ሁለት ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ በአቡዳቢ ተያዙ
ኮሮና ቫይረስን በምስል ለማሳየት በበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል የተሠራጨ
በአገሪቱ እስካሁን 45 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል
ኢዛ (ቅዳሜ የካቲት ፳፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 7, 2020)፦ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የጤና ሚኒስቴር ዛሬ እንዳስታወቀው 15 አዲስ ግለሰቦች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል። ከእነዚህም ውስጥ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል። በአገሪቱ እስካሁን 45 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ነዋሪነታቸው በዐረብ ኤምሬቶች ሲሆን፤ በዜግነት ደረጃ የመጀመሪያዎቹ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ኢትዮጵያውያን መኾናቸው ታውቋል። በኢትዮጵያም ኾነ በሌሎች አገሮች በኦፊሴል በቫይረሱ የተያዙ ኢትዮጵያውያን እስካሁን እንደሌሉ ይታወቃል።
በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች መጀመሪያ በቫይረሱ ከተያዙት አራት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ ቻይናውያን የነበሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ሁለቱን ቻይናዎች ጨምሮ አራቱም ከቫይረሱ ነፃ መኾናቸውን ይኸው የዐረብ ኤምሬቶች የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሪፖርት መገለጹን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኀን ዛሬ የካቲት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ዘግበዋል።
አዲስ የተያዙት 15 ሰዎች የተለያየ ዜግነት ያላቸው ሲሆን፤ ከታይላንድ፣ ከሞሮኮ፣ ከቻይና፣ ከግብጽና ከሕንድ አንድ አንድ፤ ከኢትዮጵያ፣ ከሳውዲ ዐረቢያና ከኢራን ሁለት ሁለት፤ እንዲሁም ከኤምሬትስ አራት ሰዎች በኮቪድ-19 (Covid-19) ቫይረስ መያዛቸውን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ይጠቁማል። (ኢዛ)



