“የስየ አብርሃ ሚስጥሮች” (ዘውገ ፋንታ)
የተስፋዬ ገብረአብ የመጽሐፍ-ሂሱ ሂስ
ዘውገ ፋንታ
መግቢያ
ደራሲው ተስፋዬ ገብረአብ፣ ስየ አብርሃ ስለጻፈው “ዝባዝንኬ” መጽሐፍ ባቀረበው “የመጽሐፍ ሂስ” ሌላ ሂስ መጻፍ ለማይቀርብ ምግብ እጅ ማስታጠብ ይሆናል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ተስፋዬ ገብረአብ ስለ ስየ መጽሐፍ ማሾፉን ለመቃወም ወይም ስየን ለመደገፍ አይደለም። ስየ ይህን ከጠበቀ በውጤቱ ሊበሳጭ ይችላል። ተስፋዬ ገብረአብም የስየ መጽሐፍ ውሸት የዋጠው ነው ያለውን ይህ ፀሐፊ ቢደግፍም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ሲገለጽ የሚያረካው አይሆንም።
ስየ የኢትዮጵያ ሕዝብ የማያውቀው ከባድ ምስጢር አለኝ የሚለው ጉዳይ ተስፋዬ ገብረአብን ቢከነክነውም፤ ይህ ፀሐፊ በዚህ ላይ የስየን አቋም ይቀበላል። ተስፋዬ ከስየ እጅግ ዝቅ ባለ ሥልጣን ላይ ስለነበር፣ ስየ በሚስጥር የሠራውንና የሚያውቀውን ሁሉ አውቃለሁ ማለቱን ይህ ፀሐፊ አይቀበልም። ተስፋዬ በስየ መጽሐፍ ላይ የሰጠውን አስቂኝ ትችት በተለይ ስለ ሰፈሩት የውሸት ቃሎቹ እና ስለዝባዝንኬነቱ መቀበል ይቻላል። ይህ ጽሑፍ ስለ ተስፋዬ ገብረአብ ከንቱ አስተሳሰብ እንጂ ስለ ስየ መጽሐፍ ቁምነገር ወይም ‘ዝባዝንኬ’ ላይ ያተኮረ አይደለም። (ተስፋዬ ገብረአብ ”የስየ ’ምስጢሮች’” በሚል ርዕስ በአቶ ስየ መጽሐፍ ላይ የፃፈውን ሂስ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)
የተስፋዬ ገብረአብ ሂስ
ከተስፋዬ የመጽሐፍ-ሂስ ብዙ ስህተቶች ተለቅመዋል። ለዚህ ሂስም የበቃው የጉድለቱ ብዛትና ጥብቀት ነው። ተስፋዬ ገብረአብ በዚህ አስተሳሰብ ሂሱን ይጀምራል፣ “ስየ አብርሃ የፃፈውን መጽሐፍ አነበብኩት። የተደጋገመውን ዝባዝንኬ እየዘለልኩ እንደምንም ጨረስኩት።” ይህ አባባል ደክሞ ያቀረበውን የመጽሐፍ-ሂስ እንዳለ ውድቅ ያደርገዋል። ሂስ የሰጠበትን መጽሐፍ ከዳር እስከዳር አላነበብኩትም ማለት ምንም መጽሐፉን ለማጣጣል የተሰነዘረ አስተሳሰብ ቢሆንም፣ እውነትነትና አስፈላጊ የጽሑፍ ሥነሥርዓት የጎደለው መሆኑን መረዳት ይቻላል። ተስፋዬ የስየን መጽሐፍ ለማቃለል ሲል የሰነዘረው እራሱን በይበልጥ ዝቅ አድርጓታል። የተስፋዬ የመጽሐፍ-ሂስ በዚህ አቋም ተጀምሮ የተደመደመ ይመስላል፣ ስለሆነም ስየ አብርሃ ስለመጽሐፉ የተሰጠው አቃቂር ይህን ሂስ ከተመለከተ ፈካ ሊል ይችል ይሆናል። ዳሩ ግን፣ ቀጥሎ የቀረበው ጽሑፍ የሱን “ዝባዝንኬ” መጽሐፍ ለመደገፍ ወይም ለማወደስ እንዳልሆን ሲረዳ ደስታው ቶሎ ያልቃል። በጠቅላላው የተስፋዬ ሂስ እንዲሁ በተራው በዚህ ሂስ ተጣጥሎ ሲገለጽ ሁሉም የቀልድ ጋጋታ ይሆናል።
የመጽሐፍ-ሂሱ ሂስ
ተስፋዬ ገብረአብ ስለ ስየ ከበድ ያለ አስተያየት አለው። በዚህም የሚገረም ሰው ላይኖር ይችላል። ተስፋዬ ገብረአብ አዙሮ ማየት የሚባለውን ነገር እንዳልቃኘው ጽሑፉ ያመለክታል። ይህን የሚያመለክቱ ከጽሑፉ ብዙ ዐረፍተ ነገሮች አሉ። በአንዱ መስመር እንዲህ ይላል፤ “ጥሩ አንባቢ ሆነህ ሳለም ታሪክህን የግድ ራስህ መፃፍ ላይኖርብህ ይችላል። ከፃፍክም ደግሞ ጥሩ አማካሪና ኣርታኢ መፈለግ ይገባ ይሆናል።” ተስፋዬ እንዲህ ብሎ የስየን ንግግር ከጠቀሰ በኋላ ዘወር ብሎ፣ “ቃል በቃል ባይሆንም ስየ ይህን ይለናል።” ብሎ ይደመድማል። ችግሩ፣ ስየን ጠቅሶ ካስቀመጠ በኋላ ቃል በቃል እንዳልሆነ መልሶ ማርዳቱ ወይም ማስረዳቱ ነው። ቀጥሎም፣ “ጥሩ አንባቢ ያልሆነ ሰው ለመፃፍ ባይሞክር ይመረጣል።” ይላል። ተስፋዬ ገብረአብ ጥሩ ፀሐፊ ነው። ግን የአጻጻፍ ሥርዓቱ ሲመጠን ብዙ ግድፈት በጽሑፉ ውስጥ ይታያል። አዙሮ ማየት ትልቁ ችግሩ ይመስላል። ይህን አጉልቶ የሚያሳየው አስተሳሰብ፣ “የሆነው ሆኖ የስየ አብርሃ መጽሐፍ ላይ ሂስ የማቅረብ ፍላጎት የለኝም። ጊዜም የለኝም። አንዳንድ ያስገረሙኝን ነጥቦች ብቻ በጨረፍታ ላነሳ ወደድኩ።” የሚለው ዕውነተኝነት ያነሰው አስተያየት ነው። በጽሑፉ ይህን አስተያየት ሲሰጥ፣ የጽሑፉ አርዕስት ግን ሙሉ የመጽሐፍ-ሂስ እንደሆነ የአንባቢ ልምዳዊ አስተሳሰብ ነው።
ተስፋዬ ወርቃማ ጊዜውን በከንቱ አባክኖ የአንባቢውን ጊዜ ማባከኑን ጠቅሷል። ይህ ቦታ የሌለው ቁንፅል አስተሳሰብ ነው። ይህን አባባል በመዘንጋት፣ “በገፅ 155 ላይ ታዲያ የራሱን አባባል እንዲህ ሲል ያፈርሰዋል።” በማለት ስየ ስለ አደረገው የሃሳብ መገለባበጥ ያመለክተናል። ተስፋዬ ገብረአብ አዙሮ የማየት ጣጣ እንዳለበት አድምቆ ያሳያል። ስለደጋገመውም የሰከነ ልምዱ ነው ብሎ ለማሰብ ያበቃል። ሌላ ማስረጃም ከጽሑፉ ጎልጉሎ ማውጣት ይቻላል። ደራሲ ተስፋዬ “እየነጠርኩ” አለፍኩት በማለት ከስየ መጽሐፍ ብዙ ያላነበበው ክፍል እንዳለ ካመለከተ በኋላ፣ ደራሲው ስየ በውሸት የጻፈውን ከየገጹ እየለቀመ አቅርቧል። ይህ ከሆነ፣ ተስፋዬ የስየን መጽሐፍ ከዳር እስከ ዳር አንብቧል ወይስ “እየነጠረ” የስህተቱን ገጽና ዐረፍተ ነገር ብቻ በአንድ ዘዴ እያገኘ ስለመጽሐፉ ሙሉ ሂስ አቅርቧል የሚያሰኘውን አስተሳሰብና ግምት ለአንባቢ መተው ተገቢ ይመስላል።
ተስፋዬ ገብረአብ ስለ ስየ ውሸት በማያጠያይቅ ሁኔታ በድርጊቶች አማካይነት እያመሳከረ አቅርቧል። ይህን ለማድረግ የስየ ውሸቶች እረድተውታል። ተጨልፎና ተጠልቆ የማያልቅ የውሸት ባህር የወያኔ አካል የሆነ ሁሉ የመዋኛ ባኅሪው ስለሆነ፤ ስየን ለሚያውቅ ኢትዮጵያዊ አዲስ ዜና አይሆንም። ተስፋዬ ጠለቅ ብሎ ከቻለ አዲስ ነገር ቢያፈልቅና የስዬን ድብቅብቅ ሚስጥር ቢያጋልጥ ኖሮ ስየ አብርሃ እንኳን በሀገር መሪነት መድረክ ቀርቶ በመንገድም ለመታየት የማይፈልግ ሰው ባደረገው ነበር። ዳሩ ግን፣ እንኳንስ ስየ ራሱ ተስፋዬ ገብረአብም ስለ ሚስጥር ጉዳይ መዘክዘክ ብዙ የቀራቸው እንጅ ያለቀባቸው አይመስሉም። በዚህ ላይ ተስፋዬ ሊያዘናጋን ሞክሯል።
ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ስለ ፖለቲካ ወይም ሌላ ዓላምው ዘመሜታ የሰጠው ምልክት አለ። ተስፋዬ፣ “በጦርነቱ የተቻላቸውን ሁሉ ሞክረዋል! ስላልተቻለም ተመልሰዋል! ሌላ ሰበብ ማብዛት ለምን አስፈለገ?” ካለ በኋላ፣ ቀጠል አድርጎ፣ “ውጊያውን በተመለከተ ወደፊት ይፋ የሚሆን ምንም እንቆቅልሽ የለም። ቢኖር እስካሁን እናውቀው ነበር። ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ስየ የማያውቀው ምንም መረጃ የለም።” ይለናል። ጉዳዩን ለመቋጨት፣ “ስየ በመጽሐፉ ይህን በግልፅ ከመናገር ይልቅ አንድ ትልቅ የሚያውቀው ሚስጥር ያለ ለማስመሰል ሞክሯል።” በማለት የሃሳብ ወይም የፖለቲካ አዝማሚያውን በዚህ ዐረፍተነገር ቁልጭ አድርጎ ያስቀመጠው ይመስላል። ስለ ጦርነቱ መጀመሪያና መደምደሚያው ምክንያት የምናውቀውን ሁሉ ተስፋዬ ከአዕምሮአችን በድፍረት ሊሰርዘው ሞክሯል። በዚህ ላይ ተስፋዬ ገብረአብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ልብና ጀርባ ሳይሆን አልቀረም። ተስፋዬ ገብረአብ በዚህ መጽሐፍ-ሂስ ያሳየው የአስተሳሰብ ድክመት፣ የምርምር ዕጥረትና የፖለቲካ አዝማሚያነት የተጋለጠበት እንደሆነ አንባቢ ሊገነዘብ ይችላል። ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የሀገር ሚስጥርን አስመልክቶ ደራሲው ስየ አብርሃ እንደሚለው “ብዙ ሚስጥር አለ ግን አንናገረውም” ቢል ኖሮ ምናልባት ተስፋዬ ገብረአብ “የምን ሚስጥር? መለስ ሚስጥር የሚለው። ውሸት ነው፤ የደበቀው ሚስጥር የለም።” ሊል እንደሚችል አዝማሚያውን አንባቢ እንዲገምት አድርጎል። ስየ አብርሃ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሆኑት አንዱ መሆኑንና ፈላጭ ቆራጭ እንደነበረ እራሱ ተስፋዬ ደጋግሞ ተናግሯል።
ታዲያ እንዴት ብሎ ተስፋዬ ስየ አብርሃ ሚስጥር እንደሌለው አድርጎ የሚነግረን? ተስፋዬ ስየ የሚያውቀውን አውቅ ነበር ወይም ለማወቅ እችል ነበር የሚል ከሆነ በስለላ ደረጃ እንጂ ከስብሰባ ጠረጴዛ ዙሪያ አብሮ ተቀምጦ እንዳልሆነ የተጻፈው ሁሉ ያስረዳል። ስየ ሚስጥር የሚያውቅ መሆኑ ተስፋዬን እጅግ የከነከነው ጉዳይ መሆኑ ጎልቶ ይታያል። “ይህን ሚስጥር፣ ይህን ስንክሳር፣ ይህን እንቆቅልሽ ወደፊት ታሪክ ያወጣዋል።” ሲል ፃፈ። ምንድነው ያ ሚስጥር?” በማለት ተስፋዬ ተገርሞ ጽፏል። ስየ ‘አትንኩን ከነካችሁን እናወጣዋለን’ የሚለው አባባል አለ። ደራሲው ተስፋዬ ግን፣ “ስየ አብርሃ ያልነገረን ምስጥር የት ይሆን ተፈልጎ የሚገኝ?” ሲል ተማሮ ጽፏል። ለተስፋዬ ሚስጥር እንዴትና የት ተፈልጎ እንደሚገኝ ለመግለጽ ስለማይቻል ‘ሚስጥር’ መባሉም ለዚህ ነው። አለበለዚያ ግን፣ ስየ እራሱን የሚያስጠፋ ወይም ሕዝብን ከቀውስ ላይ የሚጥልና ሀገርን የሚያናጋ መጥፎ ድርጊት በሚስጥር የያዘ መሆኑን ሲነግረን አለማመኑ ይከብዳል። የስየን የቀድሞ ሥልጣን ተረድቶ ማመኑ ይሻላል። ለተስፋዬ ከማመኑ አለማመኑ በልጦበታል። ዋናው ጉዳይ ግን ስየ በከፍተኛ አመራር ውስጥ የነበረ፣ ሁሉን ሚስጥራዊ ጉዳይ ሊያውቅና ከዚያም በላይ ምስጥራዊ ጉዳይ ሊፈጥርና ሊሠራ ይችል እንደነበር መገመት ለተስፋዬ ተስኖታል።
በስየ መሪነት ብዙ ዕቃዎችና መሣሪያዎች በሽሽግ በሌሊት ወደ ትግራይ እንደሚጓዙ ተስፋዬ ገብረአብ ከነማስረጃው ጭምር እያቀረበ ገልጿል። ዳሩ ግን እነ ስየ ይህን ዘረፋ የተማሩት ከሻዕቢያ እንደነበርና “ለከፈልነው ደም የሚገባን ድርሻችን ነው” የሚለውንም ፈሊጥ ከሻዕቢያ የተማሩት መሆኑ ዕውቅ ሲሆን፣ ተስፋዬ ወያኔንና ሻዕቢያን አጣምሮ ማየት የተሳነው ይመስላል። አንድ መንጋ ሆነው ሀገር የደመሰሱት አሁን እርስ በርሳቸው ሲካሰሱና ሲናቆሩ ማየቱ መጥፎ አይደለም። ገና በይበልጥ መፈነካከታቸው አይቀርም። ብዙ ሚስጥር ይወጣል፣ ተስፋዬ ገብረአብ እንደሚፈልገው አሁን ባይሆንም በኢትዮጵያ ሕጋዊ መንግሥትና አገዛዝ ሲቋቋም በተረጋጋና በሥነሥርዓት ብዙ የሚናዘዝ ይፈልቃል፣ ብዙ መጥፎ ታሪክም ይጻፋል።
መደምደምያ
ተስፋዬ ገብረአብ በርግጥ ባለው የመጻፍ ችሎታ የስየን መጽሐፍ እንደሚገባው ቀልዶበታል። ስየ አብርሃ መጽሐፉም እሱም ምንጊዜም ለዘለፋ ምቹ ናቸው። ተስፋዬ እንዳለው ስየ ፍትሕ ፈላጊ ተበዳይ ሰው አይደለም። ምሕረት ጠያቂ ሰው ግን ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብና ሀገር ላይ ስለፈጸመው ወንጀል ሲጠየቅ “ሂሳብ ልናወራርድ” አልመጣንም የሚለው ዘይቤ አለ። ዕውነቱን ነው ሂሳብ ማወራረጃ ወቅቱና ጊዜው አሁን አይደለም። ስየ መሪ ለመሆን መጣሩ ዘመኑ እጅግ የተበላሸ መሆኑን ያሳያል። ስየ ከመለስ ዜናዊ ያነሰ ኃጥያት ነው ያለኝ እና እሱ በዘውድ ላይ ከተቀመጠ እኔም ይገባኛል የሚል ይመስላል። አሁን ይህ አስተሳሰብ ትክክል ነው፣ ነገ ግን ዓለም ሲለወጥ ያሳፍራል። መለስ ነገ ይሂድ አዜብም ትንገስ ብርቱካንም ሌሎቹምይፈቱ! በኢትዮጵያ ምድር ይህ የዛሬው ጧት ተባራሪ ሃሳብ ይመስላል። እንዳፋቸው! ነገ ደግሞ ሌላ ጥሩ ሃሳብ ይወለዳል።
ተስፋዬ ገብረአብ ያቀረበውን የመጽሐፍ-ሂስ በፈገግታ እንድናነብለት ሞከሯል፣ በመጨረሻም ይህን ቀልድ ጨምሮ ስለደመደመ ተሳክቶለታል፣ “መለስ ጮማውን እንዴት ለመዳችሁት ሲባል ‘በመከራ!’” አለ አሉ ይለናል። መለስ አይልም አይባልም!
በዘውገ ፋንታ
መስከረም 2003
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.