ምስጢሩ The Secretወለላዬ ከስዊድን (ክፍል አምስት)
ምስጢሩ ወደኛ እየቀረበ ይሆን?
የምስጢሩን መጽሐፍ እያሳጠርኩ በመጻፍ ላይ እያለሁ ምስጢሩን የሚያጠናክር ነገር ገጠመኝ። ከወዳጄ ያሬድ ክንፈ ጋር አልፈን አልፈን ውሃ የምንጎነጭባት ቤት አለች። እንደወትሮው በዛው ቤት ተገኝተናል። አንዲት ወጣት ስዊድናዊት ልታስተናግደን መጣች። ለጓደኛዬ የሞቀ ሰላምታ ሰጠችው። ስትስቅ ጉንጭና ጉንጮቿ ላይ የሚወጡት ጎድጓዳ ምልክቶች ዓይን ይስባሉ።

 

"ባለፈው ጊዜ ስራ ለመቀጠር አስበሽ ያነጋገርኩሽ አይደለሽ?" አላት።

"አዎን! ተቀጠርኩ በጣም አመሰግናለሁ!"

"እኔ ምንም ያደረኩልሽ ነገር የለም እኮ"

"አንተ ሄደሽ ባለቤቱን ጠይቂው ባትለኝ አልጠይቀውም ነበር። ስለጠየኩት ተቀጠርኩ። በድጋሚ አመሰግናለሁ!" ፈገግታዋ ከጎድጓዳ ጉንጮቿ የሚረጭ ይመስላል። ተየለችን።

"ምንድነው ነገሩ? ሥራ አስቀጣሪ ሆንክ እንዴ?" ጠየኩ፤

"ባለፈው ሰሞን እዚህ መጥቼ ... ይቺ ልጅ ጎኔ ካለው ጠረጴዛ ላይ ተቀምጣ ነበር። ለጓደኞቿ እዚህ ቤት ሥራ ለመቀጠር እንደምትፈልግ አወራች። ጓደኖቿ ለንግግሯ ትኩረት አልሰጡትም፤ እኔ ጣልቃ ገባሁ። ...

"ሥራ ትፈልጊያለሽ ማለት ነው?"

"አዎን!"

"አስተናጋጅነት?"

"አዎን!"

"እዚህ ቤት?"

"አንተ ባለቤት ነህ?" ጠየቀች።

"አይደለሁም! ግን እንደምትቀጠሪ አውቃለሁ።"

"እንዴት?"

"ሂጂ ባለቤቱን ሥራ እንደምትፈልጊ ንገሪው፣ አልኳት። ነገረችው፣ ይሄው ተቀጥራ አገዃት" አለኝ።

"አንተ እንዴት እንደሚቀጥራት አወክ?"

"ምስጢሩን እኮ አነባለሁ አንዳንድ ሙከራዎችንም አደርጋለሁ። ይሄ ከስኬቶቹ አንዱ ነው" አለኝ። ስለምስጢሩ መጽሐፉን አንብቤ፣ ከመጻፌ ውጭ የምስጢሩን መከሰት በዓይኔ ያየሁትና በጆሮዬ የሰማሁት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ምስጢሩ ወደኛ እየቀረበ ይሆን?


ወደ ዛሬው የገንዘብ ምስጢር ላምራ፤


"ገንዘብን ለመሳብ ሀብት ላይ አትኩሮት ማድረግ ይኖርብሃል።"
ጃክ ካንፊልድ
"አዕምሮህ የፀነስውን ... ያገኛል"
ደብሊዊው ኤለመንት ሥቶኝ
"የመጽሐፍ ቅዱሶቹ አብርሃም፣ ኢሳቅ፣ ያቆብ፣ ዮሴፍ፣ ሙሴና ኢየሱስ የብልጽግና አስተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ እራሳቸውም ሚሊኒሮችም ነበሩ። አሁን ዓለማችን ላይ ካሉ ሚሊኒሮች በላይ ሊገመት በማይችል ደረጃ የባለጸጋ አኗኗር ስልት ነበራቸው።"
ጀምስ ሬይ


የገንዘብ ምስጢር
ገንዘብን ለመሳብ ሀብትን ለመጨመር
ማጣትን ትተኸው በማግኘት ላይ አተኩር
በገንዘብ እጥረት ላይ ወስደህበት ትኩረት
ተጨማሪ ገንዘብ አትችልም ለማግኘት
ማግኘት ይገባኛል ብለህ ያልከው ገንዘብ
ከኪሴ ተቀምጧል "አለኝ!" ብለህ አስብ
ለዚህ እንዲኖርህ ተጨማሪ ስሜት
ስለ ዳበረ ሀብት ስለገንዘብ ማግኘት
ገጓደኞችህ ጋር አንስተህ ተጫወት
የማግኛ ምልከታህ እያደር ሲለወጥ
ይጀምራል መምጣት ሀብት ወዳንተ መሮጥ
በዚህ ጊዜ ደስታን እውስጥህ ማሳደር
ቀላሉ መንገድ ነው ገንዘብ ለመጨመር
ይሄንን ልገዛው በቂ ገንዘብ አለኝ
በማለት ተነሳ ትልቅ ምኞት ተመኝ
ሆኖም በመንገዱ ዝም ብለህ አትሩጥ
ገንዘብን ለማግኘት ያንተንም ገንዘብ ስጥ
ገንዘብክን ስትሰጥ ተካፍለህ ስትበላ
ዕድል ትከፍታለህ እንድታገኝ ሌላ
በዚህ ቸርነትህ እርካታ ስታገኝ
ማለት ደፍራለህ ብዙ ገንዘብ አለኝ
በመልዕክት ሳጥንህ ወይም በግልህ ባንክ
አገኛለሁ ገንዘብ በጥሬው ወይ በቼክ
የሚል ስሜትህን ምኞትህን አዳብር
የማግኘት ኃይልህን ሚዛኑን አጠንክር


መልዕክትና አስተያየት ካለዎ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ