ካሣሁን ዓለሙ

”ወርቅ ነው፤ ወርቅ ነው የግዕዝ ፊደል፣

ሰባት እጅ የጠራ በሰባት ባሕል።” አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ

የሰውን ልጅ ዕውቀት ታሪካዊ ዕድገት ስንዳስሰው የጽሑፍ ምልክትን በመፍጠር ጀምሮ አሁን ያለንበት የመረጃ ዘመን ላይ ደርሷል። ከጥንቱ የጽሑፍ ምልክት ፈጠራ አንጻር ስንገመግምም በአሁን ጊዜ ያለው የዕውቀት ደረጃ ብዙም ሊለፈፍለት የማይገባ ይመስላል። ምክንያቱም የጥንቱ ለመጀመር የተደረገ ጥረት ነው፤ የአሁኑ ዕውቀት ደግሞ ያለውን ማስፋፋትና ማጎልመስ ነው።

 

 

ለምሳሌ አውሮፕላን ተፈልስፎ በሰማይ ላይ መብረር ከተጀመረ በኋላ ያለው የአውሮፕላን ዓይነትና የሞደል መለያየት ማሻሻል ስለሆነ የመጀሪያውን አውሮፕላን ከሠሩት የራይት ወንድማማቾች ሥሪት ወይም ለመጀመሪያ ጊዜ ንድፍን ካስቀመጠው ከዳቪንቺ ፈጠራ የበለጠ ዕይታ ሆኖ አስደንቅም። እዚህ ላይ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ”ዕውቀት ሲበዛ ማንኛውንም ነገር ለኑሮ የሚያስፈልገውን ነገር ለማግኘት መሰናክሉና ድካሙ ያንሳል” (መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር 1953፤ ገጽ 45) ያሉትን አስተውሎታዊ ገለጻ ልብ ማለት ነው። የሰው ልጅ ዕውቀት የዳበረው ደግሞ ፊደልን በጽሑፍ መጠቀም ከጀመረ በኋላ ነው።

 

ፊደል በእግዚአብሔር ገላጭነት ተገኘ?

በተለይ በሀገራችን በጽሑፍ አጀማመር ዙሪያ ሁለት ዓይነት ዕይታዎች አሉ። አንደኛው የሰው ልጅ በጥረቱ ተፈጥሮን መሠረት አድርጎ ፊደላትን በመቅረፅ ጽሕፈትን ጀምሮ አሳድጎታል የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ አዳም ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገርበት ቋንቋ ከአምላኩ በፀጋ የተሠጠው ነው፤ ከቋንቋ ጋር ፊደልን ሥሎ እንዲመዘግብበት ሰጥቶታል የሚል ነው። ፊደል ለሰው ልጅ የተሠጠው ከአዳም በኋላ በሔኖስ ጊዜ በጠፍጠፈ ሰማይ ላይ በመሳል ነው የሚል ክርክርም አለ፤ ይህ ግን ከሁለተኛው ዕይታ ጋር ተቀራራቢ ነው፡- ፊደል በሰው ልጅ በራሱ ተቀረፀ ሳይሆን በእግዚአብሔር ገላጭነት ታውቆ መጻፍ ተጀመረ የሚል።

 

እስቲ ”ፊደል ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎች በራስ ጥረታቸውና ትጋታቸው ሳይሆን በእግዚአብሔር ገላጭነት በስጦታ ያገኙት ነው” የሚለውን አቋም በመጀመሪያ እንመልከት። ይህ መከራከሪያ ቋንቋ በሰዎች በራሳቸው በጊዜ ሂደት የተፈጠረ ሳይሆን ከተፈጥሯቸው ጋር ተዋሕዶ የተሠጣቸው ነው፤ ከቋንቋ ጋር ተያይዞም ሐሣባቸውን እየከተቡ የሚግባቡበትና ከቀጣይ ትውልዶች ጋር ጭምር የሚማማሩበት ፊደል ተገልጾላቸዋል የሚል ነው። ይህ አቋም የሃይማኖተኞች (ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ) መከራከሪያ ነው። ከላይ እንደጠቆምነውም ተያያዥ የሆኑ ሁለት ክፍሎች አሏቸው። አንደኛው ቋንቋና መጻፊያው ፊደል ከፍጥረት ጋር ለአዳም ተገልጾለታል፤ ከገነት ከተባረረ በኋላም ዘሮቹ እየጻፋ ከትውልድ ትውልድ ታሪካቸውን ማሰተላለፍ የቻሉት ያንን ተጠቅመው ነው የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመጀመሪያ ለአዳም የተሠጠው መግባቢያ ቋንቋ እንጂ መጻፊያ ፊደሉ አይደለም፤ ፊደል ለመጀመሪያ ገዜ ለሰው ልጆች ጥቅም የተገለጠው በአዳም ሦስተኛ ትውልድ በሆነው ለሄኖስ ነው የሚል ነው። ይህንን የሚሉት በምን ማስረጃና ምክንያት ተነስተው ነው?

 

እንደ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አስተምህሮ ከሆነ የሰው ልጅ ”እንደ መላእክት ሃይማኖቱን በሕገ ልቦና ዐውቆና ጠብቆ ፈጣሪውን ፈርቶ አክብሮ ሊኖር እንጂ በደብተርና በእርሳስ ሊመራ አልተፈጠረም።” (መ.ሄኖክ፣ ፲፱፡-፳፪) ”ይኽ ሕገ ልቦና የተባለው ያን ጊዜ በተፈጥሮ እንደተሰጠ ያለ፤ የጸናም ሕግ ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በሕገ ልቦና ብቻ ሊጠበቅ ባለመቻሉ በግድ የጽሑፍ ሕግ አስፈለገ።” ይላሉ።(ሊቀ ጠበብት አያሌው ታምሩ፤ የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፣ ገጽ 33፤ አባመልከ ጸደቅ፤ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፤ ገጽ 13) ስለዚህ የጽሑፍ ፊደል ኋላ በሄኖስ ጊዜ የተሠጠው የሚረሳውን ማስታውስና ታሪኩንና አምልኮቱን ለትውልድ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲችል ነው። እዚህ ላይ ሊቃውንት የገለጹትን መጥቀስ ሙሉ ግንዛቤ ይሰሠጠናል። ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ፡-

 

”ምንጊዜም ቢሆን ለቋንቋ ሥሩ መገለጫው፣ ምንጩና መፍለቂያው ፊደል ስለሆነ ... የጽሑፋችን መሠረት ፊደል ነው። ፊደል ከአዳም በሦስተኛ ትውልድ በሄኖስ ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሠጠ በልሳን ተውጦና ተሰውሮ የነበረው አካሉ በሰማይ ገበታነት ተጥፎ ተቀርጦ የተገለጠ አንድ ነገር ነው። (ኩፋሌ ም.፭ ቁ ፲፰) ቋንቋ ከእግዚአብሔር ተገኝቶ በመላእክትና በሰው ዘንድ ተጠንቶ መልኩ በሕሊና ሲታወስ፤ ረቂቅ አካሉ በልሳን ሲዳሰስ ከአዳም እስከ ሄኖስ ኖሮ በኋላ በቀለምና በወረቀት ሳይሆን እንደ መላእክት በተፈጥሮው ሊሆን የተፈጠረ ሰው እውቀቱ እየደከመ ስለ ሄደና ሊጠቀምበት ስለ አልቻለ ዐይን በመመልከት እጅ በጥፈት ሕሊናውን እየረዱት ዐሳቡን በጽሑፍ በማሳረፍ ይጠቀም ዘንድ የሰላም አምላክ እግዚአብሔር የቋንቋን ሁኔታ የፊደልን መልክና ቅርጥ በሰማይ ገበታነት ጥፎና ቀርጦ ለሰው ልጅ አስተማረ።” ካሉ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማን እንደተገለጠ ሲገልጹ ”የፊደላት መልክ በሄኖስ ዘመን ታይቶና ተለይቶ ዐይንና ሕሊና እየተረዳዱ በሰጡት ውጤት የሰው ልጆች የእግዚአብሔርንስ ስም መጥራት የፊደላትን መልክ ለይቶ ማወቅና ማጥናት ሲጀምሩ የሕሊና ሐሳብ ሁሉ በአፍ በመጣፍ የታወቀ ይሆን ዘንድ ልዑል እግዚአብሔር በሰባተኛው ትውልድ በሄኖክ ዘመን ለሰው ልጆች ጥፈትን አስተማረ። (ዘፍ፣ ም.፬፡-፳፮) ከዚያ ወዲህ ሰው ሁሉ በቃል ያለ ይረሳል በመጣፍ ያለ ይወራሳል እያለ ክፉም በጎም ሆነ ማነኛውንም ዐሳቡን በብራና በወረቀት ጥፎ አፍፎ በእንጨት በድንጋይ ወይም ልዩ ልዩ በሆኑት የመዓድን ዐይነቶች ዐንጦ ቀርጦ ያስቀምጥ ጀመረ።”(ሊቀ ጠበብት አያሌው ታምሩ፤ የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፣ ገጽ 69-70)

 

ሊቀ ሥልጣናትም (የአሁኑ አቡነ መልከ ጼዴቅ) ”እንደ ቤተ ክርስቲያናችን እምነት እንደሆነ ደግሞ የፊደል ስልት አንድም አቅድ ተጀመረ የሚባለው በሄኖስ ዘመን ነው። ነቢዩ እግዚአብሔርን በማገልገል የታወቀ ደግ ስለነበር፤ ለደግነቱ መታወቂያ ይሆነው ዘንድ በቅዱስ እግዚአብሔር ፈቃድ የሕግ መሣሪያ የሚሆነው ፊደል በጸፍጸፈ ሰማይ ተገልጦ ተይቶታል፤ ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፊደልን ለጽሑፍ በር መክፈቻ በማድረግ ተጠቅሞበታል፤ ስሙንም ጽሑፍ ለማለት ፊደል ብሎታል።” በማለት ገልጸዋል። (ሊቀ ሥልጣናት ብተ ማርያም ወርቅነህ፣ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት፤ ገጽ 17)

 

የዚህን ሐሳብ ተቀባይነት በማጉላትና ተፅዖኖ በመፍጠር ትልቁን ሚና የተጫወቱት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይመስላሉ። ለዚህ በመጻሐፎቻቸው በሰፊው አብራርተውት የጻፉትን የተመለከተ ሰው ምስክርነቱን መስጠት ይችላል። ”አበገደ፡ ፊደልና ፊደላዋሪያ የልጆች አፍ መፍቻ” በሚለው በ1926 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፋቸው መቅድም ”ፊደልና ጥፈት በ፫ኛው ትውልድ በሄኖስ ዘመን ተዠምሯል። እግዜር ለሙሴ ዐሠርቱ ቃላትን በጽላት ጥፎ እንደ ሰጠው ለሄኖስም ፳፪ቱን አሌፋት በ፳፪ቱ ሥነ ፍጥረት አምሳል በጸፍጸፈ ሰማይ ጥፎ አሳይቶ እንደ ፎቶ ግራፍ ወዲያው በልቡ ሥሎበታል። ከዚያ ወዲህ ጥፈትና ትምርት የጥፈት ሥራ እየበዛ ኺዷል፤ ይህም ታሪክ በኩፋሌና በሔኖክ ይገኛል። ከዚያም ከአዳምና ከሄኖስ እስከ ራግው ድረስ ፩ የነበረው ፊደልና ቋንቋ በባቢሎን ግንብ ተለያቶ ቋንቋው እስከ ፸፪፤ ፊደሉ እስከ (፳) ኻያ ተከፍሏል።” ብለው አስቀምጠውታል።

 

ሊቁ ኪዳነወልድ ይህንን በበለጠና በተብራራ መልኩ በዋናው የሰዋሰው መጽሐፋቸው ”ፊደልና ጥፈት ለአዳም ልጆች የተገለጡና የተሰጡ በአዳም ዕድሜ ነው፤ ከዚያውም በሳብዓይ ምእት በሣልሳይ ትውልድ በሄኖስ ዘመን እንደኾነ ታውቋል። የተሰጡበትም ምክንያት ይህ ነው፤ ሰው በግዜር ምሳሌ መፈጠሩ እንደ መላእክት ሕያው ኹኖ በሕገ ልቦና ሊኖር እንጂ በተፈጥሮ የተሰጠውን ሕግ ረስቶ ዘንግቶ እንደ ገና መጽሐፋዊ ሊጥፍና ሊያስጥፍ ልቡናው በመጽሐፍ ሊደግፍ ሕይወቱንም አጥቶ ሊቀበር ከመሬት ሊወተፍ እንደ ቅጠል ሊረግፍ አልነበረም።” ካሉ በኋላ ሄኖስ እንዴት ፊደልና ጥፈትን ከእግዚአብሔር እንደተሠጠው ይተርካሉ። ሄኖስ ” ... አውታረ ልቡናው በድሕንጻ መንፈስ ተቃኝቶለት ፊደሉን ከቋንቋው ቋንቋውን ከፊደል አስማምቶ ቀኝ እጁን በነፍስ ግራ እጁን በሥጋ ዐሥር ጣቶቹን ባሥርቱ ቃላት መስሎ አነጻጽሮ ባንደበቱና በጣቱ እያነበበና እየጣፈ የፊደልን ሥራ ከሕግና ከትእዛዝ ጋራ አምልቶ አስፍቶ አስተምሯል።” ብለው በመግለጽ ስለ ሕግና ትእዛዝ ካብራሩ በኋላም ”ልጁም ቃይና እንደ ሰሎሞን ንጉሥና ነቢይ ወዲህም ፈላስፋ ነበረና ሕዝቡን እንዳባቱ በቀና መንገድ መርቷቸዋል። ከእሱም በኋላ እስከ ላሜኽና እስከ ኖኅ ተያይዞና ተከታትሎ የሚመጣው ኹሉ ተገልጦለት ለነመላልኤል፣ ለልጆቹና ለሕዝቡ በሰላውድወ እብን እየጣፈ ከቤተ መዛግብት እንዳኖረው የአይሁድ ኩፋሌ በዕብራይስጥ ቃል ይተርካል።” በማለት ይተርካሉ።

 

ከዚህ በላይ የተጠቀሰው የፊደል ከየት መጣ ታሪክ ግን በሁሉም የሀገራችን ምሁራን ተቀባይነት ያገኘ አልነበረም። ይህንን ፊደል ለሰው ልጆች የተገለጸው በሄኖስ ነው የሚለውን ከሚቃዎሙት ሊቃውንት መካከል ግንባር ቀደሙ አስረስ የኔሰው ናቸው። ከላይ የጠቀስነውን የአለቃ ኪዳነ ወልድ ሐተታን በመቃወምም ”ለአዳም ያልተገለጸ ስለምን በሄኖስ ተገለጠ? ... በግዜር ምሳሌ መፈጠሩ እንደ መላእክት ሕያው ሆኖ ሊኖር ብለዋል መላእክት መነሳታቸው ከሆነማ ይልቁንስ በ፩ድ ሰዓት የሳተ ማነው? አዳምስ ቢሰት በ፯ ዘመኑ ነው። በተፈጥሮ የተሰጠውን ሕግ ረስቶ ይላል፤ ... በተፈጥሮ የተሰጠው ሕግ ማለት እንደ ምን ነው? ፈደልና ጽሑፍ ሳያውቅ ማለት ነውን? ወይስ ጽሕፈትና ፊደልስ ዐውቆ ሌላ ያውቅ ነበር ማለት ነው? ” ብለው ከጠየቁ በኋላ ትችታቸውን ”ግን አሳብዎን ስመለከተው በፊት ዕውቀቱ በመጠን ነበር ካጠፋ በኋላ ግን እውቀቱ በዛለት ፊደልና ጽሕፈት ተገለጠለት ማለትዎ ይመስላል። ውስጠ ምሥጢሩን በኩፋሌው ላይ ባይመለከቱት ነው እንጅ ተመልክተውት ቢሆን ምዕራፍ ፭፣ ፪ ወበይዕቲዕለት አፈ ኩሉ አራዊት ወእንስሳ ዘያንስሱ ወዘይትኃውስ እምነቢብ እስመ ኩሎሙ ይትናገሩ ዝንቱ ምስለ ዝንቱ ከንፈረ ፩ደ ወልሳነ ፩ደ፤ (ይላል)። ከጥፋት በፊት የአራዊትን የእንስሳትን ቋንቋ አዋቂ ነበር በኋላ ግን የእንስሳትንና የአራዊትን ቋንቋ ማወቅ ቀረበት፤ እንግዴህ በዚህ ሂሳብ አዳም ከበደለ በኋላ ጥበብ ከቀድሞው በለጠ ከማለት ጎደለ ተቀነሰበት ማለት የተሻለ መሆኑን መገንዘብ ነው። ... ማንኛውንም አደራጅቶ ሲሰጠው ጽሕፈትና ፊደል አልገለጸለትም ማለት ከንቱ ምርምር እንጅ እርግጠኛ ከመጻሕፍቱ ምንጭ ይዞ የሚገኝ አይደለም። አዳምን ንጉሥ አልነበረም የሚል ይገኝ አይመስለኝም፤ ለአዳም ሰባቱ ሀብታት አልነበሩትም የሚል ይገኛል አይመስለኝም። ስለዚህ አዳም ፊደልና ጽፈት አያውቅም ማለት ፊደልን ጽሕፈትን ሰዎች በመመራመር በኋላ አገኙት ለማለት ይመስላል።” በማለት አቅርበው፤ ፊደል ለመጻፊያነት የተገለጠው ገና ጥንቱን ዓለም ሲፈጠር መሆኑን ያብራራሉ። በተለይ ”አጋዕዝት ዓለምን ሲፈጥሩ በነቢብ ጭምር ነው፤ በነቢብ የተነገሩ ቃላት ኦር.ዘፍ. ከ፫-፳፱ ያሉት ሲቆጠሩ ፱ ናቸው።” በማለት የዘጠኝን ቁጥር ጥልቅ ምሥጢርነት ጠቁመው ”እሽ ይሁን ዓለም በተፈጠረ ጊዜ ፊደል ከሌለ ዕለታቱ ከአንድ እስከ ሰባት በምን ተቆጠሩ? እነዚህ አሁን የሚገኙ አኀዞች ፊደሎች በዚያን ጊዜ አልነበሩም ለማለት ይታሰብ ይሆን?” እያሉ ይጠይቃሉ። (አስረስ የኔሰው፣ ትቤ አክሱም መኑ አንተ፤ ገጽ 256-257) ስለዚህ በአስረስ የኔሰው አገላለጽ ከሆነ ፊደል በመጀመሪያም በአዳም ጊዜ ነበር እንጂ በሄኖስ ተገለፀለት ለማለት አስቸጋሪ ነው ማለት ነው።

 

እነዚህ ሁለት የሊቃውንት መከራከሪያ አቋሞች የማይታረቁና የማይስማሙ ቢመስሉም በመመቻመች አንድ መሆን የሚችሉ ናቸው። እዚህ ላይ አስረስ የኔሰው ኪዳነ ወልድን የነቀፉበት አግባብ ሙሉዕ አይመስልም። ምክንያቱም እንደሳቸው አገላለፅ ከሆነ እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረው በነቢብ በመናገር ስለሆነ፤ በንግግር ውስጥ ደግሞ የፊደሎች ንባብ ስላለ ፊደል የእግዚአብሔር መፍጠሪያ የነበረ ነው፤ ወደሚል አንድምታ ይወስዳል። በዚህ ዕይታ ”ፊደል የእግዚአብሔር መፍጠሪያ የነበረ ነው” ካልን ደግሞ ”ፊደል የእግዚአብሔር ቃል ነው” ወደ ማለት ይወስደናል። ይህም የሥነ-መለኮት አስተምህሮ ላይ ጭቅጭቅን ይፈጥራል። ይህንን ችግር እንኳን ብናልፈው አስተውሎቱ ”ፊደል ከሰው ልጆች አእምሮ ጠባይ የተጻፈ ወይም በልቦና የተቀረጸ” መሆኑን ነው የሚገልጸው እንጂ በቅርጽና በመልክ ተሠርቶ በግዝፈት መጻፉን አይደለም። ይህ ከሆነ ደግሞ ሰው ሁሉ ማንም ሳያስተምረው በተፈጥረው ፊደልን ማወቅ ነበረበት፤ በተፈጥሮ ጠባዩ ግን የተሰጠው ፊደል የማወቅ ሀብትን እንጂ ራሱን የፊደል መልክ በቅርጽ አልተጻፈበትም። እንዲሁም ፊደል በሰዎች ልቦና በተፈጥሮ ጠባይ የታተመባቸው ቢሆን ኖሮ ለሰዎች ሁሉ በተፈጥሮ የሚነበበው ፊደል ተመሳሳይ መሆን ነበረበት፤ ይህ ሳይሆን ግን ፊደል የሚታወቀው በተለያየ ቋንቋ በተለያየ ቅርጽና የአጻጻፍ ስልት በልምምድ በመማር ነው። ስለዚህ ሊቁ አስረስ የኔሰው የሰው ልጅ በእጁ ቀርጾ የሚጽፈውን በልቦናው ከተቀረጸው የዕውቀት ጠባይ ለይተው አልገለጹም። ከእሳቸው ይልቅ የእነ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መከራከሪያ ሚዛን ይከብዳል፤ የልቦና ዕውቀትን ሳይክዱ በቅርጽና በመልክ አግዝፎ የሰው ልጅ መገልገል የሚችልበትን መጻፊያውን ነውና፤ የገለጹት።

 

የእነ አለቃ ኪዳነ ወልድ፣ አለቃ አያሌውና አቡነ መልከጼደቅ መከራከሪያ ምክንያታቸው ምንድ ነው? ከላይ በራሳቸው ተገልጽዋል። ”የሰው ልጅ ከስህተት በኋላ የአስተሳሰብ ሙስና ስላጠቃው በተፈጥሮው የተሰጠውን የልቦና ሕግ መጠበቅ አልቻለም፤ ስለሆነም በእየለቱ ጽፎ ይዞ በማንበብ እንዲጠቀምበት የመጻፊያ ሥርዓት አስፈለጎታል፤ በመሆኑም ለዚህ የሚሆነውን መጻፊያ ፊደል እግዜር አሳወቀው” የሚል ነው። በዚህ ዕይታ ፊደል በልቦና የተጻፈውን ዕውቀት ወይም ሕግ ከመርሳት ለማስታወስ ተብሎ የተሠጠ ሥጦታ ነው። ምክንያቱም ከስህተት በኋላ የዕውቀት ብልየት አጋጥሞታል፤ ይህንን ደግሞ ሊቁ አስረስ የኔሰውም የሚጋሩት ነው። ስለዚህ ምንም እንኳን እላይ ከጠቀስነው የአንድምታ ፍራቻ በመነሳትና የፊደል ወይም የጽሕፈት መኖርም አስፈላጊነትን አንድ ነገር እንዳይረሳ ለማስታወሻና ከትውልድ ትውልድ ዕውቀትንና ሕግን ለማስተላለፊያ በመሆኑ ፊደል ለአዳም ከሚናገር ቋንቋ ጋር አብሮ ተሰጥቶት ነበር የሚለውን መከራከሪያቸውን ባንቀበለውም በአገልግሎትና በጥቅሙ አስፈላጊነት በመስማማታቸውና ”በመገለጥ ነው የተገኘው” በሚለው አቋማቸው አንድነት አንጻር አመቻምቾ በአዎንታነቱ መውሰድ ይገባል። አንዲሁም አዳም ከእንስሳትና ከአምላኩ ጋር የሚግባበት ቋንቋ ነበረው የሚለውን ሁሉም የሀገራችን ሊቃውንት (አስረስ የኔሰውን ጨምሮ) የሚስማሙበት ስለሆነ ከልዩነታቸው ይልቅ በውሕድነት (በአንድነት) መቆማቸው ይበልጣል።

 

በአጠቃላይ ግን ፊደል ወይም ጽሑፍ የተገኘው ከእግዚአብሔር ነው የሚለው ”የሰው ልጅ እንዴት ፊደልን በመቅረጽ መጻፍ ቻለ የሚለውን ለመመለስ በቀላሉ ከሃይማኖት አንጻር መቀበል ቢቻልም እሳቤውን እንፈትሸው ካልን ግን ብዙ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል። ለምሳሌ በሰማይ ላይ የተጻፈው ፊደል የትኛው ነው? የግዕዙ ወይስ የእብራይስጡ? ነው የሌላ ቋንቋ? እሽ የየትኛውም ይሁን እና እንዴት የዓለማችን የመጻፊያ ስልት ወይም ፊደል ሊለያይ ቻለ? ይህንንም ጥያቄ ይሁን ብለን ብናልፈው እንኳን የሰው ልጆች እሳቤው ከችግር አይጸዳም። ለማንኛውም ”የመጀመሪያው የዓለማችን ፊደል የቱ ነው?” የሚለውን መነሻ በማድረግ ከታች ብንዳስሰው ተመራጭ ይሆናል።

 

ፊደልን የሰው ልጅ በራሱ ፈለስፈው?

እስቲ ”ፊደል በእግዚአብሔር ገላጭነት የሰው ልጅ ያገኘው ሀብት ነው” የሚለውን መከራከሪያ በዚህ እንግታና የሰው ልጅ የጽሑፍ ሥርዓትን በራሱ ጥረት ነው የፈለሰፈው የሚለውን መነሻ ይዘን እንመርምር። በዚህ ዙሪያ ቁም ነገር ያለው ስላልመሰለኝ ትቸዋለሁ እንጂ የዝግመተ ለውጠኞች የቋንቋ አፈጣጠርና ዕድገት ትንታኔም አለ። ይሁንና የዚህ አስተሳሰብ ብዙም አስፈላጊነት መስሎ ስላልታየኝ ማለፍን መርጫለሁ።

 

ለማንኛውም ወደ ዋናው የምርምርም ነጥብ በመግባት የሰው ልጅ መጀመሪያ ተፈጥሮ ምድር ላይ ተከሰተ ብለን እንነሣ፤ በዚህ ክስተት ጊዜም ሊቸገር የሚችልበትን ሁኔታ በአእምሯችን እንሣለው። እንኳን ሌላ ለማሳብ እንኳን የዓለማችን ፍጥረታት ወስብስብነት፣ ብትንነት፣ ግዝፈትና እርቅቀት፣ .. በሥርዓት ውል ለመስጠት ስለሚያስቸግረው ለመግለፅም እንደሚያስቸግር ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም የፍጥረታትን ብትንትንነት በየፈርጁ እና በቅደም ተከተል ሰብስቦ በአእምሮው መመዝገብ፣ውስብስብነቱን ውል ሰጥቶ ማቀናበር፣ እረቂቁን አግዝፎ (ለምሳሌ ፍቅርን፣ ፍትሕን እውነትን ...) እና ግዙፉን ነገር ደግሞ በሐሣብነት አርቅቆ ማሰብን ይጠይቃል። በዚያ ላይ ለእያንዳንዱ ነገርና ክስተት የራስን ስያሜ መስጠትና የወል (ሰው፣ እንስሳ፣ ድንጋይ፣ ... እና የተፅዎኦ ስሞችን (አበበ፣ ከበደ፣ ቶሎሳ፣ ...) ለይቶ ማገናኘትን ይፈልጋል። ለምሳሌ ሕይወት ያለውንና የሌለውን ነገር ከፋፍሎ መፈረጅ፣ ሕይወት ያላችውን ነገሮችም በፈቃዳቸው የሚንቀሳቀሱና የመንቀሳቀስ ስሜት የሌላቸው ብሎ ለመከፋፈል፣ በራሳቸው ፈቃድ ከሚንቃሰቀሱት መካከልም ማሰብ የሚችሉትና የማይችሉትን፣ ማሳብ ከሚችሉ ፍጥረታት መካከልም የማሰብ ደረጃቸውን በመበየን መረዳት ... እጅግ ውስብስብ ሊሆንበት እንደሚችል መገመት ይቻላል። በዓይነትና በቡድን ከከፋፈለ በኋላም ለእያንዳንዱ ፍጥረትም መለያ ስያሜ መስጠት ያስፈልጋል። የፍጥረት ብዛት ደግሞ ልክ የለሽ ከመሆኑም በተጨማሪ ተለዋዋጭና ተቀያያሪ ነው። ይህንንም በጥቅልና በዝርዝር፣ እንዲሁም ተያያዥነቱንና ተለያይነቱን ማወቅ ያስፈልጋል።

 

እርስ በርስ ለመግባባት የሚኖረውን ችግርም አስቡት በእጅ ወይም በሌሎች አካላት ምልክት ተጠቅሞ ከመግባባት ውጭ ምን መፍትሔ ይኖራል? ይህስ ቢሆን እንዴት አስቸጋሪ እንደሚሆን ገምቱት፤ ክስተቱ ወይም ነገሩ ከሌለ በምን ጠቁሞ ማስረዳት ይቻላል፤ ፀሐይ ወይም ብርሃን በሌለበት ሰዓት ቢሆንስ እንዴት ይገለጻል። ለምሳሌ አንድን እንስሳ ወይም የእፅዋት ዓይነት እንዴት ለይቶ ማስረዳት ይቻላል። በዚያ ላይ ብዙ በሐሣብነት ደረጃ የሚገኙ በምልክትና በመጠቆም ሊገለፁ የማይችሉ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ እውነት፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ፍትሕ ... የሚሉት ፅንሣተ ሐሳብ በምን ዓይነት መልክ ሊገለፁ ይችላሉ። በዓለም ጥንት መጀመሪያ ላይ የነበረ ሰው መግባቢያ ቋንቋም ሊኖረው ስለማይችል ሐሣቦችን ለመረዳት እንዴት ሊቸገር እንደሚችል ማስተዋል ነው።

 

ከዚህ በተጨማሪም ”ፍጥረታት ከየት መጡ? እንዴትስ ተሠሩ?” (ከየት መጣሁ?) የሚለው አስጨናቂ ጥያቄም በተለይ በጥንት ጊዜ የማይፉቁት መልስ ፈላጊ ሆኖ ማስቸገሩ አይቀርም፡- እንኳን ድሮ አሁን በተረሳሳበት ጊዜም እንኳን ጥያቄው ብቅ ጥልቅ እያለ ያስቸግራል። የሰው ልጅ ዐዋቂ ፍጥረት ሆኖ የማንነትና የምንነት ጥያቄ አያነሣም ማለት አይቻልም። የማንነት ጥያቄ ተፈጥሮው የሚያስገድደው ከሆነም ”ከየት መጣሁ? ፍጥረታትስ ከምን እንዴት ተገኙ? ምንስ እሆናለሁ? ከሌሎችስ በምን እለያለሁ? ... ” የሚሉ ጥያቄዎችን መልስ መስጠትና ለዘሮቹም መልሱን ማስተላለፍ የግድ ይለዋል። ማስተላለፊያ ሊሆን የሚችለው መንገድም ቋንቋ ነው፤ ቋንቋን ተጠቅሞም ካልተቻለ በቃል፣ ከተቻለም በጽሑፍ ነው ማስተላለፍ የሚችለው። በጥንት ዘመን በሰው በመጀመሪያው የታሪክ ክስተት ደግሞ ጽሑፍና የመጻፍ ሥርዓቱ የለም።

 

ይህንን ውስብስብ ችግር ውል ሰጥቶ ከምንም የጽሑፍ ስልትን የጀመረው ሰው አስተሳሰቡ ምን ያህል ኃያል ነበር? በዚህ ፈጠራውም ቋንቋውን ወደ ጽሑፍ ሥርዓት መቀየሩና ማሳደጉ ደግሞ አስተሳሰቡን አጎለመሰው። እስቲ እናስተውለው በንግግር ቋንቋ ለመግባባት ለረቂቃንና ለግዙፋን ነገሮች ስያሜ መስጠት ያስፈልጋል። የእያንዳንዱንም ነገር ስም በአስተሳሰብ ክፍል ውስጥ በማስገባት መፈረጅና ከሌሎች ክፍሎች ጋር በማነጻጸርና በማቃረን ማገናዘብን ይጠይቃል። ይህንን ውስብስብ ነገር ተገንዝቦ በምልክት አስቀምጦ ሰዎች እንዲረዱት ማድረግ ምን ያህል አስተዋይ አዕምሮን እንደሚጠይቅ መገመት ነው። ለነገሮች ምልክት በማበጀት ከተከታታይ ትውልድ ጋር መግባበባት ደግሞ አስፈላጊ ነበር። ያለበለዚያ የማንነት፣ የዕውቀትና የአመጣጥ ታሪክ ጥያቄ ውስጥ እንደገባ ይቀራል።

 

የሰው ልጅ በተፈጥሮው የወላጆቹን ማንነት፣ የዕውቀት ሀብትና የአስተዳደግ ሁኔታ ይወርሳል። ወላጆችም ልጆቻቸው የእነሱን ዘር ወይም ማንነት ይዘው እንዲያስቀጥሉ ተፈጥሮ ያስገድዳቸዋል። በዚህ መልክ የእነሱ የዕውቀት እንዲጠፋም፤ ልጆቻውም በዕውቀት ማነስ እንዲቸገሩ አይፈልጉም። ስለዚህ ያላቸውን ዕውቀትና ማንነት ለልጆቻቸው ከማውረስም በተጨማሪ አሻሽለው እንዲጠቀሙበትም ተፅዕኖ ያደርጉባቸዋል። የሰው ልጅም በአጠቃላይ ተፈጥሮው በተፈጥሮ የመደነቅና የተፈጥሮ ውስጠ ምሥጢርን ለማወቅ የመመርመር ዝንባሌ አለው። ይህም ዘሩንና ማንነቱን ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ካለው ተፈጥሮ ጋር አዋሕዶ የተፈጥሮን ክስተት ምንነት፣ ታሪክ፣ ሥርዓታዊ ሥሪትና ምሥጢር በመዝገብ ከትቦ ለማስቀመጥ ይጥራል። ”እና ይህንን ለማድረግ የሚያስችለው የመጀመሪያው የጽሑፍ ምልክት እንዴት ተፈጠረ ወይም ተቀረጸ?”

 

አስጀጋሪ ይመስላል። ምክንያቱም የተፈጥሮ ክስተት በመጠኑ ልክ የለሽ፣ ውሰብስብና ተለዋዋጭ ነውና። ለምሳሌ ዛፍን በምልክት ለመግለፅ የዛፍ ሥዕል ተጠቀመ ብለን ብንወስደው የዛፍ ዓይነት በመጠኑ ብዙ፣ በዓይነቱ የተለያየ፣ የተለያየ ቅርፅ ያለው፣ አንድ ሥፍራ ያለው ከሌላው የተለየ ... በመሆኑ ምን ዓይነት ምልክት መስጠት ይቻላል? ለምሳሌ በበረሃ የሚገኝ የቁልቋል ምልክት ደጋ ከሚገኝ ፅድ ጋር ወይም ከበረዶ ዕፅዋት ጋር እንዴት ተመሳሳይ ውክልና ሊያገኝ ይችላል? ለሁሉም የዕፅዋት ዓይነት በየፈርጁ ከተባለም የዛፍ ምልክት ብቻ ቆጥረው የማይጨርሱት ብዙ ይሆናል።

 

እንዲሁም የሰው ልጅ ሐሣቦችን ከሰዎች ይቀበላል፤ ለሌሎች ሰዎችም ይሰጣል ወይም ያቀብላል። ይህንን ሲያደርግም በማዕከል ላይ መግባቢያ የሚሆነው ቋንቋ ያስፈልገዋል። ይህንን ቋንቋም በቃልዊ ንግግር በመሰማማት፣ በሥዕላዊ ምልክት ወይም በቅርፅ በማየትና በማሳየት ይለዋወጠዋል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ምንም አይደለም፤ ሁሉም ነገር ተቀርጾና ተሻሽሎ አድጎ ከአማራጭ ጋር በቀላል መንገድ ይገኛል፤ በሰው ልጅ ፍጠረት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ግን ፊደልም አልነበረም፤ ድምፅንም ቀርጾ ማቆየትና ማዳመጥ አይቻልም፤ ብለናል። ስለዚህ በቋንቋ አማካኝነት የራስን ታሪክና የተፈጥሮን ምንነት ገልጾ ከቀጣይ ትውልድ ጋር እንዴት መግባባት ይቻላል?

 

እዚህ ላይ ምልክቱን የመቅረጫ (የመጻፊያውም) ጉዳይ ብዙ ሊያስቸግር አንደሚችል ማስተዋል ነው። ”ምን ነገር ተጠቅሞ በምን ላይ ይጻፍ?” የሚለው ጥያቄ ከብዙ ጥረት በኋላ መልስ ሊያገኝ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ታሪክ ጽሑፍ በግሃ ድንጋይ ተጠቅሞ በድጋይ ላይ ከመጻፍ ቅጠልን ቀጥቅጦ በመጭመቅ በብራና ላይ ወደ መጻፍ ሽግግር የተደረገው በንጉሥ ሰብታህ (2545-2515 ዓ.ዓ.?) ዘመነ መንግሥት መሆኑ ተጽፏል። ይህንን የአጻጻፍ ስልትና መጻፊያውንም (ከግሃ ድንጋይ ወደ ቅጠል ጭማቂ ቀለም፤ ከድንጋይ ላይ ወደ የበግና የፍየል ቆዳ ላይ) ለመቀየርም ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል። (አእምሮ ንጉሤ፤ ጥንታዊ የኢትዮጵያ የሰላም ጥበቃ ታሪክ (ከቅራት- ዘመናዊ ፖሊስ) ከገጽ 5-21) ስለዚህ ጽሕፈትን ለመጀመር በቅድሚያ የፍጥረትን ከስተት በፊደል መወከል፤ ይህንንም ፊደል ብዛቱን የተወሰነ አድርጎ ማስቀመጥ፣ ፊደሉንም እየጻፉ ለማስቀመጥ የሚያስችል መጻፊያ ነገሮችን ማግኘት (መፍጠር)፤ ይህንንም ኅብረተሰቡ እንዲቀበለው ማድረግን ይጠይቃል። ይህንን ስናስተውል ነው የፊደል ጥበብ አስደናቂነት የሚገባን።

 

የመጀመሪያው ፊደል (አልፋቤት) የየትኛው ቋንቋ ነው?

”በሴምና በካም በያፌት ነገድ፣

ከሦስት ተከፍሎ፣ የፊደል ትውልድ፣

በዛፍ ይመሰላል፣ ዐጽቁ ስለበዛ፣

ከርሱ ፍሬ በልተን፣ አእምሮ እንድንገዛ።” ኪዳነ ወልድ ክፍሌ

 

የሰው ልጅ ከፈጠራቸው ወይም ሊጠቀምባቸው በፀጋ ካገኛቸው ጥባባት ሁሉ ቀዳሚነትንና አስደናቂነት ይዞ የሚገኝ ጥበብ ፊደል ነው ቢባል እብለት አይሆንም። (በተለይ ከኢትዮጵያ ፊደል የበለጠ ጥበብ (ፍልስፍና) ይኖራል ብዬ በግለ አላምንም፤ ይህ እኔ የደረስኩበት መደምደሚያ ነው፤ የጥበቡን ጥልቀትም ሳስተውለው ግርምም ይለኛል።) ምናልባት ይህንን ያስተዋለው ወንደል ሂ. ሆል የተባለ ጸሐፊ ”አልፋቤት (ፊደል) የሰው ልጅ አእምሮ ከፈጠራቸው አስደናቂ ጥበባት ውስጥ ያለ ጥርጥር ታላቁ ፈጠራ ነው” (The alphabet is without doubt one of the greatest creations of the human mind.) ብሏል። በተለይ መጀመሪያ ጥበቡን የፈለሰፈው ማን ነው? የትስ አካባቢ ተጀመረ? ቀዳሚውስ የየትኛው ቋንቋ አልፋቤት (ፊደል) ነው? የሚሉት ጥያቄዎችን መልስ ማግኘት አልተቻለም።

 

በጥቅሉ ስለ አልፋቤት አመጣጥ ያጠኑ አብዛኞቹ ሊቃውንት የደረሱበት መደምደሚያ ”በአሁኑ ሰዓት በአውሮፓ ተመሥርተው በዓለም ላይ ገናና የሆኑት እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ስፔንኛ ... ቋንቋዎች ከሮማይስጥ (ላቲን) ቋንቋ የመጡ ናቸው፤ በመሆኑም አልፋቤታቸወም እንደዚሁ የሮማይስጡን መልክና ቅርፅ የወረሰ ነው። ሮማይስጥ ደግሞ ከፅርዑ (ግሪኩ) የወጣ ነው፣ እሱም ብቻ ሳይሆን የሩሲያም ቋንቋ እንዲሁ የግሪክ ድቃላ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። ”የፅርዕ ፊደልና ጽሕፈትስ ከየት መጣ?” ተብሎ ሲጠየቅም ከዕብራውያንና ከፊንቃውያ ተኮርጆ የተወሰድ መሆኑን የሥነ ልሳንና የሥነ ሰብእ ጥናቶች በምስክርነታቸው አረጋግጠዋል። የፊንቃውያን ጽሕፈት ምንጭ ደግሞ የባቢሎናዊያን ኩኒፎርምና የግብፁ ሄሮግሊፊክ መሆናቸው የጽሕፈት ስሎቶችና የአልፋቤት ቅርጾችን በማነጻጸር ተደርሶበታል። የባቢሎኑም ኩኒፎርም ቢሆን በቅርጽ፣ በአናባቢና በተነባቢ ሁኔታ ተቀያይሮ እንጂ ከግብፅ ሄሮግሊፊክ የተቀዳ መሆኑ የታመነ ሆኗል። የአረብኛም መጻፊያ ፊደል ቢሆን የዕብራይስጥ ልጅ ነው፤ ዕብራይስጥን ሙሴ ከየት አመጣው? መልሱ ከኢትዮጵያ ወይም ከግብፅ ከሚሉ አማራጮች አይዘልም። እዚህም ላይ አንዳንድ ምሁራን ሙሴ የተማረው ከኢትዮጵያዊው ዮቶር ስለሆን ከኢትዮጵያ ፊደል ወስዷል ሲሉ ይህንን አንቀበልም የሚሉ ደግሞ የግብጻውያኑን አጻጻፍ ዕብራዉያን ወስደው አሻሽለው ተጠቀሙበት ከማለት አይዘሉም።

 

የግብፁ ሄሮግሊፊክ አጻጻፍ ምንጭነቱ ባቅራቢያው ላሉት ለጠቀስናቸው ቋንቋዎች መጻፊያነት ብቻ አይደለም፤ ለከቻይናውና ለደቡብ አሜሪካው የኢንካ መጻፊያ ቁይፑም (Quipu) እንጂ። ይህ ብዙ ሐተታ የሚያስፈልገው ቢመስልም ፤ የጥናት ማስረጃዎችን መጠቃቀስ ቢያስፈልግም። ለሊቃውንቱ ግን ሥልጣኔ ካንድ ምንጭ ፈልቃ ነው ዓለማችን አጥለቅልቃ አሁን ያለችበት ደረጃ የደረሰቸው ከሚለው መከራከሪያቸው ጋር ተያይ የታመነበት እውነት እየሆነ መጥቷል። በጥቅሉ ለዓለማችን የአልፋቤት (ፊደል) ምንጭ መፈጠሪያ እኛ ምሥር የምንላት ግብፅ መሆኗ በብዛት ተቀባይነት ያለው ነው። (ይህንን ጎግል በመጠየቅ ማረጋገጥ ይቻላል) ይህ ማለት ደግሞ የዓለማችን የመጀመሪያው የጽሕፈት ፊደል ሄሮግሊፊክ የተባለው የግብፁ ሥዕላዊ የአጻጻፍ ስልት ማለት ነው።

 

በሌላ በኩል ደግሞ ብዙዎቹ ምሁራን የግብፆችን ጽሑፍ ከኢትዮጵያ የተወሰደ መሆኑን ይቀበሉታል። ለብዙ ዘመናትም በኢትዮጵያውያ መጻፊያ በመሆን ያገለግል እንደነበር የጠቆሙም አሉ። ለምሳሌ ሎሬት ፀጋዬ ”የኢትዮጵያ ሄሮግሊፊክ ፊደል” በማለት ይገልጻል፤ አባ ተስፋ ሞገስም ”ቅዱስ ማርቆስ ኢትዮጵያዊ ነው፤ የተዋሕዶ አንበሳም መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በሚለው መጽሐፋቸው ”በኢትዮጵስ ፊደል” የተጻፈው በማለት የግብፅን ሄሮግሊፊክ ጽሑፍ ይጠሩታል። ይህም የግብፆች ሄሮግሊፊክ ጽሑፍ ከኢትዮጵያውያን የተወሰደ እንደነበር ይጠቁማል። እንዲሁም ድሩሳላ ዱንጂ ሆስቶን የተባለችው የታሪክ ምሁርም ”የግብፆች ሄሮግሊፊክ ከግብፅ በበለጠ በኢትዮጵያውያን በተራው ሰው ዘንድ ሳይቀር ይታወቅና ይነገር ነበር” ብላለች።

 

በጽሑፍ ሰፍረው ከሚገኙ አንዳንድ መረጃዎችም በመመሥረት የጽሑፍ ፊደል በኢትዮጵያውያን የተጀመረ መሆኑን መገመት ይቻላል። ለምሳሌ በሰብታህ ጊዜ የነበረው ”ኃይልዋን” የተባለው የጽሑፍ አስፋፊና ተቆጣጣሪ (በአሁን ዘመን አገላለጽ የሥነ ጽሑፍ ሚኒስቴር) ”ጽሑፍ በእኛ ተመሥርታ እንዳጀማመራችን አላደግችም። ጥበብን ከኛ የተቀበሉት አሦሪውያን ለወጥ ባለ መልክ በማዘጋጀት ከኋላችን ተነሥተው ብዙ ሥራ ሠርተውበታል። እኛም እንደየችሎታችን ሠርተን ቀደምትነታችንን ማረጋገጥ አለብን።” በማለት መናገሩ በታሪክነት ተመዝግቦ ይገኛል። (አእምሮ ንጉሤ፤ ጥንታዊ የኢትዮጵያ የሰላም ጥበቃ ታሪክ ከቅራት- ዘመናዊ ፖሊስ፣ ገጽ 21) እንዳውም ”አማርኛና ትግሪኛ የመጀመሪያዎቹ የጽሐፍ ቋንቋ ናቸው” የሚሉም አሉ፡- ምንም እንኳን አጨቃጫቂ ቢመስልም።

 

በሌላ በኩል የግብፅን የሥዕል ፊደሎችን ከእኛ ከግዕዝ ፊደሎች ጋር እያነጻጸርን ብናስተያያቸው ተመሳሳይነት ያላቸው ሆነው እናገኛለን። ለምሳሌ የግዕዝ ፊደል መጀመሪያ የሆነው ”ሀ” ምልክትነቱ የሚወክለው ”ሆይ” ብሎ መጸለይን ነው። በዚህ ጋር ተያይዞም የ”ሀ” ፊደል ”ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ያለውን የዳዊትን ቃል ወክሎ የሚኖር ፊደል ነው። ይህንን ፊደል በግብፅ ሄሮግሊፊክስ ፊደል ውስጥ የ”ሀ”ን ምልክት እንደያዘ ka (ካ) ተብሎ ተሰይሟል። ይህንንም ፀጋዬ ገ/መድኅን የ”ሥላሴ”ን አስተምህሮ ከግብፃዊያን አማልክት ካባሳ (ka-ba-sa) ጋር በማያያዝ ባብራራበት መጣጥፉ የ”ካ”ን ፊደል ”ሃ” በማድረግ በመጠቀም ”ካባሳ”ን ሀበሻ በማለት ተርጉሞታል። በብዙ ጽሑፉም ”ካም” የሚለውን የተፅውኦ ስም ”ሃም” በማለት ይጠቀማል፡- ሎሬት ፀጋዬ። ለዚህም የሠጠው ምክንያት ኢትዮጵያውያን ”ከ” የሚለውን ፊደል እንደ ”ሀ” ይጠቀሙበታል የሚል ነው። (Africa Origin of Major World Religion: The Origin of the ‘Tirinity’ and Art (Ethiopian Origin to Egypto-Greek and Hebrew), page 102) ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ዶ/ር አየለ በክሪም ”ሀ”ን ከሄሮግሊፊክሱ ”ካ” ጋር ያመሳስሉታል። ሌላ ምሳሌ እንጨምር።

 

በሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ በቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አማካይነት የተዘጋጀው ስለ ግዕዝና አማርኛ ቋንቋ ታሪክ የሚያትተው መጽሐፍ በገጽ 12 የ”ፈ (ፌ)” ፊደል ውክልና ሲገልፅ ”የአፍ ሥዕል የተከፈተ አፍ መስሎ ከመላስ ጋር ይታያል።” ብሎ አስቀምጧል። ስለ ፊደሎች የቅጠል አቀያየር ታሪክ ሲናገርም ”ጥንት ግን ቅጠላቸው በቀኛቸው በኩል ነበር፤ እነ ”ፈ” ፊታቸው በቀኝ በኩል ነበር ይባላል” ብሏል (ገጽ 15)። ከእነዚህ የትርጉምና የታሪክ ጥቆማዎች ተነሥተንም የ”ፈ”ን ፊደል ከግብፁ የሄሮግሊፊ ፊደል ”ታ” ጋር ብናጻጽረው አንድ ሆኖ እናገኘዋለን። ሌሎቹንም የሄሮግሊፊክ ፊደሎች ከእኛ ፊደላት ጋር ብነጻጽራቸው ተመሳሳይ ውጤቶችን እናገኛለን። ለዚህም ይመስላል እነ ሎሬት ፀጋዬ እና እነ አባ ተስፋ ሞገስ የግብፅን ሄሮግሊፊ ”የኢትዮጵያ ፊደል” የሚሉት።

 

እንዲሁም ከላይ በጠቀስናቸው በሀገራችን ሊቃውንት ምስክርነት ፊደል ለሰው ልጅ የተሰጠው ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች መጠቀሚያ ለአዳም ሦስተኛ ትውልድ ለሄኖስ ነው፤ ቦታውም አዳም ከገነት ተባሮ ይኖርበት የነበረው ሥፍራ (ኢትዮጵያ?) ሲሆን ቋንቋውም ግዕዝ ነው። በዚህ ዙሪያ ከላይ የጠቀስናቸውን የሁለቱን ሊቃውንት አስተያየት እንጥቀስ።

 

አለቃ አያሌው ”ግእዝ ግን እግዚ፣ እግዚአብሔር አግዓዚ፣ ለኀጢያት ለጣዖት ከመገዛት ነጸ አውጥቶ ግዕዛን የሥጋ የነፍስ ነጻነትን ከሚሰጥ ጌታ ከልዑል እግዚአብሔር ተገኝቶ ለአግዓዝያን ለአዳምና ለልጆቹ የተሰጠ ስለ ኾነ ”ግ” ጋሜል፣ ግሩም ”ዕ፣ ዔ” ዐቢይ፣ ”ዝ” ዝኩር እግዚአብሔር ግእዝ ተብሎ በልዑል እግዚአብሔር ስም ይጠራል፤ እንጂ በፍጡራን ስም፤ እንዲሁም ባለቋንቋዎቹ አግዐዝያን ተብለው በስሙ ያጠሩበታል እንጂ ቋንቋው በባለቋንቋዎቹ ስም አይጠራም፤ ለቀዳሚነቱም ጠቅላላ ማስረጃ ሊሆነን ችሎዋል። አባቶቻችን ስለ ግእዝ ሲተርኩ ድምፁ በአማካይ አፍ አከፋፈት መነገሩ በአርአያ እግዚአብሔር ከማዕከለ ምድር (ቀራኒዮ) ለተፈጠረው በሰማይና በምድር መካከል ላለው በራሪና ተሸከርካሪ ፍጥረት ኹሉ የጸጋ ገዥ ኹኖ ከእግዚአብሔር በታች ከፍጡራን በላይ ማዕከላዊ ማረግ ክብር ለተሰጠው ለአዳም የተሰጠ ቋንቋ በመኾኑ ነው።” በማለት የግዕዝ ቋንቋ ቀዳሚ የሆነበትን ምክንያት ይገልጻሉ። (ሊቀ ጠበብት አያሌው ታምሩ፤ ዝኒ ከማሁ)

 

አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ አበገደ ፊደልና ፊደለ ሐዋሪያ ... መጽሐፋቸው መቀድም ”ግእዝ ማለት አንድ፣ አንደኛ፣ መዠመሪያ፣ በኩር፣ ቀዳማይ፣ ገር፣ ቅን ማለት ስለኾነ፤ የሴምን ቋንቋ ጠልቀው፣ ጠንቅቀው፣ አካተው፣ ፈጽመው ከሚያውቁ የጀርመን ሊቃውንት ስሙንና ግብሩን ተከትለው ግእዝ የአዳም ቋንቋ ነው፤ የሚሉ አሉ” በማለት የኛ ሊቃውንት ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ምሁራንም እንደሚያምኑበት ጠቁመዋል።

 

እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ሲደመሩ ፊደልና ጽሑፍ በኢትዮጵያ የተጀመሩ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ስለዚህ ፊደል (ጽሕፈት) ከሰማይም እግዚአብሔር በጥበቡ ይግለፀው፤ ከመሬትም ሰዎች በልዩ አስተውሎት ተጠበው ይፍጠሩት (ይፈልስፉት) ምንጩ የተገኘበት ኢትዮጵያ፤ ቋንቋውም ግዕዝ ወይም ኢትዮጵያኛ ነው ማለቱ አሳማኝ ይመስላል።

 

ሎሬት ጸጋየ ገ/መድኅንም በአንድ ግጥሙ፡-

አስቀድሞ ሰው ሲፈጠር በዘፍጥረት በአፍሪካ አገር፣

እዚህ አሁን ባለንበት፣ በኖርንበት ክልል ነበር።

ቀጥሎም ቋንቋና ፊደል፣ ልሣንም የፈለቀበት፣

የዓለም የሥልጣኔ እንብርት ይህችው የኛው ጦቢያ ናት።” ብሏል።

(ጦቢያ አምስተኛ ዓመት ቁ.3፣ መጋቢት 1989)


ካሣሁን ዓለሙ

 

http://kassahunalemu.wordpress.com

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!