ምሥራቃዊት ኮከብ

"ምሥራቃዊት ኮከብ" ጸጋዘአብ ለምለም ተስፋይ

ኒቆዲሞስ

እንደ መንደርደሪያ

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት/የኢኮኖሚክስ ምሩቅ፣ የዓለም ሰላምና ዕርቅ ግብረ ሠናይ ድ/ት የሥራ ባልደረባና የኢኮኖሚክስ መምህር የሆነው ወጣቱ ጸጋዘአብ ለምለም ተስፋይ በ2010 ዓ.ም. ባሳተመውና በ336 ገጾች በተቀነበበው በ‹ምሥራቃዊት ኮከብ› ፖለቲካዊ ድርሰት ላይ በጥቂቱ የግሌ ምልከታና አስተያየት የተካተተበት የወፍ በረር ዳሰሳ ለማድረግ ወደድኹ። በቅድሚያ ግን በመጽሐፉ የፊት ሽፋን ገጽ ላይ በተካተቱት ሥዕላት ላይ ጥቂት ሐሳቦችን በማንሳት ልንደርደር።

በቀስተ ደመና በተከበበች የዓለም ካርታ ራሳቸውን የመልካም ነገር ሁሉ ተምሳሌትና ምንጭ አድርገው የሚቆጥሩት፣ የሚያስቡት ምዕራባውያኑ ”ጨለማዋ አህጉር” ሲሉ በሚጠሯት በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘው አገራችን ኢትዮጵያ በብርሃን ደምቃና ጎልታ፣ አብርታና ፈክታ ትታያለች። በመካከል ላይ ደግሞ የተለያዩ የኅብረተሰባችንን ክፍል የሚወክሉ የሚመስሉ ኢትዮጵያውያን - እምነት፣ ዕውቀት፣ ድርጊት የሚል በነጭ ቀለም የተጻፈበት ብርሃናማ በትርን ይዘው ቆመው ይታያሉ።

በመጽሐፉ በግራ በኩል ደግሞ ኀዘን ያደቀቃት፣ ልቧን ያሳዘናትና ቅስሟን የሰበራት የምትመስል አንዲት ምስኪን ሴት በእንባና በሰቆቃ ውስጥ ሆና ትታያለች። በቀኝ በኩል ደግሞ በሩሕ ገጽን የተላበሰች ፍቅርን፣ ተስፋን የተመላች የምትመስል፣ ሐሤትና ደስታ በደመቀበት ፈገግታ የታጀበች ሌላኛዋ ወካይ ሴት/እናት ትታያለች። ይህች ኀዘን ደጋግሞ ያደቀቃት፣ ተስፋዋ የጨለመባት የምትመስል ወካይ ሴት/እናት ምስል በ1950ዎቹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪና ፖለቲከኛው ዶ/ር ኃይሉ አርአያን የተማሪነታቸውን ዘመን ግጥም ያስታውሰናል። የዶ/ር ኃይሉ ግጥም በከፊል እናስታውስ፡-

”… ይኽው ትታያለች ለሕዝብ በይፋ፣

ጥቁር ተከናንባ ጥቁር ተጎናጽፋ።

እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣

የእናት ሞት የአባት ሞት፣

የልጅ ሞት ያጠቃት፣

ለካ እሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት።”

ምሥራቃዊት ኮከብ
"ምሥራቃዊት ኮከብ" ጸጋዘአብ ለምለም ተስፋይ

ደራሲው ይህችን የዘመን ትንሣኤዋ እየደጋገመ የመከነባትን ‹ምሥራቃዊት ኮከብ› አገረ ኢትዮጵያን የፍቅር፣ የተስፋ፣ የምሕረት፣ የነጻነት ተምሳሌት ከሆነው ቀስተ ደመና የተቀዳውን - አረንጓዴ ቢጫና ቀዩን ሰንደቀ ዓላማችንን ከፍ አድርጎ ለዛሬዋና ለነገዋ ኢትዮጵያ ያለውን ትልቅ ሕልሙን፣ ርእዩን፣ ተስፋውን፣ በጎ ምኞቱን … የድርሰት ሥራው የፊት ገጽ ሸፋን ላይ አስቀድሞ ሥዕላዊ በኾነ መንገድ ለመተረክ የሞከረ ይመስላል። ”አንድ ምሥል ከሺሕ ቃላት በላይ ይናገራል።” እንዲሉ።

ምሥራቃዊቷ ኮከብ ኢ-ት-ዮ-ጵ-ያ፡-

”… እኛ የምንታገለው በእኛነታችን ላይ የተመሠረተ፣ እኛ ሌሎችን የምንገዛበት ሳይኾን እኛ ራሳችንን የምንገዛበት፣ የእኛነታችን አካል የኾነ፣ በዕውቀትና በምክንያት ከኹሉ በላይ በእምነታችን ላይ የተመሠረተ አገራዊ ማዕቀፋችን ውስጥ ያለው አገራዊ ርእያችንና አገራዊ ግባችን - አገራችንን በሁለተናዊ መልኩ *ምሥራቃዊት ኮከብ* የኾነችውን አገራችን በተግባር ዕውን ለማድረግ የሚተጋ የፖለቲካ ፓርቲ ይኾናል። …” (ገጽ 50)

ደራሲው ‹ምሥራቃዊት ኮከብ› አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም ካርታ ከምትገኝበት መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ/አቅጣጫን ከመጠቆም ይልቅና ባሻገር በድርሰቱ ውስጥ በይበልጥ በፍካሬያዊ ትርጉሙ ነው ጎልቶ የተገለጸው። ይኸውም ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊነት የሰው ልጆች ሁሉ ታሪክና ሥልጣኔ መነሻ አድርጎ በመበየን ኢትዮጵያዊነትን ለአፍሪካና ለሰው ልጆች ኹሉ እንደ ‹ምሥራቅ ኮከብ› ደምቆና ጎልቶ የሚታይ በሺሕ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔና ቅርስ የደመቀ ”ሰው የመኾን ሕይወት” ማንነት ተደርጎ ተሥሎአል፤ ቀርቧል። ”… ምሥራቅ ፀሐይ አይደለችም። ምሥራቋ በራሷ ምንም አይደለችም? ፀሐይ አይደለችም። መውጫዋ ግን ምሥራቅ ነው። ከዋክብት ብርሃናቸውን ከፀሐይ ይወስዳሉ። ለጨለማው ዓለም ድምቀት ኾነው ያበራሉ። ከዋክብት በቀን ምንም ናቸው። ለዚህም ሲባል አገራችን ‹ምሥራቃዊት ኮከብ› ብንል ቢያንስባት እንጂ ከግብሯ ፈቅ ያለ አይደለም። በነገራችን ላይ ምሥራቃዊት ኮከብ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሣይኾን ለመላው የሰው ልጆች ነው።” (ገጽ 65)

 ገጸ ባሕርያቱ በጽናት ቆሙለት እምነት፣ ዕውቀትና ድርጊት ውስጥ ውሉ እንደ ጠፋበት ልቃቂት ለተወሳሰበው የአፍሪካ/የአገራችን የሤራ፣ የርስ በርስ መበላላት፣ ለገነነበት ፖለቲካችን መፍትሔው - ፍቅር ፍቅር፣ ሰው ሰው የሚሸተው ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው። ይህ ኢትዮጵያዊ ማንነት ደግሞ ለአፍሪካና ለሰው ልጆች ሁሉ የፍቅር፣ የተስፋ ብርሃንን የሚፈነጥቅና ሰው የመኾን ሕይወት በተግባር የሚገለጽበት ሕያው የኾነ ማንነት ነው። የ‹ምሥራቃዊት ኮከብ› የፖለቲካ ፓርቲ ዋነኛው ተልዕኮውም - ”የኢትዮጵያውያንን አንድነትና ኅብረት የሚያጠናክሩ ኹለተናዊ ሥራዎችን የሚከውን ነው።” ይለናል።

‹ምሥራቃዊት ኮከብ› ድርሰት ይህ ኢትዮጵያዊ ማንነት በዘመናችን የተጋረጠበትን አስፈሪ የኾነ አደጋ አስቀድሞ የተመለከተና ብቸኛ መፍትሔውም ”ኢትዮጵያዊነት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ሰው መኾን ነው!” ሲል በዚህ ኢትዮጵያዊ ረቂቅ ፍልስፍና/እምነት ውስጥ ደራሲው በአፍሪካና በእናት ምድራችን ኢትዮጵያ ሰው የኾኑ ሰዎችን አድራሻቸው የትና ወዴት እንደሆነ አጥብቆ የሚጠይቅ፣ የሚፈልግ ይመስላል። በድርሰቱ ውስጥ የተሳሉት ገጸ ባሕርያት ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን፣ እምነታቸውን፣ ትውፊታቸውን … ወዘተ. ለማወቅ የሚጥሩና ሰው የመኾን ብርቱ ናፍቆትንና ጀግንነትን የተላበሱ ኾነው እናያቸዋለን። እናም በገጸ ባሕርያቱ ማንነት ውስጥ ‹እረ የሰው ያለህ!› ጩኸታቸው ብቻ ሣይኾን ሰው የመኾን ብርቱ ናፍቆታቸውና ራባቸው፣ ጽናታቸውና ቁርጠኝነታቸው ጎልቶ ይሰማል።

ይህ ሁሉ ሰው ባለበት ምድር እንደ ዲዮጋን በጠራራ ፀሐይ ፋኖስ አብርቶ ”ሰው እየፈልግን ነው።” የሚለው ብርቱ ቁጭትና ብሶት የታከለበት ፍለጋ ዛሬም በአፍሪካ/በኢትዮጵያችን ምድር መቀጠሉን ምሥራቃዊት ኮከብ ፖለቲካዊ ድርሰት በቁጭትና በተስፋ ይተርካል። በእርግጥም አፍሪካውያን ነጻነታቸውን በተጎናጸፉ ማግሥት ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ተስፋ ያደረጉት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጦች ትርጉም አልባና የግንቦት ደመና የኾነባቸው የ1960ዎቹ እና 70ዎቹ አፍሪካውያን ምሁራን the Beautifuls are not yet Born የሚል ተስፋ መቁረጥ ያየለበት ብሶትና ጩኸታቸውን እስከ መሰማት ድረስ መዝለቃቸውን የቅርብ ዘመን ታሪካችን ያስታውሰናል።

ይህ ብሶት፣ ይህ ጩኸት የበርካታ ኢትዮጵያውያንም ጩኸትና ብሶት ነበር። በ1960ዎቹ ለአገራችን ይበጃታል ባሉት የፖለቲካ መስመር ተሰልፈው ውድ ሕይወታቸውን የገበሩ የዛን ዘመን ትውልዶችን ታሪክ ስናጠና ፖለቲካችን የሔደበትን አሰቃቂ የኾነ ‹የአኬል ዳማ/የደም መንገድ› ወለል ብሎ ይታየናል። በእርግጥ ያ ሩቅ አላሚ ትውልድ ከራሱ ይልቅ ለወገኔ የሚል፣ የጭቁን ሕዝቡ መከራና ሰቆቃ ዕረፍት የነሣው፣ በቁጭትና በእልክ ራሱን ያለመሰሰት የሰጠ ቆራጥና ፋኖ ትውልድ ነበር።

ደራሲው በድርሰቱ ውስጥ ትርጉም ባለው ሐሳብና ምክንያታዊነት ለዛሬዋና ለነገዋ ኢትዮጵያችን ትንሣኤ ‹ምሥራቃዊት ኮከብ› ሕዝባዊ ፓርቲን ”ቤዛ” አድርጎ የተረከውን ያህል የቀደመው ያ ትውልድ ለአገሩና ለወገኑ የነበረውን ፍቅሩን፣ መቆርቆሩን፣ እምነቱን፣ ትዕግሥቱን፣ ወኔውን፣ ብርታቱን፣ ጽናቱን፣ ድካሙን፣ ድሉንና ሽንፈቱን … ወዘተ. ለመተረክና በትናንትናዋ፣ በዛሬዋና በነገይቱ ኢትዮጵያ ትውልዶች መካከል የመገናኛ ድልድይ ለመፍጠር በትረካው ውስጥ ያን ያህል ሲደክም፣ ሲለፋ አናየውም። ይልቁንም የቀደመው ትውልድ ለአገሩና ለወገኑ የነበረው ርእይ፣ የተጓዘበት መንገዱ፣ ሕልሙና ተስፋው በአብዛኛው ዳዋ የወረሰው፣ ጭጋግና ጨለማ ያጠላበት አስመስሎ አቅርቦታል።

በእኔ ምልከታ ያ ትውልድ ለእኔ የሚል ትውልድ አልነበረም። የዛሬዋ ኢትዮጵያችን አፍሪካችን የፖለቲካ አብዛኛው ገጽ ምዕራፍ ሲገለጽ ደግሞ ለእኔ ለእኔ የሚሉ አልጠግብ ባዮች፣ በሕዝባቸው መከራና ሰቆቃ ለመክበር ሰልፋቸውን ያሳመሩ ከሰዋዊ ባሕርይ አፈንግጠው አውሬነትን እየተለማመዱ ያሉ ‹ሰው መሰል ሰው› ጨካኞችን በአፍሪካችን/በአገራችን የፖለቲካ ሜዳ ላይ እንዳሻቸው ሲሆኑ እያየን፣ እየታዘብን ነው። ደራሲው ‹ምሥራቃዊት ኮከብ› የፖለቲካ ፓርቲ ይህን ከሰዋዊ ባሕርይ ያፈነገጠ አውሬነትን ለመታገልና ‹ሰው የመኾን ኢትዮጵያዊ ኃያልና ሕያው ማንነትን› በአፍሪካ ምድር ከፍ ለማድረግ የተቋቋመ ነው ይለናል። የዚህ ሰብአዊ ማንነት መደብዘዝ፣ የሞራል ውድቀትና ለዘመናት ጨለማ የወረሰው ለሚመስለው የፖለቲካችን መንገድና በደንበር ገተር ጉዞ- ያለ ፍቅር ለሚማስኑ፣ ያለ ራእይ ለሚደክሙ ፖለቲካኞቻችን የተስፋ ብርሃንን የሚፈነጥቀው ኢ-ት-ዮ-ጵ-ያ-ዊ ማንነት ነው ሲል ይደመድማል።

ኢትዮጵያዊነት ሰው የመኾን ሕይወት፡-

ከገጸ ባሕርያቱ አሣሣል ጀምሮ እስከ ታሪኩ አወቃቀርና ፍሰት ሃይማኖታዊ እሳቤና ፍልስፍና በጎላበት በ‹ምሥራቃዊት ኮከብ› ድርሰት ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ‹ሰው የመኾን ሕይወት› እምነት፣ ረቂቅ ፍልስፍና፣ ተግባራዊ ሕይወትና ሕያው ማንነት ኾኖ ቀርቧል። ይሁን እንጂ የምሥራቁንም ኾነ የምዕራቡን ዓለም ሃይማኖታዊና ዓለማዊ ፍልስፍና መሠረት በማድረግ ሰው የመኾን ፍካሬያዊ ትርጓሜውን በመተንተን አንጻር ‹ምሥራቃዊት ኮከብ› ሥነ-ጽሑፋዊ ውበትና ድምቀት ይጎለዋል። እስቲ በዚሁ ”ኢትዮጵያዊነት ሰው የመኾን ሕይወት” በሚለው እሳቤ ላይ በመመርኮዝ ጥቂት ሐሳቦችን ልጨምር።

ታላቁ ጠቢብ ሰለሞን በሕይወቱ ፍጻሜ ገደማ ለልጁ ለዳዊት ”ልጄ ሆይ ሰው ሁን!” ሲል ነበር ታላቅ የኾነ ምክሩን ያስተላለፈለት። ይህ ምን ማለት ይኾን … በምሥራቃዊት ኮከብ ድርሰት ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ሰው የመኾን ሕይወት ኾኖ የተፈከረበት ትርጓሜ በይበልጥ ከሃይማኖት አስተምህሮ አንጻር ሰፋ ያለ ትንታኔ ያለው ረቂቅ እሳቤ/ሃይማኖታዊ ፍልስፍና ነው። እንደ ሃይማኖታዊው አስተምህሮ ”ሰው የመለኮት ባሕርይ ተካፋይ የኾነ እጅግ የከበረ ፍጥረት ነው።” ሁሉም ፍጥረት ስለ ሰው ፍቅርና ስለ ሰው ክብር ተፈጥሯል። በሃይማኖትም ኾነ በሳይንስ ዓለም፡- ሰው የፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ ቁንጮ፣ ዕፁብ፣ ድንቅና ውብ ፍጥረት እንደሆነ ነው አብዝተው የሚናገሩት፣ የሚሞግቱት።

በስድስቱ ቀናት ከተፈጠሩት ፳፪ ፍጥረታት መካከል ሰውን የሚተካከል ፍጥረት የለም፤ አልኖረም፤ አይኖርምም። ፈጣሪ ሰውን ከፈጠረ በኋላ ”ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ መካከል ሰው እጅግ መልካም እንደሆነ ዐየ ይለናል። የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፊ ጸሐፊ ሊቀ ነቢያት ሙሴ። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ስለ ሰው አፈጣጠር ሲናገሩ ”ሰውን እጅግ ወደደው፣ ሳመው፣ አከበረውም።” ይሉናል። ”ቅዱሳት በሚሆኑ እጆቹ በርሱ አሳምሮ ፈጠረው፣ ሳመው፣ ወደደውም። የሕይወትንም መንፈስ በርሱ ላይ እፍ አለ።” እንዲሉ ሠለስቱ ምዕት/፫፻፲፰ ሊቃውንት በቅዳሴያቸው።

ይህ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ያለው ልዩ ፍቅር በሥነ ፍጥረት ታሪክ ሒደት ውስጥ ብቻ ሣይሆን ራሱ ፈጣሪ አምላክ ሰው በኾነበት አስደናቂ ፍቅሩ ”የሰው ልጅ ከተፈጠረበት የፍቅር ጥበብ ይልቅ የዳነበት የፍቅር ጥበብ ይልቃል፣ ይደንቃል ሲሉ የሃይማኖት መተርጉማን ሰው በፈጣሪው ዘንድ የተቸረውን ታላቅ የኾነውን የፍቅሩንና የክብሩን ልእልና ያመሰጥራሉ። ይህ የፈጣሪ ፍቅርም ከቤተልሔም ግርግም እስከ ቀራኒዮ ተራራ በፍቅር ተጀምሮ በፍቅር ተቋጨ ድንቅ ጥብብ እንደሆነ ያወሳሉ፤ ይተርካሉም።

በተመሳሳይም እንግሊዛዊው ድንቅ ደራሲ፣ ባለ ቅኔና ጸሐፊ ተውኔት ሼክሲፒርም በሐምሌት ድርሰቱ ውስጥ የሰውን ክቡርነትና ታላቅነት እንዲህ ይገልጸዋል፡- ”… ሰው እንዴት ዕፁብና ድንቅ ፍጥረት ነው፤ በቅርፁ በውበቱና በንግግሩስ እንዴት ያስደንቃል! በሥራውም መላእክትን ይመስላል፤ በመልኩም የፈጣሪውን! የዚህ ዓለም ድንቅ ውበት፣ ድንቅ ሥራ፣ ከፍጥረታት ሁሉ የላቀ!! ሐሳቡስ እንዴት ክቡር ነው። ለአፈጣጠሩም ጥበብ ማብቂያ አይገኝለትም።”

እንደ ሚልተን ያሉ የምድራችን ዕውቅ ባለ ቅኔም ‹Paradise Lost› በሚለው ሥራው ውስጥ ሰውን እንዲህ ይገልጸዋል፤ ”እንደ ሌሎች ፍጥረታት አራዊት ያልኾነ፣ በማሰብ ብቃቱ የተቀደሰ … በክብሩም እንደ ገነት የተፈራና የገነነ …።”‹ምሥራቃዊት ኮከብ› ፖለቲካዊ ድርሰት ኢትዮጵያዊነት፣ ኢትዮጵያዊ ማንነት- ፍቅርን፣ ትሕትናን፣ በጎነትን፣ ቅንነትን፣ ይሉኝታን፣ መከባበርን፣ ቃልንና እምነትን እስከ መጨረሻዋ ሕቅታ ድረስ ማክበርን … ወዘተ የመሳሰሉ የላቁ የሥነ ምግባር አምዶችንና ሞራላዊ እሴቶችን/High Moral Standards ከፍ የሚያደርግ ሕያው ማንነት እንደኾነ ይሰብካል።

በአንፃሩም ደግሞ ይህ የሰው ልጅ የሐሳቡን ታላቅነት፣ የክብሩን ውበት እንዲህ የማንነቱን ጥልቀት ተረድቶ፣ ከፈጣሪው የተሰጠውን ክብር፣ ፍቅር፣ ጸጋ አውቆ በዓለም ላይ የሚገባውን ስፍራ እንዲያውቅና በዚያም እንዲመላለስ ይህን ሐሳብ በድርሰት ውስጥ በስፋት ያቀነቅናል።

ኢትዮጵያዊነት በምሥራቃዊት ኮከብ፡-

*ኢትዮጵያዊነት ሰው የመኾን ሕይወት*፤ *ኢትዮጵያዊነት ምንጊዜም ያሸንፋል!!!* (ገጽ 336)

የነጻነት ታጋዩ፣ ዐርበኛውና የዓለም ሰላም ኖቤል ተሸላሚ የኾኑት ኔልሰን ማንዴላ ‹Long Walk to Freedom› በሚለው ረጅሙን የፀረ-አፓርታይድ የትግል ታሪካቸውን በተረኩበት ዳጎስ ያለ መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካና በአጠቃላይ በሰው ልጆች ታሪክና ሥልጣኔ፣ ባህል፣ ቅርስና ማንነት ውስጥ ያለውን ትልቅ መሠረትና አሻራ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፡-

Ethiopia always has a special place in my imagination and the prospect of visiting Ethiopia attracted me more strongly than a trip to France, England, and America combined. I felt I would be visiting my own genesis, unearthing the roots of what made me an African.

በተመሳሳይም ‹ምሥራቃዊት ኮከብ› ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ይገልጸዋል፣ ይፈክረዋል - የፈጣሪ ጸጋ፣ ጥበብና ውበት፣ የፍቅር ኃይል፣ የአፍሪካና የመላው ሰው ልጆች ትንሣኤ ብርሃንና ብስራት … የአሸናፊነት ኃይልና ብርቱ ጉልበት። ደራሲው በድርሰቱ መደምደሚያው ላይ፤ *ኢትዮጵያዊነት ሰው የመኾን ሕይወት*፤ *ኢትዮጵያዊነት ምንጊዜም ያሸንፋል!!!* እንዲል። እዚህ ጋር በምሥራቃዊት ኮከብ በተሳለችው ወይም ደራሲው በምናቡ በሚያስባት ኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ጥቂት የሙግት እሳቤዎችን/ጥያቄዎችን ማንሳት ያለብን ይመስለኛል።

ደራሲው ከገጸ ባሕርያቱ ስም ስያሜ ጀምሮ በአብዛኛው አይሁዳዊ/የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞችን በመጠቀም፣ የታሪኩን መቼትና ግጭቶች ውሱን በማድረግ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊ ማንነትን በተመለከተ ከሰጠው ስፋትና ጥልቅ ትርጓሜ አንጻር እምብዛም የማይስማማና የራቀ ኾኖ ይታያል። በተጨማሪም ደራሲው የኢትዮጵያዊነት ውበትና ድምቀት የኾኑ የተለያዩ ታሪኮች፣ ቅርሶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ማንነት … ወዘተ ያላቸውን ሕዝቦቿን ቢያንስ በገጸ ባሕርያቱ ስም ስያሜም ኾነ በድርስቱ ውስጥ ተገቢውን ውክልና/ስፍራ በመስጠት ረገድ የጎላ ድክመትና ተቃርኖ ይታይበታል።

ምሥራቃዊት ኮከብ እንደ ፖለቲካዊ ድርሰትም በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት በኢትዮጵያዊነት ማንነት ትርጓሜ ላይ የተነሣውን ሞጋች ጥያቄና እንደ ዋለልኝ መኮንን ያሉ ታጋይ ተማሪዎች፤ በታላቋ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ብሔረሰቦችን የታሪክ፣ የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህል …ወዘተ. ጥያቄዎችን ያፈነዳበትን፣ እንደ ኢብሳ ጉተማ ያሉ የኦሮሞ ተማሪዎች ”ማነው ኢትዮጵያዊ?!” የሚሉ ዓይነት ከሞላ ጎደልም የዛሬዋን ኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ምስል ዕውን ያደረጉ የሐሳብ ሙግቶችን፣ ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለሞችን/ነጽሮተ ዓለሞችን ወደ ጎን በማለት የኢትዮጵያዊነት ትርክቱ አገራችን ያለፈችበትን ውስብስብ የታሪክን ሒደትን የዘነጋ እንዲሆን ከማድረግም ባሻገር በትናንትናዋና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ትርጓሜ ላይ ያለውን ውዥንብርና ሙግት በደምሳሳው አልፎታል።

ምሥራቃዊት ኮከብ ከሚያቀነቅነው ጥልቅ የኾኑ የማንነት እሳቤዎች አንፃርም ኢትዮጵያዊነት በአፍሪካዊና በዓለም አቀፋዊ ማንነት ማዕቀፍ ውስጥ የሰጠው ትርጓሜውም ፍዝና ደካማ ነው። ድርሰቱ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ ቢያንስ አፍሪካውያንና አፍሪካ አሜሪካውያን ምሁራን፣ ጥልቅ አሳቢዎች፣ ፈላስፎችና ፖለቲከኞች ያቀነቀኗቸውን እሳቤዎችን አንድም ቦታ አያነሳም። እንደ ቼክ አንታ ዲዮፕ፣ ኢቫን ኢቫን ሰርቲማ፣ ማርከስ ጋርቬይ፣ አሊ ማዙሪ፣ ፓን አፍሪካኒስቶቹ - ዶ/ር ክዋሜ ንኩርማ፣ ጆሞ ኬንያታ፣ ሴዳር ሴንጎር… የመሳሰሉ የሰው ልጆች/የጥቁር ሕዝቦች መብት ታጋዮች የኢትዮጵያዊ/የአፍሪካዊ ማንነት የፍልስፍናቸው ዱካው ፈጽሞ አይታይም። በዚህም የተነሣ ኢትዮጵዊነት ከአፍሪካዊነትና ከመላው የሰው ልጆች ጋር ያለውን የታሪክ፣ የባህልና የሥልጣኔ ትስስር በማሳየት ረገድም ደራሲው የሔደበት ርቀት በጣም ውሱን ወይም ምንም ነው ማለት ይቻላል።

በአንጻሩም ደግሞ ይህ በሺሕ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔና ባህል ደመቀ ኢትዮጵያዊ ማንነትን እኛው ራሳችን ምን ያህል እናውቀዋለን፣ ምን ያህል እናከብረዋለን፣ ምን ያህልስ ተቀብለነዋል? የሚሉ ፈታኝ የኾኑ ወቅታዊ ጥያቄዎችን ምሥራቃዊት ኮከብ በጥልቀት አላነሣም። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስና አሁንም አልፎ አልፎ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ተዋርዶ ኢትዮጵያዊነት ”የራብ፣ የእርስ በርስ ጦርነትና የስደት” መገለጫ የሆነበትን አሳፋሪ ማንነት የብዙዎቻችን ሃፍረትና ውርደት ምክንያት ሆኖብን በኢትዮጵያዊነታችን አንገታችንን የደፋንበትን አጋጣሚዎችን በማንሳት ደራሲው ኢትዮጰያዊነትን በተመለከተ በዘመናችን በውስጥም ኾነ በውጭ ያጋጠመውን ተግዳሮትና በትውልዱ ላይ የተጋረጠበትን ከባድ ፈተናዎች/ጥያቄዎች በቅጡ አልተፈተሸም።

ይሁን አንጂ ‹ምሥራቃዊት ኮከብ› ፖለቲካዊ ድርሰት ይህን የዘመናት ውርደታችንን፣ ሃፍረታችንን-በፍቅር፣ በእውቀት፣ በእምነት፣ በድርጊት፣ ትርጉም ባለው የሐሳብ ልውውጥና ምክንያታዊነት ድል በማድረግ የኢትዮጵያን ትንሣኤን - ሰው በመኾን ኢትዮጵያዊ ሕይወት ውስጥ ዕውን ማድረግ እንደሚቻል አንዳች የተስፋ ብርሃንን ይፈነጥቃል፤ ያልማል፣ ይመኛል፣ ይሰብካል፣ ይቆጫል፣ ያነባል …።

‹ምሥራቃዊት ኮከብ› የፖለቲካ ፓርቲም በዚህ ኢትዮጵያዊነት ተስፋ፣ ርእይና አገራዊ ማዕቀፍ ውስጥ አዲስ ሥርዓትን ዕውን ለማድረግ የተመሠረተና የሚተጋ የኢትዮጵያውያን ፓርቲ ነው። ሊያው ደግሞ መነሻውንም ኾነ መድረሻው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ያደረገና አድማሱንም ከአፍሪካ ተነሥቶ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ያሰፋና የሰውን ዘር ሁሉ የሚጠቀልል። ዳሰሳዬን በዕውቁ ምሁርና ፖለቲከኛ በፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ኢትዮጵያዊነትን በገለጹበት ጥልቅ ሐሳባቸው ለመደምደም ወደድኹ።

ኢትዮጵያዊነት፡-

ኢትዮጵያዊነት ብዙ የተለያዩ ኅብረተሰቦች የተዋሐዱበት አካል ክፍል መሆን ነው። ኢትዮጵያዊነት ከጎሰኛነት በላይና ውጭ የሆነ አጠቃላይ ማንነት ነው።

ኢትዮጵያዊነት የዚህች ውጥንቅጥ መሬት ባለቤትነት ነው፣ ኢትዮጵያዊነት የደጋው ብርድና የቆላው ሙቀት የሚገናኙበት፣ የደጋው ዝናም ከቆላው ወንዝ ጋር የተዛመደበት ኃይል ነው።

ኢትዮጵያዊነት ለሙሴ፣ ለክርስቶስና ለመሐመድ የሚጨሰው ዕጣን በዕርገት መጥቶ የሚደባለቅበት እምነት ነው። ኢትዮጵያዊነት በቄጤማ ጉዝጓዝ ላይ የሚታየው መተሳሰብና መፈቃቀር ነው።

ኢትዮጵያዊነት የአስተዋይነት፣ የሚዛናዊነት የጨዋነት ባሕርይ ነው። ኢትዮጵያዊነት ረዥምና ተጽፎ ያላለቀ ታሪክ ነው፤ ብዙ ሰዎችም የተሰዉለት ስሜት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ሥቃይና መከራ ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ኩራትና ክብርም ነው። ኢትዮጵያዊነት ጭቆናና ጥቃት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት አሻፈረኝና እምቢ ባይነትም ነው።

የኢትዮጵያዊነት ዓላማ ያለችውንና የኖረችውን ኢትዮጵያን እንደገና ለመፍጠር አይደለም። የኢትዮጵያ ዓላማ ለኢትዮጵያዊያን በሙሉ የሚስማማ ዕድገታቸውንም የሚያፋጥንና፣ ኅብረታቸውን የሚያጠነክር ሥርዓትን መፍጠር ነው። የኢትዮጵያዊነት ችግር ኢትዮጵያ አይደለችም፣ ችግሩ የሥርዓት ችግር ነው።

ሰላም!!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!