ከለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የተላለፈ ጥሪ

ሁላችንም እንደተከታተልነው በኢትዮጵያ ተካሄደ በተባለው ”ምርጫ” የመለስ ቡድን የ99.6% አብላጫ ድምጽ በማግኘት ”አሸንፌያለሁ” ማለቱ እንኳንስ ተቃዋሚዎችን የራሱ ደጋፊዎች አፍ ያስያዘና መልስ ያሳጣ ሆኖ ሰንብቷል።ከዚህ አኳያ ባለፈው ነገር ላይ ብቻ እያተኮርን ”ምንድነው ስህተታችን?” እያልን ጊዜ ከማጥፋት ይልቅ ለነጻነታችን እና ለዘመናት በሰቆቃ ለሚኖረው ህዝባችን ምን ልናደርግ እንችላለን የሚለውን በመጠየቅ በቀጣይነት በጋራ ልናደርግ በሚገባን ነገር ላይ ውሳኔ መድረሱ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።ይህንን አብሮ የመሥራትን እና የአንድነትን ነገር ሁሉም በየፊናው እያነሳ የሚወያይበት ዕለታዊ አጀንዳ እንደሆነ ከየአካባቢው ይሰማል። ወቅታዊው ጥያቄም ”ከሁሉ በፊት ነጻነታችን” የሚለው እንደሆነ ይደመጣል።

 

ስለዚህም እኛ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ውስጥ የምንገኝ የኢትዮጵያ ጉዳይ ይገባኛል ይመለከተኛል የሚሉ ጉዳየኞችን በአንድ ቦታ ተሰባስበው ይህንን ሃሳብ ወደተግባር እንዴት እንደሚቀይሩ ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና መንገዱን ለመጥረግ ውሳኔያችን አድርገናል።ይህ ስብሰባ የሚያካትተው የሚከተሉትን ጉዳየኞች ሲሆን እነዚህም፡- የመገናኛ ብዙሐንን (የፓልቶክ ክፍሎችንም ጭምር)፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ የአርነት ንቅናቄዎችን፣ የሲቪክ ድርጅቶችን፣ የሴቶችንና የወጣቶች ማኅበራትን፣ የሃይማኖት ድርጅቶችን እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎችን እና ሌሎች ለአገራችን ቅን የሚያስቡና ለነጻነቷ የሚታገሉ የሚጨምር ይሆናል።

 

በመሆኑም ሁላችንም በአንድ ጣራ ሥር ተገናኝተን እና ተወያይተን ወደ አንድ ውሳኔ እና ግብ የምንደርስበትን ቀን ቅርብ ለማድረግ የእኛ ቁርጥ ውሳኔ ሲሆን ከእንግዲህ ወዲህ እርስበርስ በመጠላለፍ፣ በመሰዳደብ፣ በመጠላላት እና ጣት በመጠቋቆም የምናጠፋው አንዳችም ጊዜ እንደሌለ ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባናል።በአሁኑ ጊዜ የእኛ ጥያቄ በሁሉም ጉዳየኞች መካከል ያለው ልዩነት ወደ ጎን ተደርጎ ሁላችንንም በሚያስተባብርና በአንድነት እንድንሠራ በሚያደርገን ጉዳይ (እንድም እንኳን ቢሆን) ላይ መክረን ለነጻነታችን በሚደረገው ትግል በአንድነት እንድንነሳ ነው። ይህን ለማስተባበርና ዓላማውን ከዳር ለማድረስ እኛ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ውስጥ የምንገኝ ከምንግዜውም በላይ ዝግጁነታችንን ልናሳውቃችሁ እንወዳለን።

 

ይህ ልንጠራ በምናስበው ሁሉን አቀፍ አገራዊ ስብሰባ ለህዝብ ክፍት ያልሆነ ሆኖም ግን ከእያንዳንዱ ጉዳየኛ የሚወከል መሪ ወይም ተወካይ ሲኖር፤ እንዳንዱ ጉዳየኛ ድርጅት አሁን እየተንቀሳቀሰ ያለበትን ፕሮግራም ወይም ድርጅታዊ መርሐግብር በምንም መልኩ ሳይቀይር ከሌሎች ጉዳየኞች ጋር እንዴት አድርጎ በመተባበር እና መልካም ግንኙነት በመመሥረት የሚሠራበትን መንገድ የሚመቻችና የሚያስተባብር ይሆናል። አገርን እና ነጻነትን የማስቀደም ልበቅንነት ካለ ይህንን ማድረግ የሚከብድና ለማከናወን የማይቻል ተግባር እንዳልሆነ ሁላችንም የምንቀበለው ሃቅ ነው።

 

ስለዚህ ይህ ስብሰባ የሚደረግበት ቀን ወደፊት በሚወሰንበት ጊዜ የድርጅታችሁ መሪ ወይም ተወካይ በስብሰባው እንዲገኙ ጥሪችንን እናስተላልፋለን። ይህ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው ከተደረጉ ጉዳየኞች አብዛኛዎቹ ምላሽ ከሰጡን በኋላ የስብሰባውን ዝርዝር ዕቅድ የምናሳውቅ መሆናችንን እንገልጻለን።

 

ለዚህ ጥሪ ምላሽ እስከ ሰኔ 23፣ 2002 ዓ.ም. (June 30th, 2010) ድረስ ባሉት ቀናት በጽሑፍ እንድታሳውቁ በአክብሮት እናሳስባለን።

 

ይህ አገራዊ ጥሪ ለዘመናት በመከራና በሰቆቃ በኖረው ህዝባችን ስም የተደረገ ሲሆን ለዚህም ወገንን የማዳን ጥሪ አፋጣን ምላሽ በመስጠት ህዝባችን ለዘመናት ሲናፍቀው የኖረውን ነጻነት ዕውን በማድረግ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም ሊያስገኝ በሚችል ተግባር ሁላችንም ቀና ውሳኔ ለማድረግ እንድንችል ፈጣሪያችን ይርዳን።

 

ከአክብሮት ሰላምታ ጋር

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ


ለተጨማሪ መረጃ የንቅናቄውን የዕርቅ ግብረኃይል በ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ወይም ዋና ዳይሬክተሩን ለአቶ ኦባንግ ሜቶ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) በመጻፍ ወይም ድረገጻችንን ( www.solidaritymovement.org ) በመጎብኘት ለመረዳት ይችላሉ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ