20210302 adwa

የአዲስ አባባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ የክልሉ ም/ፕሬዝዳንት ሆኑ

ም/ፕሬዝዳንቱ ወደ ኢህአዲግ ጽ/ቤት ተዛወሩ

አቶ በረከት ስምዖን ወደ ፈረሰው ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሊመደቡ ይችላሉ

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ኅዳር 6 ቀን 2001 ዓ.ም. November 15, 2008)፦ ኀሙስ ዕለት የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ሹም ሽር ማካሄዱ ታወቀ። ምክር ቤቱ ባደረገው ሹም ሽር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ መሐመድን የኦሮሚያ ክልል ም/ፕሬዝደንት አድርጎ ሾመ።

 

ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ሙክታር ከድር በኢህአዴግ ጽ/ቤት እንዲሠሩ የተመደቡ መሆናቸውን የጠቆሙት ምንጮቻችን የጽ/ቤቱ ኃላፊ በሆኑት በአቶ በረከት ስምዖን ምትክ ሳይመደቡ እንዳልቀሩ ገልጸዋል።

 

የክልሉ ም/ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ ከድሬዳዋ ከተማ ከንቲባነት ተነስተው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው ከተሾሙ ገና አምስት ወራት ያስቆጠሩ ሲሆን፤ ”በአጭር ጊዜ ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ቢነሱም ካሉበት ቦታ ወደ ከፍተኛ ሹመት ነው ያደጉት” ሲሉ ምንጮቻችን ገልጸዋል።

 

በሚኒስቴር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ግንኙነት አማካሪና የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ በረከት ስምዖን፣ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊነታቸው ቦታ ምትክ አቶ ሙክታር ከድር መሾማቸውን የጠቆሙት እነዚሁ ምንጮች፤ አቶ በረከት የፈረሰው የማስታወቂያ ሚኒስቴር ስሙ ተቀይሮ በአዲስ መልክ የተዋቀረው መስሪያ ቤት ኃላፊ ሆነው ሊሾሙ እንደሚችሉ አክለው ጠቁመዋል።

 

በተጨማሪም ኀሙስ ዕለት የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ባደረገው ሹም ሽር፤ በአቶ አብዱላዚዝ ምትክ የቡራዩ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ሞትማ መቃሳ የተሾሙ ሲሆን፤ ባለፈው በተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው ሹም ሽር ከኦሮሚያ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ተነስተው የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው በተሾሙት አቶ ድሪባ ኩማ ምትክ የአርሲ ዞን አስተዳደር ኃላፊ አቶ ዑመር መሐመድ መሾማቸውን ምንጮቻችን ገልፀዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!