የኢሕአዴግ ምክር ቤት

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ (ሐሙስ ኅዳር ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 21, 2019)

የጸደቀው በሙሉ ድምፅ ነው

ኢዛ (ሐሙስ ኅዳር ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 21, 2019)፦ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ምክር ቤት የፓርቲውን ውሕደት አጸደቀ። የሕወሓት ተውካዮች ያልተሳተፉበት እንደኾነ የተነገረለት የዛሬው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ፤ የፓርቲውን ውሕደት ያጸደቀው በሙሉ ድምፅ እንደኾነ ተገልጿል።

180 አባላትን የያዘው የኢሕአዴግ ምክር ቤት አራቱ የኢሕአዴግ እኅት ድርጅቶች እያንዳንዳቸው 45 ተወካዮችን በማሳተፍ የሚካሔድ እንደኾነ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከሕወሓት ውጭ ሦስቱ ድርጅቶች ውሕደቱን በሙሉ ድምፅ በማጽደቅ በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ወደ መምከር ገብተዋል።

የዛሬውን የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስበሰባ የፓርቲውን ውሕደት ከማጽደቅ ሌላ የፓርቲው ፕሮግራም ላይ በመምከርም አጽድቆታል።

በዚህ የምክር ቤቱ ስበሰባ የኢሕአዴግ ቁጥጥር ኮሚሽን ስለውሕደቱ አስፈላጊነት ላይ፣ እንዲሁም ሕጋዊነት ላይና ከዚሁ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በዝርዝር ጥናት ያቀረበ መኾኑንም ማምሻው ላይ ስለዛሬው የምክር ቤቱ ስበሰባ ማብራሪያ የሠጡት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ ገልጸዋል።

ኢሕአዴግ አሁን ባለው ሁኔታ አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠልና የሕዝቦችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የኢሕአዴግ ውሕደት አስፈላጊ ስለመኾኑ የቁጥጥር ኮሚቴው ጥናት ማመላከቱንም ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ ስብሰባ በነገው ዕለትም የሚቀጥል ሲሆን፣ ዋነኛ አጀንዳው የብልጽግና ፓርቲ መተዳደሪያ ሕገ ደንብ ረቂቅ ላይ በመምከር ውሣኔ ማሳለፍ እንደኾነ ተጠቁሟል።

በዚህ የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ እንደማይሳተፍ አስታውቆ የስብሰባው ተካፋይ ያልኾነው ሕወሓትን በተመለከተ እስካሁን የተሠጠ ማብራሪያ የለም። ኾኖም ሕወሓት ስብሰባውን ሕገወጥ ሲል ኮንኗል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ