Prof. Fikre Tolossa ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ• ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ የአንድ አባትና እናት ልጆች ነው
• አዳም የተፈጠረው ጎጃም፤ ኖህ መርከቡን ያሳረፈው አራራት ተራራ ላይ ነው
• ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አጥንቼ አለሁ ይላሉ …

ኑሮአቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ታዋቂው የሥነፅሁፍ ምሁር ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሣ፤ የፃፉት ”የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” የተሰኘ አዲስ አነጋጋሪ የታሪክ መጽሐፍ ዛሬ (ቅዳሜ ሐምሌ 16 ቀን 2008 ዓ.ም.) ለገበያ ይቀርባል። የኦሮሞና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ ማን እንደሆነ በጥናት ደርሼበታለሁ የሚሉት ፕሮፌሠሩ፤ እስከ ዛሬ የተለያዩ የታሪክ ምሁራን ከተናገሩት ፍፁም የተለየና አዲስ የጥናት ውጤት ማግኘታቸውን ይናገራሉ። የሁለቱ ቋንቋዎች አመጣጥም በጥናቱ ተካቷል ብለዋል።

በሊንከን ዩኒቨርሲቲ በሂዩማኒቲስ የትምህርት ዘርፍ የሚያስተምሩት ፍቅሬ ቶሎሳ፤ ከዚህ ቀደም ”Heaven to Eden” እና ”The Hidden and untold History of the Jewish People and Ethiopians” የሚሉ መጽሐፍትን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያሳተሙ ሲሆን፣ ሁለቱም በኢንተርኔት “አማዞን” በተባለ የመጽሐፍ ሽያጭ ድረገፅ ላይ ከተፈላጊ መጻሕፍት ተርታ ተሰልፈዋል። በሙያቸው ፀሃፌ-ተውኔትና የሥነ ፅሁፍ ምሁር ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥልቅ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግም ይታወቃሉ። አንጋፋው ምሁር ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም በቅርቡ ለንባብ ባበቁት “አዳፍኔ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ፤ “የኦሮሞን ታሪክ ሙሉ አድርጎ ሊጽፍ የሚችለው ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ብቻ ነው” ሲሉ ለብቃታቸው ምስክርነትና ዕውቅና መስጠታቸው አይዘነጋም።

ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በርካታ ቲያትሮችን ለደረክ ያበቁ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል “ጓደኛሞቹ”፣ “ፍቅር በአሜሪካ” እና ሌሎችም ይገኙበታል። በቅርቡም ”ላሟ” የተሰኘ ባለ ሁለት ገቢር ቲያትር ጽፈው ማጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል። ፕሮፌሠሩ ለአጭር ጊዜ ዕረፍት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበረ ሲሆን፣ ወደ አሜሪካ ከመመለሳቸው በፊት ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በታሪክ ጥናቶቻቸው ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

አዲስ አድማስ፡- በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያሳተሟቸው “Heaven to Eden” እና “The Hidden and untold History of the Jewish People and Ethiopians” የሚሉት መጻሕፍት በዓለማቀፍ ደረጃ ሰፊ ተቀባይነት ያገኙበት ሚስጥር ምንድነው? በምን ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነው የሚያተኩሩት?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- የመጻሕፍቱ ይዘት ነው ወሳኙ። ተቀባይነት ያገኙት በቋንቋ አጠቃቀም ለአንባቢያን ምቹ ስለሆኑ ይመስለኛል።

አዲስ አድማስ፡- በአይሁዶች ታሪክ ላይ የሚያተኩረው መጽሐፍ፤ በጉዳዩ ላይ ከተጻፉ ሌሎች መጻሕፍትና በተለምዶ ስለ አይሁዶች ከሚታወቀው ምን የተለየ ነገር ይዟል?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- ብዙ ጊዜ ስለ አይሁዳውያን ሲወራ፣ ቀዳማዊ ምኒልክ የዛሬ 3 ሺህ ዓመት፣ 40 ሺህ አይሁዳውያንን ይዞ መጣ የሚለውን ነው የምናውቀው። ከመጡት መካከል 12 ሺህ ያህሉ ንፁህ እስራኤላውያን ናቸው። 28 ሺህ ያህሉ እነሱን በሥራ ያገለግሉ የነበሩ ኢያቡሳውያን የሚባሉ ነገዶች ናቸው። ቀዳማዊ ምኒልክ ለ12 ሺህዎቹ ልዩ ቦታ ሰጥቷቸው፣ በሀገሪቷ ላይ ካህናት አድርጎ ታቦት እያስቀረፀ፣ ኢትዮጵያ ላይ በዚህ መልክ ሾሟቸው ነበር። ኢያቡሳውያን ደግሞ ንጉሡን በእጅ ሥራና በውትድርና ያገለግሉት ነበር። ይሄ እንግዲህ አይሁዳውያን ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ሁለተኛው ፍልሰት ነው።

የመጀመሪያውና ብዙም የማይነገረው የአይሁዳውያን ፍልሰት፣ የእስራኤላውያኑ መሪ ሙሴ በሕይወት እያለ አባ ብሔር የሚባል ልዑል ነበር። የሙሴ አማች ነው። አባ ብሔር የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሊሆን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፣ አይሁዳውያን ተከትለውት መጥተው ነበር። ምክንያቱም አባ ብሔር ያገባት ልጅ የሙሴ እህት ነበረች። ሙሴ በወቅቱ ለአባ ብሔር ፅላት ቀርፆ፣ እንዲሁም ቀይ ባህርን የከፈለባትን በትር ሰጥቶት፣ ወደ ሳባ ከተማ መጥቶ ነግሷል። በወቅቱ ብዙ አይሁዳውያንም ተከትለውት መጥተው ነበር።

ሦስተኛው ፍልሰት የምንለው፣ የኢራቁ ናቡከደነፆር አሸንፏቸው በሚያሳድዳቸው ጊዜ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ አይሁዳውያን ወገኖች አሉን” ብለው ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። አይሁዳውያን በነዚህ መንገዶች ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት።

አዲስ አድማስ፡- ትክክለኛዎቹ አይሁዳውያን በኢትዮጵያ ያሉት ናቸው የሚሉ ወገኖች አሉ …?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- የኃይማኖታቸውን ሥርዓት፣ መጻሕፍትና ሕግጋት ከመጠበቃቸው አንፃር ከሌላ ህዝብ ጋር ስላልተደባለቁ ትክክለኛው ያለው እነሱ ጋ ነው። ሌሎቹ ወደ አውሮፓ፣ እስያ፣ አሜሪካ የተሰደዱት እነዚህን ነገሮች በተለያዩ ጫናዎች የተነሳ ሙሉ ለሙሉ ጠብቀው አላቆዩትም። ወደዚህ የመጡት ግን በግድ ባህላችሁን ኃይማኖታችሁን ለውጡ ተብለው በኢትዮጵያውያን አልተረበሹም፤ ነፃነት ነበራቸው። መሬትና ሁሉ ነገር የተመቻቸላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነበር። ሌላ ሀገር ላይ ቦታ እንዳይኖራቸው ተደርገው በየጊዜው ይሰደዱ ነበር። እንደውም በሩሲያ ውስጥ በድንገት አይሁዳውያንን የመግደል ድርጊት ይፈፀም ነበር። ሩሲያውያኑ ተሰባስበው፤ “ዛሬ አይሁዳውያንን ገድለን እንምጣ” እያሉ ይዘምቱባቸው ነበር። ወደ መንደራቸው ሄደው አውድመዋቸው ይመለሳሉ። ማንም ስለማይበቀልላቸው ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ ነበር የሚቀረው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከተሰጣቸው ክብር የተነሳ በትንንሽ ንጉሥነት ጭምር ይሾሙ ነበር። በርካቶቹም ካህናትና ሊቀ-ካህናት ተደርገው ለአይሁድ እምነት ተሹመል። ቀጥሎ ደግሞ የሰለሞን ዘር ነን በሚሉት ውስጥም ገብተው፣ ስርወ መንግሥት እስከ መመስረት የደረሱ ነበሩ። በዓለም ላይ አይሁዳውያን ደልቷቸው የኖሩት ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ነው። በጠቅላላው በኢትዮጵያ ሀገራት ማለትም፡- በግብፅ፣ የመን፣ ኑቢያ - ኢትዮጵያ ባስተዳደረቻቸው አካባቢዎች በሙሉ በክብር ተይዘው ነው የኖሩት። ትልቁ ማስረጃ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ፣ እናቱ ማርያምና ቅዱስ ዮሴፍ በስደቱ ዘመኑ እኛ ጋ ብቻ ነው ጥገኝነት ያገኙት። በወቅቱ ግብፅ ለሁለት ተከፍሎ ነበር። አንዱ ክፍል በሮማውያን ቁጥጥር ስር ነበር። ሁለተኛው የኢትዮጵያ ክፍል ነው። ኢየሱስ ከመወለዱ ከ880 ዓመት በፊት አማራዎች፤ አማሩላ ደልታ ወደሚባል ቦታ ሄደው፣ አክሱማይት የተባለውን ህፃን ልጅ ዙፋን በመጠበቅ ያገለግሉ ነበር። በኋላ በ800 ዓመታት ውስጥ አማሩላ ደልታ የሚባል መንደር መስርተው ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ጋርና ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር ሲሸሹ፣ እዚያ ነው ማረፊያ ያገኙት። ይሄ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም፤ እኛ ግን ከተለያዩ መዛግብት እናገኘዋለን። በወቅቱ የአካባቢው ንጉሥ አማናቱ ተትናይ ይባላሉ። ከጎጃም ከጣና አካባቢ ነው ወደዚያ የሄደው። ሌላው አይሁዳውያኑ መጽሐፍ ቅዱሳቸው ሲጠፋባቸው ከኛ ነው የወሰዱት። አፄ ደንቀዝ የተባለው ንጉሠ ነገሥት ነው ከግዕዝ ወደ እብራይስጥ አስተርጉሞ የሰጣቸው።

"የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ" ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ

አዲስ አድማስ፡- ትክክለኛውን የአይሁድ ባህልና እምነት በመጠበቅ በኢትዮጵያ ያሉት አይሁዳውያን ብቸኞቹ ናቸው ማለት ይቻላል?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- አዎ! ኦሪትን ይዘዋል። ግን በደማቸው ከኛ ተደባልቀዋል። በዚህ ምክንያት ነው ሐበሻ የተባሉት። ሐበሻ ማለት የተደባለቀ ነው። “አበሳ” ያለበት ወይም እንከን ያለበት ማለት ነው፤ ሐበሻ ማለት። በቀዳማዊ ምኒልክ ጊዜ የመጡት ከኛ ጋር ተደባልቀው 560 ዓመት ከቆዩ በኋላ በባቢሎን ስደት ጊዜ ሦስተኛዎቹ ሲመጡ፣ ነባሮችን ሲያዩአቸው በመልካቸው አይሁዳውያንን አልመስል አሏቸው። ስለዚህ፤ “እናንተማ ክልስ ናችሁ፤ አበሳ አለባችሁ” ብለው ይሰድቧቸዋል። ነባሮቹ አይሁዶች ደግሞ፤ “እናንተ ፈላሾች፤ እኛ ሀገር አለን” እያሉ ይሰድቧቸው ነበር። በዚህም “አበሻ” እና “ፈላሻ” የሚለው መጠሪያቸው ሆነ። “ሐበሻ” የሚለው ቃል እኛን አይወክለንም የምለው ለዚህ ነው፤ ሐበሻ አይሁዳውያኑን ነው የሚወክለው። እኛ የኢትዮጵያ ልጆች ነን፤ ኢትዮጵያውያን ነን።

አዲስ አድማስ፡- “በሐበሻነቴ እኮራለሁ” ስንል የከረምነውስ - ቀለጠ ማለት ነው?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- አዎ! እኔ ኢትዮጵያዊ እንጂ ሐበሻ አይደለሁም። ሐበሻ የሚለው ቃል የስድብ ቃል ነው። እኛን አይወክለንም። አይሁዳዊ ካልሆነ በስተቀር አንድ ሰው ራሱን “ሐበሻ ነኝ” ብሎ ሊጠራ አይገባውም። ስድብ አያኮራም። ብዙ ሰው ስለማያውቅ ነው በሐበሻነቴ እኮራለሁ የሚለው። በዐረብኛም ብናየው “የተደባለቀ”፤ “ንፁህ ያልሆነ” ማለት ነው። ይሄ መልካም ቃል አይደለም። ግን ሐበሻ የሚለው “አበሳ” ከሚለው እንጂ ከዐረብኛ የመጣ አይደለም። ሁለቱ አይሁዳውያን መሃል ያለ የመሰዳደቢያ ቃል ነው እንጂ፤ እኛ ኢትዮጵያውያንን አይመለከተንም።

አዲስ አድማስ፡- ”ኢትዮጵያ” የሚለውስ ከየት የመጣ ነው?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- ኢትዮጵያ የሚለው ”ኢትዮጵ” ከተባለው ሰው የመጣ ነው። ኢትዮጵ ማን ነው ካልን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው መልከፀዴቅ የሚባል የሳሌም ንጉሠ ነገሥትና ሊቀካህን ነበር። ይህ ሰው ሀገር ያስተዳድራልም፤ ኃይማኖትም ይመራል። እሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነበር። ይሄ እንዴት ይሆናል ከተባለ፣ ኢየሱስ በምፅአት ቀን ሲመጣ፣ የንጉሥ ንጉሥ፣ የካህን ካህን ሆኖ ነው፤ መልከፀዴቅም የዚህ ምሳሌ ነው። ኢትዮጵያን ከዚሁ ጋር ምን ያገናኛታል ሊባል ይችላል። በጣም የሚያኮራ ግንኙነት አለው። የመልከፀድቅ ልጅ ኢትኤል ይባል ነበር። እግዚአብሔር ኢትኤልን ካለህበት የሳሌም ምድር ለቀህ ጣና ላይ ስፈር አለው። ”ከዚያም ያንተ የልጅ ልጆች፣ እኔ ከ2000 ዓመታት በኋላ በምወለድበት ጊዜ በኢትዮጵያ ግዛት ላይ ስለ መወለዴ ኮከብ አሳይሃለሁ” ይለዋል (እንደኔ ምርምር፤ ይሄ ኮከብ የተባለው መልአኩ ገብርኤል ነው) በዚህ ሁኔታ ኢትኤል አሁን ወዳለችው ኢትዮጵያ ሲደርስ እግዚአብሔር፤ ”ኢትዮጵ” ተብለህ ተጠራ አለው። ”ኢት” - ስጦታ ማለት ነው። ”ዮጵ” - ማለት ደግሞ ቢጫ ወርቅ ነው። ስለዚህ “ቢጫ ወርቅ ስጦታ” ተባለ። በኋላ ሀገሪቷን ኢትዮጵያ አሠኛት።

አዲስ አድማስ፡- በመጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ተብሎ የሚጠቀሰው ስም የትኛዋን ኢትዮጵያ ነው የሚወክለው?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- እሱ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን ነው የሚወክለው። ግን ኢትዮጵያ የሚለው መጠሪያ እስከ 13ኛው ክ/ዘመን ድረስ ለመላዋ አፍሪካ መጠሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። በኋላም የመጣው አፍሪካ የሚለው ስም ከዚሁ ከኢትዮጵያ የተገኘ ነው። ከአፋሮች ነው አፍሪካ መጠሪያዋን ያገኘችው። በመጽሐፈ እዝራ ምዕራፍ ስድስት ላይ፤ ”አፍሪካንሳውያን” ይላል። ይሄ አፋሮችን ነው የሚወክለው። በመርከብ ሥራ በቀይ ባህር ላይ የተራቀቁ ሰዎች ነበሩ። የዛሬ 3 ሺህ ዓመት ንጉሥ ሰለሞን ቤተመቅደሱን ሲሠራ፤ ልዩ እንጨት፣ እጣን፣ ወርቅ (ኦፊር የተባለ ታዋቂ ወርቅ - በነሱ የተሰየመ) ጭምር ይነግዱና ለንጉሡ ያቀርቡ ስለነበር፣ ስማቸው የገነነ ሆኖ አፍሪካንሳውያን የተባሉት። በሳይንሱም አፋር የሰው ዘር መገኛ እያልን ነው። ኢስያውያንም ስያሜያቸውን ያገኙት ከሣባ ቀድሞ ከነገሰው ”ኢስአኤል” ከተባለው ንጉሥ ነው። ምድሪቱን ያስተዳድር ስለነበር ኢስያ ተባለች። ”አፄ” የሚለውም ከዚህ የመጣ ነው።

አዲስ አድማስ፡- ኢትዮጵያ የሚለው ከግሪክ ቃል የመጣ ነው የሚለውስ ...?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- ኢትዮጵያ የሚለው ከግሪክ ቃል የመጣ ነው የሚለው ውሸት ነው። ይሄን አጣርቻለሁ። በነሱ መዝገበ ቃላት ውስጥ ይሄ ቃል የለም። ”ፊቱ የተቃጠለ” የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ ኢትዮጵያ የሚለውን ሳይሆን ሌላ ትርጉም ነው የሚኖረው። ግሪኮቹ ከኛው ሰምተው ነው መልሠው ኢትዮጵያ ያሉን። እኛ ከነሱ በፊት ነበርን እንጂ፤ እነሱ ከኛ በፊት አልነበሩም፤ ስማችንን ሊያወጡልን አይችሉም።

አዲስ አድማስ፡- በምርምርዎ አዳምና ሄዋን የተፈጠሩበት ቦታ የት ሆኖ አገኙት?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ጎጃም፤ ዳሞትና ጣና አካባቢ ያለ ቦታ ነው።

አዲስ አድማስ፡- ለዚህ ድምዳሜ ማስረጃዎ ምንድን ነው?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- አንደኛ ኤደንን ከሚያጠጡ አራት ወንዞች ውስጥ አባይ የምንለው ነው ኤፌሶን የሚባለው። በኦፌር ወርቅ ዙሪያ የሚዞር መሆኑ ተፅፏል። በኔ ድምዳሜ፣ የኤፌሶን ወንዝ የአሁኑ ዋቢ ሸበሌ ነው። ጤግሮስና ኤፈራጥስ ደግሞ ጊዮን ራሱ ጥንት ሜዲትራኒያን ባህር ይገባ ነበር። ድሮ ሜድትራኒያን “ኪቲ” ይባል ነበር። ጥንት ጊዮን ወንዝ ሜድትራኒያን ሲደርስ ተራራ ስለነበር ተጋጭቶ ይመለስ ነበር። ከዚያ ነው መሬት ተነቃንቆ፣ ቦታው ተቆራርጦ አሁን ወዳለበት ኢራቅ የሄደው እንጂ አካባቢው እዚሁ ነበር።

አዳም የት ተፈጠረ ለሚለው በመጽሐፈ ሄኖክ ላይ “ኤልዳ” በሚባል ቦታ ተፈጠረ ይላል። ኤልዳ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለው። ምክንያቱም አስሌዳውያን ወይም ኤልዳውያን የሚባሉ አሁንም ድረስ ጎጃም ውስጥ አሉ። ሄኖክ በመጽሐፉ ኤልዳ ነው የተፈጠረው ይላል። ከዚያ ወስዶ ነው እግዚአብሔር በ40 ቀኑ ወደ ኤደን ገነት የከተተው ይላል። ሄዋንን ደግሞ ከአዳም ጎን አውጥቷት ነው በ80 ቀኗ ወደ ኤደን ገነት የከተታት። ከዚህ ተነስቶ ነው ወንድ በ40፣ ሴት በ80 ቀን ክርስትና የሚነሱት። ይሄ አይነቱ ሥርዓት በዓለም ላይ የትም የለም፤ እና ይሄ በሄኖክ መጽሐፍ የተፃፈውና አሁን ያለው እውነታ ይገኛል።

ሌላው ኮሬብ የሚባል ዋሻ ውስጥ አዳም ተቀበረ ይላል። በእርግጥ በሲናይ በረሃ አካባቢ ኮሬብ የሚባል ቦታ አለ፤ ግን በተመሳሳይ ይህ ቦታ ኢትዮጵያ ውስጥም አለ። ሌላው ኖህ መርከቡን ያሳረፈው አራራት ተራራ ላይ ነው ይላል። አራራት ተራራን ለመፈለግ ወደ ቦታው ሄጄ ነበር፤ በታንኳ ጣናን አቋርጬ። አራራት ተራራ የሚባለውን ሳገኘውና አቀማመጡን ሳጠናው፣ ለመርከብ ማሳረፊያነት በአናቱ ላይ ምቹ ሜዳ አለው። ኖህ ወይን ጠጅ ጠጥቶ ሰክሮ ነበር ይላል፤ መጽሐፍ ቅዱስ። በእርግጥም ቦታው የወይን ጠጅ ፍሬ ለማብቀል ተስማሚ ነው። አሁንም አትክልቶችና ጌሾ ይበቅልበታል። ከዚሁ ማስረጃ ሳልወጣ፣ አዲስ ዓመትን አበቦች አብበው አከበረ፤ የእንጨት መስዋዕትም አደረገ ይላል። ይሄ እንግዲህ ዛሬ በመላ ኢትዮጵያ ያለው የአዲስ ዓመት መቀበያ ሥርዓት፣ ከየት መጣነትን ሊያስረዳ ይችላል። በኋላ ወደ ክርስትናው የመስቀል በዓል ደመራነት ተለወጠ እንጂ በፊት ደመራ የሚነደው በአዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ ነው። ለዚህ ማስረጃው አሁንም ድረስ ክርስቲያን ያልሆኑ የሀገራችን ሰዎች የደመራ ሥርዓት አላቸው። ይሄ የአባታቸው የኖህ ትዝታ (ማስታወሻ) ነው፤ ሲወረስ ሲዋረስ የመጣው። በዚህና በኖህ ጉዳይ ሰፊ ጥናት እያደረግሁ ነው፤ ወደፊት ይፋ ይሆናል። አንድ እዚህ ላይ ልጠቅሰው የምፈልገው፣ ሌላ አራራት የሚባል ተራራ አርመን ውስጥ አለ። ተራራው ግን በረዶ ያለበት፣ ገደላገደል፣ እንኳን መርከብ ሊያሳርፍ ለሰው ልጅ የማይመችና የማያብብ ቦታ ነው፤ ስለዚህ ያ ሊሆን አይችልም።

አዲስ አድማስ፡- በሰንደቅ አላማው ላይም የተለየ መከራከሪያ ያቀርባሉ። ለኢትዮጵያ የተሰጠ ስጦታ ነው ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- ሰንደቅ አላማው ለኖህ ከተሰጠው ምልክት የመጣ ነው። አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የጎሉበት ቀለማት ሰማይ ላይ ታይተዋል። እነዚያ ቀለማት ናቸው ዛሬ ያሉት። ከንግሥት ሳባ በፊት የነገሰው አፄ ኢሲአኤል ነው ሰንደቅ አላማ እንዲውለበለብ ያደረገው። ሰንደቅ አላማ የሚለው የመጣው የኢስአኤል መንግሥት “ሰንደቅ አለማ” ከሚለው ነው። ከዚያ የመጣ ነው። እሱ በወቅቱ የመረጠው፡- አረንጓዴ ቢጫ፣ ቀይና ሰማያዊ ቀለማት ነበር። ለሰንደቅ አላማው ያልተገዛና ያላውለበለበ ይቀጣል ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ አስገዳጅ ሕግ ያወጣውም እሱ ነበር። በሰንደቋ አናት ላይ ኮከብ ነበር የሚቀመጠው። ኢየሱስ ሲወለድ የሚጠቁመውን ኮከብ ለማስታወስ ይጠቀም ነበር። በዓለም ላይ ሰንደቅ አላማን የፈለሰፈ የመጀመሪያው ሰውም ሊሆን ይችላል።

የኢትዮጵያ የልጅ ልጅ የሆነው ኢስአኤል ከፈለሰፈው ሰንደቅ አላማ ነው፣ ዛሬ ያሉት የሰንደቅ አላማ ቀለማት የመጡት። ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሰንደቅ አላማው ላይ ከዚህ ተነስቶ አንድ አይነት አቋም ቢይዝ መልካም ነው። ኢስአኤል ለኦሮሞውም፣ ለአማራውም፣ ለትግሬውም፣ ለአፋሩም ለሌላውም ብሔረሰብ ሁሉ አባት ነው። ከአባቶቻችን የወረደ ሰንደቅ አላማ እንጂ ከባዕድ የመጣ አይደለም።

ሰውየው እጅግ ጠቢብ ነበር፤ ልዕለ ሰብዕ (superman) ነበር። 150 አንበሳ መግደሉን ለማስታወስ ጭምር አፄ ኢስአኤል የሰብዕ እና የአውሬዎች ንጉሠ ነገሥት ብሎ ነበር ራሱን የሚጠራው። ሰውየው እጅግ ጠቢብ ከመሆኑ የተነሳ የጀነቲክ ኢንጅነሪንግን የፈለሰፈውም እሱ ነው። እንስሳን ከእንስሳ፣ ዘርን ከዘር እየቀላቀለ የፈለሰፈ የመጀመሪያው የጀነቲክ ኢንጅነር ነበር። በቅሎን የፈጠረውም እሱ ነው። አህያንና ፈረስን አዳቅሎ። ይህ ሰው የሁሉም ኢትዮጵያውን አባት ነው። የኢትዮጵ ልጅ ነው። የኢትዮጵ 10 ወንዶች ልጆች ናቸው፤ አሁን የምናያቸውን የኢትዮጵያውያን ጎሣዎች ሁሉ የፈጠሩት።

አዲስ አድማስ፡- ሰሞኑን ለአንባቢያን የሚቀርብ መጽሐፍ እንዳዘጋጁም ሰምቼአለሁ። የመጽሐፉን ይዘት በአጭሩ ሊነግሩኝ ይችላሉ?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- መጽሐፉ፤ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” የሚል ነው። አሁን ያሉት ኢትዮጵያውያን በሞላ የኢትዮጵ ልጆች መሆናቸውን ከላይ አስረድቻለሁ።

አሁን እንደምናየው በሁላችንም ላይ የማንነት ቀውስ አለ። የማንነት ቀውሱ የመጣውም እኛ ማን እንደሆንን በትክክል ባለማወቃችን ነው። ስለዚህ ይህ መጽሐፍ እኛ ማን እንደሆንን፣ በርካታ ታሪካዊ ማስረጃዎችና ሰነዶችን አስደግፎ፣ ግልጥልጥ አድርጎ ያስረዳናል። ይህ የማንነት ቀውሳችን ከተስተካከለና ራሳችንን ካወቅን፣ በመካከላችን ግጭቶች ሊኖሩ አይችሉም። መጽሐፉ፤ ፍቅር፣ ሰላምና ህብር ሊፈጥር ይችላል የሚል እምነት አለኝ። እኛ የትልቅ ሰው ዘር ነን የሚለውን በማስረጃ የሚያሳየን ነው። የሰው ዘር ምንጭ ናሙናዎች መሆናችን ይተነትናል። ማንነታችንን በትክክል ተረድተን፣ አንድ ላይ ለመጓዝ ያስችለናል ብዬ አስባለሁ - ይህ ብዙ የተደከመበት የምርምር ውጤት።

አዲስ አድማስ፡- የኦሮሞና የአማራ የዘር ሀረግ አንድ ነው የሚለውን ነው መጽሐፉ የሚያስረዳው?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- አማራና ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ሁሉም በኢትዮጵያ ግዛት ያለው ብሔር፣ ጎሣ ከ10ሩ የኢትዮጵ ልጆች ነው የመጣው። ዝቅ ሲል ደግሞ የኢትዮጵ የልጅ ልጅ የሆነ፣ ጎጃም ላይ አዳምና ሄዋን ተፈጥረዋል ብዬ ባልኩት አካባቢ አንድ ጠቢብ ሰው ነበር። “ደሴት” ወይም “ደሸት” ይባላል። እሱ ነው የኦሮሞና የአማራ አባት። የዛሬ 3600 ዓመት 4 ወንዶች ልጆች ወለደ፡- መንዲ፣ መደባይ፣ ማጂ፣ ጅማ የሚባሉ። እነዚህ 4ቱም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሀገር መጠሪያ ሆነዋል። ማጂ ደግሞ ማራ እና ጀማን ይወልዳል። ዛሬ አማራ የምንለው ማራ ነው። “ማራ” ማለት “እውነተኛ ብርሃን” ማለት ነው። አማራ ያሉት አጋዚያን ወይም የግዕዝ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። ማጂ ማራን ወለደ ካልን፤ ጀማ እና ማራ ወንድማማቾ ናቸው። ሁለቱ ወንድማማቾች በአካባቢው ካሉት ጋፋቶች ጋር መዋጋት ሰልችቷቸው፣ ሀገር ለቀው ወደ ሸዋ ሲመጡ አንድ ወንዝ ያገኛሉ። ወንዙን ጀማ አሉት። አሁን የጀማ ወይም የ“ዠማ” ወንዝ ማለት ነው። ከአካባቢው እየራቁ ሲሄዱ የጥንት አባቶቻቸውን ቋንቋ “ሱባ”ን ትተው አማርኛን መፈልሰፍ ጀመሩ። መደባይ፣ ጅማና መንዲ ደግሞ ግማሾቹ ጎጃም ላይ ቀሩ፤ ግማሾቹ ወለጋ ሄዱ፤ ሌሎቹም እየራቁ በምስራቅ አፍሪካ ተሰራጩ። ኦሮሚኛ ቋንቋ የሚባለውንም ፈጠሩ። በዚህ ሁኔታ ነው ዛሬ ያሉት ኦሮሞና አማራ የመጡት። ዘረ ደሸት ይባላሉ። የደሸት ልጆች ናቸው። የዘር ሐረጋቸው አንድ ነው። ቋንቋቸው የተለያየ የሆነው በሂደት ነው።

አዲስ አድማስ፡- ኦሮሞው የኩሽቲክ፣ አማራው የሰሜቲክ ዘር ናቸው፤ የመጡትም ከውጭ ነው የሚለው ለዘመናት የዘለቀ ታሪክስ …?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- እሱ ፈፅሞ ውሸት ነው። ሁለቱም ከውጭ አልመጡም። እንዳስረዳሁት እዚሁ የበቀሉ ናቸው። የአማራም የኦሮሞም አባት ደሸትም ሆነ ታላቁ አባት ኢትዮጵ ኩሽ ነው። መልከፀዴቅም ኩሽ ነው። ኦሮሞና አማራ ሁለቱም ኩሽ ናቸው። አማራ ሴም አይደለም፤ ኩሽ ነው።

እስከ ዛሬ ሲነገር የነበረው ውሸት ነው። ምናልባት የአማርኛ ቋንቋ ከሌሎች ጋር ሲደበላለቅ ሴሜቲክ ቤተሰብ ውስጥ ተገኝቶ ሊሆን ይችላል። ሁሉም ኢትዮጵያውያን የኩሽ ዘሮች ናቸው። በዚሁ መጽሐፌ ላይ ስለ ቋንቋም አስረድቻለሁ። በዕብራይስጥም ሆነ በዐረቢክ የሌሉ እንደ ጨ፣ቀ፣ ፀ ያሉ ድምጾች በአማርኛና በኦሮሚኛ ቋንቋ ውስጥ አሉ። ይሄን በዝርዝር በመጽሐፉ አስቀምጫለሁ።

አዲስ አድማስ፡- ኦሮሞና አማራ አንድ ነው የሚለው አመለካከት በተለይ በኦሮሞ ምሁራን ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም። በግድ ኦሮሞን አማራ ለማድረግ ነው በሚል ወቀሳ የሚሰነዝሩ አሉ …

ፕ/ር ፍቅሬ፡- እንዲህ የሚሉት ሁሉም ከኢትዮጵ ዘር የመጣው የደሸት ልጆች መሆናቸውን ባለማወቃቸው ነው። ይሄ መረጃ ስለሌላቸው ራሳቸውን እንደ ባዕድ አግልለው ስለሚያዩ ነው እንጂ፤ አሁን ይሄ እኔ ያቀረብኩትን ማስረጃ በቅን ልቦና አገናዝበው ለመረዳት ከሞከሩ፣ የትልቁ ሰው የኢትዮጵ፣ የጠቢቡና የሊቀካህናቱ የደሸት ልጅ እንደሆኑ በሚያውቁ ጊዜ፣ እነሱ እንደተሳሳቱ ተገንዝበው ወደ ማንነታቸው ላይ አተኩረው ይኮሩበታል ብዬ አስባለሁ። የመጣነው ከትልቅ ዘር ነው። ኦሮሞውም አማራውም የመጣው ከዚህ ትልቅ ሰው ነው። በዚህ ሁላችንም ልንኮራ ይገባናል።

አዲስ አድማስ፡- የአሁኗ እና የቀድሞዋ ኢትዮጵያ ልዩነታቸውና አንድነታቸው ምንድን ነው?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- በግዛት ከሄድን ጥንት መላው አፍሪካ ኢትዮጵያ ነው የሚባለው። ከየመን አልፎ ሁሉ ይሄዳል። ግብፅ ውስጥ ፈርኦኖች የሚባሉት ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ኢትዮጵያውያን ከዓባይ ላይ ከመርከብ ወርደው ሜዳ አግኝተው የሰፈሩበት ቦታ ነው፤ ግብፅ። የአፍሪካ ሁሉ ነገር ከኛ አይወጣም።

አዲስ አድማስ፡- የኢትዮጵያ ታሪክ የ3 ሺህ ዘመን ነው ይባላል። እርሶ የደረሱበት የጥናት ውጤት ምን ይላል?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- አዎ፤ በተለምዶ 3 ሺህ ዓመት ይባላል እንጂ፤ ከ7ሺ በላይ ነው፤ የኢትዮጵያ ታሪክ። ኖህ ኢትዮጵያ ላይ ነግሷል፤ ከዚያ ጀምሮ 7 ሺህ ዓመት ነው።

አዲስ አድማስ፡- እስካሁን በነገሩን ታሪክ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው በማስረጃነት የሚጠቅሱት። መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ የታሪክ ምንጭ ማድረግ ይቻላል?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ አይደለም። 42 ሰነዶችን አሁን በሚወጣው መጽሐፌ ላይ በግልፅ አስቀምጫለሁ። እነዚህ ሰነዶች በተለያዩ ሰዎች በጥንት ጊዜ የተፃፉ ናቸው። ኑቢያ ውስጥ ጀበል ኑባ በተባለ ቦታ ተቀብረው የቀሩ፣ በጥንት ፍርስራሽ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን (ከእስልምና በፊት የነበረ) ድንጋይ ሳጥን ውስጥ ተቀብረው የነበሩ የብራና ሰነዶች አግኝቻለሁ። በዚያ ላይም የተመሰረተ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ 42 ተጨማሪ የታሪክ ሰነዶችን ተጠቅሜያለሁ፤ ይሄን መጽሐፍ ሳዘጋጅ።

አዲስ አድማስ፡- ቀጣይዋ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት ይላሉ?

ፕ/ር ፍቅሬ፡- አሁን ማንነታችንን አውቀን፣ የማንነት ቀውሳችንን ፈትተን፣ ሁላችንም የኢትዮጵ ዘር፣ የአንድ አባትና እናት ልጆች ... መሆናችንን ተገንዝበን፤ በፍቅር፣ በሰላም፣ በመከባበር፣ በእኩልነት መኖር አለብን ብዬ አስባለሁ። ሁላችንንም ኢትዮጵ ያገናኘናል።

ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ