ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሠጠ መግለጫ

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በፓርቲነት የተመዘገበበት ጊዜ አንድ ዓመት ያልሞላው ቢሆንም ሠላማዊ ትግሉን ወደፊት የሚያራምዱ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። የተወሰኑ ውስጣዊ ድክመቶች ቢታዩበትም ቀላል የማይባሉ አወንታዊ ውጤቶችን አስመዝግቧል። አንድነት ከቅንጅት የወረሰውን ዓላማ ከግብ ለማድረስና ራዕዩን እውን ለማድረግ አባላቱና ደጋፊዎቹ በሙሉ ልብ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

 

ሆኖም ዘላቂ ስትራቴጂውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንዳይችል ወቅታዊ መሠናክሎች ከፊቱ መጋረጣቸው አልቀረም። ከመሠናክሎቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ የፓርቲው ሊቀመንበር የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሣ ከሕግ ውጭ መታሰርና በአንዳንድ የፓርቲው አባላት ዘንድ የሚታየው እኔ ያልኩት ካልሆነ በሕገ-ደንብና በዲሞክራሲያዊ መርኅ አልገዛም ባይነት ናቸው።

 

ፓርቲያችን ማንኛውንም አይነት ችግር በዲሞክራሲያዊ ውይይት የመፍታት ባህል እንዳለው ደጋግሞ አሳይቷል። አባላቱ ደንቡን በጠበቀ ሀኔታ በቃልና በጽሑፍ የሚያቀርቡትን ቅሬታና ጥያቄ ተቀብሎ በብዙኀን ተቀባይነት ያገኘውን ሃሳብ የሰው ኃይልና የገንዘብ አቅም የፈቀደውን ያህል ተግብሯል። ይህም ፕሮግራማችንና ደንባችን የሚያሰምርበት አካሄድ ነው። ለአብነት ያክልም የተወሰኑ የፓርቲው ብሔራዊ ም/ቤት አባላት በግንቦት ወር 2001 ዓ.ም. ቅሬታ አለን ብለው በጽሑፍ ያቀረቡዋቸውን ጉዳዮች ሰፊ ጊዜ በመስጠት መርምሮ፤ 5 አባላት ያሉት የውሳኔ ሃሳብ አቅራቢ ኮሚቴ አቋቁሞ በቀረቡት የመፍትሔ ሃሳቦች መሠረት በአብላጫ ድምፅ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

 

ሆኖም በ5/11/2001 ዓ.ም. ከሕገ-ደንባችን ያፈነገጠና ከዲሞክራሲያዊና እና ሠላማዊ አሠራር የወጣ አካሄድ በተወሰኑ አባላት አማካይነት ተፈጽሟል። በተጠቀሰው ቀን የፓርቲያችን ብ/ም/ቤት አንድነት በመለስተኛ ፕሮግራም ከመድረክ ጋር አብሮ ለመሥራት የተስማማበትን ውሳኔ ለአባላቱ ለማብራራት፤ መለስተኛ ፕሮግራሙንም ለማስተዋወቅ፤ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስና ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችን ለማብራራት በርከት ያሉ አባላት በጽ/ቤታችን ግቢ ታድመው ነበር። መዋቅራዊ ዲሞክራሲያዊና ውይይትን የማይቀበሉ በተለይም ከመድረክ ጋር አብሮ መሥራት የሚለው ሃሳብ የሚሠነፍጣቸው የተወሰኑ ግለሰቦች አፍራሽ ጽሑፍ በማዘጋጀትና ከደንብ ውጭ በመበተን በአባላት መካከል ውዥብር የመፍጠር ሙከራ አድርገዋል። አፍራሽ ተልዕኳቸውንና ድርጊታቸውን ቀደም ሲል አሣምረው ያወቁት ብዙሃኑ የፓርቲው አባላት ባሳዩት ትዕግስት ሴራው ከሽፎ የዕለቱ ስብሰባ ከመድረክ ጋር አብሮ መሥራትን በከፍተኛ ደረጃ በመደገፍ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

 

የአፍራሹ ጽሑፍ ባለቤቶች ነን በሚል ስማቸው ከተጠቀሱት ውስጥ በአብዛኛው በተለመደው የሥነ-ምግባር ጉድለታቸውና ደንብ ጣሺነታቸው እንዲሁም አፍራሽ ጽሑፎችን በየጋዜጣው በማውጣታቸው ከአመራር የታገዱ፤ በፓርቲው አቅም ማነስ ምክንያት ከወርሃዊ ውሎ አበል ተከፋይ ሠራተኛነታቸው የተነሱ፤ በተደጋጋሚ የሰብሳቢነት ሚናቸውን ረስተው የብ/ም/ቤት ስብሰባ ረግጦ የመውጣት አመል ያላቸው ናቸው። የእነዚህ ጥቂት ግለሰቦች አፍራሽ ጽሑፍ በአሉባልታና በጥላቻ የተሞላ ከመሆኑም በላይ ፓርቲው የቆመለትን የዲሞክራሲ መርኅና የአብላጫ ድምፅ ውሳኔን የሚጥስ፤ በጥቅሉ ግን የፓርቲውን ብ/ሥ/አስፈፃሚ ኮሚቴና ብሔራዊ ም/ቤቱን በተራና አልባሌ ቋንቋ የሚዘልፍ፤ ባጠቃላይም ራሳቸው ደራሲዎቹን ከፓርቲው የሚነጥል ማመልከቻ ነው።

 

እነዚህ ግለሰቦች በተለያዩ መዋቅሮች ማለትም በቋሚ ኮሚቴዎች፤ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና በብ/ም/ቤት የተሰጣቸውን ምክርና ማስጠንቀቂያ የማይቀበሉ፤ በእነዚህ መዋቅሮች ውስጥ በብዙኀን ድምፅ የተላለፉ ውሳኔዎችን የሚያንኳስሱና የሚረግጡ በመሆናቸው የተወሳሰቡ ሰበቦችን በየጊዜው እየደረደሩ በተለይ ከመድረክ ጋር አብሮ መሥራትን በተመለከተ ፓርቲው እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ካልሄደ ሥራ መሥራት እንዳይችል ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ ናቸው።

 

በተለይም ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው በግንቦት ወር ላቀረቡት የጽሑፍ ቅሬታ 4 የስብሰባ ቀኖችን በመውሰድ ም/ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ መናቅ፤ ንትርክን መቀጠልና የቀድሞን ጽሑፉ ቅጅ የሆነ ጽሑፍ እንደገና መበተን ፓርቲውን ለማዳከም ለአላቸው ዕቅድ ዋነኛው መገለጫ ነው። ምንም እንኳን የማይገናኙ ውንጀላዎችንና ክሶችን ቢደረድሩም የእነዚህ ግለሰቦች ዋነኛ ግብ ፓርቲው ያመነበት ከመድረክ ጋር አብሮ የመሥራትን ስልት ለማሰናከል ነው። ሌሎች በችግር ስም የሚደረደሩ ነገሮች ሁሉ ይህንን ስልት የማሰናከል ዓላማቸውን ለመሸፈንና ህዝብን ለማደናገር ነው።

 

በዚሁ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ጽሑፋቸው እና በሰነባበተ ተግባራቸው የምናውቃቸው ጥቂት አባላት ለውጥ መቀበል የሚያስቸግራቸው፤ ከቆየ የአስተሳሰብ ቀፎ መውጣትና የወቅቱን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ መገንዘብ ያቃታቸው፤ ሰጥቶ መቀበል የሚለው መርኅ የማይዋጥላቸው፤ አንድነት የሌሎች ፓርቲዎች ትብብር አያስፈልገውም የሚል የማንአኸሎኝነት ስሜት ያደረባቸው፤ አሊያም የአንድነት የመድረክ አካል መሆን ድክመትን ለመሸፈን ታስቦ የተደረገ የሚመስላቸው ናቸው። ለፓርቲው ዓላማ መሳካት የሚጥሩ የብሔራዊ ም/ቤት አባላትን “ሎሌዎች” እያሉ ማንቋሸሽና መዝለፍ የአንድነት ፓርቲ አባላት ባሕርይ ጨርሶ ሊሆን አይችልም።

 

ስለዚህ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በፓርቲው ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ደንቡ የሚፈቅድለትን ሕጋዊ እርምጃ ሁሉ በየደረጃው በመውሰድ ላይ ሲሆን፣ የመጨረሻው እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ያለው ብሔራዊ ም/ቤታችንም በቅርቡ ተሰብስቦ የሚሰጠውን ደንባዊ ውሳኔ ደግሞ በቀጣይ የምናሳውቅ መሆኑን እንገልፃለን። ለዲሞክራሲያዊና ደንባዊ አሠራር ሁሉም ተገዢ ይሆናል።

 

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ሐምሌ 9 ቀን 2001 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ