Birtukan Mideksa

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ (የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ)፣ (ፎቶ - ኢዛ ፋይል)

የተከበራችሁ የፓርቲዎች አመራር አባላት፣ የፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዎች እና በግላችሁ የምትሳተፉ እጩዎች!!!

ዛሬ ለ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ በእጩነት ስትመዘገቡ ወይም እንደ ፓርቲ እጩዎቻችሁን ስታስመዘግቡ ከፊታችን ያለው መንገድ ከፊል ተስፋ ከፊል ሥጋትን አዝሎ እንደሚጠብቃችሁ እንደሚጠብቀን ለሁሉም ግልጽ ነገር ይመስለኛል።

ይሁን እና ሥጋትን ለመቀነስ ብሎም ወደ መልካም ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችለን አቅም እና እድል በየፈርጃችን ይዘን ይህን የጋራ ሙከራችንን በዝለት ሳይሆን በጥንካሬ ልንጀምረው ይገባል እላለሁ።

በቀደሙ ምርጫዎቻችን ባልነበረ ሁኔታ የሒደቱን ዋና ተዋናዮች ማለትም ተፎካካሪዎቹን ግራ ወይም ቀኝ፣ ትንሽ ወይም ትልቅ፣ አገራዊ ወይስ ክልላዊ ሳይል፣ በጥረታቸው ሊያግዝ እና ሳንካቸውን ሊፈታ የተዘጋጀ፣ አቅሙን የጨመረ፣ የገለልተኝነቱን መጠን እና ስፋት ከተፅእኖ ሁሉ የሚከላከል የምርጫ ቦርድ ሒደቱን እያስተዳደረ ይገኛል።

በፍትሐዊነት በተቃኘ በጎ ሐሳብ ሳይኾን በሸፍጥ፣ ሌላውን በማክበር ሳይኾን ማንኛውንም መንገድ ተጠቅሞ በአንፃሩ የቆመውን በማጥፋት ባለመ ሐሳብ፣ የሁሉንም የዜጐችን ሐሳብን የመግለጽ ሰላማዊ እድል ሳይኾን ኋላቀር የኾነ ግጭታዊ መስተጋብርን ታሳቢ ያደረገ አቅጣጫን ያሰበ ተወዳዳሪ ቢኖር፤ ይህን ከምርጫ ፖለቲካ ውጪ የኾነ ሥራውን ለአደባባይ አውጥተው ለሰው ዓይን እና ጆሮ ሊያደርሱ የሚችሉ በቁጥር ትንሽ የማይባሉ የሚዲያ አውታሮች እንደ አገር ያለን መኾኑም ለተሻለ ሽግግር ወደፊት ለመቀጠል የሚያስችል አንድ በጎ እውነታ ነው።

የሲቪል ማኅበራቶቻችንንም አናቂ ይባል ከነበረ የሕግ ማእቀፍ ወጥተው ዜጐችን ስለእውነተኛ ምርጫ ሊያሳውቁ፤ እንዲሁም የምርጫ ሒደታችን ጉበኛ /watchman or watchwomen/ ኾኖ በታዛቢነት ለማገልገል በጣት በሚቆጠሩ ሳይኾን በመቶዎች በሚቆጠሩ አደረጃጀቶቻቸው ላይ መሰናዶአቸውን ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና ይላሉ።

የአውሮፓ እና የአሜሪካ ታዛቢዎችም ይህን ለአገራችን ትልቅ ትርጉም ያለውን ኩነት በእንግድነት ሊታዘቡ ከመንግሥት ግብዣው ደርሷቸው ከእኛው ጋር የሒደቱ አካል ሊኾኑ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ነው።

ብዙ ሌሎች የምርጫ ማሻሻያችን ብዙ ጎኖች መጥቀስ ይቻላል። ኾኖም በዚህ እንደ ብርቱካን ሚደቅሳ በማወጣው የመጀመሪያ የፌስ ቡክ መልእክቴ በዝርዝር ላሰለቻችቸሁ አልወደድኩም።

ለማጠቃለል ዛሬ ፓርቲዎች በአገራችን የተለያየ አካባቢ እጩዎችን በማስመዝገብ፣ በእጩነት በመመዝገብ የምርጫ ዘመቻውን ምዕራፍ ስትከፍቱ ለሒደቱ የሚጠቅም በጎ እሴት ለመጨመር፣ በችግር ፈቺነት በጋራ ለመሥራት፣ የፖለቲካ ጥቃትን አሮጌ ባህል ዕለት ዕለት ለመግደል (Old habits die hard ወይም ከክፉ አመል መላቀቅ በቀላሉ አይኾንም የሚለውን ያስቧል)፤ ለዘመናዊ እና ሥልጡን ውድድር ራሳችንን ለማደስ፣ ከምንም በላይ የዜጐቻችንን ባለሥልጣንነት በማክበር እንዲኾን እያሳሰበኹ፤ በዚህ አስፈላጊ እና ትልቅ ትርጉም ባለው ሥራ የሁላችንንም አብሮነት እና የእያንዳንዳችንን ድርሻ ሳንረሳ በበጎ መንፈስ የምርጫ ውድድሩን እንጀምር ስል ጥሪዬን አቀርባለሁ።

በድጋሚ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያለበትን ሕጋዊ ኃላፊነት እና ግዴታ እንደሚወጣ፣ እየተወጣም እንደሚገኝ አረጋግጥላችኹዋለሁ።

መልካም የምርጫ ዘመን!
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ (የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ