The Ethiopian Human Rights Commission (EHRC)

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

(Preliminary Findings Report) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን - ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም.

መግቢያ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ውስጥ በምትገኘው ማይካድራ ከተማ ውስጥ ተፈጸመ የተባለውን የብዙ ሰዎች ግድያ ወንጀልና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማጣራት የሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች የምርመራ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ ፈጣን ምርመራ አካሂዷል።

የምርመራ ቡድኑ ከኅዳር 5 እስከ ኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጎንደር ከተማ ተዘዋውሮ በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎችና ቤተሰቦች፣ ከዓይን ምስክሮች፣ ከመጀመሪያ እርዳታ ሰጪዎች፣ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች እና በጉብኝቱ ጊዜ በስፍራው ከነበሩ የመንግሥት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ምንጮች መረጃዎች ሰብስቧል። እንዲሁም ሆስፒታሎችን ጎብኝቷል፤ በህክምና ላይ የሚገኙ ሰዎችን እና የሚመለከታቸው አካላትን አነጋግሯል።

ይህ የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርት የፈጣን ምርመራውን አብይ ግኝቶች እና አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ እና ዋና ዋና ምክረ ሃሳቦችን በአጭሩ የሚያቀርብ ሲሆን፤ ዝርዝር የምርመራ ሪፖርቱ ተጨማሪ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ እና በማጣራት ወደፊት ይወጣል።

የፈጣን ምርመራ ግኝቶች

ስለ ማይካድራ

ማይካድራ ከተማ በትግራይ ክልል፣ በምዕራባዊ ዞን፣ በሃፍታ ሁመራ ወረዳ የምትገኝ የከተማ አስተዳደር ናት። ከተማዋ ከሁመራ ከተማ በስተደቡብ በ 30 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ፣ እንዲሁም ከምድረ ገነት ከተማ (ወይም አብዱራፊ በመባል የምትታወቅ) ደግሞ በ60 ኪ.ሜ. ርቀት በስተሰሜን አቅጣጫ ላይ ትገኛለች። በከተማዋ የትግራይ፣ የወልቃይትና የአማራ ተወላጆች እንዲሁም የሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆችን ጨምሮ ከ 45 እስከ 50 ሺህ የሚገመት ህዝብ ይኖራል። በወልቃይት የተወለዱ ወይም ለረጅም ጊዜ የኖሩ የአማራ ተወላጆች በአካባቢው በተለምዶ ወልቃይቴዎች በሚል ስያሜ ይጠራሉ።

በማይካድራ ዙሪያ በሚገኙ በተለምዶ “በረሃ” የሚባሉ ሰፋፊ የሰሊጥና የማሽላ እርሻ ቦታዎች ወቅታዊ የጉልበት ሥራ ለመሥራት በአብዛኛው ከአማራ ክልልና የተወሰኑ ከሌሎች አካባቢዎችም የሚመጡ እና የሥራው ወቅት ካለፈ በኋላ ወደ መደበኛ መኖሪያ ቀዬዎቻቸው የሚመለሱ ብዙ ወቅታዊ የጉልበት ሰራተኞች (seasonal workers) በከተማው በአንድ አካባቢ ተሰብስበው በአንድ ቤት ውስጥ እስከ 12 ሰዎች ድረስ በመሆን ይኖራሉ። እነዚህ በአካባቢው በተለምዶ “ሳሉክ” በመባል የሚጠሩ የጉልበት ሰራተኞች እንደተለመደው የዘንድሮውን የመኸር ወቅት ምርት ለመሰብሰብ ከመስከረም ወር ጀምሮ በማይካድራ ከተማ ተሰባስበው ነበር።

የጥቃቱ ቅድመ ዝግጅት እና አጀማመር

ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል መንግሥት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ውጊያ መጀመሩን ተከትሎ ማይካድራ በሚኖሩ እና የትግራይ ተወላጅ ባልሆኑ ሰዎች ላይ፣ በተለይም በአማራና ወልቃይት ተወላጆች ላይ ከባድ ሥጋት እና ተጽዕኖ ተከስቶ ነበር። ለወቅታዊው የጉልበት ሥራ የመጡት ሰራተኞች በከተማው ውስጥ በነፃነት መዘዋወር፣ ወደ ሥራ መሄድ እና ወደ መደበኛው መኖሪያ ቦታቸው መመለስ ጭምር ተከለከሉ።

ጥቃቱ ከመከሰቱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወደ ማይካድራ ለመግባት መቃረቡ ሲሰማ፣ ሁሉም ከማይካድራ የሚያስወጡ ኬላዎች በአካባቢው አስተዳደር የሚሊሽያና ፖሊስ ሃይሎች ተዘጉ። (ሚሊሽያ ማለት መደበኛ የፖሊስ አባል ሳይሆኑ ነገር ግን በክልል መስተዳድሮች የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ወይም እንደየሁኔታው በክልል የፖሊስ ኮሚሽን ስር ተዋቅረው እና የጦር መሳሪያ ታጥቀው፤ የአካባቢያቸውን ጸጥታ የሚያስጠብቁ የክልል መንግሥት የጸጥታ መዋቅር አካል ናቸው። በተለይም መደበኛው የፖሊስ መዋቅር በሌለባቸው የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች ለአካባቢው ጸጥታና ደህንነት ጥበቃ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ሰጪዎች (first security responders) የሚሊሽያ አባሎች ናቸው።)

የማይካድራ ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች በፌዴራሉ ወታደሮች ተሸንፎ እየሸሸ የነበረው የትግራይ ሚሊሺያ እና ልዩ ኃይል ያጠቃናል በሚል ሥጋት ሸሽተው ወደ በረሃው የእርሻ ቦታ ወይም "በረኸት" ወደምትባል የሱዳን አዋሳኝ ከተማ ለመውጣት ሲሞክሩ፤ በከተማው አራት ዋና ዋና መውጫዎች በተቋቋሙ ኬላዎች ላይ በተሰማሩ ሚሊሽያ እና ‹‹ሳምሪ›› የሚባል የትግራይ ተወላጆች መደበኛ ያልሆነ የወጣቶች ቡድን ተመልሰው ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ተገደዱ። በሌላ በኩል የከተማው ፖሊሶች የትግራይ ተወላጅ የሆኑና ያልሆኑ ሰዎችን ለመለየት መታወቂያ ካርድ እየተመለከቱ ማጣራት ጀመሩ።

ጥቃቱ በጀመረበት ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀኑ 5፡00 ሰዓት አንስቶ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች በብዛት በሚኖሩበት እና ልዩ ስሙ ‹‹ግንብ ሰፈር›› በሚባለው መንደር እስከ ወልቃይቴ ቦሌ (ወይም ቀበሌ 1 ቀጠና 1) የሚባለው ሰፈር ድረስ የሚገኙ ቤቶችን ፖሊስ ፍተሻ አካሂዶ ለተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው የሱዳን ‘ሲም ካርድ’ ይጠቀማሉ የተባሉ እስከ 60 የሚደርሱ አማራዎች እና ወልቃይቴዎች ብለው የለዩዋቸውን ሰዎች አሰሩ፤ የሱዳን ሲም ካርድ ነው የተባለውም በፖሊሶቹ ተነጥቆ ተሰባበረ። እንደ ተጎጂዎችና የአይን ምስክሮች ገለጻ አጥቂዎቹ የሱዳኑን ሲም ካርድ የነጠቁትና የሰባበሩት ጥቃቱን ሲፈጽሙ ህበረተሰቡ መልዕክት እንዳያስተላልፍና የእርዳታ ጥሪ እንዳያሰማ በማሰብ ነው። በወቅቱ የኢትዮጵያ ሲም ካርድ አይሰራም ነበር። ጥቃቱ ከመጀመሩ ጥቂት ሰዓታት አስቀድሞ በአጥቂው ቡድን አስተባባሪነት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ በተለይ ሴቶች እና ሕፃናት ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ አደረጉ። ብዙዎች ሴቶችና ሕጻናት እንዲሁም የተወሰኑ ሌሎችም የትግራይ ተወላጆች መውጣት ጀመሩ።

በዚያው እለት (ማለትም ጥቃቱ በተደረገበት ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም.) በግምት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ የከተማው ፖሊሶች፣ ሚሊሺያዎች እና ሳምሪ የሚባለው ኢ-መደበኛ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ቡድን በአንድነት በመሆን ወደ ግንብ ሰፈር ተመልሰው በመምጣት ጥቃቱን ጀመሩ።

የአይን ምስክሮችና የተጎጂ ቤተሰቦች ለኢሰመኮ እንዳስረዱት የአጥቂው ቡድን የመጀመሪያ እርምጃ የነበረው አብይ ጸጋዬ የተባለን የአማራ ብሄር ተወላጅ ከቤቱ ፊት ለፊት በጥይት በመግደልና ቤቱንና አስከሬኑን በእሳት ማቃጠል ነበር። አብይ ጸጋዬ በአንድ ወቅት በወታደርነት እና በሚሊሽያነት ሰርቶ ከአገልግሎት የተሰናበተ የቀድሞ ወታደር ሲሆን፤ በቅርብ ጊዜ በተፈጠረው የጦርነት ሥጋት በአካባቢው መስተዳድር ወደ ውትድርና አገልግሎት እንዲመለስ ተጠይቆ ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጾ ስለነበር፤ በዚህ የተነሳ የጥቃት ኢላማ ሳይሆን እንዳልቀረ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። አጥቂው ቡድን አብይ ጸጋዬን ከመኖሪያ ቤቱ አስገድደው በማውጣት ከቤቱና ቤተሰቡ ፊት ለፊት የቀድሞ ሥራ ባልደረባው በነበረ ሻምበል ካሕሳይ የተባለ የሚሊሽያ አባል በጥይት ተደብድቦ ከተገደለ በኋላ ቤቱን በእሳት አቃጥለው የሟችን አስከሬን ወደ እሳቱ ውስጥ እንደጣሉት የአይን ምስክሮችና የሟች ባለቤት ለኢሰመኮ በዝርዝር አስረድተዋል፤ የኮሚሽኑ የምርመራ ቡድንም በጉብኝቱ ወቅት ገና የቃጠሎው ጠረን ያልለቀቀውን ድርጊቱ የተፈጸመበትን ስፍራ ተመልክቷል።

በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ ሂደት

በአብይ ጸጋዬ ቤት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ወዲያውኑ ሳምሪ የሚባለው የወጣቶች ቡድን በአካባቢው ፖሊስና ሚሊሽያ እየተደገፈ በየጎዳናው እና ከቤት ቤት በመዘዋወር አማሮችና ወልቃይቴዎች ያሏቸውን ሲቪል ሰዎች በከፍተኛ ግፍና ጭካኔ በዱላ በመደብደብ፣ በጩቤ በመውጋት፣ በገጀራና በፈራድ (ወይም ፋስ መጥረቢያ) በመምታት እና በገመድ በማነቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድለዋል፣ ንብረት ዘርፈዋል፣ አውድመዋል።

ጥቃቱን በዋነኛነት ሲፈጽም የነበረው ሳምሪ የሚባለው የወጣቶች ስብስብ በአንድ ቡድን በአማካይ ከ20 - 30 ወጣቶች በመሆንና በየቡድኑ በግምት ከ3 - 4 በሚሆኑ መሳሪያ የታጠቁ ፖሊስና ሚሊሽያዎች እየታጀቡ የጭፍጨፋ ግድያውን ሲፈጽሙ፤ በየመንገዱ መታጠፊያዎች አድፍጠው ይጠባበቁ የነበሩት ሚሊሽያዎች እና ፖሊሶች ከጥቃቱ ለመሸሽ የሚሞክረውን ሰው በጥይት ተኩስ በመመለስ የአጥቂውን ቡድን የጭፍጨፋ ግድያ በቀጥታ ይፈጽሙና ያስፈጽሙ ነበር።

ጥቃቱ በግልጽ ብሔርን መሠረት ያደረገ እና አጥቂው ቡድን የሰዎችን መታወቂያ ጭምር እየተመለከተና አማራ እና ወልቃይቴ እያሉ የለዩዋቸው ወንዶች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፤ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆችም መገዳላቸው ታውቋል። ጥቃቱ ወንዶችን በመለየት መፈጸሙን እና ሴቶች እና ሕፃናት ላይ አለማነጣጠሩን ለማወቅ ቢቻልም፤ ቤተሰባቸውን ከጥቃት ለመከላከል የሞከሩ ሴቶችና እናቶች የአካልና የስነልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ እንዲሁም አጥቂዎቹ ‹‹ነገ ደግሞ የእናንተ ተራ ነው›› እያሉ ይዝቱባቸው እንደነበር ምስክሮች ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በከፍተኛ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት ላይ የሚገኙ፣ ሰውነታቸው በስለት እና በዱላ የተቀጠቀጠ፣ አንገታቸውን በገመድ ታስረው መሬት ለመሬት የተጎተቱ እና እጅ ለእጅ በመታሰር ጥቃት ተፈጽሞባቸው ከሞቱ ሰዎች መካከል ሕይወታቸው የተረፈ ተጎጂዎችን አነጋግሯል። የጥቀቱ ዋነኛ ኢላማ የነበረው በልዩ ስሙ ግንብ ሰፈር የሚባለው አካባቢ ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ወቅታዊ የጉልበት ሰራተኞች በብዛት ተሰባስበው የሚኖሩበት ስለሆነ፤ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከአንድ ቤት ውስጥ ብቻ ከ10 እስከ 15 ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረሳቸው፤ በአጠቃላይ ብዙ ሰው በየመኖሪያ ቤቱ እንዳለ ሊጎዳ ችሏል።

በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፈ፣ የአካል እና የንብረት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ብዛት ገና በትክክል ተጣርቶ ያልተረጋገጠ ቢሆንም፤ ኢሰመኮ ከአደጋው በኋላ ከተቋቋመው የቀብር ኮሚቴ፣ ከምስክሮችና ሌሎች የአካባቢው ምንጮች በሰበሰበው መረጃ መሠረት በአነስተኛው 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥ ይችላል። ከሞቱት ሰዎች ብዛትና አቅም ማነስ የተነሳ ቀብሩ ሶስት ቀን የወሰደ ሲሆን፣ ኢሰመኮ ሰዎች በጅምላ የተቀበሩበትን ስፍራ ጎብኝቷል፤ እንዲሁም በምርመራ ቡድኑ የጉብኝት ወቅት ገና ያልተቀበሩ በመንገድ የወደቁ አስከሬኖችም ተመልክቷል። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት አጥቂዎቹ የተወሰኑ አስከሬኖችን ከከተማው ውጪ ለመደበቅ በየእርሻው ቦታና በየጢሻው ጎትተው በመጣላቸው፤ ገና ተሰብስቦ ያልተቀበረ አስከሬን መኖሩን ከመግለጻቸውም በተጨማሪ የኮሚሽኑ ምርመራ ቡድን ጉብኝት በአደረገበት ወቅትም ከአካባቢው ገና ያልጠፋውን የአስከሬን ጠረን በከፍተኛ ሀዘን ስሜት ለመታዘብ ችሏል።

ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ የቻሉት የቤት ኮርኒስ ውስጥ በመደበቅ፣ በደረሰባቸው ድብደባ እንደሞተ ሰው መስሎ በመተኛት፣ ተደብቀው መሸሽ የቻሉት በተለምዶ በረሃ የሚባለው እርሻ ቦታዎች ሄዶ በመደበቅ እና የተወሰኑት ሰዎች ደግሞ በአቅራቢያው በሚገኘው አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን ውስጥ በመደበቅ እንደሆነ ለኢሰመኮ አስረድተዋል።

ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ገደማ የተጀመረው ጥቃት ሌሊቱን ሙሉ ቀጥሎ፣ በማግስቱ ኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠዋት ጥቃት ፈፃሚዎቹ ከተማውን ለቅቀው ወጡ። የአገር መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ተኩል ገደማ ወደ ከተማው በመግባታቸው ተጎጂዎችን ህክምና እንዲያገኙ የመርዳት ሂደት ተጀመረ። ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ የሚገኙ ሰዎችን ኮሚሽኑ በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ እና በጎንደር ሆስፒታሎች ጎብኝቷል።

በኢሰብአዊ ድርጊት መሐል ሰብአዊ ተግባር

ሳምሪ የተባለው የትግራይ ተወላጅ የወጣቶች ቡድን አሰቃቂ በሆነ የጭፍጨፋ ወንጀል ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያን እና በእርሻ ቦታዎች ሸሽገው በመደበቅ የብዙ ሰዎች ሕይወትን እንዳተረፉ ከጥቃቱ የዳኑ ሰዎች፣የአይን ምስክሮች እና በወቅቱ በነፍስ አድን ተግባር ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች ለኢሰመኮ አስረድተዋል።

ለአብነት ሊጠቀስ የሚገባ አንዲት የትግራይ ተወላጅ የሆነች ሰው 13 ሰዎችን በቤቷ ደብቃ እንዳተረፈችና አጥቂው ቡድን ተመልሶ መጥቶ እንዳያገኛቸው በመሥጋትም በሌሊት ደብቃ ወደ እርሻ ቦታ ወስዳቸው አብራቸው ተደብቃ ቆይተው ከተማው ሲረጋጋ በአንድነት መመለሳቸውን ባለጉዳዮቹ እራሳቸው ለኢሰመኮ አስረድተዋል። እንዲሁም ሌላ የትግራይ ተወላጅ ሴት አጥቂዎቹ በእሳት ሲያቃጥሉት የነበረን የአንድ ተጎጂን ሕይወት ለማትረፍ ስትሞክር በጥቃት አድራሾቹ እጇን በገጀራ ተመትታ ቆስላለች።

ግፍና ጭካኔ የተሞላበት የሲቪል ሰዎች ጭፍጨፋ ወንጀል ስለመፈጸሙ

በማይካድራ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት ተራ ወንጀል ሳይሆን የታቀደ እና በጥንቃቄ ተቀነባብሮ የተፈጸመ እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መሆኑን ጠቅላላ ድርጊቱ አና ውጤቱ ያመለክታል። በተለይም፡

• አጥፊዎቹ ሆነ ብለው፣ አቅደውና ተዘጋጅተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መግደላቸው፣

• ድርጊቱ በስፋት ወይም በስልታዊና በተቀናጀ መንገድ በሲቪል ሰዎች ላይ የብሄር ማንነትን መሠረት አድርጎ ያነጣጠረ ጥቃት አካል ሆኖ መፈጸሙ (the conduct was committed as part of a widespread or systematic attack directed against a civilian population)፣

• አጥፊዎቹ ድርጊታቸው በዚህ በስፋት ወይም በስልታዊና በተቀናጀ መንገድ በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አካል መሆኑን እያወቁ ወይም ድርጊታቸው የዚሁ አካል እንዲሆን አስበው ተሳታፊ የሆኑበት መሆኑ (the perpetrator knew that the conduct was part of or intended the conduct to be part of a widespread or systematic attack directed against a civilian population)

• ድርጊቱ የተፈጸመው በፌደራሉ መንግሥት የአገር መከላከያ ሰራዊትና በትግራይ ክልል መንግሥት የጸጥታ ሃይሎች መካከል ውጊያ እየተደረገ ባለበት የጦርነት አውድ እና በማይካድራ ከተማ የነበረው የአካባቢው አስተዳደርና የጸጥታ መዋቅር እንዲሁም የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል ከፌዴራሉ ወታደሮች ጥቃት እየሸሹ በነበረበት ወቅት የደረሰበትን ሽንፈት ተከትሎ በብሄር ማንነት በለዩዋቸው ሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑ፣

• በጥቃቱ ወቅት በስልጣን ላይ የነበረው የከተማው የጸጥታ መዋቅር ሲቪል ሰዎችን ከአደጋና ጥቃት ከመከላከል ይልቅ፤ በተቃራኒው ሳምሪ ከሚባለው የወንጀሉ ቀጥተኛ ተሳታፊ የወጣቶች ቡድን ጋር እያበረና እየተባበረ ጥቃቱን መፈጸሙና ማስፈጸሙ፣

በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች፤ በማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. እና ሌሊቱን የተፈጸመው ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል ሲሆን ምናልባትም ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) እና የጦር ወንጀል (war crime) ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ነው። ስለሆነም ኮሚሽኑ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ ያቀርባል።

ይህን አይነት ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሆነ ወንጀል ሲፈጸም በድርጊቱ በቀጥታም ሆነ በተዛዋዋሪ መንገድ በየደረጃው ተሳታፊ የሆኑ አጥፊዎች ሁሉ በተገቢው መንገድ ተጣርቶ በሕግ ፊት ተጠያቂነት ሊረጋገጥ ይገባል።

አፋጣኝ እልባት የሚሹ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሥጋቶች እና ምክረ ሃሳብ

• የኢሰመኮ መርማሪ ቡድን በማይካድራ ከተማ እስከቆየበት ጊዜ ድረስ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ወይም ከጥቃቱ ያመለጡ ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ ሰዎች በአቅራቢያው በሚገኙ ሰፋፊ እርሻዎች እና በአቅራቢያ ባሉ ከተሞች ተሸሽገው እንደሚኖሩ ታውቋል። ከመካከላቸውም የበቀል እርምጃ በመሥጋት የሸሹ የትግራይ ተወላጆችም የሚገኙ ሲሆን፤ በመገባደድ ላይ ባለው በዚህ ሕዳር ወር ሁለተኛ ሳምንት መጨረሻ የተወሰኑት ወደ ከተማዋ በመመለስ ላይ መሆናቸው ቢታወቅም አሁንም ተሸሽገው የሚገኙ ሰዎች ደኅንነት አሳሳቢ ነው። ስለሆነም በአንድ በኩል ተፈናቅለው የተሰደዱትን ነዋሪዎች የማስመለስና፤ በሌላ በኩል የደረሰውን ጉዳት በተደራጀ መንገድ መሰነድ (ሕይወታቸው ያለፈውን እና የአካል እና የንብረት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለይቶ መረጃ ማሰባሰብ እና መመዝገብ) ያስፈልጋል።

• የማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች በደረሰው ጥቃት፣ ውድመትና የቤተሰብ መለያየት በከፍተኛ ኃዘን፣ ድንጋጤ እና የስነልቦና ጉዳት ውስጥ ይገኛሉ። ኢሰመኮ የማይካድራ ከተማን በጎበኘበት ወቅት በከተማው እና መንገዶች ላይ አልፎ አልፎ የሚታዩ ገና ያልተቀበሩ አስክሬኖች በማህበረሰብ ጤና እና ስነልቦና ላይ ጭምር የሚያስከትለው ጉዳት አሳሳቢ ነው።

• ጥቃቱ በተለይ በወንዶች ላይ ያነጣጠረ ስለነበርና በአብዛኛው የቤተሰብ የእለት ጉርስ የሚያመጡ አባወራዎች በመገደላቸው ወይም ለከፍተኛ የአካል ጉዳት በመዳረጋቸው ብዙ ቤተሰቦች ለመሠረታዊ ፍላጎት አቅርቦት እጦት ወይም እጥረት ተጋልጠዋል። ሕፃናትን እና የሚያጠቡ እናቶችን ጨምሮ የአካባቢው አንገብጋቢ የምግብ እርዳታ ፍላጎት ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷል። የአካባቢው ፀጥታ በመደፍረሱ የሰብል መሰብሰብ ሥራ ስለተቋረጠ፣ የምግብ እጥረቱን አባብሶታል። ችግሩ በዚሁ ቀጥሎ ሰብሉ በወቅቱ መሰብበሰብ ካልተቻለ በአካባቢው ተጨማሪ ሰብአዊ ቀውስ ሊያጋጥም ይችላል። ስለሆነም አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብና ከተማውንና ነዋሪዎቹን መልሶ ለማቋቋም መንግሥት በአፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶችን ወደ አካባቢው በመጋበዝና አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ሊያግዝ ይገባል።

• በማይካድራ ከተማ የሚገኙ የደኅንነት ሥጋት ያጋጠማቸውን የትግራይ ተወላጆች (ሴቶችንና ሕጻናትን ጨምሮ) በአንድ ስፍራ በማሰባሰብ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ኢሰመኮ ተገንዝቧል። የተወሰኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ካሉት ሰዎች መካከል፤ በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፉ ሰዎችም እንደሚገኙ የገለጹ ቢሆንም ኢሰመኮ ይህንን ማረጋገጥ አልቻለም። በእንደዚህ አይነት የጸጥታ መደፍረስ ወቅት የተሟላ ሰላምና መረጋጋት እስኪሰፍን ድረስ ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ ሊሆኑ ለሚችሉ ነዋሪዎች ልዩ ጥበቃ መደረጉ ተገቢ ቢሆንም፤ በሌላ በኩል ለመገለለልና መድልዎ እንዲሁም ይበልጡኑ ለጥቃት ሊያጋልጥ እንደሚችል የሚያሰጋ ነው። ስለሆነም አፋጣኝ ምርመራ በማካሄድና ምናልባት ጥፋተኞች ካሉ በመለየት፤ የመጠለያ ጣቢያውን መዝጋት ያስፈልጋል።

• የቴሌኮሚኒኬሽን፣ የውሃ እና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቋረጡ ለመሠረታዊ አገልግሎቶች፣ የተጠፋፉ ቤተሰቦችን ለማገናኘት እንዲሁም የህክምና እና መሰል መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ከፍተኛ እንቅፋት በመፍጠሩ አፋጣኝ መፍትሄ ይሻል።

• የመገናኛ ብዙኃን እና የተለያዩ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች እና ተቋማት የማይካድራን አደጋ በተመለከተ የሚያሰራጯቸው መረጃዎች ከጥቃቱ በተረፉ እና ጥቃቱን በተመለከቱ ሰዎች ላይ የሚያስከትለውን ሥነ-ልቦናዊ ጫና ያገናዘበ እና ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!