ሕወሓት የብልጽግና ፓርቲን ጉዳይ ያጸናል በተባለው በዛሬው ስብሰባ ላይ አይገኝም
በአዲሱ የብልጽግና ፓርቲ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ በሚጠበቀው የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ሕወሓት አልገኝም አለች
የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በዛሬው ስብሰባ እንደማይገኙ በደብዳቤ ገለጹ
ኢዛ (ሐሙስ ኅዳር ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 21, 2019)፦ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ዛሬ ኅዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚያካሒደው ስብሰባ ላይ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንደማይሳተፉ የሕወሓት ጽሕፈት ቤት ትናንት ማምሻውን አስታወቀ።
አራቱ የኢሕአዴግ እኅት ድርጅቶች (ሕወሓት፣ አዴፓ፣ ኦዴፓና ደኢሕዴግ) እያንዳንዳቸው በ45 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት (በድምሩ 180 አባላት ማለት ነው) በሚወከሉበት የዛሬው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ሕወሓት ልገኝ አልችልም ያለበትን ምክንያት ለኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በላከው አስቸኳይ ደብዳቤ ላይ ጠቅሷል።
ሕወሓት በዛሬው ስበሰባ ላይ አልገኝም ብሎ ከጠቀሳቸው ምክንያቶች አንዱ፣ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የውሕደት አጀንዳውን ተወያይቶ ለመወሰን ሕጋዊና ፖለቲካዊ ሥልጣን የለውም የሚል ነው።
የኢሕአዴግ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ ኅዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የኢሕአዴግ ውሕደት በ27 አብላጫና በስድስት የተቃውሞ ድምፅ ያጸደቀ መኾኑ የሚታወስ ሲሆን፤ መጠሪያ ስሙን ቀይሮ “ብልጽግና ፓርቲ” ተብሎ ለመጠራት መወሰኑ ይታወቃል። በዛሬው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስበሰባም ውሕደቱን የሚያጸና ውሳኔ ይተላለፍበታል ተብሎ የሚጠበቅ እንደኾነ ይታመናል። የሕወሓትን ሙሉ መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ! (ኢዛ)



