Ethiopian Prosperity Party

ብልጽግና ፓርቲ

ከትግራይ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የተላለፈ መልእክት

አኩሪው የትግራይ ሕዝብ የጸረ ጭቆና ተጋድሎና መሥዋዕትነት በከሠሩ ኃይሎች ኣይራከስም ፤ የቡዱናዊ ፍላጎት መጠቀሚያም አይሆንም እጅግ የተከበርከውና ከባድ የሕይወት መስዋእትነትን ጨምሮ ውድ ዋጋ በመክፈልና መራራ ትግል በማካሔድ ለራስህ ብቻ ሳይሆን ለወገኖችህ የሚተርፍ ድል ያስመዘገበከው መላው የትግራይ ሕዝብ እንኳን ለ45ኛው የካቲት 11 በዓልህ በሰላም አደረስህ።

ውድ የትግራይ ሕዝብና የተግሉ ሰማእታት ቤተሰብና የትግሉ ሰለባዎች በሙሉ

ከ45 ዓመታት በፊት ይደርስብህ የነበረው የዘመናት ጭቆናና አፈና ይልቁኑም በወታደራዊው መንግሥት ደርግ የተወሰዱትን መጠነ ሰፊ የግድያ፣ የአፈናና የጭቆና እርምጃዎችን በመቃወም በጥቂት ልጆችህ በተጀመረው ሕዝባዊ መነሳሳትና የትጥቅ ትግል በሰፊው ተቀጣጥሎ መላ አገሪቱ ማዳረሱ ከ29 ዓመታት በፊት ተጠናቆ ለአገራችን ኢትዮጵያ የአዲስ ጉዞ ምዕራፍ እንዲከፈት መሰረት እንዲጣል ማድረጉ የማይካድ ሐቅ ነው።

ሆኖም ይህን አኩሪና የሕይወት መስዋእትነትን የጠየቀው ተጋድሎ በአንድ በኩል የትግሉ ዓላማን በማጠልሸት መስዋእትነቱን ለማራከስ በሚዳክሩ የከሰሩ ኃይሎች፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተከፈለውን ሕዝባዊ መስዋእትነት ለራስ ጠባብ ቡዱናዊ ዓላማ ለማዋል በሚፈልጉ ኃይሎች መካከል በሚደረግ የገመድ ጉተታና አንቶ ፈንቶ ጨዋታ ባለቤት የሆነውን የትግራይ ሕዝብ የሚጋፋ መኾኑ እንገነዘባለን።

ትግሉና ትግሉ የጠየቀው መስዋእትነት ተገቢውን ስፍራ ሊያገኝ ሲገባው “እሳት ተኝቶ አመድ ጐበኘው” እንዲሉ የየካቲት 11 በዓል ዝክር ተምሳሌነቱ ሕዝባዊ እምቢተኝነትና የመሥዋዕትነት ተጋድሎ እሳት የተቀጣጠለበት መኾኑን ዘንግተው የትግሉን የሕዝብ ልዕልና አስኳል ጥያቄ ወደ ጐን ትተው አመድ የሆነውን የፖለቲካ ጨዋታ ሊጫወቱበት ሲከጅሉ ማየት ቢያሳዝንም ታሪክ ሰሪውና አስተዋዩ የትግራይ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ሁኔታውን በጥሞና እንደሚከታተለው በጥልቅ እንገነዘባለን።

በወቅቱ በመላው ትግራይ የተቀጣጠለውን የእምቢተኝነትና የጭቆና ተጋድሎ በትጥቅና የፖለቲካ አመራርነት ጫፍ ያደረሰው መሪው ሕወሓትም በብዙ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች አልፎ ኢትዮጵያን እስከ ቅርብ ጊዜ የመራውን ኢሕአዴግ እንዲመሰረትና እንዲደራጅ ጉልህ የአመራርነት ሚናን ተጫውቷል። በዚህም በመላው የትግራይ ሕዝብና የትግሉን ቋያ በተቀላቀሉት ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው መኾኑ ላይ መተማመን ሊኖር ይገባል።

የኢሕአዴግ የመንግሥትነት ዘመን ከነሙሉ ውስንኖቶቹ የዴሞክራሲ፣ የአንፃራዊ ሰላምና ፍትሐዊ የሕዝቦች የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ረጅም ጉዞ ጅማሬን ያረጋገጠ መኾኑን መካድ ዛሬ ከትላንት የተፈጠረ መኾኑን እንደመካድም የሚቆጠር ሲሆን፣ ዛሬን በትላንት ለመኖር የሚደረግ ሙከራም በተመሳሳይ ደረጃ የሕዝብን ተጋድሎ ከንቱ የሚያደረግ መኾኑ ሊሰመርበት ይግባል።

የተሻለች የነገይቱን ኢትዮጵያ የመፍጠር ሕልማችን በታሪክ ቅብብሎሽ የሚፈፀምና ያለንባቸውን ሁኔታዎቻችን በስክነት መረዳት፣ የአሁኑ ግዜ ሁኔታዎቻችን እውነትና አረዳድ በጋራ መግባባት ላይ መመሰረትና የወደፊት መፃኢ ጊዜያችንን በይቅር ባይነትና በመቻቻል በጊዜ ሂደት ለመቅረፅ ዘመኑ ትልቅ የአደራ ሸክም ጭኖብናል። ይህ ሸክም መላ የአገሪቱ ሊሂቃንና ሕዝቦችን የሚመለከት መኾኑ ሊሰመርበት ይገባል።

በአሁኑ ሰዓት አገራችን ከመቸውም ጊዜ በላይ የተጋረጠባትን አጠቃላይ ውስጣዊ አደጋ ከአለማቀፋዊና አከባብያዊ ተለዋዋጭ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ለውጦች ጋር አያይዞ መገምገም የችግሩ ሙሉ ስእልና መፍትሄ ለማግኘት የሚረዳ ሁኖ ሳለ አንዳንድ የፖለቲካ ሀይሎች ባረጃና ባፈጀ ክሱር የሴራ ፖለቲካ ስሌት ሕዝብን ሲያደናግሩን የሕዝብን መከራ ማብዛታቸው የሙሉ ጊዜ ስራ አድርገው ሲሰሩ መመልከት እጅግ አሳዛኝ ወቅታዊ ልምምድ ነው።

በየካቲት 11 በተለኮሰው ሕዝባዊ እንቢተኝነትና የትጥቅ ትግል የትግራይ ሕዝብ መስዋእትነት የከፈለ በተሸለ የነፃነት የሰላምና የዴሞክራሲ ጥማት ሁኖ ሳለ ከብዙ አመታት በኋላም በልዩ የፖለቲካ ውጥረትና ወከባ የትግራይ ሕዝብ አሁንም የተረጋጋ አየር ለመተንፈስ አዳጋች ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። ሕዝቡ ውጥረት ውስጥ እንዲገባ ቀደም ሲል እንደተገለጸው የሕዝቡን ትግል በሚያንቋሽሹ ኃይሎችና የሕዝቡን ትግል የቡዱን ትግል ለማደረግ በሚፈለጉ ኃይሎች ምክንያት እየተከሰተ ያለ መኾኑ እንገነዘባለን። ስለሆነም ጉዳዩን ለማረገብ ሕዝቡ ሰላምና ደህንነት እንዲሰማው፤ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች ሆን ተብለው የሚሰነዘሩ ጠባጫሪ ንግግሮች በአስቸኳይ ሊታረሙ የሚገባና ለወደፊትም ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባ በአፅንኦት ለማሳሳብ እወዳለሁ።

ዛሬ ሃገራችንን ሰንጐ የያዛትን አክራሪ ብሄርተኛነትና የፅንፈኝነት ክፉ በሽታ ምንጭና ምክንያት እንዳለው ልናስተውል ይገባል። የህብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ስርዓቱ ምስረታ የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነት ባህልና ታሪክ ሙሉ እውቅናና ጥበቃ የሚሰጥ ሲሆን የብሔር ማንነትና የሕብረብሔር አንድነት በተመጣጠነ ሚዛን ለሐገረ መንግሥትነት ግንባታ ተግባር ማዋልን የሚጠይቅ፤ ይህንንም በብሔራዊ መግባባትና ቅቡልነት ባለው የህግ ስርዓት ፅኑ መሰረት ላይ የመጣል ታሪካዊ ተልዕኮ መወጣትንም ጭምር ያካትታል።

ሆን ተብለው የሚወረወሩ የጥላቻ ቃላት በወቅቱ ፖለቲካ በሰከሩ የፖለቲካ፣ የሚዲያና የአክቲቪዝም ልሒቃን አቧራ ማሰባሰቢያ ዲስኩሮች ቢሆኑም አሁንና በሒደት ብዙ ዋጋ የሚያስከፍሉንና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይም ጥቁር ነጥብ የሚያስቀምጡ በመሆናቸው ማናቸውም ሰብዓዊ ፍጡራንና ለሰላም ለይቅር ባይነትና ለሀቀኛ ለውጥ የሚታገሉ ኃይሎች አጥብቀው ሊኮንናቸው ይገባል።

በሌላ በኩል የሕዝቡን የነፃነትና የእኩለነት ትግል ለቡደናዊና ግላዊ ዓላማ ለማዋል የሚደረገው ሙከራ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው። የፖለቲካ ክስረት ዋነኛ መገለጫ ሕዝባዊ መሰረትን ማጣትና ተራማጅ የፖለቲካ ሃሳቦችን በማፍለቅ ለመምራት የሚያስችል ብቃት ንጥፈት ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው። የፖለቲካ መሪዎች የፖለቲካ ስልጣንን ከሕዝብ መገልገያ መሳሪያነት ወደ ግልና ቡድናዊ የጥቅም ትስስር መጠቀሚያነት ካሸጋገሩት አመታት የተቆጠሩ ከመኾኑም ባሻገር ይህ ዝቅጠት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ የኪሳራ ዋጋ ሕዝብንና አገርን እያስከፈለ ይገኛል።

የፖለቲካ አመራሩን ብቃትና ንቃት በሚመለከትም ተራማጅ አስተሳሰቦችን ለመፈተሽና ፈጥኖ ለመማር ከሕዝብ ተጨባጭ ፍላጐት ጋርም በማጣጣም በዝግጅት የማዳበር ስራ ባለመስራቱም የከፋ የሐሳብ ድህነትና የፖለቲካ ንቃት ጉድለት የአመራር ደረጃ ክፍተታችን ሆኖብናል።

የሚዲያ ተቋማቶቻችንና ማሕበረሰቡ በስፋት የሚጠቀምባቸው ማኅበራዊ ሚዲያዎቻችንም የሚያወጧቸውና የሚያሰራጭዋቸው አሉታዊ መልዕክቶች ምክንያት በሕዝቦቻችን መካከል ሰላምና ዴሞክራሲ እንዳያብብ አድርጎታል። በአጠቃላይ እንደ ማሕበረሰብ ግንዛቤያችንና አዝማሚያችን አደገኛ አቅጣጫ መያዙን ስንገነዘብ በሚድያ መስክ ሃላፊነታችንን ለመወጣት የሰራነው ስራ ውጤት ያላስገኘ መኾኑን ለመረዳት በመስኩ የሚታየውን አጠቃላይ ምስቅልቅል መመልከት በቂ ነው።

በተለይም አንዳንድ የማሕበረሰብ አንቂዎች የተፅእኖ ፈጣሪነታቸውና የተቀባይነታቸው መሠረት ሕዝብና የሕዝብ ዘላቂ ፍላጐት መኾኑን በመገንዘብ ሃላፊነታቻውን በቅንነት በመወጣት በጐ ተግባር ከመፈፀም ይልቅ ኃላፊነት በጐደላቸው መልእክቶቻቸውን በመሰራጨት በሕዝቦች መከከል መቃቀር በፈጠር ላይ ይገኛሉ። እነዚህ የአክቲቪዝም ኃይላት ለጊዜያዊ ጥቅምና ከንቱ ውዳሴ ሲሉ ሚዛናዊ ያልሆኑ አንዳንድ ግዜም ሐሰተኛ መረጃዎችን በመፈብረክና በማሰራጨት በሃገርና ሕዝብ ላይ ክህደት ሲፈፅሙ ማየት የወቅቱ አይነተኛ አደጋ ሆኖ ተጋርጦብናል፤ ይህም በመስኩ አሳዛኝ ክሽፈት ነው ብለን ልንጠቅሰው እንችላለን።

ይህ ሲባል ሁሉም የሚዲያና የማበረሰብ አንቂዎች በዚህ ይፈረጃሉ ማለት ሳይሆን ለእውነትና ለሕዝብ ጥቅም የቆሙ ሚድያዎችም መኖራቸው ሊዘናጋ አይገባም።

በመጨረሻም የየካቲት 11 ክብረ በዓል አከበበርና ድምቀትም በአንድ በኩል የተከፈለውን መስዋእተነትና ለማራከስ በሚፈልጉ ኃይሎች፤ በሌላ በኩል ድግሞ ሕዝባዊ ትግሉን ለግልና ቡዱናዊ ፍላጎት ለማዋል በሚፈልጉ ኃይሎች ኘሮፖጋንዳ ሳይጠለሽ እንዲከበር የትግራይ ሕዝብ ለዴሞክራሲ መሥዋዕትነት በመክፈል የጋራ ታሪክ ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአጠቃላይ ማሕበረሰቡ ልዩ ጥበቃ እንዲያደርጉለት ጥሪዬን እያስተላለፍኩኝ በአሉን ስናከብር ለነፃነት ለፍትህ ለሰላም ለዴሞክራሲ ሲሉ ውድ ህይወታቸውን ለከፈሉ ሰማዕታት ያለኝን የላቀ ክብር እየገለጽኩ ለመላው የትግራይ ሕዝብ በአሁኑ ሰአት ወቅቱ የሚጠይቀውን የመቻቻል የአንድነት የሰላምና የብልጽግና ጉዞውን ከሌሎች ወንድማማች ሕዝቦች ጋር ከማንኛውም ጊዜ በላይ ተባብሮና ተከባብሮ የሚኖርበትንና የጋራ ብልጽግናና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥበት እንዲሆን እመኛለሁ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!
አብርሃም በላይ በርኸ ዶ/ር
የብልጽግና ፖርቲ አመራር አባልና የትግራይ ቅርንጫፍ አስተባባሪ
የካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ