ጉምቱው የማስታወቂያ ባለሙያና የቀድሞው የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዝዳንት አረፉ

አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ
አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ በሕክምና ሲረዱ ነበር
ኢዛ (እሁድ የካቲት ፳፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 1, 2020)፦ በኢትዮጵያ የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደ ፋና ወጊ የሚቆጠሩት አቶ ውብሸት ወርቃለማው ትናንት ምሽት ከዚህ ዓለም ተለይተዋል። አቶ ውብሸት ባደረባቸው ሕመም በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ነበር።
የአንበሳ ማስታወቂያ ድርጅት በመሥራችና ባለቤት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ማስታወቂያን በገበያ ውስጥ በመጀመር እስከዘመናዊ የማስታዋወቅ ደረጃ ከ60 ዓመታት በላይ አገልግለዋል።
አቶ ውብሸት በማስታወቂያ ሥራቸው እንደብሔራዊ ሎተሪ ያሉ ድርጅቶች ውስጥ ሠርተዋል። የፊሊፕስ ኩባንያን በማስተዋወቅም የሚታወቁ ሲሆን፣ በዚህ የሥራ ዘርፍ ቀዳሚውን ሥፍራ የያዙም ናቸው።
ከዚህ አንቱ ከተባሉበት የማስታወቂያ ሙያቸው ባሻገር፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ70 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላቸው የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶችን በፕሬዝዳንትነት የመሩ ናቸው። (ኢዛ)