ያቶ ስየ ስንክሳር ለኔ እንደተሰበቀኝ
ጌዲዎን በለጡ
የዛሬው ትኩረቴ መጥሐፉ በጥቅል ሃሳቡ ባስተላለፈልኝ ፍሬ ጉዳይ ላይ ብቻ ያነጣጠረ በመሆኑ እንዲያ ብቻ ይተርጎምልኝ፤ ባለ 439 ገጹ “ነፃነትና ዳኝነት” ስለያዘው ዝርዝር ጉዳይ የተገለጠልኝን ያህል ለማለት በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ለወጉ ይመቸኝ ዘንዴ አለፍ አለፍ ብዬ በመግቢያቸው በመጀመሪያውና በሁለተኛው አንቀጽ የተጠቀሰውን ላመል መነካካት አሻኝ፤ ...
እንዲህ ይላል “… የታሰርን ዕለት ማታውኑ ከጠ/ሚንስትሩ ጽ/ቤት የወጣው መግለጫ አሳሪያችን የፖለቲካ ባላጋራዬ ራሱ የህወሓት ሊቀመንበርና ጠ/ሚሩ አቶ መለስ ዜናዊ መሆኑን በእስሩ ላይ ዳኛም ይሁን የፀረ-ሙስና ኮሚሽን እጁን አለማስገባቱን ከራሱ ከመግለጫው ይዘት ግልጽ ሆኖአል ….” በማለት አስከትለው “… በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ … ለድራማ ትዕይንት እንዲመች ተዋንያንና መድረክ አዘጋጅቶ ሕያው የፍትህ ቲያትር … በመስራት በፍትህና በዳኝነት ሥርዓት ስም ማፌዝና ማበጨጭ ...” (የተሰመረበት ቃሉ የኔ) የተለመደ ነው ሲሉ ነግረውናል (ቃል በቃል አልቀሸርኩት እንደሆን ይቅርታ ይደረግልኝ)፤ ሊመሰገኑ ይገባል።
በጥቅሉ አቶ ስየ ራሳቸውን እማኝ አርገው ባቀረቡት በዚህ ጽሁፍ፦
1. በኢትዮጵያ ከፍርድ በፊት ፖለቲካዊ ውሳኔ የላቀና የሞቀ መሆኑን፣
2. ፖለቲካዊ ውሳኔ እንጅ የፍትህ ሥርዓት ቦታ የሌለው መሆኑን፣
3. ዳኝነትና የዳኝነት ሥርዓት የሚባሉት ተቀጥላዎች ቀለም የተቀባቡ “የፍትህ አለ” ድራማ አምሳያ ገጸ-ባህርያት እንጅ የሚያዝ-የሚዳሰስ እጅ-እግር የሌላቸው ማጨናበሪያ ቃላት ናቸው የሚሉ ግልጥ ያለ ጩኸት ነው እኔ የሰማሁት፤ ሀሰት የለውም እግዜር ይስጣቸው።
ያቶ ስየን ስንክሳር አንብቤ ስጨርስ ከነገሩ ሁሉ፤ ከሚያነጋግረው፤ ብስል-ተጥሬ ሃሳብ በሞላ ተጠቃሎ የመጣብኝና የተሰበቀኝ ባለ ብዙ ገቢሩ ድራማና የአተዋወኑ ስልት ነበር።
ልብ በሉ! “የከሳሽ-ተከሳሽ” ድራማ ከመፈብረኩ በፊት እነ አቶ ስየና የድራማውን “ልዩ የፍርድ ቤት ክፍል” በመጨመር አስተካክለው የጻፉት አቶ መለስ የመጀመሪያ ተፋላሚዎች ነበሩ።
በድንገት አቶ መለስ ግብረ አበሮቻቸውን ይዘው ከዋናው ፍልሚያ የሚወጡበትን ገቢር ጨመሩበትና ጨዋታውን “ዳኛ” ለሚባሉ ተፋላሚ አሳልፈው በመስጠት እሳቸው የሕጉና የጨዋታው ሥርዓት አስከባሪ ሆነው ቁጭ ሲሉ፤ አቶ ስየ በተከሳሽ ሳጥን ውስጥ ቆመው ተገኙ።
ይሄኔ ትዕይንቱ ተቀየረና ዋነኛው ተጋጣሚ “የጨዋታው ሥርዓት አስከባሪ” ሆነው ብቅ ሲሉ ፍልሚያው ዋናውን ጉዳይ እንዲያጨናብሩ በተደነቀሩ (ስቶፐርስ) እና ባላጋራዬን አታስመልጡኝ መንገዴን ልቀቁልኝ በሚሉት በእነ አቶ ስየ መሃከል ሆነ። አዲስ ድራማ!!
በተራ ቋንቋ - ስየና መለስ ተጣሉ፤ በግራ ቀኛቸው ያሉት የስየንና የመለስን እሰጥ አገባ እየሰሙ ሳለ በድንገት ጨዋታው ተቀየረና አቶ ስየና አቶ “ዳኛ” የተባሉ ፊት ለፊት ተፋጠጡ፤ አቶ መለስ እንደሁሉጊዜ ባህሪያቸው ሹልክ ብለው ወጥተዋል።
ስየ ዞር ብለው ሲመለሱ መለስ የለም፤ ከሆነ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ተቀምጠው ከስየ ጋር ምንም እንዳልተባባሉ ሁሉ የተቀየረው ጨዋታ ተመልካች ሆነዋል።
ስየ ቡጢውን ሊያሳርፍ እየተንደረደረ ሳለ ከፊቱ ከዚህ በፊት ያላየውና የማያውቀው ሰው በመለስ ቦታ እንደ ጅብራ ተገትሮአል፤ ...
አዲሱ “ዳኛ” መሳይ ዞምቢ (ምስለ-ሰው) አቶ ስየ ላይ ያፈጥና “… ሌባ! ሌባ! …” እያለ ያጣድፈዋል … “ምን ታመጣለህ? ጉዴ ሳይፈላብህ … ንብረቴን መልስ! ...” ይለዋል።
ለስየ ይሄ ያልተጠበቀ አዲስ ነገር ነበርና፣ “... መለስ የታለ!? ጠቤ ከሱ ነው! … አንተ ደግሞ ማነህ? ... ምን ጥልቅ አረገህ? ...” ለማለት ይዳዳዋል። እንደጅብራ የተገተረው “ምስለ-ሰው” ምላሽ ቢነፍገው መልስ ፍለጋ አሻቅቦ ሲመለከት፤ አቶ መለስ ካናቱ ላይ ሆኖ እንደ ሌላው ታዛቢና፤ የጨዋታ ሕግ አስከባሪ ይቁለጨለጫሉ፤ በስየ ላይ አዘቅዝቆ ያገጣል፤ ስየ ይበሽቃል፤ ግን ምን ያደርጋል? ከፊቱ አፍንጫውን አድቅቀው፤ አጥንቱን ወደ አቡዋራነት ለመቀየር ያሰፈሰፉ ባለጡንቻ ዞምቢዎች ተደርድረዋሉ። ወደ መለስ ለማንጋጠጥ በቅድሚያ እነዚህን ማለፍ ይጠይቃል።
ሳይወድ በግድ አዲሱን ፍልሚያ ለመፋለም ራሱን ያዘጋጃል፤ … “ቆይ ይሄን ልጨርስና መለስን አገኘዋለሁ …” ይላል በልቡ።
ምን ያረጋል! ልክ ስየ አዲሱን ፍልሚያ ሲጀምር መለስ አሸናፊ ሆኖ ወጥቶአል።
ከዚህ በኋላም ሌላው ተመልካችና ታዛቢ ወገን በስየና በመለስ መሀል ተጀምሮ ነበረውን ፍልሚያ ዘንግቶታል። አሁን ቀልቡን የሳበው በስየና ከፊቱ በተጀበረው “ዳኛ” መሀከል የተጀመረው ግጥሚያ ነው። አዲሱ ግጥሚያ ደግሞ ዘልዛላ ነው፤ ቶል አይቆረጥም፤ ጭራ ሲወጣለት፤ ክር ሲመዘዝለት፤ ሲንዘላዘል ከርሞ፤ እንኩዋን ተመልካቹን ስየን ራሱን ይዞት ይነጉዳል።
ቀናት፣ ወራት፣ ዓመታት ሲያልፉ፤ ድንገት ሁሉም ጉዳይ የመሰንበት ይሆንና ስየ ጉልበቱንም፣ ኃይሉንም፣ መንፈሱንም፣ እልሁንም ማሰሪያ በሌለው ጉዳይ ላይ አባክኖ ብንን ሲል፤ እሱም ራሱ የተነሳበት ውሉ ተደናግሮታል።
አሁን መለስ ሌላ ቦታ ነው። ስለዚህ ስየ የቀረው ቂም እንጂ ለጊዜውም ቢሆን መለስን የሚመታበት ክንዱ ልሞአል። ያለውና የቀረው ምርጫ ከዜሮ አገግሞ መነሳት ነው። ይህ ደግሞ ቀላል አይደለም፤ ከየት? እንዴት? እና መቼ? መጀመር እንዳለበት በጥንቃቄ ማሰብ ነበረበት።
ስየ በተዘጋጀለት ወጥመድ ገብቶ በእስር ቤትና በፍርድ ቤት ድራማ ጊዜውንና ዕድሜውን ሲፈጅ፤ መለስ በበኩሉ ጡንቻ፣ አዳዲስ ምስለ-ሰውና ሀብት አከማችቶ ሰባተኛው ሰማይ ላይ ተሸጋግሮአል።
አሁን ያኔ ጎን ለጎን ሆነው እንደሚፋለሙት የእኩያማቾች ጠብ ለስየ የሚቀል አይደለም፤ ስየም አዲስ፤ መለስም “አቶ” ሆነዋልና።
ካቶ ስየ ስንክሳር በጥቂቱ ተጠቅልሎ የተሰበቀኝ ባጭሩ እንዲህ ያለው ጨዋታ ነው፤ ስየ ባንደበታቸው ራሳቸውን ዋቢ አድርገው የተረኩልን ድርሳን በአያሌዎች ላይ ሲፈፀም የኖረና አሁንም ያላባራ የዕለት-ተዕለት ክስተት ነው። የስየ ከእልፍ እውነት መሃል የተመዘዘ አንድ ሰበዝ ነው።
በሁሉም ቦታ በሌላም ሁኔታ እየሆነ ያለው ይሄው ነው። የአቶ መለስና አጃቢዎቻቸው ጉዞ ሁሌም ይሄው ነው። ጥሎ ማለፍ። ከፊታቸው ስለሚያጋጥማቸው ማናቸውም ጉዳይ ተጨንቀውና አስበው አያውቁም፣ ወይም ዛሬ የሠሩት ነገ የፈለገውን አደጋ ቢያመጣ አያሳስባቸውም፤ ወይም በሠሩት ስተት አይደነግጡም፤ በተናገሩት ውሸት አያፍሩም።
እነሱ ከፊታቸው የሚያገኙትን ማንንም ቢሆን ካልተመቻቸው እየጠቀጠቁና እየረጋገጡ መሄድ ነው። ከፊታቸው የሚገተርን በነሱ ቋንቋ “ተቸካዮችን” እያስፈነጠሩ መገስገስ!
በአዲሱ ጎዳና ሁልጊዜ አጃቢ አለ። በአዲሱ ቅኝት ሁልጊዜ ድምፅ የሚያወጣ፤ የሚያንጎራጉር “ምስለ-ሰው” አለ። ያን ይዞ መቀጠሉ ነው፤ ድምፁ የጎረነነና አይሆንልኝም ያለ እሱ! ይቸከል። ምንችግር አለ! እንደፈለጉት የሚቃኝ ... “የተመቸና የሚመች … ዞምቢ” ሞልቶ ባገር።
ዋናው ጉዳይ በየቦታው ለሚንጠባጠበው በተቻለ መጠን ቋንቋ ማሳጣት ወይም ለሁሉም ለየራሱ ቋንቋ መፍጠር፤ ሁሉም በየራሱ የሚገባው የሚተረጉመው እንጂ በጋራ የሚግባባበት እንዳይሆን ብቻ ተጠንቅቆ ማዘጋጀት። አለዚያ “ተቸካዩ” ከተባበረ ወደፊት የማያራምድ የእሾህ አጥር ይሆናል።
አሁን የእሾህ አጥር የለም፤ እሾሃማ የሚመስሉ ለስላሳ ገላዎች ላይ መረማመድ ተችሎአል። ምናገባው መለስ? የጣፈጠውን እያቀመሰ፤ ያልጣፈጠውን ጨርሶ እንዲመረው፤ ያንዱን ምሬት ከሌላው ምሬት እያለያዩ ተመራሪዎችን እርስ በርሳቸው አንዱን የሌላው ምሬት ምንጭ አድርጎ በማናከስ መገስገስ ነው። ፊት-ለፊት እንዳይተያዩ፣ እንዳይደማመጡ፣ እንዲደናቆሩ፣ …
በሌላ በኩል (Like charges repeal) የሚለውን የፊዚክሱን ሕግ በማኅበራዊው ሕይወት ተርጉሞ ሥራ ላይ እንደማዋል ነው። በተቻለ መጠን በግራና በቀኝ በተመሳሳይ ቻርጅ የተሞሉና የተሰበከላቸው፤ እሱን ብቻ የሚያላምጡ ዜጎችን መደርደር ነው። እነሱ ሲፈራቀቁ በመሀል መንገድ ክፍት ይሆናል።
ይህ ሁኔታ እስኪለወጥና፤ በተቃራኒ ቻርጅ የተሞለ (Unlike charges attracts) ነውና፤ ዜጎች በግራና ቀኝ ሰልፍ ተራ ገብተው ማጠራቀቅ እስኪጀምሩ መለስና በየጀምበሩ የሚፈበርካቸው ዞምቢዎች የልብ ቁስሉ እንደሆኑ ይቀጥላሉ።
የሆነስ ሆነና እንደ ፊሊጶስ በራሳችን፣ በእያንዳንዳችን ላይ ሲፈፀም ካላየነው አናምንም ወይም አይገባንም የሚሉት “የኔ ቢጤዎች” መቼ ይሆን የሚባንኑት?
ከምስለ-ሰውነትና ዘግይቶም ካለመባነን ይጠብቀን!!
ጌዲዎን በለጡ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.