Takele Uma Banti the acting deputy mayor of Addis Ababa

ኢንጂነር ታከለ ኡማ

እርምጃው በአዲስ አበባ 116 በሚኾኑ ወረዳዎች ላይ የሚወሰድ መኾኑ ታውቋል

ኢዛ (ሐሙስ ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 2, 2020)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ ናቸው ያላቸውን ግንባታዎች ቀን ቆርጦ ለማፍረስ መነሳቱን ማሳወቁ አነጋጋሪ ኾኗል።

የከተማዋ ከንቲባ ሰሞኑን ይፋ እንዳደረጉትና ትናንት ታኅሣሥ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በጉዳዩ ላይ በሠጡት ማብራሪያ፤ አስተዳደሩ በ116 የከተማው ወረዳዎች ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ ናቸው ያላቸውን ግንባታዎች ከጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ማፍረስ የሚጀምር መኾኑን አስታውቀዋል።

በትናንትናው ዕለት ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት በቅርብ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው ሕገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተደረገ ነው ብለዋል። እርምጃው በአዲስ አበባ 116 በሚኾኑ ወረዳዎች ላይ የሚወሰድ እንደሚኾን የተገለጸ ሲሆን፣ እርምጃውን ለመውሰድ በሚደረገው እንቅስቃሴ የአዲስ አበባ ፖሊስ የፌደራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ይሳተፋሉ ተብሏል።

እንደ ከተማዋ አስተዳደር መረጃ በየወረዳው በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶችን የመለየት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ይጠቅሳል።

እርምጃው ከሕገወጥ ግንባታው ጋር የተያያዙ የሥራ ኃላፊዎችንም የሚመለከት እንደሚኾንና በሕገወጥ መንገድ የተገኘ መረጃ ያላቸውን ግለሰቦችንም የማጣራት ሥራ ይሠራል ተብሏል። ይህ እርምጃ ግን ብዙዎችን ያፈናቅላል የሚል አስተያየት እየተሠጠበት ሲሆን፣ ሕገወጦችን በማስነሳቱ ሒደት ሊፈጠር የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ተገቢ ነው የሚሉም አሉ። አንዳንድ ወገኖች እርምጃው የዘገየ ነው ሲሉ ቀድሞም መቆጣጠር ባለመቻሉ የተፈጠረ በመኾኑ፤ አስተዳደሩም ተጠያቂ ነው በማለት ይተቻሉ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ