ኢንጂንየሯ ከሜቴክ ጋር በተያያዘ ተከሰሱ
ኢንጂንየር አዜብ አስናቀ የቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ
የክሱ ጭብጥ ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘ ነው
ኢዛ (ዓርብ ታኅሣሥ ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 27, 2019)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሲመሩ የቆዩት ኢንጂንየር አዜብ አስናቀ ከሜቴክ ጋር በተያያዘ ክስ ተመሠረተባቸው። የክሱ ጭብጥ ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘ መኾኑ ታውቋል።
ኢንጂንየር አዜብ ከቀድሞ የብረታብረትና ኢንጂንየሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከነበሩት ኮሎኔል ሙሉ ወልደ ገብርኤልን ጨምሮ 50 ሰዎች በሚገኙበት የክስ መዝገብ ክስ እንደተመሠረተባቸው ታውቋል።
የክሱ ጭብጥም ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ተካሒዷል በተባለ የደን ምንጣሮ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል። ከኢንጂነር አዜብ ክስ ጋር በተያያዘ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተሠጠው ማብራሪያ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ የሚያርፍበት 123,189 ሔክታር ስፋት የሪዘርቬየር ክሉሪንግና ባዮማስ ዝግጅት ሥራ ደኖችን የመመንጠር፣ የማጽዳትና ከአካባቢው (ከግድቡ አርቆ) ወደተዘጋጀለት ቦታ የማጓጓዝ ሥራን ለመሥራት ከኢፌዴሪ ብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር በብር 5,158,611,599.03 (አምስት ቢሊዮን አንድ መቶ ሃምሳ ስምንት
ሚሊዮን ስድስት መቶ አሥራ አንድ ሺሕ አምስት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ብር ከዜሮ ሦስት ሣንቲም) በተዋዋሉት ውል መሠረት ሥራው መጠናቀቅ በሚገባው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻሉ፤ ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግሥት ገንዘብ እንዲባክንና ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመኾኑ፤ ሁሉም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ተከሳሾች በፈጸሙት በሥልጣን አላግባብ መገልገል፣ አንዳንዶቹ የማይገባ ጥቅም ለራሳቸው ለማገኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብና ኃላፊነታቸውን በመጠቀም ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
ኢንጂንየር አዜብ አስናቀ በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል። (ኢዛ)



