ሰሎሞን ተሰማ ጂ.

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” (1948) በታተመው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደበየኑት፣ “ፊደል ማለት ቀለም፤ ምልክት፤ የድምፅና የቃል መልክ፤ ሥዕል፤ መግለጫ ማስታወቂያ፤” ነው (ገጽ 616)። ደስታ ተክለ ወልድም በበኩላቸው፣ በ1962 ዓ.ም. ባሳተሙት “ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት” መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ “ፊደል ማለት የነገር፣ የቃል ምልክት፣ የድምፅ ሥዕል፣ ማጉሊያ፤ መግለጫ ነው፤” (ገጽ 988)። በሁለቱም ሊቃውንት አተያይ ውስጥ ፊደል የድምፅና የቃል ምልክት መሆኑን በአጽንዖት ተገልጧል።

 

ስለሆነም፣ እንደማንኛውም የሰው ልጆች ፈጠራና ቅርስ ከጊዜ ጋር ሊለወጥና ሊሻሻልም መቻሉን ጠቋሚ ሁናቴ በትርጓሜው ውስጥ አለ።

 

የዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነን፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ በአዲስ ታይምስ መጽሔት (ቅጽ 1፣ ቁጥር 6) ላይ ያወጡት “የአጻጻፍ ሥርዓታችንን ስለማሻሻል” የሚለውን ጽሑፋቸውን ካነበብን በኋላ ነው (ገጽ 14-15ና 26 ላይ ይመልከቱ)። ጽሑፉ በርካታ ቁምነገሮችን ይዟል። ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ስለፊደልና ስለአጻጻፍ ሥርዓታችን ጉዳይ ደግመው በዚህ ዘመን ላለውም አንባቢ ስላነሡትና የአንባቢያንን አስተውህሎትም ለመቆስቆስ ስለሞከሩ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። በተጨማሪም፣ የሃሳቡን ማጠንጠኛ እንዝርትና ቀሰም በወጉ ስላቀረቡልንና የትኛውንም የሃሳብ ጎራ እንደሚደግፉም በአደባባይ ወጥተው ስለገለጹልን ላቅ ያለ ሥራ ሰርተዋል።

 

ዶ/ር በድሉ በጽሑፋቸው ውስጥ የሃሳብ ጎራቸውን ከመለየታቸውም በተጨማሪ፣ ሁለቱን “እምነቶቻቸውን” በጠራ ቋንቋ ገልጠውልናል። የመጀመሪያው እምነታቸው፣ ስለሞክሼ ፊደላት ጉዳይ ሲሆን፣ “አንድን ድምጽ ለመወከል ሲባል ሁለትና ከዚያም በላይ የሆኑ ሞክሼ ፊደላት መደጋገማቸው አስፈላጊ አይደለም፤” የሚል ነው። በሁለተኛ ደረጃም የጠቀሱት መከራከሪያቸው፣ “ጽሕፈትን/ፊደልን ለማሻሻል የሚገባው፣ ቋንቋ ከጊዜ ጋር እየተለወጠ የሚሄድ አኃዝ ስለሆነ ነው፤” ሲሉ ያቀርባሉ። በመጨረሻም፣ “የአንድን ቋንቋ የአጻጻፍ ሥርዓት ለማሻሻል ሲነሱ ሁለት ደረጃዎች አስፈላጊ ናቸው። እነርሱም፣ በመጀመሪያ የአጻጻፍ ሥርዓቱ ችግር አለበት ወይ ወይንስ “ብቁ” ነው በሚለው ላይ እንነጋገርበት፤” ሲሉ አንባቢያኑን ይጋብዛሉ። በማስከተልም፣ “በሁለተኛው ደረጃ ላይ ደግሞ፣ ፊደላችንና የአጻጻፍ ሥርዓታችን “ችግሮች አሉበት” የምንል ከሆነ፣ ችግሮቹ እንደምን ይስተካከሉ” የሚለው ነጥብ ላይ ኋላ እንመለስበታለን” የሚል ገንቢ ጥያቄ ነው ያነሱት።

 

የዶ/ር በድሉ ጽሑፍ ስለፊደላት ጉዳይ ሲያወሱ በአመዛኙ የሀገራችንን የፊደላት ክርክር ታሪክ ትተው፣ በውጭው (ማለትም በቱርክና በጃፓኖች) የፊደላት ለውጥ ጉዳይ ላይ አተኩረዋል። በተጨማሪም፣ በርካታ የፊደላትነ ለውጥ የሚደግፉ ንድፈ ሃሳቦችን በሰፊው አቅርበዋል። ይበል የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን፣ የእኛን ጓዳም በተመለከተ በዝርዝር ስላልከለሱልን (ሙያቸው ነውና በቅጡ ያውቁታል)፣ ይህንን ጽሑፍ ለአንባቢያን እዝነ ሕሊና ይበጃል ስንል ጽፈነዋል። ስለፊደላችን ጉዳይም ጠቅለል ያለ መረጃ ለአንባቢያን ይሰጣል ብለን እናምናለን።

************************

 

የአማርኛ ፊደላትን ስለማሻሻል ልዩ ልዩ አማራጭ ሀሳቦች ከሃዳሲያን (ከተሃድሶ ፈላጊዎቹ) ሊቃውንት ዘንድ በይፋ መደመጥ የጀመረው ከዛሬ ሰማኒያ አመት ወዲህ ነው። (ቀደም ብሎ ግን ጉዳዩ በለሆሳስ ነበር የሚብላላው።) ለምሳሌ በዚሁ አርእስተ ጉዳይ ላይ ሀ) “መዝገበ ፊደላት ሴማውያት” ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ድሬ ዳዋ፣ በ1926 ዓ.ም.፤ ለ) “አዲስ የአማርኛ ፊደል” ከትምህርትና ሥነጥበብ ሚኒስቴር፣ በ1939 ዓ.ም.፤ ሐ) “ፊደልን ማሻሻል” ከትምህርት ወዳጆች፣ በ1940 ዓ.ም.፤ መ) “የአማርኛ ፊደል ሕግን እንዲጠብቅ ለማድረግ የተዘጋጀ ሪፖርት” በኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት፣ ቅጽ 8፣ ቁ.-1፣ በ1962 ዓ.ም.፤ ሠ) “ስለአማርኛ ፊደል መሻሻል ጥናትና ውሳኔ” አ.አ፣ 1973 ዓ.ም. ተጽፈዋል።

 

መንግሥቱ ለማ (መንግሥቱ ለማ - ደማሙ ብዕረኛ (ግለ ታሪክ)) በሚል ርዕስ በ1988 ዓ.ም. በወጣው መጽሐፋቸው ላይ በ1940-1943 ዓ.ም. ስለነበረው የፊደል ክርክሩ ጭብጥ ሲያወሱ፣ “ከፊደል ይሻሻል ባዮቹ ይበልጥ፣ ፊደላችን በላቲን የአጻጻፍ ሥርዓት ይተካ፣ የላቲን ፊደላትም ሙሉ በሙሉ ፊደሎቹን ይተኳቸው የሚል ሃሳብ ያላቸውን፣ ከመቶ ዘጠና አምስቱ እጅ፣ ጣሊያን ተመልሶ ይግዛን እንደማለት ነበር የቆጠረው። ሆኖም ግን፣ መድረክ ላይ ተከራካሪ የነበሩት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ባለሥልጣኖች ስለነበሩ፣ ሕዝቡ ቆሽቱ ቢያርም ፈርቶ ዝም ብሎ ነበር፤” ሲሉ ያስታውሱታል (ገጽ 121)። ሆኖም፣ በባለሥልጣናቱ አካባቢ የነበረውን “ፊደል የማሻሻል ቀናዊነት” መንግሥቱ ለማ በአርምሞ ነው የሚያልፉት። በፊደሎቻችን አማካይነት የራሳችንን መጽሐፍት የማተሙ ፍላጎት በቤተ መንግሥት አካባቢ የተጀመረው ከአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት አንስቶ ነው። ባለሥልጣናቱም የዚያ “ሥልጣኔ” አቀንቃኞች ነበሩ።

 

ፊደሎቻችንን ለማተሚያ መሣሪያ እንደያመቹ ተደርገው መፊደሎቻችን መጽሐፍት የማተም ፍላጎት የተወጠነው በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት በ1513 ዓ.ም. ነበር። “ልብነ ድንግል ለፖርቹጋሉ ንጉሥ በጻፈው ደብዳቤው ላይ ግልጽ እንዳደረገው፣ “በፊደላችን መጽሐፍት መተም የሚችሉ” የእጅ ሥራ አዋቂዎችን ላክልኝ ብሎ ጠይቆት ነበር። ነገር ግን፣ የማተሚያ መሣሪያው ጉዳይ ከነገሥታቱ ሕሊና አልጠፋም ኖሮ፣ በአፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት በ1887 ዓ.ም. ፈረንሳያዊው ደራሲ ሞንዶ ቪደልዬ በአፄ ምንሊክ ትእዛዝ ገዝቶ ማምጣቱን፤” (የፕሮፌሰር ሥርግው ኃብለ ሥላሴ፤ “አፄ ምንሊክ የአዲሱ ሥልጣኔ መሥራች”፤ በሚል ርእስ ማሳተሙት መጽሐፍ በገጽ 337 ላይ በዝርዝር ቀርቧል)። ሆኖም፣ የማተሚያ መሣሪያው ታትሞ ከመጣም በኋላ የፊደላችን ነገር ለመሣሪያው እንዲያመች ሆኖ መሻሻል ነበረበትና አፄ ምንሊክ ጉዳዩን በእጅጉ ገፍተውበት እንደነበር ፕ/ር ሥርግው ዋቢ ጠቅሰው ያስረዳሉ (ገጽ 370)።

 

ያነሷቸው ጥያቄዎች በከፊል ከዳግማዊ አፄ ምንሊክ ዘመን ጀምሮ ቢያንስ በአራት ትውልዶች ተነስተዋል። አሁን ስንነጋገርበት እንግዲህ በአምስተኛው ትውልድ ዐይን፣ ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። የመጀመሪያዎቹ ትውልዶች፣ ማለትም እነአፄ ምኒሊክ “ፊደላችን ለምስጢር መልእክትና ለቴሌግራፍ አጻጻፍ አልተመቸንም” ከሚል ሃሳብ ተነስተው ነበር። ስለሆነም፣ ፊደላችን በላቲን ሥርዓት ይተካ ሳይሆን፣ “ለሚስጢር መልዕክትና ለቴሌግራፍ መልዕክቶች መላላኪያ እንዲያመች ሆኖ ይሻሻል፤” የሚል መነሻ ነበር ግንዘቤያቸው። ጉዳዩን በብዙ ገፍተውበት የሚከተሉትን ፊደላት እስከ እርባታቸው ለማሻሻል ጥረት አድርገው ነበር።

(ምንጭ፣ ሥርግው ሀብለ ሥላሴ፤ አፄ ምንሊክ የአዲሱ ሥልጣኔ መሥራች (ዓ.ም. የለውም)፤ ገጽ 369)

 

ሁለተኛው ትውልድም የፊደልን ጉዳይ ያነሳው ከጣሊያን ወረራ ቀደም ብሎና በኋላም ባለው ዘመን ነበር። አብዛኞቹ ተሃዳሲያንም የቤተ-ክሕነት ሊቃውንት ነበሩ። “የነአለቃ ለማ ትውልድ” ብለን ልናወሳው እንችላለን። ይኼኛው ትውልድ ደግሞ፣ “የአማርኛ ፊደሎች ጊዜያቸው አልፏል፤ አርጅተዋል፤ አሮጌ ሆነዋል፤ አይረቡም፤ ለማተሚያ መኪናና ለቅልጥፍና አይመቹም” የሚል ክርክር ነበር ያነሳው። በአመዛኙ የቀዳሚውን ትውልድ ጥያቄ በቤተ-ክህነት ዙሪያ ሆነው እንደገና ለማራገብ ነበር የጣሩት። ስለሆነም፣ “የቅዱሳን ሰማዕታትና የፃድቃን ገድል የተጻፈበት ፊደል ካረጀባችሁ፤ ከጃጀባችሁ፤ ለምን ከሁለት ያጣ እንሆናለን። የግዕዙ ፊደል ይቅር ካላችሁ፣ ለምን የሙስሊም ወንድሞቻችን ለዘመናት የተጠቀሙበትን የአረቢኛ ፊደል አንጠቀምም። ምን የነጭ ፊደል ያዋውሰናል?!” የሚል ደገኛ ክርክር ነበር ያነሱት (መንግሥቱ ለማ - ደማሙ ብዕረኛ፣ 1988 ዓ.ም.፣ ገጽ 124)። ጉባኤው በአለቃ ለማ ሀሳብ ድንብርብሩ ወጥቶ ተበተነ።

 

ሦስተኛውም ትውልድ የዘመኑን ችግሮች ለመፍታት ጥሯል። ዋናው ችግር የነበረው፣ “ፊደላችን ለጽሕፈት መኪና (ለታይፕራይተር) የተመቸ አይደለም፤” የሚል ነበር። በዚህኛውም ትውልድ እንደመጀመሪያው ሁሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሚኒስትሮች ሳይቀሩ ጎራ ለይተው ተከራክረዋል። በዚህኛው ጊዜም ክርክሩ እጅግ የበረታ ነበር። በወቅቱ የጤና ጥበቃ ም/ሚ/ር አበበ ረታ፣ የጽሕፈት ሚ/ሩ ብላታ ዘውዴ በላይነህ፣ መርስዔ ሀዘንም ከ1943 ጀምሮ የጤና ጥበቃ ም/ሚ/ር ነበሩ። አቶ መኮንን ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ነበሩ። ኮለኔል ታምራት ይገዙም የትልቅ መኳንንት ዘርና ባለወገን ናቸው። በአንፃሩ ደግሞ፣ እነአቶ ብርሃኑ ድንቄና እነመንግስቱ ለማ ከካህናቱ ወገን ሆነው ነበር የሚከራከሩት። ከላይ እንዳልኩት፣ ይኼኛው ክርክር በሦስት ረድፍ ያሉ ተሟጋቾች ናቸው የተከራከሩበት። ፊደላችን በላቲን ፊደል ይተካ የሚሉት ወገኖች በነራስ እምሩ፣ በመርስዔ ሀዘን ወልደ ቂርቆስና በነታምራት ይገዙ አቀንቃኝነት ሲወከሉ፤ “የለም! ፊደላችን በላቲን አይተካም ግን ማሻሻል አለበት” የሚለውን ሃሳብ ደግሞ እነ ሚ/ር አበበ ረታና ብላታ ዘውዴ በላይነህ ነበሩ የሚያራምዱት። በሦስተኛው ረድፍ ያሉት ወገኖች ደግሞ መሠረተ ካህናት ስለነበሩና የፖለቲካ ስልጣናቸውም እስከዚህም ስለሆነ መድረክ ተነፍጓቸው ነበር። ዋና ዋናዎቹ ተከራካሪዎችም አቶ ብርሃኑ ድንቄ፣ የኔታ አስረስ የኔሰውና አቶ መንግስቱ ለማ ነበሩ። አቶ መንግሥቱ ከሁሉም በእድሜ ታዳጊው ወጣት ነበሩ (መንግሥቱ ለማ - ደማሙ ብዕረኛ (ግለ ታሪክ)፣ 1988 ዓ.ም.፣ ገጽ 115-124)።

 

ወደአራተኛው ትውልድና ወደፊደል ክርክሩ እንለፍ። ይህም ትውልድ የሀዲስ አለማየሁን “ፍቅር እስከ መቃብር” እያነበበ የተማረና በስነ ልሳን እውቀቱም ቢሆን ወደፊት የተራመደ ነበር። የዚህም ትውልድም ዋናው ችግር “የፊደሎቻችን ቁጥር በዛ፣ የሚክሼ ሆሄያት ድግግሞሽ ይቅር፣ የሚጠብቁና የሚላሉትን የማርኛ ቃላት በወጉ ካለየናቸው ተማሪዎቻችን ለማስተማር አስቸጋሪ ሆነውብናል፤” ከሚል ነበር። በአመዛኙ ከማስተማርና ከስነዘዴው ጋር የተያያዙ ችግሮችን ያማከለ ነበር። በዚህ ዘመን “የፊደል ሠራዊት” የሚባል የማንበብና የመጻፍ ትምህርት ለጎልማሶች ይሰጥ ስለነበር፣ የፊደል መምህራኑ ከፍተኛ ችግር ገጥሟቸው ነበር። ለአብትም ያህል እነአቶ ሀብተ ማርያም ማርቆስ፣ በየዛሬይቱ ኢትዮጵያ (መጋቢት 6ና 13/1961 ዓ.ም.) ላይ በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ሰፊና አስተማሪ የሆነ ጽሑፍ አውጥተው ነበር (ገጽ 5፣7 ላይ ይመልከቱ)።

 

አቶ ሀብተ ማርያም በጽሑፋቸው መቋጫ ላይ ሲደርሱም፣ “አጻጻፋችንን አሻሽለንስ? ከዚያ በፊት በተለመደው አጻጻፍ የተመዘገበው ጽሑፋዊ ቅርሳችንን ሁሉ ምን እናድርገው? ለመጪውስ ትውልድ እንዴት አድርገን ጽሑፋዊ ቅርሳችንን እናስተላልፈው? የታሪክንስ ክር ለመበጠስ መሞከር አይሆንብንምን?” የሚሉ ወገኖች በብዛት ይደመጣሉ ካሉ በኋላ፤ “በተለይም ንግግር ከጊዜ ጋር አብሮ የሚለወጥ ስለሆነ፣ ንግግሩ በተለወጠ ቁጥር ጽሕፈቱስ አብሮ ሊለወጥ ነው ወይንስ ምን ሊደረግ ነው?” ሲሉ ሞጋች ጥያቄዎችን ያነሳሉ። በመጨረሻው ላይም፣ “ብንስማማም-ባንስማማም፣ አጻጻፋችን ለብዙ ጊዜያት አሁን ባለበት ሁኔታ የሚቆይ ይመስላል፤” ሲሉ ተስፋቸውን ገልጠዋል (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ መጋቢት 13/1961 ዓ.ም.፣ ገጽ 7)።

 

በተመሳሳይ ሁናቴም፣ አቶ ከበደ ዮ. ቤርተሎሜዎስ የተባሉ መምህር “የአማርኛ ፊደልን ስለማሻሻል የቀረበ ጥናት” በሚል ርእስ ሥር ስለሚክሼ ፊደላትና እንደምን ሆነውስ ሊሻሻሉ እንደሚችሉ አጭር ቅኝትና አማራጭም አቅርበዋል። አብዛኛውም ሃሳባቸው ሄዶ ሄዶ ደራሲ/አምባሳደርና/ሚኒስትር ሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር መግቢያ ላይ ካሰፈሩት ሃተታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው (ኧረ እንዲያውም ድጋፍ ነው፤) ሆኖ ይቋጫል (አዲስ አመን፣ ሰኔ 12/1961 ዓ.ም.፣ ገጽ 2)።

 

ይኼው የአራተኛው ትውልድ የፊደል ክርክር ሙሉ ለሙሉ ለአራተኛው ትውልድ ብቻ የተተወ አልነበረም። በተለይም የኔታ አስረስ የኔሰው ለዚህ ትውልድ ስለፊደል ምንነት በሠፊው ለማስተማር በማሰብ አራት መጽሐፍትንና አንድ የጋዜጣ ላይ መጣጥፍም አሳትመዋል። እነርሱም፣ ፍኖተ ሰላም (1940)፣ ፍኖተ ጥበብ ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር (1958)፣ የካም መታሰቢያ (1951)፣ ትቤ አኩሱም መኑ አንተ (1951) ሲሆኑ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ደግሞ “የአማርኛ ፊደል ክርክር” የሚል ሃተታ በነሐሴ 1/1955 ዓ.ም. አውጥተዋል። አስረስ በሁሉም ጽሑፎቻቸው ላይ ስለአማርኛ ጽሑፍ አመጣጥ ካወሱ በኋላ፣ እያንዳንዱ አማርኛ ከግዕዝ የተዋሰው ፊደል ስንት ድምጾች እንዳለው ሲመልሱ እንዲህ ነበር ያሉት። “የግዕዝ ፊደሎች 26 ናቸው። እነዚህም 26 ፊደሎች በ7ቱ አናባቢዎች ተባዝተው 182 ይሆናሉ። እነዚህም የፊደላት ብዜቶች የሚወክሉት የፍጥረታት መጀመሪያ ዕለት ከሆነው ከሚያዝያ 1 ቀን ዕለተ እሑድ ጀምሮ እስከ መስከረም 31 ቀን ዕለተ ቅዳም/ቅዳሜ ያሉትን 26ቱን እሑዶች፣ 26ቱን ሰኞዎች፣ 26ቱን ማክሰኞዎች፣ 26ቱን ረቡዑዎች፣ 26ቱን ሐሙሶች፣ 26ቱን ዐርቦችና 26ቱን ቅዳሞዎች የሚወክሉ ፊደሎች ናቸው እንጂ በዘፈቀደ የመጡ አይደሉም፤” ሲሉ ይከራከራሉ። ስለዚህም፣ እንደየኔታ አስረስ አስተምህሮት ከሆነ የአማርኛ ፊደሎች ድምጽን ብቻ የሚወክሉ ሳይሆኑ፣ ፤መለኮታዊ የሆነ ሚስጢርም” ያላቸው እንደሆኑ ያብራራሉ።

 

ሌላው የአራተኛው ትውልድ መለዮ የሆኑትን ሃሳቦች ማሳያው በ1956-1966 ድረስ የወጡት ጽሑፎች ናቸው። አንዱ ስለ”ቋንቋና ፊደል መሻሻል ጉዳይ” መነጋገር ይገባናል ሲል፣ ሌላው ወገን ደግሞ፣ “ፊደሉ ትተን ሌላውን ለማሻሻል እንሞክር፤” ሲል ያጣጥለዋል (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ሚያዝያ 3 ቀንና ግንቦት 15/1956 ዓ.ም.፤ አዲስ ዘመን፣ ታኅሣሥ 10ና መጋቢት 7/1961 ዓ.ም.)። በመጨረሻም፣ ከየካቲት 6-9 ቀን 1972 ዓ.ም. ድረስ በናዝሬት አዳማ ራስ ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ተሰብስቦ-ስለአማርኛ ቋንቋ ፊደላት፣ ስለአማርኛ ሞክሼ ቃላት፣ ስለፍንቅጽ ሆሄያት፣ ስለስርዓተ ነጥቦችና ስለአማርኛ ቁጥሮችም ባለአስር ነጥብ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። በጉባኤውም ላይ፣እነሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ አቶ አሰፋ ሊበን፣ አቶ አበበ ወርቄ፣ አቶ ሀብተ ማርያም ማርቆስ፣ አቶ መንግሥቱ ለማ፣ አቶ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ፣ አቶ ሠይፉ መታፈሪያ፣ ከዶክተሮቹም መካከል-ዶ/ር ኃይሉ አርአያ፣ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ፣ ዶ/ር መርዕድ ወ/አረጋይ፣ ዶ/ር ብርሃኑ አበበና ዶ/ር አባ ገብረየሱስ ኃይሉ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በአብላጫ ድምጽም በዘጠኝ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አስተላልፈዋል (ስለአማርኛ ፊደል መሻሻል ጥናትና ውሳኔ፣ አ.አ 1973 ዓ.ም.፤ ገጽ 45-48)።

 

ወደአምስተኛው ትውልድና ስለፊደል ጉዳይ ያሉትን ነጥቦች እናንሳ። ይህ ትውልድ ከ1980ዎቹ ጀምሮ ያለውን ትውልድ ይመለከታል። የአማርኛ ፊደላት በግልጽ የፖለቲካና የፖለቲከኞችም አጀንዳ ሲሆኑ ባይኑ በብረቱ አይቷል። ብዙዎቹ የኩሽና የናይሎ ሰሃራ ቋንቋዎች ወደ ላቲን ፊደላትና የአጻጻፍ ሥርዓት ድርስም ብለው ሲነጉዱ ተመልክቷል። ስለሆነም፣ ስለፊደልና ስለአጻጻፍ ሥርዓታችን መሻሻል ሲነሳ በጥርጣሬና የሻጉራ ነው የሚመለከተው። ዞሮ ዞሮም፣ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባሕል፣ ሃይማኖትና ቅርስ ላይ የተቃጣ በትር አድርጎም ነው የሚያየው። ትውልዱ በእጅጉ የባዕዳን ተፅዕኖና የእጅ አዙር የባሕል ወረራ አንገፍግፎታል። ያንንም በኮሮጆ ውስጥ ድምጹን በመክተት፣ በአብያተ ክርስቲያናትና በቤተ መስጊዶችም ውስጥ በይፋ እየታገለው ነው። ባዕድ አስተሳሰብንና የባዕዳን ሴራ ነው ብሎ የተጠራጠረውን ሁሉ ጠልቆ ለመመርመር አይሻም። በደፈናው ይጠላዋል፤ ያጥላላዋል። ስለዚህም፣ የሕዝቡን ስስ ብልቶች በዘዴና በመላ መደባበሱ ነው የሚሻለው።

************************

 

የቋንቋ እድገት ወይም አጠቃቀም ከፊደልና ከአኃዝ ጋር ተያይዞ እንደሚጓዝ አይካድም። በተለይም፣ በዚህ የብዕር፣ የወረቀትና የመቀምር (የኮምፒውተር) ዘመን፣ ፊደል የሌለው ቋንቋ ሊያድግ ቀርቶ ሊኖርም አይችልም ይባላል። ስለዚህም ነው፣ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የላቲን ፊደሎችን ወደመዋሱና መጠቀሙ ያዘነበሉት። ከላይ እንዳልኩት አዲስ ነገር አላመጡም። በአለቃ ለማ ትውልድና በመርስዔ ሀዘን ትውልድ ጊዜ የነበረውን ሀሳብ ነው ለሥልጣኔና ለዕድገት ይበጃል ብለው ያደረጉት። ተደጋግሞ የሚነሳውም የቱርክ ፊደሏን ትታ የላቲን ፊደልን መቀበሏና የጃፓን ፊደሏን ሳትቀይር በሥልጣኔ የመገስገሷ ታሪካዊ ተሞክሮ ነው። የኛ አገር የብሔር ፖለቲከኞችና አመራራቸው የቱርኩ ልምድ ይሻለናል ብሎ ከወሰነ፣ ይኼው ሁለት አስርት አመታት ገደማ ተቀጠሩ።

 

ብዙዎቹ የሴም ቋንቋዎች በዚህ በኩል በጣም የታደሉ ናቸው። በተለይም አማርኛ እድለኝነቱ አያጠራጥርም። የራሱ ፊደል፣ ሥነ ጽሑና የራሱም አኃዝ (ቁጥሮች) አሉት (ማለትም ከግዕዝ የተዋሳቸው)። ያም የሚያኮራና የሚያስመካ ነው። ያም ሆኖ እክሎች ቢኖሩበት አያስደንቅም። እንደሌሎቹ የሰው ልጅ ሥራዎች ሁሉ ገና “ለፍጽምና” አልደረሰም። “ሆሄያቱ ለቴሌግራፍ መልዕክት ማስተላለፊያነትና ለጽሕፈት መኪና አጠቃቀም ያስቸግራሉ፤” የሚለው የአንደኛውና የሦስተኛው ትውልድ ጥያቄዎች ከኮምፒውተርና ከsoftwares መፈጠር ጋር ያከተሙ ጉዳዮች ሆነዋል። የአራተኛው ትውልድ ያነሳው ለማስተማር ያስቸግራሉና መሻሻል አለባቸው የሚለው ሃሳብም በቴክኖሎጂው ረዳትነትና በዘመኑ መንፈስ ተቃኝቶ መፍትሄ እንደሚያገኝ ተስፋ አለን።

 

የአማርኛ አኃዞች ለሒሳብ ሥራ አለመመቸታቸው እሚካድ አይደለም። ሌላው ቀርቶ የአማርኛ አኃዝን ማንበብና መጻፍ ለማስተማር እንኳ ከባድ ናቸው የሚሉ ሊቃውንት አሉ። ስለዚህም ነው ይሄንን ከፍተኛ የሆነ የማንነት ጥያቄ ፈተና በለሆሳስ አልፈነው፣ የአውሮፓውን ቁጥር ለብዙ አሰርት ዓመታት በሂሳብ ማስተማሪያነት የምንጠቀመው። ይህም ቢሆን አያስገርምም፤ አያሳፍርምም። ፊደሎቻችንም ሆኑ አኃዞቻችን የተፈጠሩት ቴሌግራፍ፣ የጽሕፈት መኪናና የሒሳብ ስሌቶች ወረቀትና መቀምር ላይ መጻፍ ከመጀመራችን አያሌ ዓመታት በፊት ነው። ያን ጊዜ መሠረታዊ ትምህርት (የፊደል ሠራዊት) አጣዳፊ አጀንዳ አልነበረም። መማር የሚያስፈልገው ለቤተ ክህነት አገልግሎት ብቻም ነበር። እስከ ሰባና ሰማንያ ዓመታትም ድረስ፣ ሚሊዮን የሚባለው ቁጥር በኅብረተሰባችን መዝገበ ቃላት ውስጥም አልነበረ። (እነ”ሚሊዮን ነቅንቅ” የሚባሉት ስሞች የመጡት ከ1925 ዓ.ም. በኋላ ነው።) ቢሊዮንማ የታወቀውም በ1958/59 ገደማ እንደነበር አዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያን ማየቱ ብቻ ይበቃል። ከዚያ በፊት፣ “አንድ ቢሊዮን ለማለት ሲፈለግ አንድ ሺ ሚሊዮን፣” ነበር የሚባለው። ሚሊዮንና ቢሊዮን የሚባለው ሒሳብ በሕብረተሰባችን አኗኗር ውስጥ ያልገባ ስለነበረ ነው። (ቸር እንሰንብት!)

ሰሎሞን ተሰማ ጂ. (semnaworeq.blogspot.com)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!