Dereje Bekele

አቶ ደረጀ በቀለ የኢትዮጵያ የፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሊቀመንበር

ከገለልተኛ አካል ማረጋገጫ አልተሰጠም
በሕወሓት ይመራል የተባለው ቡድን ጽሕፈት ቤቱን አዲስ አበባ ሊያደርግ ወሰነ

ኢዛ (እሁድ ግንቦት ፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 17, 2020)፦ በመቀሌ ከተማ ሊካሔድ በነበረው የኢትዮጵያ የፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ መቀሌ ለመሔድ ሲዘጋጁ የነበሩ የጥምረቱ አመራሮች ታስረዋል ሲል የትግራይ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው በኩል የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው አቶ ገብሩ በርሀ፣ ልጅ መስፍን ሽፈራው፣ አቶ ተሻገር አረጋ፣ ወይዘሪት መዲና ኢማም እና አቶ ጉዑሽ ገብረሥላሴ የተባሉ የጥምረቱ አባላትና ሊቀመናብርት ናቸው የታሰሩት።

ስለጉዳዩ በመረጃው ላይ የተጠቀሱት አምስቱ የጥምረቱ አባላት ወደ መቀሌ ከሚበሩበት አውሮፕላን ውስጥ ተወስደው መታሰራቸውን ነው መረጃው ያመለከተው። ሲወሰዱም የኮሮና ምርመራ ይደረግላችኋል ተብለው እንደኾነም ይጠቅሳል።

ከአምስቱ ሌላ ሌሎች ሁለት የጥምረቱ አባላት (አቶ ዓብዲ ዑመር እና አቶ አባስ ሐጂ መሐመድ) ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሲያመሩ ስለመያዛቸው የሚገልጸው ይኸው መረጃ፤ ድርጊቱን ከዚህ ቀደም ወደ መቀሌ ሊጓዙ ሲሉ መንግሥት ክልከላ አድርጓል ብሎ ከሚገልጸው ድርጊት ጋር አያይዞታል።

ይህ ድርጊት ተፈጸመ በተባለበት ዕለት የፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሊቀመንበሩን ጭምሮ አብዛኛዎቹ የጥምረቱ አባላት በአዲስ አበባ ባደረጉት ስብሰባ፤ ከሌሎቹ የጥምረቱ ጥቂት አባላት ውጭ የምርጫውን መራዘም ደግፈው አቋማቸውን ገልጸዋል።

በሕወሓት የተፈጠረ ነው የሚባለው ይህ ጥምረት፤ በአዲስ አበባ ባደረገው ስብሰባ ምርጫው መራዘም የለበትም የሚለውን አቋሙን ከመቀየሩም በላይ በመቀሌ ያለውን የድርጅቱን ጽሕፈት ቤት ወደ አዲስ አበባ ለማዛወር ውሳኔ እስከማሳለፍ ደርሷል።

ስለመታሰራቸው በተገለጹት የፌዴራሊስቱ አባላት እስካሁን ከገለልተኝ አካል ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠበትም። የፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ከወራት በፊት በመቀሌ መጀመሪያ “ፎረም” በሚል፤ ከዚያም “ጥምረት” በሚል የተመሠረተ ነው። በዚህ ጥምረት ውስጥ 25 የሚኾኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳሉ ይጠቀሳል። ጥምረቱ በመጀመሪያ 35 ፓርቲዎችን ያካተተ እንደነበር አይዘነጋም። ለዚህ ጥምረት መፈጠር ከጥንስሱ ጀምሮ መሪ ኾኖ ሲንቀሳቀስ የቆየው ሕወሓት መኾኑ ይታወቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ