ጥምቀት በጎንደር

ጥምቀት በጎንደር ሲከበር

“ለጥቃቱ ያሰማራቸውን አካል በቅርቡ ይፋ አደርጋለሁ” ብሔራዊ የደኅንነት አገልግሎት

ኢዛ (ዓርብ ጥር ፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 17, 2020)፦ የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ በመኾን በዩኔስኮ እንዲመዘገብ እውቅና የተሠጠው የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ዋዜማ ላይ በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው አንዱ በኾነው በጎንደር በተኩስ የተቀናጀ ከፍተኛ ፍንዳታ ለመፈጸም በዝግጅት ላይ የነበሩ የጥፋት ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ።

ዛሬ ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት ላይ የብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎት እንዳስታወቀው፤ በጎንደር የጥምቀት በዓል ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ ለማድረስ በዝግጅት ላይ የነበሩ ሁለት የጥፋት ቡድን አባላት ተይዘዋል።

እነዚህ ጥፋቱን ለማድረስ በዝግጅት ላይ ነበሩ የተባሉት ሁለት አባላት የተያዙት ከአራት ኤፍዋን ቦንብና ከሁለት መቶ ጥይቶች ጋር መኾኑም ተገልጿል።

ከብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎት የወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ጥፋቱን ሊያደርሱ የነበሩት ግለሰቦቹ በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤትና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚሠጣቸው ለጥቃቱ ካሠማራቸው አካል ቃል እንደተገባላቸው ጠቅሷል። አያይዞም ለጥቃቱ ያሰማራቸውን አካል በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ሳይገልጽ አላለፈም።

ይሄንን መረጃ አስመልክቶ የተለያዩ ወገኖች አስተያየት እየሠጡ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ለብሔራዊ ድኅንነት ተቋሙ ጥቃቱ ከመከሰቱ በፊት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስመክልቶ ምስጋና ያቀረቡ ሲኖሩ፤ በተቃራኒው ጉዳዩን በጥርጣሬ የተመለከቱም አልጠፉም። የተለመደው የመንግሥት ድራማ ነው ሲሉ የተቹም አሉ። በምሥራቅ ጎጃም ሞጣ በቤተ እምነቶች ላይ የደረሰውን ጥቃት ከወራት በፊት ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጥቆማ ደርሶ ሳለና ጥቃቱን መከላከል ሲቻል የደኅንነት መሥሪያ ቤቱና መንግሥት የት ነበሩ? የሚሉ ወገኖች አልታጡም።

ከዚህም ሌላ የመንግሥትንም ኾነ የፀጥታ ኃይሉን በአገሪቱ ሰላም የማስከበር፣ የማስፈንና በሕዝቡ ዘንድ የሰፈነውን ሰላም የማጣት ሥነልቦናዊ ቀውስ ማረጋጋት አለመቻላቸውን አጥብቀው የሚተቹም አሉ። በቅርቡ የታገቱትን 21 ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጉዳይ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ለደረሱ ጥቃቶችና የሰው ሕይወት የቀጠፉ ክስተቶች የተጠያቂዎቹ አለመያዝ፣ ተይዘዋል የተባሉትም መጨረሻቸው ምን እንደኾነ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተከታታይ የኾነ መረጃ ለሕዝቡ ይፋ አለመደረጉን ትችቱን የሚያቀርቡ ወገኖች ይጠቅሳሉ።

የመንግሥትንም ኾነ የብሔራዊ ደኅንነቱን መሥሪያ ቤት ለሕዝብ ያላቸውን ተዓማኒነት ማረጋገጥ የሚችሉባቸው ተብለው በአጽንኦት ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ፤ የደኅንነት መሥሪያ ቤት “ለጥቃቱ ያሰማራቸውን አካል በቅርቡ ይፋ አደርጋለሁ” ከማለቱ ጋር የተያያዘ ኾኖ ተገኝቷል። “እነዚህን አካላት ለጥፋት ያሰማራው አካል ማንነት ሳይውል ሳያድር ይፋ ሊደረግ ይገባል፤ ያ ካልኾነ ግን የመንግሥትን ብቃት ማነስ የሚያሳይ ነው” የሚሉ ጥያቄ አዘል አስተያየት በስፋት እየተነገረ ይገኛል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!