Awassa

በሲዳማ ዞን የምትገኘው የደቡብ ሕዝቦች ክልል ዋና ከተማ አዋሳ። (ፎቶ ኢዛ)

የምርጫ ምዝገባ ቁሳቁሶች በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ባለመድረሳቸው ነው ለዛሬ የተዛወረው

ኢዛ(ሐሙስ ጥቅምት ፳፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 7, 2019)፦ የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ላይ ለሚካሄደው ሕዝበ ውሣኔ፤ የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ ዛሬ ጥቅምት 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በይፋ ይጀመራል።

የዞኑን የክልልነት ጥያቄ በሕዝበ ውሣኔ ለመለየት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ፕሮግራም መሠረት የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባውን ከትናንት ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ለመጀመር ቢሆንም፤ ጥቅምት 25 ቀን ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የመራጮች ምዝገባ በአንድ ቀን ተራዝሞ ዛሬ እንዲጀመር ወስኗል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የምዝገባውን ቀን በአንድ ቀን ያራዘመው የምርጫ ምዝገባ ቁሳቁሶች በተወሰኑ ርቀት ባላቸው የምርጫ ጣቢያዎች አለመድረሱን በመረዳት ነው።

ምዝገባው በሁሉም ቦታዎች በእኩል እንዲጀመር በማሰብ ምዝገባው ከዛሬ ጀምሮ እንዲካሄድ ሊወስን መቻሉንም ቦርዱ ገልጿል።

ይህንን ሕዝበ ውሣኔ ለማካሄድ ቦርዱ 6000 የሚሆኑ ምርጫ አስፈፃሚዎችን መልምሏል።

በዚህ ሕዝበ ውሣኔ ላይ የቀረቡት ሁለት ምርጫዎች መኾኑ ታውቋል። አንደኛው “ሲዳማ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ እንዲቆይ እፈልጋለሁ” ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ “ሲዳማ ራሱን ችሎ በክልልነት እንዲደራጅ እፈልጋለሁ” የሚል ነው። ድምፅ የሚሰጠው በነዚህ ምርጫዎች ላይ ይሆናል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ