ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢሕአዴግ/ ምክር ቤት የተሠጠ መግለጫ

ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢሕአዴግ/ ምክር ቤት የተሠጠ መግለጫ

መግለጫው የአዲሱን ፓርቲ የወደፊት አቅጣጫ ያመለከተ ነው

ኢዛ (ዓሙስ ኅዳር ፲፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 22, 2019)፦ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አዲሱን ውሕድ ፓርቲ ሕገደንብ በማጽደቅ ሲያካሒድ የነበረውን ስብሰባ በማጠናቀቅ አዲሱ ፓርቲ የወደፊት አቅጣጫን ያመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

ምክር ቤቱ በዛሬው የስብሰባ ውሎው አዲሱ ውሕድ ፓርቲ ሕገደንብ ላይ በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ ስለማሳለፉ ያስታወቀ ሲሆን፣ ለሁለት ቀናት የተካሔደው ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎም መግለጫ አውጥቷል። የመግለጫው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው።

ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢሕአዴግ/ ምክር ቤት የተሠጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢሕአዴግ/ ምክር ቤት ከኅዳር 11—12 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በፓርቲ ውሕደት፣ በፕሮግራምና ሕገ ደንብ ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ኢሕአዴግ አገር መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች በርካታ ለውጦችን ያስመዘገበ ድርጅት ነው፡፡ የድህነት ምጣኔን በመቀነስ፣ ተከታታይና ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ፣ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት እና በመሳሰሉት ጉልህ ስኬቶችን ማስመዝቡም ይታወቃል፡፡ በማኅበራዊ ዘርፍም በትምህርትና ጤና አገልግሎት ተደራሽነት መልካም ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡

ይሁን እንጂ በስኬቶቹ ልክ በርካታ ጉድለቶችም የተስተዋሉበት መሆኑን መገምገማችን ይታወሳል፡፡ በተለይም በብሔራዊ ማንነት እና በአገራዊ አንድነት መካከል ሚዛን ጠብቆ በመሄድ፣ ማኅበራዊ ፍትህን በማረጋገጥ፣ እውነተኛ ፌደራላዊ ሥርዓት በመገንባት ረገድ ጉድለቶቹ የበዙ ነበሩ፡፡ እንደዚሁም አርብቶ አደሩን የአገራችንን ክፍል የወከሉ ድርጅቶች “አጋር” በሚል አግላይ አሰራር በአገራቸው እጣ ፈንታ ላይ ቀጥተኛ ውሳኔ የማይሰጡ የሩቅ ተመልካች እንዲሆኑ ተደርገው ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ ለውጡን መምራት የሚችል፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚወከሉበት፣ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች አንዳችም ልዩነት ሳይደረግባቸው እኩል የሚሳተፉበት፣ ዘመኑን የዋጀ የነገ ፓርቲ በመሆን እውነተኛ ሕብረ ብሔራዊ ፌደራላዊት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን ለማድረግ ራሱን ፈትሾ የአደረጃጀት፣ የአሰራርና የፕሮግራም ማሻሻያ ማድረግ የግድ እንደሚለው በየጊዜው ሲካሄዱ በነበሩ ጉባዔዎችና ድርጅታዊ መድረኮች አቅጣጫ ሲቀመጥ ቆይቷል፡፡

በድርጅቱ 11ኛ መደበኛ ጉባዔ የፓርቲ ውሕደት አጀንዳ አንኳር ከነበሩት የውይይት አጀንዳዎች ተጠቃሽ ነበር። በጉባዔውም የውሕደት ሂደቱ ከሚገባው በላይ የተጓተተ መሆኑን በመገምገም ጥናቱ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል። የኢሕአዴግ ምክር ቤትም ጥናቱን እንዲፋጠን በማድረግ ተከታትሎ በማስፈፀም ሃላፊነቱን እንዲወጣ አቅጣጫ ተቀምጦ እንደነበር ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት ጥናቱ በዘርፉ ልምድና የካበተ እውቀት ባላቸው ምሁራን ተካሂዶ ለየብሄራዊ ድርጅቶች ሊቀ መናብርት፣ ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ቀርቦ ውይይትና አስተያየቶች ተሰጥተውበት እየዳበረ እንዲመጣ ተደርጓል። የኢሕአዴግ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽንም ውሕደቱ በሁሉም ብሄራዊ ድርጅቶች አባላትና አመራር ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ እንዲሁም በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የተከናወነ ስለመሆኑ በተናጠል ባደረገው ጥናት ያረጋገጠ ሲሆን ይህም ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በመጨረሻም የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከኅዳር 06 እስከ 08/ 2012 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በጥናቱ ላይ ዝርዝር ውይይት አድርጎ በአብላጫ ድምፅ ካፀደቀው በኋላ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለምክር ቤቱ አስተላልፏል። ምክር ቤቱም በአሰራሩ መሰረት ለሁለት ቀናት ባካሄደው ውይይት የውሕደት ውሳኔ ሐሳቡን፣ የፓርቲውን ፕሮግራምና ሕገ ደንብ በዝርዝር ካየና ካዳበረ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

ምክር ቤቱ ውሕድ ፓርቲው በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት ቀሪ ሂደቶችን በፍጥነት አጠናቆ የቆመላቸውን አላማዎች ወደሚያሳካባቸው ተጨባጭ ስራዎች እንዲሸጋገር የሚያስችሉትን አቅጣጫዎችም አስቀምጧል።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ሲያስተላልፍ እስካሁን የነበረው የኢሕአዴግ አደረጃጀትና ፕሮግራም የአቃፊነት ጉድለት የሚታይበት በመሆኑ የባለቤትነት እና የባይተዋርነት አሰላለፍን እንደፈጠረና ይህም ድርጅቱን እና አገራችንን ወደ ከፋ ክፍፍል ያመራና ፅንፈኝነትን እየወለደ የሄደ መሆኑን በመገንዘብ አቃፊ የፖለቲካ አቅጣጫን መከተል እንዳለበት በማመን ነው፡፡ ለተፈጠረውም አገራዊ ችግር መፍትሔው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ባለቤት የሆኑበት፤ በአገራቸው ጉዳይ ራሳቸው የሚወስኑበት ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ መገንባት እና የቡድንና የግለሰብ መብቶች ተጣጥመው የሚሄዱበት የፖለቲካ አውድ መገንባት መሆኑን ምክር ቤቱ አምኖበታል።

ውሕደቱ በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ አዲስ የአስተሳሰብ ለውጥና እመርታ የሚያመጣ የአንድነት፣ የአብሮነትና የእኩልነት መንፈስን የሚፈጥር ነው። የፓርቲ ውሕደቱ ሁሉንም የሚያካትት፣ ተደራሽና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንነቱ ሳይገደብ የሚሳተፍበትን ሁኔታ በመፍጠር ጠንካራ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ ያስችላል። በተጨማሪም የቡድንና የግል መብትን እንዲሁም ብሄራዊ ማንነትንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጣጣም በህገ መንግስታችን ላይ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ራዕይ እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው።

ውሕድ ፓርቲው የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ግዙፍ አላማ ማእቀፍ ውስጥ የሕዝቦች መሰረታዊ ፍላጎቶችን በዘላቂነት ለማሟላት ጥራትና ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው ኢኮኖሚ በመገንባት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋግጥ፣ የሕዝቦችን ድህነት፣ እርዛትና ኋላቀርነትን ቀርፎ ሁሉን አቀፍ ብልጽግና በአገራችን እውን ሆኖ ለማየት የሚሰራ ፓርቲ ነው። ለዴሞክራሲ ባህል ማበብ አስፈላጊ የሆኑ ባህልና ተቋማት በመገንባት፣ የሕዝቦች ነፃነትና እኩልነት ተረጋግጦ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብረውላቸው፣ ሕብረ ብሄራዊ አንድነቷ የተረጋገጠባት ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በፅኑ መሰረት ላይ ማቆም ፓርቲው ከሚታገልላቸው ቁልፍ አጀንዳዎች አንዱ ነው። በማኅበራዊ ልማት መስክም መልካም አገራዊ እሴቶችና ባህሎችን በማዳበር በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ማፍራት፣ ለኑሮ ምቹ የሆነ አካባቢን መፍጠር፣ የማህበረሰብ ጤና ተጠብቆ፣ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም እንዲዳረስ እና በሕዝቦች መካከል አዎንታዊ ሰላም ተፈጥሮ ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ ይተጋል።

መላው የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፤

ድርጅታችን በታሪኩ ያስመዘገባቸውን መልካም ስኬቶች በማስቀጠልና ስህተቶችና ድክመቶችን በማረም የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገው ትውልድ ፓርቲ ይሆን ዘንድ ትግል ስታደርጉ ቆይታችኋል። እነሆ ትግላችሁ ፍሬ አፍርቶ ሕብረ ብሄራዊ ቅርፅና አካታችነት መገለጫው የሆነ አገራዊ ፓርቲ ለመሆን በቅተናል። በመሆኑም ምክር ቤታችን ለዚህ አዲስ ምዕራፍ በመብቃታችን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ይወዳል።

ውሕደቱ እውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ፌዴራላዊና ሕብረ-ብሔራዊ ሥርዓትን እውን የሚያደርግ፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ማንነታቸው በተገቢው መልኩ እውቅና አግኝቶ ሳይሸራረፍ ተግባራዊ የሚሆንበት፤ በመቻቻልና በመከባበር ላይ የተመሠረተች አገር ለመገንባት የሚያስችል ሥርዓት እውን እንዲሆን እና ሁሉም የሚሳተፍበት የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር የሚያስችል አደረጃጀት ስለሆነ ለስኬቱም መላ አባላትና ደጋፊዎቻችን ከምንጊዜው በላይ ርብርብ እንድታደርጉ ምክር ቤቱ ጥሪ ያቀርብላችኋል።

ለአጋር ድርጅቶች አመራርና አባላት፤

በኢሕአዴግ ጉባዔዎች ጨምሮ በሁሉም የፓርቲ መድረኮች የኢሕአዴግ አባል ፓርቲ እንዳትሆኑ መታገዳችሁ አሳማኝ ምክንያት የሌለው አግላይ አካሄድ መሆኑን በማንሳት ስትታገሉ ቆይታችኋል። ኢሕአዴግም የዚህን ጥያቄ ተገቢነት በማመን ለማስተካከል ከወሰነ አመታት አልፈዋል። ይህን በመፈፀም ረገድ የነበሩ እግር የመጎተት ችግሮች አሁን ተፈትተው ለዚህ ታሪካዊ ቀን በመድረሳችሁ የኢሕአዴግ ምክር ቤት እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ይወዳል። እንኳን ለዚህ የአጋርነት ታሪክ ምእራፍ የተዘጋበትና አካታች አዲስ የትግል ምዕራፍ የተሸጋገራችሁበት መድረክ አበቃችሁ።

ውሕድ ፓርቲው ሁላችንም በእኩል የምንታይበትና የምንሳተፍበት አዲስ ፖለቲካዊ ምኅዳር በመፍጠር አገራችን ያለችበትን ሁኔታ ለመቀየር በሚያደርገው ርብርብ በጋራ ጠንክረን እንድንሰራ ጥሪውን ያቀርብላችኋል።

ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ፤

በአገራችን ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መደማመጥ፣ መቻቻል፣ መከባበርና ሚዛናዊ ትብብርና ፉክክር መገለጫው የሆነ የሰለጠነ ፖለቲካ በአገራችን እውን እንዲሆን፣ የጥላቻና የሴራ ፖለቲካ እንዲቀር መስራት ውሕድ ፓርቲው ከሚታገልላቸው አጀንዳዎች ውስጥ ዋነኛው ነው። በመሆኑም እውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲሰፍን በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰራን በማያግባቡን ጉዳዮች ላይ ደግሞ በሰለጠነ፣ ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ እየተደራደርን ችግሮችን በመፍታት አገራችንን ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የበኩላችሁን ገንቢ ሚና ትጫወቱ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

መላ የአገራችን ሕዝቦች፤

ፓርቲያችን አሁን የደረሰበት ደረጃ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በማንነታቸው ሳይገደቡ፤ ቤተኛና ባይተዋር ሳይሆኑ እኩል የሚሳተፉበት የሁሉም መታገያ መድረክ ለመሆን ከመብቃቱም በላይ ይህንኑ እውን የሚያደርግ ፕሮግራም ይዞላችሁ ቀርቧል።
ውሕድ ፓርቲያችን ሁሉንም ብሔሮች የሚያሳትፍና ከቀደመው አግላይ አካሄድ የምንማርበት፣ የሕዝብን ጥያቄ በተናበበ ሁኔታ የምንመልስበት፣ በፓርቲ ውስጥ መግባባትን በማጠናከር አጠቃላይ በአገራችን ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚያስችለን በመሆኑ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት እውን የሚሆንባት፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በምናደረገው ርብርብ ሁሉ ድጋፋችሁ እንደማይለየው ፓርቲያችን ርግጠኛ ነው። በመሆኑም ብዝሃነታችንን ጠብቀን ለበለፀገች ኢትዮጵያ ግንባታ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንሰራ ጥሪ እናስተላልፍላችኋለን።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት
ኅዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ