Dr. Yinager Dessie

ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ

ግለሰብ በቀን 200 ሺህ፣ ኩባንያዎች በቀን 300 ሺህ ብቻ ማውጣት ይችላሉ

ኢዛ (ማክሰኞ ግንቦት ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 19, 2020)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ አስቀማጭ ግለሰቦችና ኩባንያዎች በየዕለቱ ከባንኮች የሚያወጡትን ጥሬ ገንዘብ የሚገድብ አዲስ መመሪያ ከዛሬ ግንቦት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ አዋለ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ይህ መመሪያ የወጣው ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠርና ከዚህ በተጓዳኝ የሚታዩ ሕገወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ነው።

በዚሁ መሠረት በአዲሱ መመሪያ አንድ ግለሰብ በቀን ከባንኮች ማውጣት የሚችለው ጥሬ ገንዘብ 200 ሺህ ብር መኾኑንና፤ በወር ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን ብር ያልበለጠ ጥሬ ገንዘብ ነው ማውጣት የሚችለው። በተመሳሳይ ኩባንያዎችም በቀን በጥሬ ገንዘብ ከባንክ ለማውጣት የተፈቀደላቸው 300 ሺህ ብር ሲሆን፤ በወር ማውጣት የሚችሉት የጥሬ ገንዘብ ደግሞ ከ2.5 (ሁለት ነጥብ አምስት) ሚሊዮን ብር የበለጠ እንዳይኾን በዚህ መመሪያ ተገድቧል።

ገዥው ዶ/ር ይናገር ደሴ እንዳመለከቱት፤ ይህ ማለት ግን ከገደቡ በላይ ሰዎችም ኾኑ ግለሰቦች ገንዘብ ማንቀሳቀስ አይችሉም ማለት ሳይኾን፤ ከገደቡ በላይ የሚኾነውን የገንዘብ መጠን የሚያንቀሳቅሱት በሌላ የክፍያ ሥርዓት ነው።

ይህም ከገደቡ በላይ ያለውን የገንዘብ መጠን ከአካውንት ወደ አካውንት ወይም በቼክና በሲፒኦ ገንዘቡን ለተለያዩ ክፍያዎች ማዋል የሚችሉ በመኾኑ፤ ገደቡ በጥሬ ገንዘብ በሚወጣው ገንዘብ ላይ እንጂ፤ ከገደቡ በላይ ያለውን ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱት በሌሎች አማራጮች ነው።

እንደ ዶ/ር ይናገር ደሴ ገለጻ፤ ይህንን መመሪያ መተላለፍ ያስቀጣል። በመመሪያው በተቀመጠው መሠረትም አንድ ባንክ ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን በላይ ክፍያ ከፈጸመ፤ ከገደቡ በላይ ከተሰጠው ገንዘብ ውስጥ 25 በመቶ የሚኾነውን ይቀጣል።

ይህም ከገደቡ በላይ አንድ ባንክ 10 ሚሊዮን ብር ቢከፍል፤ 2.5 (ሁለት ነጥብ አምስት) ሚሊዮን ብር ይቀጣል በማለት ስለቅጣቱ ገዥው ማብራሪያ ሰጥተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!