“መጽሐፉ ሠላምና ፍቅርን የሚሰብክ፤ ወደ አንድነት እንድንመጣ የሚረዳን ነው” ፀሐፊና ጋዜጠኛ ገነት አየለ

“መጽሐፉ ባለፉት 25 ዓመታት አማራና ኦሮሞን ለማራራቅ ሲጥሩ የነበሩ ፀረ-አንድነት ኃይሎችን አንገት ያስደፋ ነው” አስተያየት ሰጭዎች

Prof. Fikre Tolossa signing his new book in Dire Dawa, 11th Aug. 2016.

Ethiopia Zare (ሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. August 22, 2016):- በቅርቡ ”የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” በሚል ርዕስ አዲስ መጽሐፍ ያሳተሙት ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፤ በድሬዳዋ ከተማ ትናንት እሁድ ነኀሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በኤምኤ ሆቴል ከአካባቢው ነዋሪዎችና ታዋቂ ሰዎች ጋር የመጽሐፍ ንባብ፣ ውይይት እና የፊርማ ሥነሥርዓት አካሄዱ።

በዚህ ዝግጅት ላይ በርካታ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፣ የፕ/ር ፍቅሬ የትምህርት ቤት አብሮ አደጎችን ጨምሮ ጋዜጠኞች፣ ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ተሳታፊ ሆነው በመጽሐፉ ላይ ውይይት አካሂደዋል። ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ተወልደው ያደጉት በድሬዳዋ ከተማ ሲሆን፣ በዚህ ዝግጅት ላይ ስለፕሮፌሠሩ እድገትና አመለካከት ትውስታቸውን ለተሳታፊዎቹ ካካፈሉት ውስጥ ወንድማማቾቹ አቶ መሐመድ አብዱላሂ እና አቶ ቶፊቅ አብዱላሂ ይገኙበታል።

ፕ/ር ፍቅሬ ስለመጽሐፋቸው ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ከህዝብ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል። ስለድሬዳዋ እና ሐረር ከተሞች ሲያብራሩም፣ በእነዚህ ከተሞች የተለያዩ የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ተቻችለው በፍቅር የሚኖሩባቸው ከመሆናቸውም በላይ ብዙዎቹ ነዋሪዎች አምስትና ስድስት ቋንቋዎች የሚናገሩ እንደሆኑ ገልጠዋል። በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ተማሪዎች በሚያደርጉት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ፖሊስ ሲፈልጋቸው፤ ኡማ አሻ (የወንድማማቾቹ የአቶ መሐመድ እና ቶፊቅ አብዱላሂ እናት) ቤት ይደበቁ እንደነበርና፤ ኡማ አሻን እንደእናታቸው ያዩዋቸው እንደነበር ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የልጅነት ትውስታቸውን አካፍለዋል።

ኢትዮጵያ ዛሬ በዚህ ዝግጅት ላይ ከተገኙት መካከል የመጽሐፉ ይዘት ምን እንደሚመስል ጥያቄ ካቀረበላቸው ሰዎች ውስጥ ፀሐፊና ጋዜጠኛ ወ/ሮ ገነት አየለ የሚገኙበት ሲሆን፣ ፀሐፊዋ “የኦሮሞና የአማራ ብቻ ሳይሆን፣ ጠቅላላ የኢትዮጵያ የዘር ምንጭ ከአንድ ግንድ (ኢትዮጵ) መሆናቸውን፤ የኢትዮጵ የልጅ ልጅ የሆነው ደሸት ደግሞ የኦሮሞና የአማራ አባት መሆኑን መጽሐፉ ይገልጻል። ከዚህም በተጨማሪ ሠላምና ፍቅርን የሚሰብክ፤ ወደ አንድነት እንድንመጣ የሚረዳን ነው” በማለት ጠቅለል በማድረግ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።

ከድሬዳዋው ምረቃ በፊት፣ ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በወመዘክር በተካሄደው የዚሁ መጽሐፍ የፊርማ ሥነሥርዓት ከተገኙት ተሰብሳቢዎች ውስጥ አንድ ግለሰብ፤ “እኛን የሚያስታርቀን ነው፣ እኔ አባቴ ኦሮሞ ነው፣ እናቴ አማራ ነች፤ ይሄ የሚያስታርቀን መጽሐፍ ነው።” በማለት አስተያየታቸውን ስለመጽሐፉ መስጠታቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

በበርካቶች ዘንድ መጽሐፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ተወዳጅነትን ያተረፈ ሲሆን፤ ብዙዎች በመጽሐፉ ላያ ያላቸው አስተያየት፤ “የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲስ የጻፈ ነው፤ በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት ሁለቱን ብሔረሰቦች (አማራና ኦሮሞን) ለማራራቅ ሲጥሩ የነበሩ ፀረ-አንድነት ኃይሎችን አንገት ያስደፋ፤ ሠላምን፣ ፍቅርን፣ መተባበርን፣ እኩልነትንና አንድነትን የሚሰብክ፤ ...” የሚል ሲሆን፤ ብዙዎች በወቅታዊነቱ ላይ በደማቁ ማስመራቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ መጽሐፉን ካነበቡ የተለያዩ ወገኖች ያሰባሰበቻቸው አስተያየቶች ያመላክታሉ።

Prof. Fikre Tolossa signing his new book in Dire Dawa, 11th Aug. 2016. ፕ/ር ፍቅሬ መጽሐፋቸው ምን ያህል ተቀባይነት እንዳገኘ ከኢትዮጵያ ዛሬ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “ህዝቡ በከፍተኛ ደረጃ ነው የተቀበለው፤ ካሰብኩት በላይ ነው ተቀባይነትና ተወዳጅነት ያገኘው፤ ገና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች አልተዳረሰም። አንዳንድ አካባቢዎችም እንዲደርሳቸው ጥያቄ እያቀረቡ ነው ያሉት” በማለት መልሰዋል። ከአዲስ አበባ በተጨማሪ፤ በናዝሬት፣ በባህርዳር፣ በአምቦ፣ በሐረር እና በተለያዩ ከተሞች መጽሐፋቸው ተወዳጅነት ማግኘቱን ፕ/ር ፍቅሬ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጠዋል።

ከሁለቱ ከተሞች ሌላ የፊርማና የውይይት መድረክ እንደሚያዘጋጁ ፕ/ር ፍቅሬን ጠይቀናቸው፤ ቀጣዩ ናዝሬት ወይንም ደሴ እንደሚሆን አስረድተውናል። የድሬዳዋው ዝግጅት ተወልደው ያደጉበት ከተማ በመሆኑ፤ ከልጅነት እስከእውቀት የሚያውቋቸው ሰዎች ተገኝተው የተለያየ አስተያየት የሰጡበት ስለነበር ለየት ያለ አቀራረብ እንደነበረው ፕ/ሩ አልሸሸጉም።

ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ፀሐፊ-ተውኔት፣ ገጣሚ፣ ፀሐፊ እና የሥነጽሁፍ ምሁር ሲሆኑ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በሊንከን ዩኒቨርሲቲ በሂዩማኒቲስ የትምህርት ዘርፍ መምህር ናቸው፤ ነዋሪነታቸውም በሰሜን አሜሪካ ነው። ፕ/ሩ ከሚታወቁባቸው ሥራዎቻቸው ውስጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ከፍተኛና ጥልቅ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ሲሆን፣ በቅርቡ ካሳተሙዋቸው መጻሕፍት ውስጥ ”Heaven to Eden” እና ”The Hidden and untold History of the Jewish People and Ethiopians” የሚሉት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የጻፉዋቸው መጻሕፍት ተወዳጅነትን አትርፈውላቸዋል።

ፕ/ር ፍቅሬ ለመድረክ ካበቁዋቸው ቲያትሮች ውስጥ “መቃብር ቆፋሪው”፣ “ፍቅር በአሜሪካ” እና “ጓደኛሞቹ” የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ካሳተሙዋቸው የአማርኛ መጻሕፍት ውስጥ “ወለላ” የተሰኘው የልብወለድ መጽሐፍ እና “ይቺ ናት ሀገሬ” የተሰኘው የግጥም መጽሐፋቸው ይገኙበታል። በ2000 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 2008) “Multicolored Flowers” (የተቅለመለሙ አበቦች) የተሰኘው ፊልማቸውን ለህዝብ ዕይታ ማብቃታቸው አይዘነጋም።

መጽሐፉ ባለፈው ሐምሌ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ለገበያ የቀረበ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ክረምት ከታተሙ መጻሕፍት በከፍተኛ ሁኔታ በመሸጥ ላይ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያም ሆነ በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከታተሙ መጻሕፍት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሦስት ጊዜ በመታተምም ሆነ በቅጂ ብዛት ክብረወሰን ማስመዝገቡን የአሳታሚ ድርጅቱ (“ነባዳን” የሚዲያ ማማከር ኃ/የተ/የግል ማኅበር) ተወካይ አቶ ዳንኤል ተፈራ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ገልጠዋል። አቶ ዳንኤል እንደገለጡልን ከሆነ፤ አራተኛው ሕትመት በዚህ ሣምንት ማተሚያ ቤት ይገባል።

ነባዳን አሳታሚ፤ የፖለቲካና የታሪክ መጻሕፍትን በማሳተም ላይ ያተኮረ ድርጅት ሲሆን፣ መጻሕፍትን ከማሳተም በተጨማሪ የአርትዖት ሥራ እና የግራፊክስ ሥራዎችን የሚሠራ ድርጅት ነው። በቅርቡ የአቶ አሰፋ ጫቦን እና የፕ/ር አስራት ወልደየስን መጻሕፍትን አሳትሟል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!