የሁለት ምርጫዎች ወግ Yehulet Mirchawoch Wog ተስፋዬ ገብረአብ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

የበረከትን መጽሐፍ አነበብኩት …

በእውነቱ ህትመቱ ቆንጆ ነበር። ሽፋኑ እንደ ሃብታም ጉንጭ ይለሰልሳል። ከቻርልስ ዲክንስ ታዋቂ መጽሐፍ የተኮረጀ ቢሆንም ርእሱም ቢሆን አሪፍ ነው - የሁለት ምርጫዎች ወግ። የበረከትን መጽሐፍ ያሳተመው መሐመድ አሊ አልአሙዲ የተባለው ነጋዴ መሆኑን ፍትህ ጋዜጣ ላይ አንብቤ ነበር። መጽሐፉ 314 ገፆች እና 10 ምዕራፎች ይዞአል። ዋጋው 90 ብር ነው።

 

 

ሪፖርተር በዜና ዘገባው፣ ሼኽ መሐመድ ዓሊ አልአሙዲ የበረከት ስምኦንን አዲስ መጽሐፍ ሳያነቡ፣ “መጽሐፉ ለወደፊቱ ትውልድ ጠቃሚ ነው” ሲሉ መናገራቸው እንዳስገረመው ፅፎአል። ምን ችግር አለው? ገንዘብ ወይም ስልጣን ካለህ የሚያዳምጥና የሚስቅልህ አታጣም። “ሃብት ያለው! ልብ አለው!” እንዲሉ። በረከት የመጽሐፉን ርእስ፣ “የሁለት ምርጫዎች ሞት” ቢለው ይሻል እንደነበር አስተያየት የሰጡም አሉ። ይልቁን ይቺን አስተያየት ወድጄያታለሁ።

 

እና በአንድ አዳር አነበብኩት …

 

ከዚህ ሁሉ ክምር መካከል ገፅ 312 ላይ ያሰፈረች አንዲት አረፍተነገር ይበልጥ ትኩረቴን ሳበችው። ሌላው ገለባ ነበር። ይህቺ አረፍተነገር የወደፊቱን የኢህአዴግ እቅድ ትጠቁማለች። በርግጥ በበረከት ስምኦን የህይወት ታሪክ ዙሪያ ጥቂት ድብቅ ነገሮች አሉ። ለአብነት እነዚህን መጠየቅ ይቻላል …

 

- የበረከት ወንድም በማን ተገደለ?

 

- የበረከት እውነተኛ ስም ማነው?

 

- በረከት የአባቱን ስም ለምን ቀየረ?

 

- ለመሆኑ አቶ ስምኦን ማናቸው?

 

- ካሳሁን ገብረህይወት እምነቱ ምን ነበር?

 

ከላይ ያሉት ጥያቄዎች የበረከት ስምኦን አዲሱ መጽሐፍ ውስጥ አልተካተቱም። እኔ ግን በዚህች አጭር መጣጥፍ ሁሉን እንደወረደ አወጋችሁዋለሁ። ያንን ከመግለፄ በፊት ግን በመጽሐፉ ዙሪያ አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳ …

 

 

 

በረከት መረጃ ከመስጠት ይልቅ ትንታኔ መርጦአል። መተንተኑ ባልከፋ። የሚሰጠው አስተያየት እና ትንታኔው ግን በውሸት ላይ የቆመ ነው። ለምሳሌ እንዲህ ሲል አስፍሮአል፣

 

“… የኢህአዴግ አመራርና ታጋዮች ህዝብ ሲበደል አይወዱም። ኢህአዴግም ከህዝቡ ሌላ ጌታ የለውም።”

 

በረከት ስለየትኛው ህዝብ እንደሚናገር ግራ ያጋባል። እንዲህ ፃድቅ ሆነው የተገኙት በርግጥ የኢህአዴግ አመራር አባላት ናቸው? በረከት ተቃዋሚዎችን በተቻለው መጠን ሁሉ ተሳድቦአል። ወይም ለመወንጀል ሞክሮአል። ሜድያዎችን ወርፎአል። ኢሳት ቴሌቪዥንን በተመለከተ፣

 

“… ሎርድ ሜየር እና የጥፋት ባልደረቦቹ እነ አና ጎሜዝ ከግብፁ የናይል ሳተላይት በተከራዩት ጣቢያ የምርጫው እለት ስርጭት ጀመሩ …” ይላል።

 

የኢትዮጵያን ባለሃብትና ነጋዴ ደግሞ እንዲህ ሲል ያዋርደዋል፣

 

“… ሁለት ባላ ትከል፣ አንዱ ሲሰበር ባንዱ ተንጠልጠል … የሚለው ብሂል ዛሬ ገና የተገለጠለት ይመስል ለኢህአዴግ በግራ እጁ ከሰጠ፣ ቀኝ እጁን ለቅንጅት ይዘረጋል …”

 

ስለ ቪኦኤ ጋዜጠኞችም ፅፎአል። አንዳንዶቹ በኢህአፓ ትግል ውስጥ አብረውት እንደነበሩ ይገልፃል፣

 

“… .በአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ክፍል ኢህአፓ እያለን አብረናቸው የታገልን፣ ነገር ግን በሂደት በአቋም የተለየናቸው ሰዎች ይገኛሉ።” ካለ በኋላ “… የኢትዮጵያ ህዝቦች ከአምባገነኑ ደርግ ጋር ሲፋለሙ፣ ለህይወታቸው ፈርተው ሸሽተው አሜሪካ የገቡ!” ሲል ይዝትባቸዋል። ጌታሁን ታምራትን ማለቱ ሳይሆን አይቀርም።

 

በረከት ሲፅፍ ተራ ብሽሽቅ ውስጥ ይገባል። ነገደ ጎበዜን፣

 

“… ቀይ ሽብር ይፋፋም! የሚለውን መፈክር የፈለሰፉ” ይላቸዋል። ማስረጃ ግን አያቀርብም።

 

መረራ ጉዲናን፣ “… ወደ ጥፋት የሚያመሩ አደገኛ ቃላትን ከማምረት የማይቦዝን …” ይለዋል።

 

አንድ ቦታ ደግሞ፣ “አደገኛ ቦዘኔ’ ያልነው ስራአጡን ሳይሆን ስራጠሉን ነው” ሲል በቃላት ቁማር ሊሸውድ ይሞክራል። ለምን እንዲህ ይጨነቃል? “ተሳስተን ነበር። ይቅርታ” ብሎ ባንድ ቃል መገላገል በተሻለው። አንድ ቦታ እንኳ “ተሳስተን ነበር” ብሎ ሳይናገር መጽሐፉን ጨረሰው። በረከት ቢያንስ ‘ታሪክ ያነበበ ሰው ነው’ ብዬ እገምት ነበር። እንደማየው ግን ያጠራጥራል። ታሪክ ያነበበ እንዴት ከታሪክ መማር አይችልም?

 

ዶክተር በየነ ጴጥሮስን በተመለከተ እንዲህ ይላል፣

 

“… ዶክተር በየነ ‘ስልጣን አይበቃችሁም ወይ? ለምን ለወጣቶቹ አታስረክቡም?’ ተብለው ሲጠየቁ፣ ‘ዛሬ ምን ወጣት አለ ብላችሁ ነው፣ ወጣት ድሮ ቀረ’ ብለው መለሱ …” ሲል ይወርፋቸዋል። እዚህ ላይ ታዲያ ስለ ኢህአዴግም በተነፃፃሪ ያነሳል። “… ወጣት አመራሮች የትግሉን በትረሙሴ ከነባሩ አመራር ትውልድ እየተረከቡ ነው” ይለናል።

 

ኢህአዴግ ስልጣኑን ለወጣቶች ማስረከብ ጀምሮአል እንዴ? አልሰማሁም ነበር። ዜናው አምልጦኝ ይሆናል። እነማናቸው ግን ወጣቶቹ? ሬድዋን ሁሴን እና አዜብ መስፍን? ወይስ ቻይና ትምህርት ላይ ያሉት የአመራር አባላቱ ልጆች? ግልፅ አላደረገም …

 

ስለ ብርሃኑ ነጋ፣

 

“ዶክተር ብርሃኑ ይቅርታ ጠይቆ አሜሪካ ከመሸገ በኋላ የስራ ባልደረባውን አንዳርጋቸው ፅጌን ወደ ኤርትራ እየላከ ከኢሳይያስ አፍወርቂ ጋር ሴራ በመጎንጎን …” በሚል ያጠቋቁረዋል።

 

አንዳርጋቸው ፅጌን በተመለከተ፣

 

“… አንዳርጋቸው ከለንደን፣ ‘መደራደር ለምን? ፓርላማ መግባት ለምን? የተዳከመና በህዝብ የተጠላ መንግሥትን ገፍትሮ መጣል ነው እንጂ’ እያለ በእሳት ላይ ነዳጅ በማርከፍከፍ ላይ ነበር …”

 

ስለ ብርቱካን ሚደቅሳ ሲገልፅ ደግሞ፣

 

“… የብርቱካን ነገር በሞኝ እጅ የዘንዶ ጉድጓድ ይለካል የሚሉት አይነት ነው። የቅንጅት መሪዎች በብርቱካን መታሰር ደስታ ተሰምቷቸዋል። መታሰሯ የመንግሥትን ክፋት ለማጋለጥ የሚያስችል አንድ መልካም አጋጣሚ ሆኖ ተሰምቷቸዋል …”

 

ስለ ስየ አብርሃ፣

 

“… በቅርቡ ባሳተመው ‘ነፃነት እና ዳኝነት በኢትዮጵያ’ በሚለው መጽሐፉ ላይ በተሃድሶው ዘመን አቶ ስብሃት ላቀረበለት ጥያቄ፣ ‘ስማ ስብሃት! የኔን ወንድነት እና ሱሪ ትጠራጠራለህ እንዴ?’ በማለት እንደመለሰለት የሚገልፀው ስዬ ጀግንነት በሱሪና በቀሚስ የሚለካበት የእነእምዬ ምኒልክ ዘመን እንዳለፈ ዛሬም የገባው በማይመስል አኳሁዋን ስለራሱ ጀግንነት አውርቶ አይጠግብም …”

 

የመጽሐፉ ዋና የጥቃት ኢላማ ብርሃኑ ነጋ ነው ማለት ይቻላል። ሆኖም ብዙ ሊመታው ሞክሮ ምንም ሳይነካው መጽሐፉ አለቀ። ትልቅ ነገር ብሎ ያነሳው፣ “ብርሃኑ ከአና ጎሜዝ ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበረው” ሚለውን ነው። ቀደም ሲል ከነገሩን የተለየ ማስረጃ ግን አላቀረበም። መለስ ለአና ጎሜዝ በፃፈው ደብዳቤ ላይ ግን፣ ከቲና ተርነር የዘፈን ግጥም አንድ መስመር ተውሶ፣ what’s Love got to do with it.’ ብሎ አሽሙር ቢጤ ጣል ማድረጉን አስፍሮአል። በረከት በዚህ በመለስ አሽሙራዊ አፃፃፍ ተደንቆ ከጣራ በላይ መሳቁንም ይነግረናል። እንዲያው ለነገሩ አና ጎሜዝ በብርሃኑ ፍቅር ወድቃ እንደነበር ቢረጋገጥስ? በውነቱ የ97 ምርጫ መጭበርበር በዚህ መረጃ ምክንያት ሊሸፈን ይችላል?

 

(… መለስ እንዲህ የፍቅር ነገር መፃፍ ከጀመረ ጥሩ ነው። በቅርቡ በፍቅር ስንኞች የተሞላ አንድ መጽሐፍ ጀባ ይለን ይሆናል። “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” እያለ ከሚያንገላታን፣ “አብዮታዊ ፍቅር” የተባለ ተከታታይ ድራማ ቢጀምሩልን በተሻለ። መለስም ግን እንደ በረከት አንዳንድ ጊዜ ወሰድ መለስ ያደርገዋል። በቅርቡ፣ “መለስ ከልጅነት እስከ እውቀት” የተባለውን በትኩእ ባህታ የተፃፈውን መጽሐፍ ሳነብ፣ ገፅ 150 ላይ “የመለስ ጥቅስ” ተብሎ የቀረበ አገኘሁ። “የአፍሪቃ ውድቀት ሁሌም የግለሰቦች አምልኮ ነው” ካላ በኋላ የእነዚህ አምባገነኖች ስም በ“M” ፊደል እንደሚጀምር ይገልፃል። “መለስ ከታምራት ገለታ ጥንቆላ ተማረ እንዴ?” ብዬ በጣም ገርሞኝ፣ ስማቸው በ“M” የሚጀምረውን አምባገነን መሪዎች መፈለግ ጀመርኩ። መንግሥቱ፣ ሞቡቱ፣ ሙጋቤ፣ ሙሴቪኒ፣ መለስ፣ ምቤኪ፣ መሃመድ ጋዳፊ፣ በጣም ሳቅሁኝ። ኢሳያስ ግን ስሙ በ“M” አይጀምርም። መለስ ለካስ መስፍን ወልደማርያምን እንዲህ አጥብቆ የሚፈራቸው ስማቸው በ“M” ስለሚጀምር ኖሮአል? መለስ ጨዋታ ጨምሮአል። እንዲህ አልፎ አልፎ ቢያዝናናን ጥሩ ነበር …)

 

በረከት የፕሮፓጋንዳውን ስራ አልቻለበትም። ጋዜጦች እንደገለፁት ከበረከት መጽሐፍ አስገራሚ አላማዎች አንዱ በ1997 የምርጫ ፉክክር ወቅት በአደባባይና በሕዝብ ፊት ያሳፈሯቸውንና ባዶነታቸውን ያጋለጠባቸውን ዶክተር ብርሃኑ ነጋን መበቀል ነው።

 

በረከት በመጽሐፉ እራሱን ሲያደንቅም ሃፍረት የሚባል አልፈጠረበትም። እንዲህ ይላል፣

 

“… በኤሊ ሳይሆን በአቦሸማኔ ፍጥነት በመለወጥ ላይ ያለች ኢትዮጵያ ውስጥ እንኖራለን። ትልቅ ምስጋና ይህን ለውጥ አቅደው ላስፈፀሙት የልማት መሪዎች …” የስምኦን ልጅ በጣም ደፋር ነው። እንዲህ ሲል አስፍሮአል፣ “..ሶማሊያ ውስጥ ‘ፊልም አየህ ተብሎ ሰው በጠራራ ፀሃይ ይገደላል’ …”

 

ጤና ይስጥልኝ በረከት!!

 

አሰፋ ማሩ ለምን በጠራራ ፀሃይ ተገደለ? ኦቦ ደራራ ከፈኔ በጠራ ጨረቃ ለምን ተገደሉ? በረከት ስለሶማሊያ እስርቤት በመጽሐፉ አንስቶ ነበር፣ “… የሶማሊያ አክራሪዎች እስርቤት ውስጥ የዜጎችን ጀርባ በጅራፍ በመተልተልና ህዝቡን በሽብር ሸብበው …” እያለ ሲተነትን ‘ይሄን መጽሐፍ የፃፈው ሌላ በረከት ስምኦን ይሆን እንዴ?’ ብዬ ተጠራጥሬያለሁ። አዲሳባ እስርቤት ምን እንደሚፈፀም አያውቅም? ይህን ሲል አብረውት የሚሰሩትን እንኳ አያፍራቸውም? “… የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ዳኞች ከየትኛውም የመንግሥት አካል አንዳችም ተፅእኖ ሳይደርስባቸው ብይን እንደሚሰጡ የተመሰከረለት ነው …” የሚለው ገፅ ላይ ስትደርሱ ልብ ድካም ያለባችሁ አደራ ተጠንቀቁ።

 

በረከት በመጽሐፉ ተቃዋሚዎችን ርስበርስ ሊያጋጭ ይችላል ያላቸውን ለቅሞ አትሞአል። ቆርጦ የመቀጠል ልምዳቸው እዚህም ተደግሞአል። ገፅ 236 ላይ እነ ብርሃኑ ለሽማግሌዎቹ ፈረሙት የተባለውን የይቅርታ የፊርማ ወረቀት ለመለስ እንደተፃፈ በማስመሰል ሁለት የተለያዩ ደብዳቤዎችን አጣብቆ አትሞታል። በቅርቡም ይህን አይነት የመቀጣጠል ድራማ ደበበ እሸቱ ላይ ፈፅመውታል።

 

በጥቅሉ የበረከት መጽሐፍ በቅጥፈት ትንታኔዎች የተሞላ ነው። አንዳንድ የሚጠቀምባቸው ቃላት ግራ ያጋባሉ። መለስ በፖሊት ቢሮ ስብሰባዎች ተናገረ ብሎ ያቀረባቸው አረፍተነገሮች ያበደ ወይም የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው የሚናገራቸው ነበር የሚመስሉት፣

 

“… ስራ አስፈፃሚው ሩጫ ከመጀመሩ በፊት ለራሱ፣ ‘ምን ያህል ጊዜ አለን? በምን ያህል ፍጥነትስ ልንሮጥ ይገባናል?’ የሚሉ ጥያቄዎችን አቀረበ። ከኤሊ ወይም ከቀንድ አውጣ ትንሽ ሻል በሚል ወይም በአቦሸማኔ ፍጥነት መጓዝ በሚቻልበት ሁኔታ … ተሃድሶው በከፍተኛ ፍጥነት ከሚወርድና በየደቂቃው በፍጥነት ከሚጓዝ ናዳ አምልጦ፣ ጠንካራ ከለላ ለማግኘት …” እንዲህ ያሉ የሚንኳኩ ድንጋያማ ቃላት የሞሉበት መጽሐፍ ሲሆን፣ ቃላቶቹ እንደ ቢንቢ ጆሮ ላይ ይጮሃሉ እንጂ ምን እንደሚናገሩ መረዳት ያስቸግራል …

 

ስለ አዲሳባ የተረከው ክፍል በጣም አስገርሞኛል፣

 

“… አዲሳባን ሲያስተዳድር የቆየው አመራር እንዲቀየር ከተወሰነ በኋላ ከየክልሉ ከተማ ቀመስ ሰው እየተፈለገ ተመልምሎ አዲሳባ እንዲገባ ተደረገ።” ይላል።

 

እነዚህ ከተማ ቀመሶች ደግሞ አርከበ ኡቅባይ እና ህላዌ ዮሴፍ መሆናቸውን ይነግረናል። ይሄ እውነት አይደለም። ዓሊ አብዶ አዲሳባን መምራት ያልቻለው ከተማ ቀመስ ስላልሆነ አልነበረም። ዓሊ አዲሳባን እንዲመራ ነፃነቱ አልተሰጠውም። በወቅቱም አዲሳባ እንድትለማ ፍላጎት አልነበረም። ኋላ ግን የአዲሳባን ህዝብ ልብ ለማግኘት ታቀደና ለአርከበ ከሙሉ ስልጣን ጋር የፌደራሉ ሙሉ ድጋፍ ተመረቀለት። ስለዚህ ከዓሊ የተሻለ ስራ ሰራ። አርከበ ከለቀቀ በኋላ ለኩማ ደመቅሳ ሙሉ ስልጣን አልተሰጠውም። በረከት ይህን ያውቃል። እያወቀ ግን “አርከበ ከተሜ በመሆኑ አዲሳባ ላይ ለውጥ አሳየ” ይለናል። ለመሆኑ የአርከበ ከተሜነት የት ነው? መቀሌ ወይስ አድዋ? ህላዌስ ቢሆን? የ18 ዓመት ጎረምሳ ሆኖ አዲሳባን ከለቀቀ በኋላ አያውቃትም። አዲሳባ ላይ የኖረ ቢሆንስ? ከተማን ለማስተዳደር የብቃት መመዘኛ ይሆናል? የበረከት አገላለፅ፣ አርከበና ህላዌ በቀጥታ ከለንደን ከንቲባነት ወደ አዲሳባ መዘጋጃ ቤት የተዛወሩ ይመስል፣ “ከተሜዎች ተመርጠውና ተፈልገው አዲሳባ እንዲገቡ ተደረገ” ይለናል።

 

እንዲህ ይላል ደግሞ፣

 

“… ኢህአዴጎች ጥገኛ ዝቅጠት ከተንሰራፋ ሊከተል ስለሚችለው አደጋ የሚሰጡት ምላሽ አርማጌዶን የሚል ነበር። የአርማጌዶን አደጋ ፈጦ በወጣበት፣ አገሪቱን ወደ ህዳሴ ሊያመሩ የሚችሉበት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ በተነደፉበትና ለተግባር ምላሽ ሊሆኑ በሚችሉበት፣ አመራሩም አገሪቱን ይዞ ከአደጋው ለማምለጥ በከፍተኛ ፍጥነት ለመሮጥ በተስማማበት ወቅት የኢትዮጵያን ፈጣንና የማያቋርጥ እድገት እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች …”

 

ከላይ የተገለፀውን ደጋግሜ ባነበውም ሊገባኝ አልቻለም።

 

በረከት ምንድነው ሚያወራው? ስለ ኢትዮጵያ ነው ወይስ ስለ ፉጂ ደሴት? በተለይ፣ “አመራሩ አገሪቱን ይዞ ከአደጋው ለማምለጥ በከፍተኛ ፍጥነት ለመሮጥ” የሚለውን በምናብ ለማየት ሞክሬ ነበር። አይኑ እንደ በርበሬ የቀላ ሰው፣ ኢትዮጵያን በነጭ ከረጢት ውስጥ ከቶ፣ በጨለማ ውስጥ እየጮኸ ሲሮጥ ነበር የታየኝ። ጭንቀት ያለበት ሰው የቅዠት አለም ውስጥ ገብቶ የፃፈው የተዘበራረቀ ዶሴ ሆኖ ተሰማኝ።

 

እነሆ! የበረከት መጽሐፍ እንዲህ ባሉ ቃላት የተሞሉ ናቸው።

 

ይህን መጽሐፍ ለማንበብና ይህችን አስተያየት ለመፃፍ በጥቅሉ 21 ዓአታት አባክኛለሁ። ከበረከት ስምኦን ጋር መስራት ካቆምኩ 12 ዓመት ሆኖኛል። ምንም አልተለወጠም። አሁንም ያገኘው ሰው ላይ እንደ ግንድ መገንደሱን ቀጥሎአል። አሁንም ለሌሎች ትክክል የመሆንን እድል አይሰጥም። አሁንም ክብሩን አይጠብቅም። መሐመድ አሊ አልአሙዲ የተባለው ሲራራ ነጋዴ፣ እንደ ማንቆርቆሪያና ጀበና “ከሆስፒታል አንጠልጥዬ አወጣሁት” እያለ ሲናገር በረከት ቁጭ ብሎ እየሰማ እስከ ጆሮው ይስቃል። በዚህ እድሜው እውነት መናገር አልቻለም። ሌላው ሁሉ ቀርቶ ለተሰዋ ታላቅ ወንድሙ እንኳ ታማኝ መሆን አልቻለም።

 

የበረከት ቅጥፈት ገፅ አንድ ላይ ይጀምራል። ገና መጽሐፉን ስትገልጡት፣ “መታሰቢያነቱ ለወንድሜ ለካሳሁን ገብረህይወት” ይላል።

 

ይሄ ውሸት አይደለም። በረከት ካሳሁን የሚባል ወንድም አለው። የበረከት የልጅነት ስም ከእነአባቱ፣ “መብራህቱ ገብረህይወት” ይባላል። ወደ ትግል ከወጣ በኋላ ስሙን “በረከት ስምኦን” ሲል ቀየረው። ስሙን ከእነ አባቱ ለምን እንደቀየረው ብዙ ሰዎች አያውቁም። በትግሉ ጊዜ ስምህን እንጂ የአባትህን መቀየር የተለመደ አልነበረም። ለምሳሌ መለስ፣ ስብሃት፣ ስዬ፣ ሳሞራ፣ ሃየሎም፣ ህላዌ፣ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። ስማቸውን እንጂ የአባታቸውን ስም አልቀየሩም። ምክንያቱም ስም መለወጥ ያስፈለገው ለቤተሰባቸው ደህንነት ሲባል ብቻ ነበር። የአባት ስም ለመለወጥ ምክንያት አልነበረውም። እንዲያውም ብዙዎቹ ደርግ ከወደቀ በኋላ ወደ ልጅነት ስማቸው ተመልሰዋል። በረከት ከእነዚህ ሁሉ ተለይቶ ስሙን ብቻ ሳይሆን የአባቱንም ስም ቀየረ። በዚያውም ፀና።

 

የአባትህን ስም ለመቀየር የግድ አንድ ምክንያት መኖር አለበት። ምናልባት አባትህን የምትጠላ ከሆነ፣ ዲቃላ ሆነህ በእንጀራ አባትህ የምትጠራ ከሆነ፣ የመሳሰሉ ምክንያቶች የአባትህን ስም ሊያስቀይሩ ይችላሉ። ስትቀይርም የእውነተኛ አባትህን ስም ታደርጋለህ። ወይም አባትህ ስሙ የማይታወቅ ከሆነ የእናትህን አባት ስም ልታደርግ ትችላለህ። አሊያም ደግሞ እንደ በአሉ ግርማ በአሳደገህ ሰው ስም ልትጠራ ትችላለህ። ይሄ ተለመደ ነው።

 

በቅርብ እንደማውቀው በረከት ወላጅ አባቱን በጣም ያከብራል፣ ይወዳልም። በጎን የተወለደም አይደለም። መልኩም አባቱን ነው የሚመስለው። ወላጅ አባቱ አቦይ ገብረህይወት ባህላዊ መሃንዲስ ነበሩ። በጎንደር ዙሪያ የሚገኙ ቤተክርስትያናትን በአብዛኛው የገነቡት እሳቸው ናቸው። ቤተሰባቸውን አጥብቀው የሚወዱ፣ ልጆቻቸውን ለመስተማር እና ጥሩ ደረጃ ለማድረስ የደከሙ አባት ነበሩ። እና ታዲያ በረከት ስምኦን እንዲህ ያሉ ድንቅ አባቱን ከስሙ ላይ ፍቆ ለመጣል ለምን ወሰነ? ታሪኩ አስቂኝ ነው …

 

በረከት ስምኦን የሚባል የኢህአፓ ታጋይ ነበር።

 

አዲሳባ ተወልዶ ያደገ፣ ሊሴ ገብረማርያም የተማረ ኤርትራዊ ነው። በትግሉ ወቅት ይህ ልጅ ባልታወቀ ምክንያት ከትግሉ ሜዳ ተሰወረ። ድንገት ስለተሰወረ ብዙዎች የኢህአፓ አባላት በረከት ስምኦን የተሰዋ መሰላቸው። በዚህ ጊዜ መብራህቱ ገብረህይወት በረከት ስምኦን የተባለውን የተሰዋ የትግል ጓዱን ለማስታወስ ስሙን በስሙ ሰየማት። እናም በረከት ስምኦን እየተባለ መጠራት ጀመረ።

 

የሚያስገርመው ታሪክ ግን እውነተኛው በረከት ስምኦን አልተሰዋም ነበር። እውነተኛው በረከት ስምኦን አሁንም በህይወት ፓሪስ ይገኛል። በህይወት እያለ፣ በጠራራ ፀሃይ ስሙ በመዘረፉ በጣም እንደሚበሳጭም ሰምቻለሁ። እውነተኛው በረከት፣ ሩት እና ሃና የተባሉ እህቶች አሉት። ሃና ስምኦን ፓሪስ ላይ የኤርትራ አምባሳደር ነበረች። አሁን የት እንዳለች አላውቅም። ሩት ስምኦን የሻእቢያ ታጋይ እና ጋዜጠኛ ስትሆን፣ አስመራ ትገኛለች። ባልተሰዋ ሰው ስም፣ በአላማ በማይገናኙ ሰው ስም፣ ራሱን የሚጠራው ታሪከኛው መብራህቱ አማራ ሳይሆን አማራ ነኝ ይላል፣ በረከት ስምኦን ሳይሆን በረከት ስምኦን ነኝ ይላል። ይሄ ሰውዬ መቼ ነው እራሱን የሚሆነው? ጤነኛ የሆነ ሰው የራሱን ስም ሙሉ በሙሉ ሰርዞ፣ ያልሞተን ሰው ስም ከእነ አባቱ እንዴት ይዘርፋል?

 

(እውነተኛው በረከት፣ ፎቶኮፒውን በረከት በመክሰስ ስሙን ማስመለስ ይችላል። በርግጥ የህግ ሰዎች አስተያየት ሊሰጡበት ይችላሉ። ፓሪስ የሚገኙ ጋዜጠኞችም እውነተኛውን በረከት ቢያነጋግሩት ጥሩ ነው። በህይወት እያለ በስሙ ይሄ ሁሉ ግፍ ሲሰራ ዝም ማለት ያለበት አይመስለኝም …)

 

ወደ ዋናው ነጥብ ልመለስና የመብራህቱ ገብረህይወት ታላቅ ወንድም ካሳሁን ገብረህይወት ይባላል። ስለዚህ መጽሐፉን “ለወንድሜ ለካሳሁን ገብረህይወት መታሰቢያ ይሁን” ማለቱ ውሸት የለበትም። ዝቅ ብሎ ግን እንዲህ ይላል።

 

“እነሆ በተለምክልኝ መንገድ እጓዛለሁ”

 

እዚህ ላይ በረከት እንደገና እውነትን ገለበጣት። ካሳሁን ለበረከት የፖለቲካ መንገድ አልተለመለትም። ካሳሁን ኤርትራ ተወልዶ ጎንደር አደገ። ከዚያም የኢህአፓ ታጋይ ሆነ። በኢህአፓ ውስጥ ሳለ የጎሳ ፖለቲካን የሚቃወም፣ እንደማንኛውም የወቅቱ የኢህአፓ ወጣት ህብረብሄራዊ አደረጃጀት እና መስመርን የሚመርጥ ነበር። በግልባጩ መብራህቱ በታላቅ ወንድሙ ተፅእኖ የብሄር አደረጃጀትና አስተሳሰብን የሚቃወም ሆኖ ነበር ትግሉን የጀመረው። ካሳሁን የተሰዋው ከህወሃት ጋር በተደረገው ጦርነት ነው። ማለትም ካሳሁን የተገደለው በህወሃት ጥይት ነው። በረከት ስምኦን ወደ ህወሃት የገባው ከካሳሁን መገደል በኋላ ነው። እንዴትና በየት በኩል ነው፣ ካሳሁን ይህን የወያኔ አላማ ለበረከት ያወረሰው? ካሳሁን ምንም እንኳ ወንድሙ ቢሆንም፣ በዚህ መንገድ ታሪኩን ሊያበላሽበት መብት የለውም …

 

በረከት በጣም የተምታታበት ሰው ነው።

 

ኢትዮጵያን ይዞአት ገደል ሳይገባ መሄጃውን ቢፈልግ ለዚህች አገር ትልቅ ውለታ እንደሰራ ይቆጠራል። ከበረከት የተምታቱ ታሪኮች ዋናው በዘሩ ኤርትራዊ ሆኖ ሳለ የአማራ ድርጅት መሪ መሆኑ ነው። ይሄ ከሞራል አንፃር ለአማራ ህዝብ ስድብ ነው። በረከት በህብረ ብሄራዊ ድርጅት ውስጥ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያን ቢመራ ጥያቄ ባልተነሳበት። ሰው ተወልዶ ያደገበት አገሩ መሆኑ ይታመናል። የዘር ፖለቲካ የሚያራምድ ግን የግድ እሱም ዘሩን ግልፅ ማድረግ ይጠበቅበታል። “አማራ በዘሩ መደራጀት አለበት” ብለው ሲያበቁ፣ አማራ ያልሆነ እንዴት አማራን ይወክላል? ኢህዴን ወደ ብሄራዊ ድርጅት ሲለወጥ፣ በረከት ለራሱም ሆነ ለአማራ ህዝብ ክብር ሲል ራሱን ከአማራ ድርጅት መሪነት ማግለል ነበረበት። በረከት ስምኦን ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፉ ላይ አላነሳም። ይልቁን በቀጣይ 20 ዓመታት እንዴት ኢትዮጵያን እንደሚያስተዳድራት ፍንጭ ሰጥቶናል። ይህን ማስታወሻ ለማስፈር የተነሳሁትም በመቋጫው መረጃ ምክንያት ነው።

 

“… (አሮጌው) የአመራር ትውልድ ቦታውን ለአዲሱ የአመራር ትውልድ የሚያስረክብበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ስለዚህም ከፊት መስመር ገለል ብለን፣ ከኋላና ከጎን ሆነን መደገፍ አለብን በተባባልነው መሰረት የአመራር መተካካቱን ማስፈፀም ጀምረናል…”

 

የተሰመረበት አረፍተነገር የኢህአዴግን የ2015 እቅድ የሚጠቁም ነው። እንደተሰመረበት መረጃ ከሆነ መለስና በረከት መንግሥታዊ የኃላፊነት ቦታቸውን ሊለቁ ተዘጋጅተዋል። ማለትም “ከፊት መስመር ገለል” ይላሉ። “ከኋላና ከጎን” ሆነው ይደግፋሉ። “እስከመቼ?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የለውም። አስር ወይም ሃያ ዓመታት! በዚህ ስልት አገዛዙ ይቀጥላል። “መደገፍ” ሲሉ መንዳት ማለታቸው ነው። መርጠው የሚያመጧቸው እንደ ጋሪ ፈረስ ለመነዳት ፈቃደኛ የሚሆኑትን ይሆናል። መለስና በረከት ፑቲን የፈፀመውን አይነት ቁማር ሊጫወቱ የቤት ስራቸውን ሰርተው ጨርሰዋል። ይህንንም በቅርብ ጊዜ በተግባር የምናየው ይሆናል። “ከጎን መርዳት” የሚለው በምክትል ሚኒስትርነት የሚቀመጡትን የሚጠቁም ነው። ለአብነት ብርሃነ ገብረክርስቶስ ሃይለማርያም ደሳለኝን ከጎን ሆኖ እየመራው ነው። ስለዚህ ነባሮቹ የምክትል ሚኒስትሮችን ቦታ እየያዙ፣ አሻንጉሊቶችን በሚኒስትርነት ያስቀምጧቸዋል። “በተባባልነው መሰረት” የሚለው አባባል የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ውሳኔን የሚመለከት ነው። በቀጣዩ ያልታወቁ ዓመታት ኢትዮጵያን እንዴት መምራት እንዳለባቸው የደረሱበትን ውሳኔ ጠቁመውናል።

 

ርግጥ ይህ መረጃ ጥብቅ ምስጢር አልነበረም። ከሃይለማርያም መምጣት በኋላ በፑቲን ስልት በመጓዝ ላይ መሆናቸውን ስንገምት ቆይተናል። መተካካቱ፣ “ከኋላና ከጎን” እንደሚደገፍ (እንደሚነዳ) በአደባባይ ሲያረጋግጡልን ግን ይህ የመጀመሪያው ነው። ይህ የበረከት መጽሐፍ የመወያያ አጀንዳ እንዲሆንም ይፈልጉ ይሆናል። እዚህ ላይ መታለል አይገባም። መጽሐፉን ከአጀንዳ ውጭ በማድረግ ወደሚቀጥለው ስራ መግባት ብልህነት ነው።

 

በቅርቡ አዲሳባ ላይ ታላቁ ሩጫ ሲካሄድ፣ “ሳንፈልጋቸው - ሃያ ዓመታቸው!” እያለ የተቃውሞ ድምፁን ያሰማው ወጣት፣ “ሳንፈልጋቸው - አርባ ዓመታቸው!” እያለ የሚዘምርበት ቀን እንደሚመጣ እየቀለዱ ከጣራ በላይ ይስቁ ይሆናል። ሆኖም ረግጠው መግዛቱን ለመቀጠል ያላቸው ቁርጠኛነት ሊሳካ የሚችለው ትግል ባይኖር ነበር። ትግል ግን አለ። የመረረ ትግል አለ። ጥቂት አጋጣሚ ብቻ የሚጠብቅ፣ በቋፍ ላይ ያለ ያመፀ ህዝብ አለ። ያም ሆኖ መለስና በረከት ለልጆቻቸው፣ ለሃገራቸውና ለስማቸው ሲሉ የተበላሸውን ለማስተካከል አጭር ቀሪ ጊዜ አላቸው። ጋዳፊ ላይ የደረሰው ይደርስባቸው ዘንድ ማንም አይመኝም። ሊደርስ ግን ይችላል። ስለዚህ አንድ ነገር ማስታወስ ይገባቸዋል። በመጨረሻ የሚስቅ ረጅሙን ሳቅ ይስቃል …

 


ፀሐፊውን ለማግኘት፣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!