PM Dr. Abiy Ahmed (left), Getachew Reda (right)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መልእክት ሲያስተላለፉ (በግራ)፣ አቶ ጌታቸው ረዳ በዛሬው ቃለምልልሳቸው ላይ

በፓርቲው ምሥረታ የሚከሱን በአማራጭ ሐሳብ ይሞግቱን ብለዋል

ኢዛ (ሐሙስ ኅዳር ፲፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 28, 2019)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በብልጽግና ፓርቲ ላይ የሚሰሙ ክሶችን ከማቅረብ፤ አማራጭ ሐሳብ ይዞ በመምጣት መሞገት የሚሻል መኾኑንና የአዲሱ ፓርቲ ምሥረታ ሒደት ሕጋዊ ስለመኾኑ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው እንደገለጹት፤ አንዳንድ ኃይሎች እንደሚሉት አኀዳዊ ሥርዓት ለመፍጠር ነው የሚለውንም ክስ በተመለከተ፤ ትክክል ያለኾነ ምልከታ ነው ብለዋል። አንዳንድ ኃይሎች አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ አኀዳዊ ሥርዓትን የሚያመጥ፤ የፌዴራል ሥርዓትን የሚያጠፋ ነው የሚል አሉባልታ ሲነገሩ እንደሚደመጡ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ትክክል እንዳልኾነም ጠቁመዋል።

ይህንንም በተመለከተ፤ “ብልጽግና ፓርቲ በግልጽ እንዳስቀመጠው ሕብረ-ብሔራዊነት ፌዴራላዊት ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን የሚያጠናክርና የሚገነባ እንጂ፤ የማያፈርስ መኾኑን በንግግር ብቻ ሳይሆን በፓርቲው ፕሮግራም ውስጥ የተካተተ ነው” በማለት ገልጸዋል።

ሌሎች ፓርቲዎች ብልጽግና ፓርቲን በመክሰስ ሳይኾን አማራጭ በማምጣት እንዲሞግቱትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ሐሳብ ይዘው እንዲቀርቡ ጥሪዬን ላቀርብላቸው እፈልጋለሁም ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ መሠረቱ በኦሮሚያ የቄሮ ትግል፣ በአማራ የፋኖ ትግል፣ በደቡብ የዘርማና ሌሎች የወጣት አደረጃጀቶ በጋራ ያደረጉትን ትግል ከተረት ተረት ወደ እውነተኛ ብልጽግናና ሰላም ዴሞክራሲና አንድነት ለማሸጋገር የተደረገ ሒደት መኾኑ ታምኖ፤ ቄሮዎችና ፋኖዎችን እንኳን ደስ ያላችሁም የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

የፓርቲው የምሥረታ ሒደት ሕግን ተከትሎ የተከናወነ ስለመኾኑም በማስታወስ፤ “የብልጽግና ፓርቲን የመመሥረት ሒደት በምሁራና ሲጠና ቆይቶ፤ በየደረጃው ሁሉም አመራሮች ሲወያዩበት እንደቆዩ ያስታወሱት ዶ/ር ዐቢይ፤ በትናንትናው ዕለት የኦዴፓና አዴፓ አስቸኳይ ጉባዔ ውሕደቱን በሙሉ ድምፅ አጽድቀዋል” ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም ለአስቸኳይ ጉባዔ የተቀመጠው ደኢሕዴን በተመሳሳይ ያጸድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል። ይህም አካሔድ የብልጽግና ፓርቲ ምሥረታው ሁሉንም ሕጋዊ መሠረት የያዘና ሕግን ተከትሎ የተፈጸመ መኾኑን ስገልጽላችሁ በታላቅ ደስታ ነው በማለት ተናግረዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራሙን ያሻሻለ፣ ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የሚወስደውን እቅድ የነደፈ፤ ይህንንም ከመላው ሕዝብና አባላት ጋር የሚወያይበትና የሚያዳብረው ስለመኾኑም በዚሁ በዛሬው መልእክታቸው ገልጸዋል።

አያይዘውም፤ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለመውሰድ ሕልማችን እውን የሚያደርግበት ትክክለኛ መንገድ የተጀመረ ስለመኾኑ የጠቀሱበትም ነበር።

ተጨማሪ ዜና፤

የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልእክት ተከትሎ ከትግራይ ማስ ሚዲያ ኤጀንሲ ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ “ብልጽግናም ፓርቲ ተባለ፣ ኢሕአዴግም ተባለ፣ እገሌም ተባለ፤ አሁን በሚደረገው ውድድር (መጭውን አገራዊ ምርጫ ማለታቸው ነው) እኔ ብቻ ነኝ የማሸንፈው ብሎ ካላለ በሥተቀር ባይ ኹክ ኦር ክሩክ በዚህም በዚያም ብዬ እኔ ነኝ የማሸንፈው ብሎ ካላመነ በሥተቀር፤ ሁልሽም ድርጅት እዚህ ላይ ካልተጠረነፍሽ ብሎ የሚልበት ምክንያት ምንድን ነው?” ብለዋል።

ይህንን አስተያየታቸውን በዚሁ ቃለምልልስ ላይ የሠጡት አቶ ጌታቸው፤ የዛሬውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልእክት እንዳልሰሙት ገልጸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ