሞታል!

“VX’ በሚባል፣ የደም ሥር ስተሮ የሚገል መርዝ ነው የገደለው” አለ የምርመራው ውጤት። የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት VXን ሕዝብን በጅምላ መፈጃ መሳሪያ ነው Weapon of mass destruction ነው ብሎ መድቦታል።

* * * * * * * *

1984 አስታወሰኝ! Big Brother is Watching You! በየአውሮፕላን ማረፊያው የሚጠብቅ CCTV (Closed Circuit Television) ካሜራ አለና ሴትየዋም ተካፋዮችም ይያዛሉ። አገር ጥለው የፈረጠጡ አራት ሰሜን ኮርያውያንም እየታደኑ ነው።

ከዚያ በኋላ ያለው ትንሽ ትያትርነት ያለው ይመስላል። የሰሜን ኮሪያ አምባሳደር “አስከሬኑ ይሰጠን! መመርመርም የለበትም!” ይላል። “የምርመራውንም ውጤት አንቀበልም!” ይላል። ትያትርነቱ እዚያ ላይ ነው። ሟቹ “ምናችሁም አላማረኝም!” ብሎ ተሰዶ ይኖር የነበር ነው። እንደጠላት ያዩትም ስለነበር ነው ያስገደሉት ማለት ይቻላል። አሁን ታዲያ ደርሶ “ቅቤ አንጓች!” መሆናቸው አይገርምም? ወይም የበለጠ አያስጠረጥርም? ከዚህ ሌላ የተገደለውን ሰው ሬሳው አይመርመርብን፤ ከተመረመረም ውጤቱን አንቀበልም ማለት የበለጠ አያስጠረጥርም? ወይስ የድንቁራንን ደረጃ መግለጫ ነው?

እንዳለኩት ኋላ ቀር ቢሆኑም አገዳደላቸው ዘመናይ ነው። ከዚያ በተረፈ ያለው እውነተኛነት፤ እርግጠኛ ኋላ ቀርነታቸውን መስካሪ ይመስለኛል።

ምስኪን የሰሜን ኮርያ ሕዝብ!! ምኑን ሰጣቸው!! ይሰውረን!!

አሁን በመጨረሻ ገደማ የተደረሰበት መረጃ አስረዳ እንደሚባለው፤ ይህ የተገደለው የመሪው ትልቅ ወንድም፤ ስደተኛው፤ የሰሜን ኮሪያ ስደተኛ መንግሥት መሪ እንዲሆን በሌሎች ስደተኞች በተለይም አውሮጳና አሜሪካ በሚኖሩር ተጠይቆ ነበር። ይህ ይሆናል ቃታውን ለመሰባ፤ ይቅርታ መርዝ ለመርጨት ዋና ምክንያት የሆነው ይላሉ ውስጥ አዋቂ ተንታኞች ነን የሚሉ።

* * * * * * * *

አሁን ደግሞ ወደቤተሰብና ወደማኅበራዊ መገኛኛዎች፤ በተለይም ወደ Facebook ልመለስ።

Facebook ትምህርት ቤት ሆኖኛል ያልኩኝ መስሎኝ። ጥሩውን፣ መጥፎንና ጥፉውንም ለማየት መንገድ ይከፍታል። ጥሩ ሲገኝ በርግጥ መነጋገሪያችን ላይ ሐሳብ፤ ቃላት፤ አዝማሚያ ሊሰጥ የሚችል ይሆናል። ያዳብራልም! ለዛሬ አንድ ካሳ አንበሳው የለጠፈውን እዚህ እንዳለ እለጥፈዋለህ።

Kassa Anbessaw

”ተክሌ syndrome በሰፊው እያስተዋልኩ ያለሁበት ሁኔታ ነው ያለው፤ ወያኔ ተረስቷል፤ ፌስ-ቡክ በአጼ ምኒልክ፣ በቴጌ ጣይቱ እና በአባት አርበኞች ተጥለቅልቋል፤ አባቶቻችን ነጻነቷን የጠበቀሽ፣ የተፈራች እና የተከበረች አገር አስረክበውናል፤ ይሄንን ጠብቆ ማቆየት እና እኛም ለልጅ ልጆቻችን የማስተላለፍ ታሪካዊ አደራ አለብን፤ ኑ! አገራችንን ከወራሪው ወያኔ ነጻ እናውጣት! ዳይ!

(የግርጌ ማስታወሻ:- “ትክሌ syndrome” እውነታን አሸሽቶ ታሪክ ውስጥ የሚያሸጉጥ የበሽታ ምልክት ነው፤ ይህ በሽታ ጎልቶ የታየው ተክሌ ይሻው ላይ በመሆኑ “ተክሌ syndrome” ተብሎ ተሰይሟል።)

* * * * * * * *

እኔ ግርዳ ላይም አምጥቼ ለጥፌው ነበር። ያለምንም ተጨማሪ አስተያየትና ማዳበሪያ! ይህንን ያነበበ አንድ ወዳጄ ከካናዳ ደውሎ ሳቅ በሳቅ ሆነ።። ”ምነው?” ስለው “ስለዚህ የአማራ መሸጫ ሱቅ ስለአቋቋመው ተክሌ ይሻው እምለው አጥቼ ይህ ሰው አለልኝ” አለ። ሱቅ የሚለው ተክሌ “ምጽአተ አማራ” የሚል አንዳች የሚያክል መጽሐፍ ጽፏልና ነው። መጽሐፉን እየዞረ የሚሸጠውን ለማለት ነው። መጽሐፉን አንድ ወዳጄ ከዋሽንግቶን ዲሲ ልኮልኝ ትንሽ አገላብጬ አስቀመጥኩ። ፈርቼ ያስቀመጥኩት የመጀመሪያው መጽሐፍ መሆን አለበት።

ሁለተኛው፣ ትላንት Facebook ላይ የለጠፍኩት እንዳለ ይኸውና:-

Assefa Chabo

“የጋራ ቤታችን! ቅርሳችን! ውርሳችን!” የሚል ጽሁፍ ጀምሬ ነበር። አልሔድልኝ፣ አላልቅልኝ አለ። ውስጤ የቀረ ነገር አለ ማለቱ ነው ብዬ ተረጎምኩት። በዚያ ምክንያት ከኢትዮጵያ ታሪክ ውጭ ስለሰው ልጅ አብሮ የመኖር ታሪክ ማሰስ ጀመርኩ።

በዚህ አሰሳ Identity Politics የሚል አገኘሁ! “የማንነት ፖለቲክ!” ፖለቲካ ማለት። በዚህ ምክንያት ያገኘዃቸውን 3 ጽሁፎች፤ 1. Identity Politics are Ripping Us Apart፣ 2. Identity Politics Run Amak እና 3. Identity Politics/Philosophy Talk Facebook ላይ ለጠፍኩ።

ዛሬ አራተኛው ይሁን አምስተኛ ቀን ሆኖታል። ዞር ብሎ ያየው በጣት የሚቆጠር ነበር። እኔ ደግሞ ወደ 7,000 ወዳጆች (Friends) አሉኝ። “ወዳጆቼን ምን ነካቸው!” ማለቴ አልቀረም። ከወር በፊት ጣቴን በድል ምልክት (V) ቀስሬ የተነሳሁትን ፎቶግራፌን ለጥፌ እንኳን ወደ 700 የሚጠጋ ሰው ጎብኝቶታል።

ለዚህ መነሻ የሆነኝ ዛሬ በተለየ በዲያስፖራ የሚገኙ ”የአማራና ኦሮሞ ሊቃውንት ነን” የሚሉ ከኢትዮጵያ ተፋተው ስለመንደራቸውና “ነን!” ብለው ስለሚያስቡት ጎሣ (ሥራዬ ብዬ ብሔረሰብ አላልኩም) ብቻ ያወራሉ። የቀረነውን ኢትዮጵያውያንን “እኛ!” እና “እነሱ!” በሚል ፈርጀውታል። “እኛ!” የሚሉት “ብቸኛ ተጠቂ!”፣ “እነሱ!” የሚሏቸው “አጥቂ!” የኦሮሞ “ምሁራን ነን” የሚሉትማ ኢትዮጵያ የሚል ቃል ራሱ የሚያንገሸግሻቸው ያስመስሉታል። ከኢትዮጵያ ውስጥ የሚጠሩት ቃል ቢኖር “አማራ!” የሚል ቃል ብቻ ይመስላል።

ዛሬ ደግሞ ይህንን First Peoples የሚል የPBS Utube ይኸው ለጥፊያለሁ። እባካችሁን እናድምጠው! አድምጡት! ይህኛው ክፍል 1 ስለ አፍሪቃ ብቻ የሚያወጋው ነው። ሌላ 4 ስለቀሩት አህጉራት የሚያወጋም አለ። እሱንም እናዳምጥ!

ዋናው ነገር፤ ለኔ ዋናው ነገር፣ ቆም ብለን “ነው እንዴ?!” እንድንል ነው። ዕይታችን ሰፋ እንዲል ነው! መንጽራችንን እንድንቀይር ነው! በተመዘገበ እውነት ላይ ተመስርተን እንድንወያይ ነው! “የጋራ ቤታችን!” ጉዳይ ስለሆነ የጋር ቤታችን በአክብሮት ጭምር እንድናይ ነው። “ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም!” እንዲሉ

PBS First Peoples 2 of 5 (Africa)

በማነንት ፖለቲክ ላይ አንበቡ እናንብብ ለማለት ነው።

* * * * * * * *

አሁን ስለቤተሰባችን ትንሽ:-

የካቲት 4, 2009፤ ድሬዳዋ ከተማ፤ ከዚህ ዓለም የተለየው የትልቁ ልጄ፤ ኤፍሬም አሰፋ፣ ልጅ ሊዲያና አብነት ገብረጊዮርጊስ ጋብቻቸውን ፈጽመዋል። እመቤት አስፋ፤ እህቴ ግምብነሽ ጫቦ፤ ባሌቤትዋ ባልቻ ሙሊሳ ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ከአዲስ አበባ ተጉዘዋል። ስለሠሰርጉ የሚነግሩኝን ማዳመጥ ”አንድ ሺህ አንድ ለሊት”ን The Arabian Night እንደማንበብ ነበር። የሊዲያ እናት፣ ተቀባሽ አንጣል፣ በስልክ ውስጥ ክንፍ አውጥታ የምትበር ነበር የመሰለችኝ። እመቤት “አሴ ብችል ድሬዳዋ መኖር እፈልጋለሁ!” አለች። “ምነው?” ስላት “ሰው ሁሉ እንደልጅ ግልጽና ፊት ለፊት ተናጋሪ ነው!” አለችኝ።

ቅድመ አያትነት በሬን እያንኳኳ ነው ማለት ነው።

ሌላው ከሎንዶን ካትሪን ጫቦ Catherine Chabo ደወለችልኝ። ተዲ ባለፈው ወር Sandhurst Military Acadamy ገብቷል ለማለት። ተዲ ማለት ቴዎድርስ እሸቱ ጫቦ ማለት ነው። ካቲ የቴድ እናት ነች።

ተዲ Sanhurst Military Acadamy የገባው ሁለተኛ ድግሪውን (Masters) ከተቀበለ በኋላ ነበር። “አንዱ አይበቃም ነበር ወይ?” ስለው፤ “ሁለተኛው ሲኖር ጀኔራል ለመሆን ያፋጥናል (accelerate) ብዬ ነው” አለ።

እንግዲህ በጥቂት ዓመታታ ውስጥ ቴዎድሮስ የሚባል የእንግሊዝ ጀነራል ሊኖር ነው። ለእንግሊዝም፤ በተለየ ለኛ ታሪካዊ የሚሆን መሰለኝ። መቅደላ አፋፉ ላይ አንድ ሐውልት ተከልን እንደማለት ይመስለኛል ነው። አሁን 150 ዓመት ሆነው አይደል?

የተሻለ ሳምንት ይጠብቀን!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ