Coronavirus in Sweden

በስዊድን ኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 11 ደረሰ

በዛሬው ዕለት አራት፣ ትናንት ደግሞ አምስት ተጨማሪ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል ተባለ

ኢዛ (ዓርብ የካቲት ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 28, 2020)፦ በዛሬው ዕለት አራት ሰዎች በሦስት የተለያዩ ከተሞች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን የስዊድን መገናኛ ብዙኀን ዘገቡ። በትናንትናው ዕለት ደግሞ አምስት ሰዎች፣ ከትናንት በስቲያ አንድ፣ ከሳምንታት በፊት አንድ ሰው በቫይረሱ የተያዙ መኖራቸው ታውቋል። እስካሁን በስዊድን በቫይረሱ የተያዙት ቁጥር አስራ አንድ ደርሷል።

በዛሬው ዕለት (ዓርብ የካቲት 20 ቀን 2012 ዓ.ም.) በኮሮና ቫይረስ በስዊድን የተያዙት ሰዎች

በዛሬው ዕለት በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡት አራት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ በስቶክሆልም ከተማ፣ አንድ በየንሸፒንግና አንድ በኡፕሳላ ከተማ መኾኑን ቴቬ ፊራ ዛሬ ማምሻውን ዘግቧል።

በስቶክሆልም ከተማ ኮሮና የተገኘባቸው ሁለቱ ሰዎች ቫይረሱ በአገር ውስጥ የተላለፈባቸው መኾኑ ታውቋል። ለሁለቱ ግለሰቦች ቅርብ ከኾነችና ከኢራን ቫይረሱን ተሸክማ ወደ ስዊድን ከገባች ግለሰብ ጋር ንክኪ ነበራቸው። ይህች ግለሰብ በትናንትናው ዕለት (ሐሙስ የካቲት 19) ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጡት ሰዎች ውስጥ አንድዋ መኾንዋን በስቶክሆልም የተላላፊ በሽታዎች መከላከል ኃላፊ ዶክተር ፐር ፎሊን ለቴቬ ፊራ ገልጸዋል። ሁለቱ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀው ከሴትዮዋ ጋር የነበራቸውን ንክኪ መሠረት በማድረግ ክትትል ሲደረግላቸው ስለነበር መኾኑን ዶ/ር ፐር አስረድተዋል።

ሦስተኛውና በየንሸፒንግ ከተማ ቫይረሱ የተገኘበት ግለሰብ በ50ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ በጣሊያን ሰሜናዊት ከተማ ካደረገው ጉዞ ሲመለስ ነው ቫይረሱ እንዳለበት የታወቀው። አራተኛዋና በኡፕሳላ ከተማ የተያዘችው ግለሰብ ደግሞ በመካከለኛው ዕድሜ የምትገኝ ሴት ስትኾን፤ ኢራን አገር ደርሳ ስትመለስ ነው በቫይረሱ መያዝዋ የተረጋገጠው። እነዚህ ሁለት ግለሰቦች በቫይረሱ የተያዙት በአገር ውስጥ በነበረ ንክኪ ወይም የቫይረሱ ሥርጭት አለመኾኑ ታውቋል።

በትናንትናው ዕለት (ሐሙስ የካቲት 19 ቀን 2012 ዓ.ም.) በሦስት ከተሞች አምስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል

በትናንትናው ዕለት ደግሞ በስዊድን በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል የተባሉ አምስት ተጨማሪ ሰዎች መገኘታቸውን የስዊድን ብሔራዊ የጤና ኤጀንሲን በመጥቀስ የአገሪቱ ዕለታዊ ጋዜጣ አፍቶንብላደት ዘግቧል።

እንደ አፍቶንብላደት ዘገባ ከኾነ፤ በትናንትናው ዕለት ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሦስቱ በጉተንበርግ (የተቦሪ) ከተማ ሲሆን፣ አንዲት ሴት በኡፕሳላ ከተማ፣ ሌላ አንዲት ሴት በስቶክሆልም ከተማ እንደኾነና የጤና ክትትል እየተደረገላቸው መኾኑን ጠቅሷል።

በትናንትናው ዕለት በጉተንበርግ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሦስቱ መሐከል ሁለቱ በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ካለውና ቫይረሱ ከትናንት በስቲያ (ረቡዕ የካቲት 18) ከተገኘበት ጋር ንክኪ ስለነበራቸው መኾኑን የአፍቶንብላደት ዘገባ ያስረዳል። ይኼ በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለው ግለሰብ በሰሜናዊ የጣሊያን ከተማ ለጉብኝት ሔዶ ከተመለሰ በኋላ ነው ቫይረሱ እንዳለበት የታወቀው።

በጉተንበርግ ከተማ በቫይረሱ ከተያዙት ሦስተኛው ግለሰብ ደግሞ፤ በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ ቫይረሱ የያዘው በሚኖርበት ከተማና በስዊድን ከነበረው ንክኪ አለመኾኑ ታውቋ። ግለሰቡ ወደ ጣሊያን ተጉዞ የነበረ ሲሆን፣ ከጣሊያን ሚላን ከተማ ወደ ስቶክሆም ፌብሩዋሪ 25 በረራ አድርጎ እንደነበር ይኸው የአፍቶንብላደት ዘገባ ያስረዳል። በመኾኑም ከሚላን ከተነሳው በረራ ጀምሮ እስከ ስቶክሆልም ከተማ የሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ፤ እንዲሁም ከስቶክሆልም ተነስቶ ጉተንበርግ ከተማ እስከሚደርስ ድረስ የተነካካቸው ሰዎች ላይ ክትትል እየተደረገ መኾኑ ታውቋል።

በስቶክሆልም በትናንትናው ዕለት ቫይረሱ የተገኘባት ሴት ስትኾን፤ በከተማዋ የመጀመሪያዋ የቫይረሱ ተሸካሚ ልትኾን ችላለች። ግለሰብዋ በመካከለኛው ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፤ ቫይረሱ የተላለፈባት ስዊድን ውስጥ አለመኾኑ ታውቋል። ግለሰብዋ ኢራን ደርሳ ስትመለስ በተደረገላት ምርመራ ነው ቫይረሱ እንዳለባት ሊረጋገጥ የቻለው። (ከላይ ባለው ዘገባ ላይ በዛሬው ዕለት ሁለቱ የስቶክሆልም ነዋሪዎች ቫይረሱ የተላለፈባቸው ከዚህች ግለሰብ መኾኑል ልብ ይሏል።)

በተጨማሪም በስቶክሆልም ለዘጠና ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው፤ ከኢራን ከተመለሰችው ይህቺ አንዲት ሴት በቀር ሌሎቹ ደኅና መኾናቸውን በትናንትናው ዕለት ጋዜጣው ዘግቦ ነበር። በስዊድን ስለኮሮና ቫይረስ ጥያቄ ያለው ሰው በ 113 13 ለመንግሥት ጤና ኤጀንሲው መደወል እንደሚችል ዘገባው አስታውቋል።

ትናንት ሐሙስ የካቲት 19 ቀን ቫይረሱ ከተገኘባቸው 5ኛዋ ሴት በኡፕሳላ ከተማ ነዋሪ ስትሆን፣ ጀርመን አገር ቆይታ ስትመለስ ነው በቫይረሱ መያዝዋ የታወቀው። በኡፕሳላ ሆስፒታል ውስጥ በለይቶ ማቆያ ተገልላ እንድትቆይ ተደር፤ጎ ክትትል እየተደረገላት መኾኑ ታውቋል።

“የቫይረሱን የሥርጭት ሁኔታ በየጊዜው እየተከታተልን ለሕዝብ መረጃ እንሠጣለን፤ ለጊዜው ከዚህ ቀደም ከሠጠነው ምንም የተለየ ነገር የለም” በማለት የገለጹት በስዊድን ብሔራዊ የጤና ኤጀንሲ፤ የተላላፊና የበሽታዎች መከላከል ክፍል ኃላፊ የኾኑት ወ/ሮ ብሪታ ቢዮርክሆልም በትናንትናው ዕለት ገልጸው ነበር።

ወ/ሮ ብሪታ ከዚህ ቀደም፤ በስዊድን ሕብረተሰቡ ውስጥ የቫይረሱ የመሠራጨት አቅም እጅግ ውስን መኾኑን አስታውቀው የነበረ ሲሆን፤ ቫይረሱ በሰፊው ወደ ተሠራጨባቸው አገሮች ጉዞ አድርገው የነበሩና በቫይረሱ ከተያዙት ጋር ንክኪ ያደረጉ ሰዎች ናቸው ለጊዜው በቫይረሱ እየተያዙ ያሉት ብለው ነበር።

ከትናንት በስቲያ ረቡዕ የካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም.

ረቡዕ ዕለት በኮሮና ቫይረስ መያዙ የተገለጸው ግለሰብ በ30ዎቹ ዕድሜ ላይ ያለ ሲሆን፣ ወደ ሰሜን ጣሊያን ተጉዞ ከተመለሰ በኋላ በሚኖርባት ከተማ ጉተንበርግ ውስጥ ነው መያዙ የታወቀው። ግለሰቡ በስዊድን በቫይረሱ ለመያዝ ሁለተኛው ሰው ነው።

ይህ ግለሰብ ከጣሊያን ሚላኖ ከተማ ማክሰኞ ዕለት ተነስቶ ወደ ስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም በአውሮፕላን ይገባል። በመቀጠልም ረቡዕ ዕለት ከስቶክሆልም ወደሚኖርባት ጉተንበርግ ከተማ በሕዝብ ማመላለሻ ባቡር ይጓዛል። በወቅቱ የሕመም ስሜት ስለተሰማው ወደ ሆስፒታል ይደውልና ስለጉዳዩ ያስረዳ፤ "መጥተህ መመርመር አለብህ" የሚል መልስ ያገኛል፤ ከዚያም ከቤቱ መኪናውን አስነስቶ ወደ ሆስፒታል ይሔዳል፤ ምርመራ ይደረግለትና ቫይረሱ እንዳለበት ይረጋገጣል።

አብረውት በአውሮፕላን ከተጓዙትና በተለይም ግለሰቡ ተቀምጦበት በነረው የአውሮፕላን መቀመጫ ቅርበት የነበራቸውን ከ23 ያላነሱ ሰዎችና በባቡር በተጓዘበት ሰዓት በአቅራቢያው ነበሩ ተብለው የተገመቱ ሰዎችን (የክፍለ አገር ባቡሮች የመቀጫ ቁጥር አላቸው) ወዲያውኑ ለማግኘት ተሞክሮ ክትትል መደረግ ይጀመራል። በአጠቃላይ 40 የሚኾኑ ሰዎች ከግለሰቡ ጋር ንክኪ ሊኖራቸው ይችላል ተብሎ ስለታመነ ክትትሉ ይቀጥላል። ከላይ እንደተዘገበው ትናንት ሐሙስ የካቲት 19 ቀን በጉተንበርግ በቫይረሱ ከተያዙ ሦስት ሰዎች ውስጥ ወደ ሁለት ሰዎች ቫይረሱን ያጋባባቸው ይሄ ግለሰብ ነበር።

በስዊድን ቫይረሱ የተገኘባት የመጀመሪያዋ ግለሰብ

በስዊድን የመጀመሪያዋ የኮሮና ቫይረስ ተሸካሚ የተገኘችው የንሸፒንግ የተባለች ከተማ ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም. (ጃንዋሪ 31 ቀን 2020 እ.ኤ.አ.) ሲሆን፣ ቻይና ዉሃን ግዛት አካባቢ ተጉዛ ጥር 15 ቀን ወደ ስዊድን የተመለሰችው ነበር። ግለሰብዋ ስዊድን ከገባች በኋላ የበሽታው ምልክት በማሳል መልክ እንደጀመራት ነበር ወዲያው ወደ ሆስፒታል የሔደችው። ሆስፒታሉም በአፋጣኝ በለይቶ ማቆያ አኑሯት አስፈላጊውን ክትትል እያደረገላት ይገኛል።

በስዊድን የመተላለፉ ጉዳይ

በስዊድን ያለውን የቫይረሱን ሥርጭት በተመለከተ የዚህ ዜና አጠናካሪዎች (የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጀት ክፍል አባላት) ለመገንዘብ እንደቻልነው፤ ከተያዙት 11 ሰዎች ውስጥ 7ቱ ሰዎች ከስዊድን ውጭ ወዳሉና ቫይረሱ በሥፋት ወደተሠራጨባቸው አገሮች ደርሰው የተመለሱ ናቸው። በዚህም መሠረት 3ቱ ጣሊያን፣ 2ቱ ኢራን፣ አንድ ጀርመንና አንድ ቻይና መኾኑን ከመረጃዎቹ ለመረቻት ችለናል።

ከ11ዱ ሰዎች ውስጥ አራቱ ሰዎች በአገር ውስጥ ቫይረሱ የተላለፈባቸው ሲሆኑ፣ 2ቱ ኢራን ደርሳ ከመጣ ሴት፣ ሁለቱ ደግሞ ሰሜናዊ ጣሊያን ደርሶ ከመጣ ሰው መኾኑ ከላይ ካጠናከርነው ዘገባ መገንዘብ ይቻላል።

ስዊድን

በስዊድን ዛሬ የካቲት 20 ቀን 4 ሰዎች፣ ትናንት 5 ሰዎች፣ ከትናንት በስቲያ አንድ ሰው፣ ከአራት ሳምንታት በፊት አንዲት ሴት፤ በድምሩ 11 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች በሙሉ ክትትል እየተደረገላቸው እንደኾነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ባልደረባና ከዚህ ዜና አጠናካሪ አንዱ፤ በስቶክሆልም በዛሬው ዕለት በሕዝብ ማመላለሻ ባቡር ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች አፋቸውንና አፍንጫቸውን የሸፈኑ መንገደኞችን ማየት ችሏል።

በኦፊሴል የኮሮና ቫይረስ መነሻ ዉሃን የተሰኘችው የቻይና ግዛት እንደኾነች ይታወቃል። የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኀኖም ቫይረሱን አስመልክቶ በሠጡት መግለጫ፤ የቫይረሱን አሳሳቢነትና አደገኝነት አስመልክቶ ድርጅታቸው ከፍተኛ የማስጠንቀቂያ ደረጃ መሥጠቱን ገልጸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ