"ማንም ከፓርቲው ህልውና በላይ ሊሆን አይችልም" ዶ/ር ኃይሉ አርአያ (ሪፖርተር ጋዜጣ)
"ከዚህ በኋላ ዝም አንልም" እነፕሮፌሠር መስፍን
በአሰግድ ተፈራና ኃይሌ ሙሉ
(ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ረቡዕ ሐምሌ 7 ቀን 2001 ዓ.ም.)፦ አንድነት ፓርቲ "ሥርዓት ጥሰዋል" ባላቸው የአመራር አባላቱ ላይ እርምጃ መውሰዱንና ይህም እርምጃ ወደ ፊት እንደሚቀጥል፣ ማንም ከፓርቲው ህልውና በላይ ሊሆን እንደማይችል የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለሪፖርተር ገለፁ። እነፕሮፌሠር መስፍን "የአንድነት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሥልጣን መባለግ" በሚል ርዕስ ባወጡት ጽሑፍ የሥራ አስፈፃሚውን የአሰራር ብልሹነት "ከዚህ በኋላ ዝም አንልም" ብለዋል።
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ "የአንድነት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሥልጣን መባለግ" የሚል "የአሉባልታ ሰነድ" ለፓርቲው አባላት አሰራጭተዋል ያላቸውን የቋሚ ኮሚቴ አባላት ከኃላፊነት አግዷል። ፕሮፌሠር መስፍን ወልደ ማርያምን ጨምሮ በሌሎች የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ላይ ስለሚወስደው እርምጃ ለመምከር በመጪው ቅዳሜ ስብሰባ እንደሚካሄድም ተገልጿል።
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት የተለያዩ ኃላፊነት ያላቸው የፓርቲው አባላት ያሰራጩት ጽሑፍ በአሉባልታ ላይ የተመሰረተ፣ ችግር እንኳን ቢኖር በፓርቲው መዋቅር መሰረት ስርዓትን ተከትሎ ለመሚለከተው አካል መቅረብ የነበረበት መሆኑን ተናግረዋል።
ሐምሌ 2 ቀን 2001 ዓ.ም. "የአንድነት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሥልጣን መባለግ" በሚል ርዕስ በፓርቲው የተለያዩ ኃላፊነት ያላቸው አባላት ስም፣ የሥራ ኃላፊነትና ፊርማ የተሰራጨው ጽሑፍ ፓርቲው ለሌሎች ጉዳዮች በተለይም ከመድረክ ጋር መቀላቀልን በተመለከተ ለአባላቱ መግለጫ ለመስጠት ባለፈው እሁድ በጠራው ስብሰባ ላይ የተሰራጨ ነው።
በጽሑፉ መጨረሻ ስማቸውና ፊርማቸው የተቀመጠው የፓርቲው አባላት ፕሮፌሠር መስፍን ወ/ማርያምን ጨምሮ ሃያ አንድ ናቸው። የጽሑፉን መሰራጨት ተከትሎ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰኞ እለት አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል። ዶ/ር ኃይሉ እንዳሉት አራት የቋሚ ኮሚቴ አባላት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተወስኗል።
በትናንትናው ዕለት በተካሄደው ቀጣይ ስብሰባ ጽሑፍና ፊርማቸውን ካኖሩት መካከል የቋሚ ኮሚቴና የብሔራዊ መማክርት አባላት የሆኑትን ሳይጨምር ተመሳሳይ ከኃላፊነት የማንሳት እርምጃ መወሰዱን ዶ/ር ኃይሉ ጨምረው ገልፀዋል።
ዶክተር ኃይሉ እንዳሉት በፕሮፌሠር መስፍንና በሌሎች የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ላይ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ያለው ብሔራዊ ምክር ቤቱ ነው። ሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ የራሱን አካሄድ ያቀርባል። "የአንድነት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሥልጣን መባለግ" በሚል ርዕስ ሐምሌ 2 ቀን 2001 የተፃፈው የእነፕሮፌሠር መስፍን ጽሑፍ የፓርቲው ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከታሰሩ በኋላ ኢንጅነር ግዛቸው በወንበሩ ላይ በተጠባባቂነት ከወጡ ጀምሮ በሥራ አስፈፃሚው በኩል የተደረገው ገንቢ የሥራ እንቅስቃሴ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ይገልፃል። የፓርቲው ገንቢ እንቅስቃሴዎች አብዛኛዎቹ ሥራዎች በወጣቶች የተከናወኑ እንደሆኑም ያስረዳል።
የፓርቲው ዋና ፀሐፊ ሚያዚያ 13 ቀን 2001 ዓ.ም. ለአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የተሰነዘሩ ቃላቶችን እየመነዘረ በአሽሙር የራሱን አስተያየት የሚሰጠው ይሄው መግለጫ ዋና ፀሐፊው በሰጡት መልስ ላይ ተሳልቋል። አንዳንድ ጊዜም ከደርግ ጋር አመሳስሏቸዋል።
"እነዚህ ባዕድ የምልህ አካላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፍነው ደብዳቤ የመጀመሪያውን ድራፍት አይጋ ፎረም ለተባለ ድረ-ገጽ ልከውት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመድረሱ ከሃያ አራት ሰዓታት በፊት ታተመ" ሲሉ ዋና ጸሐፊው ለጋዜጣው የተናገሩትን ይኸው ጽሑፍ "ምነው ራሳቸውን ቢጠይቁ" ሁሉም ነገር በጃቸው፣ ደንብንም የመሻር የፖለቲካ ውሳኔ በጃቸው" ረቂቁን በማስተላለፍ የፖለቲካ ውሳኔ አድርገው ከሆነስ ሲል ይሳለቃል።
በፓርቲው ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች የፖለቲካ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ ኢንጂነር ግዛቸው ለጋዜጣው የሚቀጥለውን ተናግረው ነበር። "የፓርቲ ሕግ በጣም ጥብቅ የሆነ ነው። ይህ የፖለቲካ ሥራ እንደመሆኑ መጠን አንዳንዴ ፖለቲካዊ ውሳኔ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፣ ሌሎችም ይህንን አንደሚጋሩኝ አምናለሁ፣ አለበለዚያ ደንብን የጠበቀ ውሳኔ የምንለው የት ያደርሳል የሚለው አሳሳቢ ሆኖብናል፤ ፖለቲካዊ ውሳኔ አሁን ለድርጅታችን ህልውና ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ።"
እርሳቸው ለአውራምባ ታይምስ ለሰጡት ለዚህ አስተያየት የአሽሙር ምላሽ የሰጠው የእነፕሮፌሠር መስፍን ጽሑፍ "ማሰብ እንዲህ ነው" ደርግም እንደርስዎ ቸግሮት ይሆን በፖለቲካ ውሳኔ ሰዎችን የረሸነው" እባብ የልብን አይቶ ...” ይላል።
በእነፕሮፌሠር መስፍን የተበተነው ይህ ጽሑፍ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ጥቃቅን ጉዳዮችን አንስቶ ከሥራ አስፈፃሚው ጋር ልዩነት እንዳለው ከመግለፁ ውጪ መሰረታዊ የአመለካከት ልዩነት እንዳለ አያመለክትም።
"የአንድነት መጀመሪያ ዓመት ሲከበር ለበአሉ የመጡት እንግዶችና አባላት በኃይለኛ ፀሐይ ሲነፍሩ የዋሉት ድንኳን ለመከራየት ገንዘብ ባለመኖሩ መስሎን ነበር። ነገር ግን በሰኔ 20 የቃሌ ምሽት ላይ የተጋበዙት ተናጋሪ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስለነበሩ ዝግጅቱን በኢምፔሪያል ሆቴል ለማድረግ የሥራ አስፈፃሚው ችሏል።" ተብሎ የተጠቀሰው ጥቃቅን ልዩነቶች ጎልተው የተነሱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።
የእነፕሮፌሠር መስፍን ጽሑፍ በመደምደሚያው ላይ እንዲህ ይላል "በሙሉ ልባቸው በሰላማዊ ትግል ዓላማችን ለማሳካት የሚጥሩ እንጂ ከትግል በፊት እጅ የሚሰጡ መሪዎችን አንሻም፤ በአባሎች መዋጮ እየኖሩ እነዚያኑ አባሎች በአደባባይ የሚወነጅሉ መሪዎችን ልናምናቸው አንችልም። የሀሳብ ልዩነትና ክርክርን እንደጦር የሚፈሩና በሀሳብ የሚከራከሯቸውን እንደ ጠላት የሚመለከቱ መሪዎች ፖለቲካ ምን ማለት እንደሆነ አልገባቸውም በካድሬነታቸው የተጫኑትን ጭፍን አሠራር ገና አላራገፉም . . . ከዚህ በኋላ ዝም አንልም" ይላል።
ፕሮፌሠር መስፍን ቀደም ሲልም ሆነ አሁን ያቀረቧቸው የነበሩት መረጃዎች መሰረት የሌላቸው እንደነበሩ፣ በአሉባታዎች ላይ ሳይገኝ በስብሰባ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ በተላለፈባቸው ጉዳዮች ላይ ዘግይተው የተቃውሞ አስተያየት መሰንዘር የተለመደ ተግባራቸው እንደሆነ ያስረዱት ዶ/ር ኃይሉ አንዳንድ የፓርቲው አባላት "እናከብርዎታለን፣ እንወድዎታለን፣ ነገር ግን እየተሰራ ያለው ሥራ ትክክል አይደለም በሚል በተደጋጋሚ ቢገልጹላቸውም እሳቸው ግን ስህተታቸውን ማረም አልቻሉም" ብለዋል።
"በተደጋጋሚ ጥፋት ከሰሩ ለምን እርምጃ አትወስዱም? እሳቸውን ትፈራላችሁ?" በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ "አንፈራም። የምንፈራበት ምክንያት የለም። ፕሮፌሠር መስፍን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ቢሆኑ ኖሮ ሰኞም ሆነ ዛሬ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰድባቸው ነበር" በማለት ዶ/ር ኃይሉ መልስ ሰጥተዋል። አያይዘውም "ፕሮፌሠር መስፍን የታወቁ፣ ኢትዮጵያን ያገለገሉና ለአገራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ የምናከብራቸው ግለሰብ ናቸው በሚል እስከ አሁን ቆይተናል። ወደፊት ግን ብሔራዊ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለን እናምናለን" ብለዋል።
ዶ/ር ኃይሉ እንዳሉት የልዩነቱ መሰረት የሆነው ከመድረክ ጋር አብሮ ለመሥራት የተጀመረው ግንኙነት ይቀጥላል። አንድነት ፓርቲ ጠንካራ ሆኖ በጥንካሬው ሳይመካ ከሌሎቹም አጋር ፓርቲዎች ጋር አብሮ እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ዶ/ር ኃይሉ ለሚቀጥለው ምርጫም ሆነ ከምርጫው በኋላ ላለው እንቅስቃሴ በሕብረት የመሥራት ባህል ለፓርቲው የበለጠ ኃይልና ጥንካሬ እንደሚሰጠው አመልክተዋል።



