ተክለብርሃን ገብረሚካኤል

"የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ" ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ”የኦሮሞና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” በሚል ርዕስ በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. አሳትመው ያወጡት መጽሐፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ምርምርና ጥናት አዲስ ፈር ቀዳጅ ለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። አንደኛ የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ውጪ (ከማዳጋስካር፣ ከኢስያ ክፍሎች) ወደ ኢትዮጵያ ፈልሶ የገባ ሲባል የኖረውን አፈ ታሪክ አሳማኝ ናቸው በሚባሉ ማስረጃዎች አስደግፈው ከእውነቱ የራቀ መሆኑን አሳይተዋል። ሁለተኛ አማራ የገዥ መደብ ተብሎ በአማራ ሥርወ መንግሥት ኦሮሞን ጨምሮ ሌሎች የባህል ገጽታዎቹን በኃይል ጭኖባቸዋል የሚለው ውግዘት ምንም ታሪካዊ መሠረት እንደሌለውና እንዲያውም፣ በአግአዚ/ሰሎሞናዊና በዛጉዌ ሥርወ መንግሥታት በንጉሠ ነገሥትና ደረጃ አማሮች የበላይነት ይዘው እንደማያውቁና ይልቁንም በዚህ የሥልጣን ደረጃ አብዛኞቹ ኦሮሞዎች እንደነበሩ አረጋግጠዋል። በተጨማሪም በዘመነ መሳፍንት በባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴነቱ በኢትዮጵያ ሥልጣን ይቀራመቱ የነበሩት አማሮች ሳይሆኑ፣ በተለይ የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውን ቁልጭ አድርገው ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ አመልክተዋል። ሦስተኛ አማሮች የዘር ምድባቸው ሴማዊ (ሴሜቲክ) ሳይሆን እንደ ኦሮሞ ኩሻዊ መሆኑን፣ ሁለቱም ጎሳዎች (ጎሳ በቋንቋ መወሰኑን አመልክተዋል) የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥንታዊ አባት ከሆነው ኩሻዊው ኢትዮጵያ ልጅ ከደሽት (ከደሴት) የመጡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ጂኦግራፊያዊ ወይም መልክዓ ምድራዊ ምንጫቸው ዛሬ ጐጃም እየተባለ የሚጠራው አካባቢ መሆኑን አመልክተዋል። እነዚህ ሁሉ አዳዲስ ታሪካዊ ግኝቶች ናቸው።

የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ሌላው ዓቢይ ገጽታ ከልዩነት ይልቅ አንድነትና ተመሳሳይነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከበቀል ይልቅ ርኅራኄንና ምሕረትን፣ ከመሻኮት፣ ከመነታረክና ከመጠፋፋት ይልቅ መቻቻልንና በእኩልነት አብሮ መኖርን የሚሰብክ በመሆኑ፣ ሻዕቢያ ሕወሓት/አሕአዴግ ከሚያቀነቅኑት የቂም በቀል፣ የመለያየትና የመጠፋፋት አስተምህሮ ተቃራኒ አመለካከትና ርዕዮት ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በዚህም ምክንያት ሊሆን ይችላል ገና ካሁኑ አንዳንድ ሰዎች (መጽሐፉን ያነበቡ) ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን የኢትዮጵያ ታሪክ አባት ብቻ ሳይሆን፣ የፍቅር አባት እያሉ ሲጠሯቸው የሚሰማው። የታሪክ አባት የተባሉት ብቸኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊና ተመራማሪ ስለሆኑ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ከጥንታዊ ሥረ መሠረቱ ጀምሮ ለማየት በመሞከራቸው ይመስለኛል። ከዚህ በመቀጠል የመጽሐፉን አንኳር ይዘቶች፣ በተለይም በአዲስ ግንኙነት ሊመደቡ የሚችሉትን ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

የመጽሐፉ ዓበይት ይዘቶች

መጽሐፉ በሦስት ዋና ክፍሎቹ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን፣ ክፍል አንድ ”ኦሮሞ ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያበረከተው አስተዋጽኦ” የሚል ንዑስ ርዕስ ያለው ሲሆን፣ ክፍል ሁለት ”የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ እውነተኛው የዘር ምንጭ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ቀርቧል። ክፍል ሦስት ርዕስ ሳይሰጠው፣ ስለኢትዮጵያ ሥርወ መንግሥታት፣ ስለዘመነ መሳፍንት፣ ስለንግሥት ሳባ ማንነት ሲያወሳ ማጠቃለያና መደምደሚያ የቀረቡት በዚሁ ክፍል ነው።

ከላይ በመግቢያው ላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች ሌላ መጽሐፉ አያሌ ቁም ነገሮችን አካትቷል። በክፍል አንድ ከተጠቀሱት ኦሮሞ ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ካበረከታቸው አስተዋጽኦዎች፣ ኦሮሚኛ (አፋን ኦሮሞ) ለአማርኛ ቋንቋ ብልፅግና ያደረገው አስተዋጽኦ ተመልክቷል። ስንቶቻችን ነን የሚከተሉት የአማርኛ ቃላት ከኦሮሚኛ የተገኙ መሆናቸውን የምናውቀው? ጮማ፣ ጭኮ፣ ወጌሻ፣ ደንቃራ፣አንጋፋ፣ በርጩማ፣ ዳክዬ፣ ቡራ ከረዩ፣ አባወራ፣ ቀልብ፣ ወዳጅ፣ ቀዬ፣ ጀብዱ፣ ቢላዋ፣ ወዘተ። የኦሮሚኛ ፍልስፍናዊ የአስተሳሰብ ሥርዓትን የሚያመለክቱ በርካታ ፈሊጣዊ አነጋገሮችና ይትብሐሎች በአማርኛ ቋንቋም ውስጥ መገኘታቸው በሁለቱ ማኅበረሰቦች መካከል የባህል መወራረሶች መኖራቸውን ያሳያሉ። ”ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል”፣ ”የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው”፣ ”የወደቀ ግንድ ምስጥና ምሳር ይበዛበታል”፣ ”ህልም ፈርተው ሳይተኙ አያድሩም”፣”አህያ ከአልጋ ሲሉት ከአመድ”፣ ወዘተ ከኦሮሚኛ የተወረሱ ብሂሎች ናቸው።

በአምልኮና በሃይማኖት ዘርፍም የኦሮሞ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። ኦሮሞ እንደ አማራ በአንድ እግዚአብሔር (ዋቃ) ያምናል። በመናፍስት ደረጃ ቦረንትቻና አቴቴ ከኦሮሞ የተወረሱ ናቸው። ውቃቢም ከአቴቴና ከአውሊያ ጋር ተመሳሳይ ነው። በፈረስ ግልቢያና በፈረስ ላይ ጨዋታ፣ ጉግስ፣ ሶምሶማ፣ ደንገላሳና ሽምጥ ከኦሮሞ የተቀሰሙ የፈረስ ግልቢያና የጨዋታ ጥበቦች ናቸው። በሌላ በኩል በአማርኛ ቋንቋ የሚጠበቡ የኦሮሞ ደብተራዎች፣ ሊቃውንትና ቀሳውስት እንዳሉና እንደነበሩ ስንቶቻችን እናውቃለን? ስመ ጥሮች አለቃ ጥበቡ ገኔ፣ አለቃ ደስታ ነገዎ (የገብረ ክርስቶስ ደስታ አባት)፣ መሪ ጌታ ወልዴና መሪ ጌታ ከበደ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው። በተመሳሳይ ኦሮሞዎች ለኢትዮጵያ ዳንኪራ፣ ሙዚቃ፣ የንድፍ ጥበብ፣ ወዘተ ያደረጉዋቸው አበርክቶዎች ከፍተኛ ናቸው።

ከላይ እንደተመለከተው በተለይ የኦሮሞ ዘር ምንጭን በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ከታወቁት ኢትዮጵያውያንና የውጭ የታሪክ ተመራማሪዎች ጋር ልዩነት አላቸው። አባ ባሕርይ፣ አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ፣ አለቃ ታዬ፣ ተክለጻዲቅ መኩሪያ፣ ይልማ ደሬሳ፣ ጀርመናዊው ኤ ሃበርላንድ፣ መሐመድ ሐሰን፣ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፣ ወዘተ ስለኦሮሞ አመጣጥ (በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ውጭ በፍልሰት) የጻፉትን ፕ/ር ፍቅሬ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አይቀበሉትም። አብዛኞቹ እነዚህ መጻሕፍት እንደሚነግሩን፣ ፕ/ር ፍቅሬ የአማራ ሴማዊነትንና የኦሮሞ ኩሻዊነትን በልዩነት አይቀበሉትም። እሳቸው ሁለቱም ማኅበረሰቦች ኩሻዊ መሆናቸውን ነው የሚያምኑት። ፕ/ር ፍቅሬ አማርኛና አማራ እንደ ቋንቋና እንደ ሕዝብ ከሦስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ የነበሩ መሆናቸውን አመልክተዋል። ኦሮሞን በተመለከተ ደግሞ የዘር ግንዱ ከመደባይ፣ ጅማና መንዱ ከሚባሉ ነገዶች መምጣቱን ይገልጻሉ። የሚገርመው የኦሮሞም ሆነ የአማራ ጥንታዊ የጋራ ቋንቋቸው ሲባ የተባለው መሆኑ ነው። ያም ሆነ ይህ የኦሮሞና የአማራ ጥንታዊ አባቶች ኢትዮጵያና ዳሸት ነበሩ።

የቀዳማዊ ምኒልክ የልጅ ልጅ ታላቁ አክሱማይት ከሁለት ሺሕ ስምንት መቶ ዓመት በፊት የግብፅ ፈርኦን ሆኖ ሲነግሥ፣ ዙፋኑን የጠበቁለት አማሮች ነበሩ። እንዲሁም ታላቁ አክሱማይት የመላ ኢትዮጵያ (ያኔ ግዛቷ በጣም ሰፊ ነበር) ንጉሠ ነገሥት ሲሆን፣ ሴት ልጁን ለሜስፖቶሚያ ንጉሥ ለናቡከደነፆር ሲድርለት አጅበውት የሄዱት የአማራ ወታደሮች ስለነበሩ፣ በዛሬዋ ኢራቅ ”አማራ” የተባለች ከተማ የተሰየመችው ለአማሮች ክብር ነው። ሌላው አስደናቂ ነገር ፕ/ር ፍቅሬ ስለቅዱስ ያሬድ ዝርያ የጻፉት ነው። ዛሬ ብዙ ኢትዮጵያውያን እንደሚያምኑት ቅዱስ ያሬድ ትግሬ ሳይሆን፣ የኦሮሞ አያት ካላት መደበይ ይወለዳል። እርግጥ አክሱም ኖሮአል (የተወለደው 505 ዓ.ም. ነው) ።

የኦሮሞና የአማራ የዘር ምንጭን በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ ከአራት ሺሕ ዓመት በላይ ወደኋላ ሄደው የዘር ግንዱን ከካምና ኩሽ አያይዘው፣ በመልከ ፄዴቅ በኩል የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥንታዊ አባት ከሆነው ”ኢትዮጵ” (ለእግዚአብሔር የቢጫ ወርቅ ስጦታ) ጋር ያጣምሩታል። በዚህም መሠረት፣ ”ኢትዮጵያ” የሚለው ስያሜ ”ፊቱ በፀሐይ የተቃጠለ” ከሚል የግሪክ ቃል (የግሪክ መዝገበ ቃላት ይህን አይልም) የመጣ ሳይሆን፣ ከጥንታዊው የኢትዮጵያውያን ሁሉ አባት ስም የተገኘ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከግሪክ ሥልጣኔ ቀድሞ የተከሰተ እንደመሆኑ፣ ግሪኮች ለኢትዮጵያውያን ስም ሊያወጡ እንደማይችሉ ፕ/ር ፍቅሬ ይነግሩናል። በመሆኑም ”ኢትዮጵያ” የሚለው ስያሜ የተገኘው የኢትዮጵያውያን ሁሉ አባት ከሆነው ከኢትዮጵያ ሲሆን፣ እሱ ከሚስቱ ሲና የወለዳቸው አሥር ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆቹ አያሌ ጎሳዎችና ነገዶች አፍርተው የሁሉም ኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች ለመሆን በቅተዋል ይሉናል ፕ/ር ፍቅሬ።

በፕ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ ውስጥ ሌላው አዲስ ነገር ሆኖ የቀረበው ጉዳይ የጎሳንና የነገድን ትርጉም የሚመለከት ነው። ጎሳ ”ጎፊ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን፣ ትርጉሙም ”ተናገረ” ማለት ነው። በዚህም መሠረት ጎሳ አንድ የጋራ ቋንቋ ያለው ማኅበረሰብ ማለት እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ይገልጻሉ። ነገድ የጎሳ ቅርንጫፍ ወይም ክፍል ሲሆን፣ በዘዬ የሚለያዩ ነገር ግን መሠረታቸው አንድ የሆነ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ማኅበረሰቦችን ያመለክታል። የባህል ልዩነቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የሶማሌ ሕዝብ ነው። በመሠረቱ ቋንቋቸው አንድ ቢሆንም ብዙ ነገዶችን ያካትታል። ከእነዚህም ነገዶች መካከል ኢሳ፣ ሀብረወል፣ ገደቡርሲ የሚጠቀሱ ናቸው። ለማንኛውም በፕሮፌሰሩ ትርጓሜ መሠረት ኦሮሞና አማራ ጎሳዎች ናቸው። በውስጣቸው ተመሳሳይ ቋንቋ (በዘዬ የሚለይ) እና ለየት ያሉ ባህሎች ያሏቸው ነገዶች ይኖራሉ። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ጎሳ የዘር ወይም የደም ምደባ ሳይሆን የቋንቋ ምደባ መሆኑን መገንዘብ ነው። እንደ ፕ/ር ፍቅሬ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ከአንድ የዘር ግንድ የመጡ እንደመሆናቸው፣ ልዩነታቸው በአብዛኛው የቋንቋ እንጂ የዘር ወይም የደም አይደለም። ይህ ከሕወሓት/ኢሕአዴግ አስተሳሰብ የተለየ ነው። በፕ/ር ፍቅሬ አመለካከት፣ ”ብሔር”፣ ”ጎሳ” ለሚለው ቃል ምትክ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ”ብሔር” የቦታ ስያሜ ነው (ዘብሔረ ቡልጋ፣ ዘብሔረ አማራ፣ ዘብሔረ ኦሮሞ እንዲሉ)። በመሆኑም ይላሉ ፕሮፌሰሩ፣ በኢትዮጵያ ያለው ጥያቄ ”የብሔረሰብ ጥያቄ” ወይም ”የብሔር ጥያቄ” ሳይሆን፣ የጎሳ (የቋንቋ) ጥያቄ ነው።

”አገር” የሚለው ቃል ደግሞ ጎሳ የሚኖርበት አካባቢ እንጂ መላ ኢትዮጵያ ማለት እንዳልሆነ ፕሮፌሰሩ ያመለከቱ ሲሆን፣ ለመላ ኢትዮጵያ ”ዜጋ” የሚለው ቃል እንደሚሻል አሳስበዋል። በዚህም መሠረት ጎንደር፣ ጐጃም፣ ወለጋ፣ ሸዋ… አገር ናቸው። በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ”ጠቅላይ ግዛት”፣ በደርግ ጊዜ ደግሞ ”ክፍለ አገር” ይባሉ ነበር። ይህም ሆኖ ፕ/ር ፍቅሬ ”አገር” የሚለውን ቃል እስካሁን በለመድነው መንገድ (ማለትም ለኢትዮጵያ) ብንጠቀምበት ጉዳት እንደሌለው አመልክተዋል። ቋንቋን በተመለከተ የባቢሎን ግንብ እስከፈረሰበት ጊዜ የሰው ልጅ ቋንቋ (ልሳነ-ሰብዕ) ሱባ የሚባለው ቋንቋ እንደነበርና ከዚያ በኋላ ግን የካህናት ቋንቋ ብቻ ሆኖ በኢትዮጵያ ከመልከ ፄዴቅ ወደ ኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ ወደ ደሸት (ደሴት)፣ ከደሸት ወደ እስያኤል (እሴ ወይም አፄ) ተላልፎ፣ በመጨረሻ ንግሥት ሳባ እሴን ገድላ በዙፋን ከተቀመጠች በኋላ በወለደችው (ከሰለሞን) ቀዳማዊ ምኒልክ በአዋጅ እንዲጠፋ ተደርጐ በግዕዝ እስኪተካ ድረስ መገልገያ ቋንቋ ሆኖ ጠቅሟል።

የዛሬዎቹን ጃማይካዎች በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ የሚሉት አስገራሚ ነው። ጃማይካውያን በግራኝ መሐመድ ለዓረቦች የተሸጡ የጀማና የአማራ ልጆች ሲሆኑ፣ የተጫኑባቸው መርከቦች በስፔናውያን ተማርከው በአሁኗ ጀማይካ ሊኖሩ መቻላቸውን ነግረውናል። እውነትም ያስገርማል። በሌላ በኩል የኦሮሞ ዝርያዎች ወደ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ ድረስ ዘልቀው መሄዳቸውን ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል። ምናልባትም እነአለቃ አፅመ ጊዮርጊስ፣ እነ አለቃ ታዬና እነ አቶ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ በኩል ከእስያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ጎሳ ነው እስከማለት የደረሱት በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የንግሥት ሳባና የሰለሞን ልጅ ቀዳማዊ ምኒልክ የሱባን ቋንቋ ከማጥፋቱም በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ (የመደባዮች፣ የአማሮች) የኮከብ ዓርማ በይሁዳ አንበሳ ምሥል ተክቶታል። በሱባ ቋንቋ የተጻፉ መጻሕፍትን ሲያቃጥል፣ ሌሎቹን ከጥፋት ለማዳን የሞከሩት መደባዮች ስያሜአቸው ወደ ኦሮሞ ተለውጧል። በሱባ ቋንቋ ኦሮሞ ማለት ”ዕውቀት ገላጭ፣ ተርጓሚ፣ ብልህ” ማለት ነው። ይህን ሁሉ የሚነግሩን ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ናቸው። እንዲሁም ኢትዮጵያውያን (መደባዮችና አማሮች) ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር ከእስራኤል የመጡ አርባ ሺሕ ሰዎች (በአብዛኛው ከጋዛ ነው የመጡት) ጋር እንዲደባለቁ ተገድደው የሱባ ቋንቋን ትተው ግዕዝ ተናጋሪዎች ለመሆን እንደበቁ ፕሮፌሰሩ በመጽሐፋቸው ውስጥ ይገልጻሉ። እነዚህ አርባ ሺሕ አጋዚያን ራሳቸውን ያዳቀሉ ”አቡሳውያን” ሲሆኑ፣ ሐበሻ የሚለው ቃልም ከዚሁ የመዳቀል ገጽታ የመጣ ቃል ነው። ሐበሻ የሚለው ቃል ”አበሳ” (በመከለስ ወይም በመዳቀል የመጣ አበሳ ወይም እንከን) የሚል ክብረ ነክ ፍቺ ያለው መሆኑን ፕሮፌሰሩ ነግረውናል። ያም ሆኖ የሸዋው ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ራሳቸውን ”የጋላ እና የኢቢሲኒያ ንጉሥ እያሉ ሲጠሩ፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ደግሞ ”ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ስዩመ እግዚአብሔር ድል አድራጊው የይሁዳ አንበሳ” በሚል የማዕረግ ስም ይጠሩ ነበር። ይህ ደግሞ በሰለሞናዊው (የቀዳማዊ ምኒልክ) ሥርወ መንግሥት ስም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለመሆን የማይታለፍ ግዴታ ነበር። ሁሉም ግን የኦሮሞ መሠረት ያላቸው ናቸው። የሰለሞናዊውን ሥርወ መንግሥት ያስመለሰው ይኩኖ አምላክ ጭምና መሠረቱ ኦሮሞ ነው። ይኩኖ አምላክ የጊፍቲ መንደያ ልጅ ነው።

ሌላው ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ አስደናቂ ግኝት የግዕዝ ፊደል እየተባለ ስለሚጠራው ያሰፈሩት ሐሳብ ነው። ይህ ፊደል ብዙ ጊዜ እንደሚባለው፣ ከአርመን የፊደል ገበታ የተቀዳ ሳይሆን፣ ከሁለት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የነበረ ነው። በመሆኑም ጉዳዩ የተገላቢጦሽ ነው። ግሪኮች ናቸው ፊደል ከኢትዮጵያ የቀዱት። ከግሪክ ፊደል በፊት የኢትዮጵያ የሱባ ቋንቋ ፊደል ነበር። እውነትም አስገራሚ ግኝት! ምን ይኼ ብቻ፣ ራሱ የላቲን ፊደል ከሱባ ቋንቋ ፊደል ሳይኮርጅ ይቀራልን? ከዚህም ተነስተው፣ ፕ/ር ፍቅሬ ኦሮሚኛን በላቲን ፊደል መጻፍ የሚያኮራ ሳይሆን የሚያሳፍር ድርጊት ነው ይሉናል። ከዚህም በላይ ኦሮሚኛን በሳማዊ (በግዕዝ) ፊደል (ከጊዜ በኋላ ሱባ ወደ ሳባ ቋንቋ ተቀይሮአል) መጻፉ በአምስት ዓበይት ምክንያቶች ተመራጭ እንደሚያደርገው ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው።

1. የግዕዝ ፊደላት ከላቲኑ በተሻለ የኦሮሞን የንግግር ድምፆች ይወክላሉ፣

2. ኦሮሚኛን በኢትዮጵያ ፊደላት መጻፍ ጊዜና ገንዘብ ይቆጥባል፣

3. ሳባዊ/ግዕዝ ፊደላት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በደንብ ይታወቃሉ፣

4. ሳባዊ/ግዕዝ ፊደል ኦሮሞን ጨምሮ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አንጡራ የባህል ሀብት ነው፣

5. ከላቲን ይልቅ በግዕዝ ፊደል መጠቀም ኦሮሞዎችን እንደ ባዕድ ከመታየት ያድናቸዋል (ከላይ እንደተመለከተው ኦሮሞዎች የኢትዮጵያ መሥራች ሕዝብ ናቸው)። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፕ/ር ፍቅሬ ኦሮሚኛ በኢትዮጵያ ከአማርኛ ጐን ለጐን ሁለተኛው የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሐሳብ አቅርበዋል። በተጨማሪም ፕ/ር ፍቅሬ ኦሮሞዎችን ”ኦሮሚያ” በምትባል ጠባብ ቦታ መገደብ ከመሠረቷት ኢትዮጵያ ማራቅ ስለሆነ፣ ሐሳቡን እንደማይደግፉ ገልጸዋል።

አስደናቂ ሊባሉ የሚችሉ ሌሎች ቁም ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል።

”የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተፈጠረችው ከሦስት ሺሕ አራት መቶ ዓመት በፊት በንግሥና ስሙ ”ሰንደቅ ዓላማ” ይባል በነበረው አፄ ወይም እሴ ነው። ሙሴን በእግዚአብሔር ሥርዓት ያሠለጠነው ኢትዮጵያዊው ጥንት አባት የትሮአብ ነው። የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበረው አፄ ወይም እሴ (ከላይ የተጠቀሰው) በዚህች መሬት ላይ 480 ዓመት ኖሮአል። የግራኝ መሐመድ ወታደሮች ሙስሊሞች ብቻ አልነበሩም፤ ክርስቲያን አማሮች፣ ኦሮሞዎችና ሌሎች ጎሳዎች ነበሩባቸው። ሰአፄ ዮሐንስ በአፄ ቴዎድሮስ ላይ ቂም የያዙት የቴዎድሮስ ወታደር ሆነው ሲዋጉ ጀብዱ ባለመሥራታቸው ቴዎድሮስ ዝቀተኛ የሆነውን የባላምባራስ ማዕረግ ስለሰጧቸው ነው።”

በመጽሐፉ ክፍል ሦስት ከተመዘገቡ አበይት ፍሬ ነገሮች መካከል ደግሞ የሚከተሉት የሚጠቀሱ ናቸው።

”አማራው እንደ ሥርወ ኢትዮጵያን አልገዛም። በየክፍለ አገሩ ግን የአማራ ንጉሦች ነበሩ (በንጉሠ ነገሥትነት አይደለም) ። በተመሳሳይ፣ የትግሬ ወይም የኦሮሞ ሥርወ መንግሥታት የሚባሉ አልነበሩም። ባለፉት ሦስት ሺሕ ዓመታት የነበሩት ሥርወ መንግሥታት የሰለሞንና የዛግዌ ሥርወ መንግሥታት ሲሆኑ፣ በእነዚህ ውስጥ ለሰባት መቶ ዓመታት በንጉሠ ነገሥትነትና በንግሥተ ነገሥትነት የገዙት የኦሮሞ ጎሳ አባላት ናቸው። አማሮች የገዥ መደብ አካላት ተደርገው የሚወሰዱት በተለይ አማርኛ አገራዊ የመግባቢያ ቋንቋ ሆኖ ስላገለገለ ነው። አፄ ምኒልክ አልገብርም ካሉት የአካባቢ ንጉሦች በስተቀር፣ በሰላም የገቡትን መሪዎች በአካባቢያቸው የነበራቸውን ሥልጣንና ጥቅም አልነኩም። ባለፉት አራት ሺሕ ዓመታት በኢትዮጵያ አራት ሥርወ መንግሥታት ነበሩ። እነሱም ኩሻዊ፣ የኢትዮጵ፣ ሰለሞናዊና የዛጉዌ ሥርወ መንግሥታት ናቸው። የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት መሥራች ንጉሥ ሰለሞን ሳሆይ ከምትባል ኢትዮጵያዊት ሴት (ከንግሥት ሳባ ጋር ሰለሞንን ለመጐብኘት የሄደች) የወለደው ነው። ቀዳማዊ ምኒልክ በአሥራ አራት ዓመቱ አባቱን ሰለሞንን ለመጐብኘት ወደ እስራኤል ሄዶ ሲመለስ፣ አርባ ሺሕ የኢየሩሳሌምና የጋዛ ወታደሮችን አስከትሎ ስለነበር፣ የአገሬው ሰዎች የነበሩት ራያና አዘቦ አናስገባም በማለት ጦርነት ገጥመውት የነበረ ቢሆንም፣ በድል አድራጊነት ዙፋን ላይ ሊቀመጥ በመቻሉ፣ በኢትዮጵያውያን ላይ የአይሁድ ሥርዓተ አምልኮና ባህል ሊጭን ችሏል፤ ወታደሮቹንም (አይሁዳውያንና የነገደ የቅጣን አባላት) ”አግአዚ” የሚል ስያሜ አውጥቶላቸዋል። ግዕዝ ከክርስቶስ ልደት ከአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመት በፊት ጀምሮ የአግአዚ መንግሥት ቋንቋ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፣ እስካሁንም በቤተክርስቲያን እያገለገለ ይገኛል። ትግሬዎች (ተጋሩ፣ ተጋሩዎች) ከክርስቶስ ልደት በፊት በ330 ዓ.ዓ. አካባቢ ከጥንቷ ባቢሎን (ከዛሬዋ ኢራቅ) እና ከሶሪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ናቸው። በመሆኑም ተጋሩዎቹ ከአግአዚያኖቹ የተለዩ ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ዕድሜው ከ22 እስከ 25 ዓመት በነበረበት ጊዜ ለሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሮአል። የክርስትና ሃይማኖት በይፋ የኢትዮጵያ ሃይማኖት የሆነው በአራተኛው ክፍለ ዘመን ይሁን እንጂ፣ ሃይማኖቱ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከአንደኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው። በኢትዮጵያ ከ325 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1951 ዓ.ም. ድረስ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርኮች ይሾሙ የነበሩት ከግብፅ አሌክሳንደሪያ ነበር። ሼህ ሁሴን ጅብሪል (የወሎው ኦሮሞ ነብይ) የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በእናታቸው ላይ ቅድመ አያት ናቸው። አፄ ኃይለ ሥላሴ በወንድ አያታቸው በኩል ደግሞ ቅድመ አያታቸው ወልደ መለኮት የሚባሉ የትግሬ ሰው ናቸው። ”የብሔር ብሔረሰቦች ነፃነት እስከ መገንጠል” የሚለው መብት፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ለውስጥ አስተዳደር ነፃነት ራስ ገዝነትን ጨምሮ” በሚል ቢተካ ይመረጣል። ከሪፐብሊክ በተቃራኒ ያለው የዲሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ወደፊት በጥልቀት መጠናት አለበት።”

ከላይ የተገለጹትና ነጥብ በነጥብ የተዘረዘሩት ፍሬ ነገሮች ለእኔ አዲስ የመሰሉኝና እንዲሁም አንድምታቸው ክብደት የሚሰጣቸው ናቸው ያልኳቸው ሲሆኑ፣ በመጽሐፉ ውስጥ የንዑስ ርዕስ ሥር የተመለከቱትን ዝርዝር ትርክቶች ለማወቅና ለመረዳት ሙሉ መጽሐፉን ከዳር እስከ ዳር ማንበብ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። ከዚህ ቀጥለን ለማየት የምንሞክረው፣ የመጽሐፉን ይዘት ተዓማኒነት ይሆናል።

የመጽሐፉ ተዓማኒነት

ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በመጽሐፋቸው ውስጥ ከአራት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በላይ ወደኋላ እየሄዱ የትርክታቸውን መሠረት ስለሚገነቡ፣ ከጊዜው ርቀት አኳያ የተዓማኒነት ጥያቄ ቢነሳ የሚያስገርም አይሆንም። ለሩቆቹ ዘመናት ፕሮፌሰሩ ከተጠቆሙባቸው የመረጃ ምንጮች መካከል በሱዳን የዛሬ ሃምሳ ዓመት ከቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ ውስጥ የተገኙ ጥንታዊ የግዕዝ ብራና ጥቅሎች ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህም ”መጽሐፈ ሱባዔ” እና ”የኢትዮጵያ ትንሳዔ ታሪክ” በሚሉ ርዕሶች የተጻፉ ሰነዶች ናቸው። ሰነዶቹ ከአራት ሺሕ ዓመት በፊት የነበረውን ታሪክ የሚናገሩ ቢሆንም፣ ዕድሜያቸው ግን ሦስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ግድም ነው። ሰነዶቹ በመጀመሪያ የተጻፉት በጥንታዊው የኢትዮጵያ ቋንቋ በሱባ ቋንቋ ሲሆን፣ አክሱማዊው ሲራክ የተባለ ሰው (በ879 ዓ.ም. አካባቢ የነበረ) ከሱባ ቋንቋ ወደ ግዕዝ ተርጉሞታል። አፄ ላሊበላ ከሱዳን ቋንቋ ወደ ግዕዝ ተርጉሞታል። አፄ ላሊበላ በሱዳን በኩል ሲያልፍ፣ የኑቢያ (የሱዳን) ንጉሥ ለላሊበላ ”የመጽሐፈ ሱባዔን” ቅጂ እንደሰጠው ይታመናል። ላሊበላም ቅጂውን አባዝቶ በቤተ መጻሕፍቱ እንዳኖራቸውና ከዚያም አፄ አምደ ጽዮን ቅጂዎቹን እንደገና አባዝቶ በየገዳማቱ እንዳኖራቸው ተገምቷል። ይሁንና ከግብፅ የመጣው ፓትሪያርክ ቅጂዎቹን ሲያወድም አንድ ቅጂ ተርፎ፣ ይህ የተረፈው ቅጂ ነው በቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ ውስጥ የተገኘው።

እዚህ ላይ የሚነሱት የተዓማኒነት ጥያቄዎች ሰነዶቹ እንዴት ሦስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ሊቆዩ ቻሉ?

አክሱማዊው ሲራክ የሱባ ቋንቋን ማወቁ እንዴት ይረጋገጣል? ሲራክ ያውቃቸው የነበሩት ሁለት ሌሎች ቋንቋዎች (ከግዕዝ ሌላ) የትኞቹ ነበሩ? የግብፅ ፓትሪያርክ (ለኢትዮጵያ የመጣው) የመጽሐፉን ቅጂዎች በሙሉ (ከአንድ ቅጂ በስተቀር) እንዴት ሊያስወድማቸው ቻለ? አፄ አምደ ጽዮን ቅጂዎቹን በየገዳማቱ አሰራጭቷቸው ስለነበር፣ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ለማውደም (ሴራው ሳይደረስበት) አስቸጋሪ አይሆንም ነበር ወይ? ሰነዶቹ ወደ ግዕዝ ሲተረጎሙ፣ የትርጉም ስህተቶች ሊኖሩ አይችሉም ወይ? በአጠቃላይ ሰነዶቹ በተቀነባበረ ሴራ የተቀመሩ የፈጠራ ታሪኮች አለመሆናቸውን በምን እናረጋግጣለን? ስለነዚህ ጥንታዊ ሰነዶች የዚህን ያህል የተዓማኒነት ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ፣ የእስካሁኖቹ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊዎች (የአገር ውስጥም የውጭ አገርም ተመራማሪዎች) የተጠቀሙባቸው የመረጃ ምንጮች ሁሉ ዋጋ ቢስ ይሆናሉን? በሌላ በኩል የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት የሚጠራጠሩ ሰዎች፣ ለምሳሌም ከክርስትና ውጪ ያሉ ሃይማኖቶችና በሳይንስ ብቻ ነው የምናምነው የሚሉ ኢ አማኒያን፣ ከቅዱስ መጽሐፍ የተጠቀሱትን ማስረጃዎች እንዴት አምነው ሊቀበሉ ይችላሉ? ለምሳሌ አፄ ወይ እሴ 480 ዓመት ኖረ የሚለውን አንድ በሳይንስ ብቻ ነው የማምነው የሚል ኢ አማኒ እንዴት ሊቀበለው ይችላል? ትግሬዎች ከሶሪያና ከኢራቅ ነው የመጡት የሚባለውን ትግሬዎች ይቀበሉታል ወይ?

በሌላ በኩል በሳይንስ ጭምር የሰው ልጅ መገኛ ኢትዮጵያ መሆኗ ስለተረጋገጠ (ሉሲና አርዲ)፣ የሰው ልጅ ሥልጣኔም የጀመረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ቢባል ያስኬዳል። ኦሮሞና አማራ በጊዜ ሒደት በቋንቋ ተለያዩ እንጂ የዘር ግንዳቸው አንድ ነው፣ አገራቸውም ኢትዮጵያ ነች ቢባል ከሳይንሱ ተነስቶ መላምትም ቢሆን፣ ተቀባይነት የሌለው ሐሳብ አይሆንም። ከግብፅ፣ ከግሪክ፣ ከሮም፣ ከቻይና፣ ከህንድ በፊት የሰው ልጅ ሥልጣኔ የጀመረው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሆነ፣ የሱባ ቋንቋ ሥልሳ ሰብ ነበር፣ የመጀመሪያው የሰው ልጅ ፊደል የሱባ ፊደል ነበር ብንል ማን ይረታናል? በተመሳሳይ፣ ከጥንታዊ ሥልጣኔአችን በመጀመሪያ በሱባ ቋንቋ በኋላ በግዕዝ የተተረጐሙ ”መጽሐፈ ሱባዔ”፣ ”የኢትዮጵያ ትንሳዔ ታሪክ”፣ ወዘተ የተባሉ የብራና ሰነዶች እጃችን ገብተዋል ብንል፣ የሰው ልጅ መገኛ እስከሆንን ድረስ ማነው ደፍሮ የሚጠይቀን? ፕ/ር ፍቅሬ እንደሚሉት በስንፍናችን ነው ጥንታዊ ታሪካችንን ለሌሎች አሳልፈን የሰጠነው! እናም ለወጉ ያህል የተዓማኒነት ጥያቄዎች አነሳሁ እንጂ፣ የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ትርክት ለእኔ በጣሙን ነው የተመቸኝ። ቀጥለን መጽሐፉ ወደፊት ለምንገነባት ኢትዮጵያ ያለውን አንድምታ ለማሳየት እሞክራለሁ።

የመጽሐፉ አንድምታዎች

መጽሐፉ ተደብቀው የኖሩ አዳዲስ የኢትዮጵያ ታሪክ ገጽታዎችን ይፋ ስላደረገ፣ የአገሪቱን ታሪክ በአዲስ መልክና ዕይታ እንደገና ለመጻፍ ያስችላል ብዬ እገምታለሁ። ለምሳሌ ኦሮሞ በማዳጋስካር በኩል ከእስያ የመጣ ጎሳ ነው የሚባለውን አፈ ታሪክ ከእንግዲህ ለመቀበል አዳጋች ነው የሚሆነው። ይህን ነገር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም በመጽሐፋቸው (የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ) ውስጥ ገልጸውታል። እሳቸው ኦሮሞ ከየትም የመጣ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ነባር ሕዝብ መሆኑን አስምረውበታል። በፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከሁሉም የዓለም ሥልጣኔዎች (ከግብፅም ጭምር) ቀደምትነት ያለው (የሰው መገኛ ኢትዮጵያ ስለሆነች) እና በተለይ በአካባቢው ወዳሉት አገሮች (ግብፅ፣ ዓረቢያ፣ ሲሪያ፣ ኢራቅ፣ ህንድ፣ ወዘተ) ተስፋፍቶ የነበረ መሆኑን አስረግጦ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ እንደገና በአዲስ መልክ መጻፍ የሚቻል ይመስለኛል። ሆኖም የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ (ቢያንስ ከ4,500 ዓመታት በፊት ጀምሮ) በጊዜ ሒደት ወደ ዘመናዊ (የአውሮፓ) ሥልጣኔ መሸጋገር ስላቃተው፣ መጨንገፉን መካድ የሚቻል አይመስለኝም።

አገረ ኢትዮጵያን በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን አስተምረውናል። በመጀመሪያ ”አገር” የሚለውን ቃል የምንጠቀምበት ለተወሰነ አካባቢ መጥሪያ ቢሆንም፣ በጊዜ ሒደት ለመላ አገሪቱ መጠሪያ ስለሆነ፣ በዚሁ መቀጠሉ የሚበጅ መሆኑን ቢያሳስቡም፣ የእሳቸው ምርጫ ግን ”ዜጋ” የሚለው ቃል መሆኑን ነግረውናል። እኔም ”አገር” የሚለው ቢቀጥል እመርጣለሁ።

ከፕ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ እንደተረዳሁት፣ ”ኢትዮጵያ” በግሪክኛ ቋንቋ ”በፀሐይ የተቃጠለ ፊት ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባት አገር” ማለት ሳይሆን፣ ከጥንታዊ የኢትዮጵያውያን አባት ከ”ኢትዮጵ” የመጣ መጠሪያ መሆኑን ነው። ትርጉሙም ”ለእግዚአብሔር የቢጫ ወርቅ ስጦታ” ማለት ነው። ይህም በጣም ተመችቶኛል። እንዲሁም ባለሦስት ቀለማቱ የኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማ ከ3,400 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን፣ በመጀመሪያ የነበረው ዓርማ ኮከብ፣ በኋላ ደግሞ ይታይበት የነበረው ዓርማ የይሁዳ አንበሳ እንደነበር ፕሮፌሰሩ ገልጸውልናል። የዚህ አንድምታ ግልጽ ነው። ኮከቡ ከክርስትና ሃይማኖት ጋር የተያያዘ በመሆኑና እንዲሁም የአንበሳው ዓርማ ከይሁዲነት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ (የሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት)፣ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሙስሊሞችም አገር ስለሆነችና የይሁዲነትን የበላይነት የምንቀበልበት ምክንያት ስለሌለ፣ ሁለቱም ምልክቶች በባንዲራችን ላይ መኖር የለባቸውም ወደሚለው ሐሳብ አጋድላለሁ። በዚህም መሠረት ከኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ የኢሕአዴግ ኮከብም መነሳት ያለበት ይመስለኛል።

”ብሔር ብሔረሰብ” ስለተባለው ድርብ ቃል ፕ/ር ፍቅሬ የጻፉት አሳማኝ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ”ብሔር” የቦታ ስም ነው፣ ዘብሔረ ቡልጋ እንዲሉ። ”ብሔረሰብ” ደግሞ የሰው አገር እንደማለት ነው። ፕ/ር ፍቅሬ በእነዚህ ቃላት ፈንታ በ”ጎሳ” እና ”ነገድ” ተጠቅመዋል። ”ጎሳ” በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፍቺ አለው። ለምሳሌ ኦሮሞ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ሕዝብ ወይም ጎሳ ነው። ”ነገድ” የጎሳ ቅርንጫፍ ነው። የኢሕአዴግ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ለ”ብሔር”፣ ”ብሔረሰብ” እና ለ”ሕዝብ” አንድ ትርጉም ነው የሰጠው። በመሆኑም ልዩነታቸውን ማወቅ አይቻልም። በአሳሳችና በአደናጋሪ ቃላት ከመጠቀም ይልቅ፣ ትርጉማቸው ግልጽ በሆኑት ”ጎሳ” እና ”ነገድ” መጠቀሙ ስለሚሻል፣ ”ብሔር” እና ”ብሔረሰብ” የሚባሉትን ቃላት አሁን ባላቸው ትርጉም ባንጠቀምባቸው እመርጣለሁ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሕወሓት/የኢሕአዴግ ”የብሔር ጥያቄ” በፕ/ር ፍቅሬ ትርጉም ”የጎሳ ጥያቄ” ስለሚሆን፣ ይህ ደግሞ የቋንቋ ጥያቄ ስለሚሆን፣ የችግሩ አፈታት ኢሕአዴግ ከተጠቀመበት መፍትሔ በጣም የተለየ ነው የሚሆነው። ፕ/ር ፍቅሬ ከአማርኛ ቀጥሎ ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚናገሩት ኦሮሚኛ ቋንቋ (አፋን ኦሮሞ) ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሐሳብ አቅርበዋል። በእኔ ግምት ትክክለኛው መፍትሔ ይህ ይመስለኛል። የሚጻፈውም በግዕዝ ፊደል ይሆናል።

ሌላው ክብደት የሚሰጠው አንድምታ አማራ እንደ ሕዝብ፣ እንደ ሥርወ መንግሥት ወይም እንደ ገዥ መደብ ማንንም አልጨቆነም ብለው ፕ/ር ፍቅሬ ከደረሱበት ድምዳሜ የሚመነጨው አመለካከትና የፖሊሲ ሐሳብ ነው። ከዚህ አመለካከት ተነስተን፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሌሎች ማኅበረሰቦችን (ጎሳዎችን) በተለይም ኦሮሞውን ”ከአማራ ጭቆና ነፃ አወጣኋችሁ” የሚለው ምንም ታሪካዊ መሠረት የሌለውና ለራሱ ሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ብቻ ሆኖ መታየት እንዳለበት መገንዘብ እንችላለን። እንዲያውም በአሁኑ ጊዜ ”የኦሮሞ ደም የእኔ ደም” ነው የሚለው አማራና ”የአማራ ደም የእኔ ደም ነው” የሚለው ኦሮሞ፣ ለእውነታው የቀረበ አገላለጽ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በሌላ በኩል ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ”ኦሮሚያ” የተባለውን ክልል በተመለከተ፣ ለኢትዮጵያ ልጅ ኦሮሞ ትጠበዋለች፤ የተፈጠረባትና ያስተዳደራት ሰፊዋ ኢትዮጵያ እያለችለት፣ በጠባቧ ”ኦሮሚያ” መወሰንና መገደብ አይገባውም ይላሉ። የዚህም አንድምታ ግልጽ ባይሆንም፣ ፕሮፌሰሩ ”ኦሮሚያ” የሚባለው ክልል ጨርሶ ቢታጠፍ፣ ቢታጠር ወይም ባይኖር የሚቃወሙ አይመስለኝም። በእሳቸው አተያይ ኦሮሚያ የቋንቋ (የጎሳ) ክልል ከሆነና ኦሮሚኛ ቋንቋ የመላ ኢትዮጵያ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሐሳብ ካቀረቡ፣ ኦሮሚያ እንደ ቋንቋ ክልል የሚኖርበት ምክንያት አይኖርም። በተመሳሳይ አማራ ክልል የቋንቋ (የአማርኛ) ክልል ስለሆነ፣ አማርኛ ደግሞ የመላ ኢትዮጵያ የመግባቢያ ቋንቋ እንደመሆኑ፣ የአማራ ክልል መኖር ትርጉም የለውም።

የፌዴራል አወቃቀርን በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ የሚደግፉት ይመስላል። ግን የኦሮሞንና የአማራን በቋንቋ መካከል (ኦሮሚያና አማራ ክልሎች) ስለማይደግፉ፣ በጎሳ ላይ የተመሠረተውን ፌዴራሊዝምን የሚቃወሙ ይመስለኛል። ይህ ከሆነ ፕሮፌሰሩ የሚደግፉት በጎሳ ላይ ያልተመሠረተ ፌዴራሊዝምን ነው ብሎ መደምደም የሚቻል ይመስለኛል። በዚህ ጉዳይ ላይ የመጽሐፉ አንድምታ ይህ እንደሆነ መገመት ይቻላል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የጎሳ ያልሆነውም ፌዴራሊዝም በከፊልም ቢሆን የጎሳ ፌዴራሊዝም የሚሆንበት ተጨባጭ ሁኔታ ስላለ፣ የውስጥ አስተዳደር ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለኢትዮጵያ የሚበጃት ዴሞክራሲያዊ አሀዳዊነት (ዲሞክራቲክ ዩኒተሪ ስቴት) ይመስለኛል። የጎሳ ባልሆነም ፌዴራሊዝም ትግራይ ክፍለ አገር ትግራይ ሆና ስለምትቀጥልና ፌዴራሊዝሙ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ትግራዊነትን እያጎላ ስለሚሄድ፣ ይህንን አሉታዊ አዝማሚያ በዴሞክራሲያዊ አሀዳዊነት መግታቱ ብልህነት ነው። በትግራይ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ አዝማሚያ በአፋር፣ በኦጋዴን፣ በጋምቤላ፣ ወዘተ እየጠነከረ የሚሄድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የመንግሥት ሥርዓትን በተመለከተ ፕ/ር ፍቅሬ ከዴሞክራሲ ይልቅ ሪፐብሊካኒዝምን እንደሚመርጡ ገልጸዋል። እዚህ ላይ ብዙ ግልጽ ያልሆነ ነገር አለ። ሪፐብሊክ የሚቋቋመው በዴሞክራሲ አይደለም እንዴ? በሌላ በኩል ሪፐብሊክ ብዙ ጊዜ የሚመራው በሕዝብ በተመረጠ ፕሬዚዳንት ስለሆነ፣ እኔ ከማስበው ሥርዓት ጋር የተጣጣመ ነው። በእኔ አነስተኛ አመለካከት ለኢትዮጵያ የሚበጃት ዴሞክራሲያዊ፣ አሀዳዊ፣ ፕሬዚዳንታዊ የፖለቲካና የመንግሥት ሥርዓት ነው።

ለማጠቃለል፣ መጽሐፉ የተመሠረተባቸው የሩቅ ጊዜ ማስረጃዎች የተዓማኒነት ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አብሮነትን የሚሰብክ መጽሐፍ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ እጅግ አዎንታዊ እንደሚሆን እገምታለሁ። ከጥንታዊ አባቶቻችን ከኢትዮጵያና ከደሸት ያስተዋወቁንና በሁሉም ኢትዮጵያውያን መካከል ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን የሚሰብኩት ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ የታሪክና የፍቅር አባት ቢባሉ አይበዛባቸውም እላለሁ። ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን።
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ