በመላው አገሪቱ የተፈጠረው የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ መንሥኤው አልታወቀም
በአዲስ አበባ ያለው በኤሌክትሪክ የሚሠራው የከተማ ውስጥ ባቡር
በጉዞ ላይ የነበሩ ባቡሮች ባሉበት ለመቆም ተገድደዋል
ኢዛ (ዓርብ የካቲት ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 28, 2020)፦ ዛሬ በኢትዮጵያ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እስካሁን ምክንያቱ በትክክል ባልታወቀና ባልተለየ ሁኔታ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቱ ተቋርጧል።
ከምሽቱ ወደ 12 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ከተሞችን በጨለማ ውጧል። ማምሻውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪካ ኃይል ለኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከሠጠ ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፤ እስካሁን የኃይል መቆራረጡ ምክንያተ ለመሥሪያ ቤቱም ያልታወቀ መኾኑን ነው። ኾኖም ኃይሉን ለመመለስ መሥሪያ ቤቱ እየሠራ መኾኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደጠቆመው፤ ችግሩ ከግልገል ጊቤ ሦስት ከሚቀርበው የኃይል መስመር ጋር የተያያዘ ሊኾን ይችላል የሚል ግምት ያላቸው መኾኑን የድርጀቱ የኮምዩኒኬሽን ባለሙያ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ በቅርቡ በሥራ ላይ የዋለው የከተማይቱ ባቡርም ሥራ አቁሞ የነበረ ከመኾኑም በላይ፤ መብራቱ በተቋረጠበት ሰዓት በሥራ ላይ የነበሩት ባቡሮች በጉዞ ላይ በነበሩበት ቦታ ለመቆም ተግድደዋል። በዚህም ምክንያት የከተማይቱ ነዋሪዎችና የባቡር ተጠቃሚዎች የትራንስፖርት እጥረት አጋጥሟቸው እንደነበር የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለመረዳት ችሏል።
ይህ ዜና ከተሰማ ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ በአዲስ አበባ የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ቀስ በቀስ ተመልሷል።
የኃይል መቋረጡ በአዲስ አበባ በርካታ አገልግሎቶችን ያስተጓጎለ ሲሆን፤ ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ትክክለኛውን የጉዳት መጠን ለማወቅ አልቻልንም። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኤሌክትሪክ በፈረቃ ማከፋፈል መጀመሩን በይፋ ካስታወቀ የዛሬ ወር የፊታችን መጋቢት አሥራ ሁለተኛ ዓመቱ እንደኾነ ይታወሳል። (ኢዛ)



