አሊባባ በአዲስ አበባ

ጃክ ማ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ዛሬ የአንድነት ፓርክን ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በመኾን ጎብኝተዋል
አሊባባ ግሩፕ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ዓለም አቀፍ የንግድ መገናኛ ማዕከል ለመገንባት የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር ተፈራረመ
ኢዛ (ሰኞ ኅዳር ፲፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 25, 2019)፦ በኤሌክትሮኒክስ ግብይት በዓለማችን ቀዳሚ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የኾነው አሊባባ ኩባንያ ሊቀመንበር ጃክ ማ እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መጀመሪያ በስዊዘርላንድ፣ ከዚያም በኋላ ሚያዝያ 2011 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ በቻይና ተገናኝተው በጋራ ሊሠሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረው ነበር። በቻይና ሃንግዙ የሚገኝውን የአሊባባ ዋና መሥሪያ ቤት ጠቅላይ ሚንስትሩና የልዑካን ቡድናቸው በጃክ ማ አስጎብኝነት ተመልክተዋል። ስለኩባንያው አውግተዋል። በውይይታቸው መደምደሚያ ላይ አዲስ አበባ ለመገናኘት ቀን ቆርጠው ይለያያሉ።
እነኾ የቀጠሮ ቀን ደረሰና አሊባባ ኅዳር 14 ቀን ምሽት ላይ አዲስ አበባ ገብተዋል። እኒህን እንግዳ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከአዲስ አበባ ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትሩ ኢንጂንየር ጌታሁን መኩሪያ ጋር በመኾን ተቀብለዋቸዋል።
አሊባባ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ብቻ አልመጡም። እርሳቸው የሚመሩት ግዙፉ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ አሻራውን እንዲያሳርፍ ቀድሞ በነበር ምክክር መሠረት በኢትዮጵያ ሊሠሩ ያሰቡትን ለመተግበር የሚያስችል ስምምነት ለመፈራረም ጭምር ነው። ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማስረጽ ያለመ ስምምነት እንደኾነም ታውቋል።
ይህ ዛሬ ኅዳር 15 ቀን የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ፤ አሊባባ ግሩፕ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ዓለም አቀፍ የንግድ መገናኛ ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል ነው። ማዕከሉ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት ብሎም አጠቃላይ የዲጂታልና የዲጂታል አቅም ግንባታ ለመሥጠት የሚያስችል እንደኾነ ተገልጿል።
በስምምነቱ መሠረት ማዕከሉ ሥር ሲጀምር፣ ኢትዮጵያ ከሩዋንዳ ቀጥላ ሁለተኛዋ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የንግድ ሥርዓት የሚኖራት አፍሪካዊ አገር እንድትኾን ያስችላታል።
ወደተለያዩ አገሮች የሚደረገውን የወጪ ንግድ በዚህ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ተፈጻሚ ለማድረግ ጭምር እገዛ የሚያደርገው ይህ የማዕከሉ ግንባታ፤ ለበርካቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ይታመናል።
ማዕከሉን ለመገንባት የሚያስችለው ስምምነት ላይ የተገኙ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት በአፍሪካ በኢኮኖሚ አቅማቸው በቀዳሚነት ሊጠቀሱ ከሚችሉ አምስት አገሮች አንድዋ ለመኾን የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት አስተዋጽኦ የሚያበረክት እንደኾነ አመልክተዋል።
በዚህ ማዕከል ግንባታ ለኢትዮጵያውያን የሥራ እድል የሚፈጥር መኾኑን የጠቆሙት ጃክ ማ ደግሞ፤ እንዲህ ያለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር በማድረጋቸው ደስተኛ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
አሊባባ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከ40 ሚሊዩን በላይ ለሚኾኑ ሕዝቦች የሥራ እድል የፈጠረ መኾኑን የሚጠቀስ እንደኾነ ይታወቃል።
በአሊባባ ጉብኝትና ዛሬ ስለተደረሰው ስምምነት አስመልክቶ የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክስ የዓለም መገበያያ ማዕከሉ በብዙ ዘርፎች በመላው ዓለም በፍጥነት እያደገ በመጣው ዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካይነት የአገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያበለጽግ ነው። ከዚህም በላይ የኢትዮጵያና የመላው አፍሪካ ነጋዴዎች የተሳለጠ ዓለም አቀፍ ንግድ እንዲያካሒዱ እንደሚረዳ ይኸው የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት መረጃ ጠቅሶ፤ “ይህ ኤሌክትሮኒክስ የዓለም መገበያያ ማዕከል በኢትዮጵያ ንግድና ዲጂታል ኢኮኖሚን የሚያበረታታ የላቀ ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት፣ አገልግሎት አሠጣጥና የቁጥጥር ማዕከል ይኖረዋልም” ይላል።
ጃክ ማ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ዛሬ የአንድነት ፓርክን ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በመኾን ጎብኝተዋል።
ጃክ ማ ማነው?
የቀድሞ መጠሪያ ስሙ “ማ ዮን” የተወለደው በቻይና ሃንግዙን ከተማ ጳጉሜን 5 ቀን 1956 ዓ.ም (ሴፕቴምበር 10 ቀን 1964 እ.ኤ.አ.) ሲሆን፣ ከአሊባባ ግሩፕ መሥራቾች አንዱና የበርካታ ታዋቂ ድረገጾች ባለቤትም ነው። ከቀዳሚ ተጠቃሾቹ ውስጥ Alibaba.com እና Taobao.com ይገኙበታል። አንዲት ወጣት “ማ ዮን” የሚለውን ስሙን ለመያዝ ስለከበዳት “ጃክ” ብላ ከጠራችው በኋላ “ጃክ ማ” የሚለውን ስም ይዞ ዘለቀ።
ጃክ ማ ከሥራና ከትምህርት ጋር ሳይሸሽግ ከሚናገራቸው የሕይወት ታሪኩ ውስጥ፤ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ለመማር 10 ግዜ አመልክቶ አንዴም ሳይቀበለው ቀርቷል፤ 40 ግዜ ሥራ አመልክቶ ቀጣሪዎቹ አልተቀበሉትም፤ KFC (ኬንታኪ ፍራይድ ቺክን) የተባለው የፈጣን ምግቦች ሬስቶራንት ቻይና ሃንግዙ ከተማ ቅርንጫፍ ሲከፍት 24 ሰዎችን ለመቅጠር መዝግቦ 23ቱን ሲቀጥር ጃክን ግን ሳይቀጥረው ቀርቷል።
ሕጻን ልጅ እያለ፣ በአስራ ቤቶቹ ውስጥ፣ ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረው ለአገር ጎብኝዎች አስጎብኝ በመኾን ነበር ሥራ የጀመረው። ሃንግዙን የመምህራን ኮሌጅ ለመግባት ሁለት ጊዜ ወድቆ ሦስተኛው ላይ 1984 እ.ኤ.አ. ተመዝግቧል። በእንግሊዝኛ የባችለር ዲግሪውን ከዚሁ ኮሌጅ በ1988 አግኝቷል። ከ1988 እስከ 1993 ዓ.ም. በሃንግዙ የኤሌክትሮኒክስና ኢንጂንየሪንግ ተቋም (አሁን ሃንግዙ ዲያንዚ ዩኒቨርሲቲ) በእንግሊዝኛ መምህርነት ሠርቷል። እ.ኤ.አ. በ1994 የመጀመሪያውን የግሉን ድርጅት “ሐይቡ አስተርጓሚ ኤጀንሲ” የተሰኘውን ከፍቶ በትርጉም ሥራ ላይ ተሰማራ።
በ1995 ዓ.ም. ወደ አሜሪካ በሔደበት ጊዜ፣ ከኢንተርኔት ጋር ሲተዋወቅ የቻይና ድረገጾች ያላቸውን ድክመትና ምን ያህል ኢንተርኔት በኢኮኖሚ ላይ ያለውን ከፍተኛ ተጽእኖ አስተዋለ። ወደቻይና እንደተመለሰም በቻይና የመጀመሪያውን የኢንተርኔት ካምፓኒ ቻይና ፔጅስን መሥርቶ ለቻይና ነጋዴዎች ድረገጾችን መሥራት ጀመረ። ከዚያም ለቅቆ እ.ኤ.አ. ከ1998 እስከ 1999 ለንግድና ኢኮኖሚ ሚንስቴር መሥሪያ ቤት ሲሠራ ከቆየ በኋላ፤ አብረውት ይሠሩ የነበሩትን የሥራ ባልደረቦቹን በማሳመን ሃንግዙ ገብተው አሊባባ ግሩፕን አቋቋሙ። በወቅቱ የአሊባባ ዓላማ የቻይና ጥቃቅንና አነስተኛ ቸርቻሪዎችንና ነጋዴዎችን የንግድ ልውውጥ ስምምነት በኢንተርኔት እንዲፈጥሙ ማድረግ ነበር። የመስከረም 2012 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 2019) የሩብ ዓመቱ ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ የአሊባባ ሀብት 162.231 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። (ኢዛ)