Attorney General Adanech Abebe

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ስብሰባዎች ተከልክለዋል፤ ቤት ኪራይ መጨመር፣ ሠራተኛ መቀነስና ውል ማቋረጥም አይቻልም

ኢዛ (ቅዳሜ ሚያዝያ ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 11, 2020)፦ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ያስችል ዘንድ ትናንት በፓርላማ የጸደቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈፀም አራት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ደንብ ይፋ ኾነ። የደንቡን አጠቃላይ ይዘት ማብራሪያ በመሥጠት ይፋ ያደረጉት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ናቸው።

ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 3 ቀን በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይፋ የኾነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብ ክልከላዎችን የሚያስቀምጥ፣ ግዴታዎችን የሚጥል፣ የአስፈፃሚ አባላት ክንውን እና የተለያዩ ድንጋጌዎችን የያዘ መኾኑን የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል።

ከክልከላዎቹ አንዱ ማንኛውም ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ እድር፣ ደቦ፣ እቁብና ሌሎች ከአራት ሰዎች በላይ የሚገኙባቸው ስብሰባዎች ተከልክለዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ ገደቡ ውስጥ ቤት ተከራዮች በራሳቸው ፍላጉት ካልወጡ በስተቀር ማስወጣትና ኪራይ መጨመር ተከልክሏል። ሠራተኞችን መቀነስና የሥራ ውል ማቋረጥም የተከለከለ መኾኑን የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መረጃ አስረድቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ በዓቃቤ ሕግ የመረጃ ገጽ ላይ የሰፈረው መረጃ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈፀሚያ ደንብ

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 93 ንኡስ ቁጥር 4 መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብ ማውጣት እንዳለበት ይደነግጋል።

በዚህም መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን ማስፈፀሚያ ደንብ አጠቃላይ ዝርዝር በሚመለከት ወይዘሮ አዳነች አብራርተዋል።

ማስፈፀሚያ ደንቡ አጠቃላይ አራት ዋና ዋና ከፍሎች ያሉት ሲሆን ይሄውም ክልከላን የሚያስቀምጥ፣ ግደታዎችን የሚጥል፣ የአስፈፃሚ አካላትን ክንውን እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑ ተጠቅሷል።

ክልከላን በሚመለከት ማንኛውም ሃይማኖታዊ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣ የግል ድርጅቶች ይሁን ፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ እድር፣ ደቦ፣ እቁብና ሌሎችም ከ4 ሰው በላይ ስብሰባዎች ክልክል ናቸው።

አራት ሰዎችም ቢሆኑ ሁለት የአዋቂ ሰው እርምጃ የጠበቀ መሆን እንዳለበት ዓቃቤ ሕጓ አብራርተዋል።

ቀብርና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ሲኖሩ ግን እየታዩ ሊፈቀዱ የሚችሉበት አሠራር መኖሩን ጠቁመዋል።

ታራሚዎች ከጠበቆቻቸው ጋር አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲገናኙ የሚፈቀድ ቢሆንም ጥየቃ ለሚሔዱ ሰዎች የማይፈቀድ መኾኑ ተገልጿል።

በፖሊስ የተያዙ እስረኞችንም ስንቅ ከማቀበል በስተቀር መገናኘት የተከለከለ መኾኑን አስረድተዋል።

በድንበር አካባቢ ከካርጎ፣ የደረቅና ፈሳሽ ጭነት አገልግሎቶች በስተቀር ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዝግ ተደርገዋል።

የቤት ተከራዮች በራሳቸው ፍላጎት ካልወጡ በስተቀር ማስወጣትና ኪራይም መጨመር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተከልክሏል።

በሠራተኛና አሠሪ አዋጅ የሚተዳደሩ የግል አሠሪ ድርጅቶች ሠራተኞችን መቀነስና የሥራ ቅጥር ውል ማቋረጥም መከልከሉን ወይዘሮ አዳነች አብራርተዋል።

በዚህ ደንብ መሠረት ተማሪዎችና መምህራን በኦን ላይን ወይም ከአካላዊ ንክኪ ወጭ ባሉ ሌሎች መገናኛ ዜዴዎች ካልኾነ በአካል እንዲገናኙ አይፈቀድም።

ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ የሕፃናትም ይሁን የሌሎች መጫወቻ ስፍራዎች እንዲሁም የእጅ መጨባበጥ ሰላምታ የተከለከለ ነው።

በትራንስፖርት ዘርፍም አገር አቋራጭ፣ የከተማ ውስጥ የታክሲ አግልግሎት የሚሠጡ እንዲሁም የፐብሊክ ሰርቨስ የሚሠጡ ካለው ወንበር ከ50 በመቶ በላይ ተሳፋሪ መጫን የተከለከለ ነው፡፡

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ