እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሠላም አደረስዎ! … “መስከረም ባበባው ሠርግ በጭብጨባው ይታወቃል” ይላሉ አበው። አንድም መስከረም ርዕሰ ዓውደ ዓመት፣ የዘመን መለወጫ በመሆኑ ወርኃ አደይ ወወርኃ ጽጌ ተብሏል።

 

እናም ኢትዮጵያውያን በርዕሰ በዓልነት ታላቅ ማዕዘን ላይ ያስቀመጡት ወርኃ መስከረም፣ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን አቅፏል። ከነዚህም ውስጥ ከዕንቁጣጣሽ በዓል ቀጥሎ በሠፊው የሚታወቀው በዓለ መስቀል የተባለው ነው።

 

መስቀል ምንም እንኳ በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ፣ የራሱ የሆነ ትርጉም ያለው ቢሆንም ከኃይማኖታዊ ክንዋኔው ባሻገር፣ ባህላዊ በሆነ ገፅታ የሚያከብሩት የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ለምሣሌ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚካኼዱት ልዩ ልዩ ዝግጅቶችና ሬቻ ተብሎ የሚታወቀው የኦሮሞ ህዝብ በዓል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

 

ይኼ ጽሑፍ የሚያጠነጥው ግን በኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን ተከብሮ የሚውለውን በዓለ መስቀል ታሪካዊ ዳራ ለማስታወስና በዚህ ታሪካዊ በዓል ላይ የአንዳንድ ሊቃውንት አስተያየቶችን መጠቋቆም ነው።

 

ስለመስቀል በዓል አከባበር መነሾ፣ በጽሑፍና በቃል የተላለፉ መረጃዎች እንደሚነግሩን ኢየሱስ የተሰቀለበት መስቀል በተዓምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑ፣ አይሁድ በቅንአት ተነሣሥተው ከ300 ዓመታት በላይ በቆሻሻ መጣያ ጥለውት ነበር።

 

ይሁንና በ326 ዓ.ም. የቄሳር ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ፣ ኪራቆስ በተባለ አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ ጠቋሚነት፣ መስቀሉ የተጣለበትን አካባቢ ተረዳች። ከዚያም በኋላ ደመራ ደምራ በእሳት ባቀጣጠለችው ጊዜ፣ ጢሱ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ያረፈበትን ሥፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታዋለች።

 

ንግሥተ እሌኒ በጭሱ ምልክትነት፣ መስቀሉን ለማውጣት ለሰባት ወራት ያህል ማስቆፈሯን ማለትም መስከረም 17 ቀን አስጀምራ በመጋቢት 10 ቀን እንዳስወጣቸው ይነገራል። ዛሬ በኦርቶዶክስ ምዕመናን ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንን ታሪክ ተከትሎ እንደሆነ የሊቃውንቱ ምስክርነት አለ።

 

በነገራችን ላይ ስለመስቀል በዓል ስናነሣ ልዩ ክብሩ በተዋህዶ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ዘንድ ብቻ መሆኑን ማውሳት ያስፈልጋል። የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ወይም ክርስቲያኖች በኢየሱስ ተሰቅሎ መሞትና በመስቀሉ የማይረሳ ውለታ የሰው ልጅ መዳኑን ቢያምኑም እንደ ኦርቶዶክስና ሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ትውፊትን ስለማይቀበሉ፣ የመስቀል በዓልን ኃይማኖታዊ በዓል አድርገው አይመለከቱትም። እናም በኢትዮጵያ የመስቀል በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብቻ መሆኑን መረዳት ይገባል።

 

ወደ ተነሳንበት ነጥብ ስንመለስ፣ ስለመስቀል በዓል በአንዳንድ ሊቃውንት የተለያየ አስተያየት ሲሰነዘር ቆይቷል። ከዚህ ውስጥ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው መስቀሉን ለማግኘት ሰባት ወራት ያህል እንደፈጀ ቢነገርም በአንዳንድ ሊቃውንት ህሳቤ ደግሞ መስቀሉ የተገኘው መስከረም 17 ነው ሲሉ በአጽንዖት ይናገራሉ። ይሁንና አብዛኛው የቤተክርስቲያኗ ሊቃውንት ግን “መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ነው፣ ይህ ወር ግን የዐቢይ ጾም ወር በመሆኑ በዓሉ በመስከረም 17 እንዲሆን ሊቃውንቱ ተስማምተው አቆይተውናል” ሲሉ የላይኛውን ሃሳብ ያፈርሳሉ።

 

ስለመስቀሉ ጉዳይ ስናነሳ አንድ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ አለ፤ ይኸውም በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት፣ ኢየሱስ የተሰቀለበት ቀኝ ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል የሚባለው ጉዳይ ነው። ስለዚህ መስቀል መምጣት የቤተክርስቲያኗ ጸሐፍት በተለያዩ ሠነዶቻቸው የተረኩ ሲሆን፣ ንጉሡ አፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን አስመጥተው በኢትዮጵያ አድባራት ሁሉ በመዞር፣ ሊያሳርፉበት ያልሞከሩበት ቦታ አልነበረም፤ ነገር ግን መሬቱ እየተንቀጠቀጠ አስቸጋረ። በመጨረሻ ግን “መስቀሌን በመስቀልያ ሥፍራ አስቀምጠው” የሚል መለኮታዊ ምሪት ስለደረሳቸው፣ አሁን ግሼ አምባ በተባለ ሥፍራ እንዳስቀመጡትና ይህም ሥፍራ መስቀልያ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ እንዳለው ይነገራል።

 

እንግዲህ ስለመስቀል በዓል ታሪካዊ ዳራ ይኼን ያህል ካልን፣ ከዛሬ ዘጠና ሁለት ዓመት በፊት ማለትም መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም.፣ በሀገራችን ስለተከናወነ አንድ ታሪካዊ ድርጊት እናውሳ።

 

በብዙ አንባብያን ዘንድ እንደሚታወቀው ይኼ ወቅት ከዐፄ ሚኒልክ መሞት በኋላ እርሳቸውን የተኩት አቤቶ ኢያሱ ሥልጣን ላይ የነበሩበት ጊዜ ነው። ይሁንና ልጅ ኢያሱ ዕድሜያቸውን ምክንያት ያደረገ የተለያዩ ክሶች ቀርቦባቸው፣ ከአልጋው እንዲወርዱና የተሻለ ንጉሥ ለመምረጥ አድማ የተደረገባቸው ጊዜ ነበር።

 

እወቁ የሥነ ጽሑፍ ሰው መርስዔ ኅዘን ወልደቂርቆስ “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት” በሚል ርዕስ ለንባብ ካበቁት መጽሐፍ መረዳት እንደሚቻለው፣ ልጅ ኢያሱን በሌላ ንጉሥ የመተካት አድማ የተደረገው ማክሰኞ መስከረም 16 ቀን 1909 ዓ.ም. ነው።

 

በበጅሮንድ ይገዙ በሀብቴ፣ በሊጋበ በየነ፣ በደጃዝማች ኃ/ማርያምና በፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ መሪነት የተካኼደው ይኸው አድማ፣ አቤቶ ኢያሱ ሠለሙ ተብሎ መወራቱን ተከትሎ ሌሎችም በዘመኑ ከአንድ ንጉሥ ይጠበቃል የማይባል ድርጊት መፈጸማቸው ተነገረ። እናም የአድማው አደረጃጀት ስር መስደዱ ከታወቀ በኋላ ለወትሮው መስከረም 16 ይደረግ የነበረው የወታደር ሠልፍ በየደብሩ እንዲሆን በመታዘዙ ሰልፉ ሳይታይ ቀርቷል።

 

በማግስቱ ማለትም ረቡዕ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም. በ3 ሰዓት አቡነ ማቴዎስና እጨጌ ወ/ጊዮርጊስ እንዲሁም ሚኒስትሮችና መኳንንት፣ ሻለቆችና ሻምበሎች በቀኝና በግራ በየማዕረጋቸው ከተቀመጡ በኋላ፣ ልጅ ኢያሱን ለመሻርና አዲስ መንግሥት ለማቋቋም የተፈለገበትን ምክንያት ለህዝብ ለማስረዳት፣ በአድማው መሪዎች የተዘጋጀውን ጽሑፍ ተነብቦ አቤቶ ኢያሱ ከሥልጣን የወረዱበት ዕለት የመስቀል ደመራና በዓል መሆኑን ታሪክ ይዘክራል። (ታሪኩን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!