ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል ይደረጋል
ኖቤል ሎሬት ዐቢይ አሕመድ
ለአዲስ አበባና ለአካባቢዋ ነዋሪዎች ጥሪ ተደርጓል
ኢዛ (ረቡዕ ታኅሣሥ ፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 11, 2019)፦ በትናንትናው ዕለት የዓለም የሰላም ኖቬል ሽልማትን የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ነገ ታኅሣሥ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ተገለጸ። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጋራ የሚደገው የአቀባበል ዝግጅት ነገ ማለዳ ላይ የሚከናወን ነው።
በአቀባበሉ ዙሪያ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ እንደገለፁት “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀግና አቀባበል ይደረግላቸዋል” ብለዋል። የአቀባበል ሥርዓቱ ነገ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ብሔራዊ ቤተመንግሥት ድረስ የሚታጀብ ይኾናል ተብሏል።
ይህንን የአቀባበል ሥነሥርዓት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አስተዳደርና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚያዘጋጁት መኾኑ ታውቋል። በዚህ የአቀባበል ሥነሥርዓት ላይ ለከተማዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጥሪ የተላለፈ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ለአቀባበሉ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።
ለአቀባበሉ የሚኾን ቲሸርቶችንም የተለያዩ ግለሰቦች በማሳተም በነፃ ለማደል እየተዘጋጁ መኾኑም ታውቋል። በዚሁ የአቀባበል ፕሮግራም ላይ መግለጫ የሠጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክተሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቬል ሽልማት ዓለም ትኩረቱን ኢትዮጵያ ላይ እንዲያደርግ አስችሏል። የአቀባበል ሥነሥርዓቱም ስለሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት መልእክት የሚተላለፍበት ነው ብለዋል። (ኢዛ)



